Translate

Monday, January 27, 2014

ደቡብ ሱዳን በጎሣ ፖለቲካ እሳት እየተበላች ነው!

የኃያላኑ የንዋይ ጥማትና የደቡብ ሱዳን የጎሣ ፍልሚያ

south sudan and the superpowers


ከተመሠረተች ምንም ያህል ያልሰነበተችው ደቡብ ሱዳን ሕዝቧ ሰላሙንና ነጻነቱን በደስታና በጸሎት አጣጥሞ ሳይጨርስ በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ ከወደቀች አንድ ወር አልፏታል፡፡ ጎሣን መሠረት በማድረግ የተቀሰቀሰው ፍልሚያ ግን የተጀመረው ገና ደቡብ ሱዳን አገር ከመሆኗ በፊት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ በደቡብ ሱዳን ሣር ላይ የኃያላኑ ዝሆኖች የእጅ አዙር ጠብና ፍጥጫም አብሮ የሚጠቀስ ነው፡፡

አፍሪካ ከምዕራባውያን ቅኝ ግዛት ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ የመፈንቅለ መንግሥትና የእርስበርስ ጦርነት ትዕይንቶችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ ይህን “coup-civil war trap” አዙሪት በአብዛኛው የመከሰቱን ሁኔታ የፖለቲካ ተኝታኞች የሚስማሙበት ነው፤ ዋንኛውንም ምክንያት ጠንካራ ተቋማት ያለመመሥረታቸው ውጤት እንደሆነ ያሰምሩበታል፡፡
አዲስ አገርም ሆነ መንግሥት ምስረታ ወቅት የሚከሰቱ ሁለት አካሄዶች አሉ፡- በሕዝብ ይሁንታ ሳይሆን በጠብመንጃ ኃይል ወደ ሥልጣን የሚመጣው ቡድን በአንድ በኩል የፖለቲካ ተቋማት እንዲመሠረቱና ሥልጣንን ለተቀናቃኞቹ በማካፈል ተቀባይነት ያለው አመራር ለመመሥረት ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሥልጣን ማጋራቱ ተቀናቃኞቹን ኃይለኛ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ ወደፊት እነዚሁ ተቀናቃኞች ኃይላቸውን አስተባብረው መፈንቅለ መንግሥት ያደርጉብኛል የሚል ሥጋት ውስጥ ይገባል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥቱ ስጋት ሥልጣንን ከማጋራትም ሆነ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ከማድረግ ስለሚበልጥበት አስቀድሞ ማካፈል የጀመረውን ሥልጣን በመፈንቅለ መንግሥት ፍራቻ መልሶ መሰብሰብ ይጀምራል፡፡
በቀጣዩም የራሱን ታማኞች በዙሪያው በማድረግ ራሱ ያጥራል፤ ሥልጣኑንም ያጠናክራል፡፡ የደኅንነቱንና የፖሊስ እንዲሁም የጦሩን ኃይላት በራሱ ጎሣ አባላት ወይም ቁልፍ ታማኞች ጠቅልሎ ይይዛል፡፡ ተቀናቃኞቹን በተወሰነ የሥልጣን ሣጥን ውስጥ በማስገባት በዓይነቁራኛ መከታተል ይጀምራል፡፡
የታማኝነት መለኪያው በጣም እየጨመረ ሲሄድ የሥልጣኑ አጥር ከጎሣ በማለፍ በቤተሰብ ደረጃ ይወርዳል፡፡ የፖለቲካ ተቋማትን በማጠናከር ሕዝብን ሙሉ የመብቱ ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ መፈንቅለ መንግሥትን በመፍራትና በሥልጣን ወሰን ለሌለው ጊዜ ለመቆየት ሲባል በሚወሰደው እርምጃ የራስ ወገኖችን በግልጽ የመጥቀም አሠራር ይንሰራፋል፡፡ ሙስና፣ ንቅዘት፣ ወንጀል፣ “የመንግሥት ሌብነት”፣ ወዘተ ይጠናክራል፡፡ በአንጻሩ ቀድሞ የትግል ጓዶች የነበሩ የሥልጣን ክፍፍሉ እያነሳቸው ሲሄድ ቂም፣ ጥላቻ፣ “እንዴት ተቀደምኩ”፣ ወዘተ የሚል እልህ ውስጥ በመግባት በራሳቸው ጎሣና ቤተሰብ ዙሪያ ኃይል ማስተባበር ይጀምራሉ፡፡
SudaneseSoldierሁኔታው በዚህ መልኩ እየተፋጠጠ ገሃድ ከመውጣቱ በፊት አሰቀድሞ የመፈንቅለ መንግሥት ፍራቻ የነበረበት ኃይል ቀድሞ የመምታት እርምጃ በመውሰድ በታማኞቹ ድጋፍ ሥልጣኑን የማዳን ጊዜያዊ ዕድል ይገጥመዋል፡፡ የተገፉትና የተገለሉት ኃይሎች ወዲያው የመቋቋም ኃይል ካላቸው ፊትለፊት ይገጥሙታል፤ አስቀድመው ከተመቱ ግን ለጊዜው ተሸናፊ ቢሆኑም ቀኑን ጠብቆ ሊነሳ ወደሚችል የጎሣና የዘር እንዲያም ሲል የቤተሰብ ግጭት ውስጥ መግባታቸው የጊዜ ጉዳይ ይሆናል፡፡
መፈንቅለ መንግሥትን ለመከላከልና በሥልጣን አለገደብ ለመቆየት ሲባል የአፍሪካ መሪዎች ወደ እንደዚህ ዓይነት የማያባራ ሰቆቃ ሕዝብን እየመሩ “ሕዝባዊ ነን”፤ “በ99%” አብላጫ ምርጫ አሸንፈን ወንበር ይዘናል፤ “ልማታዊ መሪዎች ነን”፤ “ሁሉም ነገር ወደ ልማት”፤ “ጉዞ ሕዳሴ፣ ውዳሴ” በማለት ራሳቸው ሰክረው ሕዝብን አስክረው ለማደንዘዝ ይሞክራሉ፡፡ ለዓመታት ሲረጩት የቆዩትን የጎሰኝነት መርዝ በልማት ማር ለመቀባት ይሞክራሉ፡፡ ሥልጣኔን ከማጣ የእርስበርስ ዕልቂት ይከሰት፣ ደም ይፋሰስ፣ ህጻናት በማያባራ ሰቆቃ ውስጥ ይግቡ፣ እናቶች ዕድሜላካቸውን ያልቅሱ፣ ዜጎች መቅኖ ቢስ ይሁኑ፣ … በማለት የራስን ዘርና ጎሣ ብቻ ለዘላለም ሲጠቅሙ ይኖሩ ይመስል ራሳቸውን መልሶ በሚያወድም የማያባራ መከራ ይጥላሉ፡፡ በሥልጣን ለመቆየት የእርስበርስ ጦርነትን ይጋብዛሉ፤ ራሳቸው የቀበሩት ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳው ቦምብ ግን ልማትን ከዘርና ጎሣ እንደማይለይ የዘነጉት ይመስላል፡፡
በደቡብ ሱዳን የኃያላኑ ፍጥጫ
21ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮጳውያኑ አቆጣጠር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች የመጣችውን ቻይና ልዕለ ኃያልነትን ለዓመታት በብቸኝነት የተቆጣጠረችውን አሜሪካ በሁሉም መስክ እየተገዳደረች ትገኛለች፡፡ ሁኔታው ያልጣማት አሜሪካ ይህንን የቻይና አካሄድ ለመገደብ ከተቻለም ለማስቆም ዕቅድ አውጥታ ስትንቀሳቀስ ቆይታለች፡፡ በተለይም ቻይና ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር በብድርም ሆነ በተዘዋዋሪ ስጦታ መልክ የምታከናውነው ስምምነት የምዕራባውያኑን በተለይም የአሜሪካንን ውቃቢ ያስቆጣ ተግባር ሆኖ ከርሟል፡፡
በዓለምአቀፍ ደረጃ ሸቀጧን እያራገፈች ያለችው ቻይና በፍጥነት እያደገ ያለውን ኢኮኖሚዋን ለማስቀጠል ከየትኛውም አገር ለምታገኘው ጥሬ ሃብት በተለይም ነዳጅ ከፍተኛ ዋጋ ትከፍላለች፡፡ ይህ የቻይና “ጭፍን” አካሄድ ደግሞ ምዕራባውያን ቻይናን ለማጥመድ የሚጠቀሙበት አይነተኛ መሣሪያ ሆኖላቸዋል፡፡
ከጅምሩ ከአልበሽር ሱዳን ጋር “በነዳጅ ፍቅር” የተለከፈችው ቻይና፤ ሱዳን ምዕራባውያን የሚያደርሱባትን ማዕቀብም ሆነ ማስፈራሪያ እንድትቋቋም በተለያዩ መንገዶች ረድታታለች፡፡ አልበሽር በዓለምአቀፉ ፍርድቤት ቢከሰሱም ሆነ ከምዕራብ መንግሥታት ውግዘት ቢደርስባቸውም ቻይና ከአፍሪካ አምባገነኖች ጋር በመሆን “አንለያይም” ስትቀኝባቸው ነበር፡፡ በመሆኑም ሱዳንን ለማንበርከክም ሆነ ለመቅጣት እንዲያም ሲል የቻይናን የኢኮኖሚ ጥቅም ለማጨናገፍና ኢንቨስትመንቷንም ለመከፋፈል ድርብ ተጽዕኖ የሚያመጣው ዕቅድ በምዕራባውያን ተነደፈ – ሱዳንን መከፋፈል፡፡
ለዓመታት ደቡብ ሱዳንን ነጻ ለማውጣት ሲታገል የነበረው ኤስ.ፒ.ኤል.ኤ. ይህንን አጀንዳ የሚያስፈጸም ሁነኛ መሣሪያ ሆነ፡፡ በጆን ጋራንግ ዘመን ወደ ስምምነት እየመጣ የነበረው የአማጺያኑና የሱዳን ውዝግብ ጋራንግ ከሞቱ በኋላ አቅጣጫውን በመቀየር ደቡብ ሱዳን በአገር ደረጃ እንድትመሠረት አሜሪካ ግልጽ አቋም በመያዝ ተጸዕኖ አደረገች፤ ከበቂ በላይ ፕሮፓጋንዳም ነፋች፡፡south sudan oil
በሌላ በኩል የአልበሽርን ሱዳን ይበልጥ መልከጥፉ ለማድረግና የነጻዪቱን ደቡብ ሱዳን መመሥረት ለማፋጠን የዳርፉር ቀውስ በአሜሪካና እስራኤል ምሥጢራዊ ድጋፍ ያገኝ ቀጠለ፡፡ በመጨረሻም ከ2 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያለቀበት ጦርነት በደቡብ ሱዳን መገንጠል ተጠናቀቀ፡፡ የምዕራባውያን በተለይም የአሜሪካ ታላቅ ውለታ ያለባት ደቡብ ሱዳን ገና ነጻ አገር ሳትሆን የዓለምአቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አባል ለመሆን ማመልከቻ በማስገባት ለአሜሪካ ቀብድ መክፈል ጀመረች፡፡
ለደቡብ ሱዳን ነጻ መውጣት ቀጥተኛና ግልጽ ድጋፍ ትሰጥ የነበረችው አሜሪካ ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር ከሆነች በኋላ እንደታሰበው በአገሪቷ ላይ ሙሉ ቁጥጥር ማድረግ አልቻለችም፡፡ እጅግ ኋላ ቀር የሆነው የደቡብ ሱዳን ኢኮኖሚ ከቻይና ቁጥጥር ሥር ሙሉ በሙሉ ሊወጣ አልቻለም፡፡ ሱዳን ከመከፋፈሏ በፊት የ20 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት የነበራት ቻይና ከክፍፍሉ በኋላ በደቡብ ሱዳን ብቻ የ8ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት አላት፡፡
ይህ ከፍተኛ የሆነ በነዳጅ ላይ ያተኮረ ኢንቨስትመንት የቻይናን የነዳጅ ጥማት የሚያረካ ባይሆንም የዛሬ ወር አካባቢ የእርስበርስ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በነበሩት 10ወራት ብቻ ቻይና ከደቡብ ሱዳን 1.9ሚሊዮን ቶን ነዳጅ ወይም 14ሚሊዮን በርሜል ቀድታለች፡፡ ቢቢሲ እንደዘገበው ከሆነ ይህ የነዳጅ መጠን ቻይና ከናይጄሪያ በዓመት ከምታስመጣው በእጥፍ የሚበልጥ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የቀድሞ ምክትላቸው ሬክ ማቻር ዲንካ እና ኑዌር በማለት ዘር ለይተው ፍልሚያ ከጀመሩ ወዲህ ግን የነዳጅ ምርቱ 20በመቶ ወርዷል፡፡ ዋናው የእርስበርስ ጦርነት በነዳጅ በበለጸጉት የዩኒቲ እና ኧፐር ናይል ጠቅላይ ግዛቶች አካባቢ መሆኑ የጦርነቱ ዋንኛ አካሄድ ምን ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገላጭ ነው፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የአሜሪካንን እና የእስራኤልን ድጋፍ ሲያገኝ የነበረው የደቡብ ሱዳን ነጻ አውጪ ግምባር አሁንም በሳልቫ ኪር አገዛዝ ከሁለቱ አገራት የሚያገኘው ጥቅም አልቀረበትም፡፡ የቻይና ኢኮኖሚያዊ የበላይነትና በአፍሪካ መንሰራፋት የልዕለኃያልነት ጥያቄ ያስነሳባት አሜሪካና ተባባሪዎቿ ጉዳዩን ሲያጠኑና ተግባራዊ እርምጃ ሲወስዱ ቆይተዋል፡፡ በተለይ በአፍሪካ የአሜሪካ ወታደራዊ ዕዝ (አፍሪኮም – AFRICOM) መቋቋም አንዱና ዋንኛው የቻይናን የንግድ እንቅስቃሴ የመቆጣጠሪያ መንገድ መሆን እንዳለበት ወታደራዊ ጠበብቶች ስታቴጂካዊ ጥናቶች ያደረጉበት ነው፡፡
imiደቡብ ሱዳን ነጻ ከወጣች በኋላ አሜሪካና ደጋፊዎቿ ወዲያውኑ የኢኮኖሚ የበላይነት ለመቆጣጠር ባይችሉም ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ግን ቆይተዋል፡፡ በተለይ ከነጻነት በኋላ እስራኤል ከደቡብ ሱዳን ጋር ውሃ ለማጣራት፣ የውሃ ጨውነትን ለማስወገድ፣ ውሃ ለማመላለስ፣ እንዲሁም ለመስኖ ስምምነት ፈርማ ነበር፡፡ በእርግጥ ስምምነቱ በዚህ መልኩ ቢፈረምም ሥራውን በዋንኛነት የሚያከናውነው በውሃ ቴክኖሎጂ ሳይሆን በመሣሪያ ማምረት የታወቀው የእስራኤል ወታደራዊ ኢንዱስትሪ (አይ.ኤም.አይ.) መሆኑ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የአሜሪካ ወዳጆችን አቅጣጫ የሚያሳይ ነው፡፡ በእርግጥ አይኤምአይ ከውሃ ጋር በተያያዙ እና ሌሎች ፕሮጀክቶች ላይ እንደ አማካይ ሆኖ የሚሠራ ቢሆንም ወታደራዊ ተቋም እንደመሆኑ ለግጭቶች፣ ለጦር መሣሪያዎች እና ገንዘብ ዝውውር እንደ አማካይ ሆኖ እንደሚሰራ ጉዳዩን የሚከታተሉ ይጠቁማሉ፡፡
የቻይናን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና የበላይነት ለመገደብ በተቀነባበረ ሁኔታ እየተካሄደ ያለው የደቡብ ሱዳን ግጭት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳሄድ አሜሪካ ግጭቱ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ “ዲፕሎማሲው” ላይ ተግታለች፡፡ የጋዳፊን አገዛዝ በመገርሰስ ቻይናን ከ20ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሣራ ላይ እንድወድቅ የተደረገበት የምዕራባውያን ዕቅድ፤ በደቡብ ሱዳን ላይ ተግባራዊ ሲሆን በአካባቢው ባሉ አገራት (በተለይ በኢትዮጵያ) ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ተሰግቷል፡፡ በመሆኑም “ሁኔታውን አስቀድሞ መቆጣጠር ኃላፊነቴ ነው” ያለች የምትመስለው አሜሪካ፤ የሳልቫ ኪር ወዳጅ የሆኑትን እና በአሜሪካ ጥቅም አስከባሪነታቸው የሚታወቁትን ዩዌሪ ሙሴቪኒን የመጀመሪያ ተሰላፊ አድርጋለች፡፡ ለአሜሪካ ሲሉ በጎረቤት አገር ጦርነት እስከመክፈት የሚታወቁት መለስ ሞት ቀደማቸው እንጂ ለዚህ ተላላኪነት ገጣሚ ሰው ነበሩ፡፡
ግጭቱ እንደጀመረ ሙሴቪኒ ጣልቃ ለመግባትና ሳልቫ ኪርን ለመደገፍ ጊዜም አልወሰደባቸውም፡፡ በቅልጥፍና የወሰዱት እርምጃም አስቀድሞ ትእዛዝ የተሰጣቸው ወይም ግጭቱን “በተስፋ” ሲጠብቁ የነበረ አስመስሎባቸዋል፡፡ 1,600 ወታደሮቻቸውን ወደዚያው በመላክ የተላላኪነት ሥራቸውን የጀመሩት የዑጋንዳው አምባገነን፤ ሬክ ማቻር በአዲስ አበባ ላይ በሚደረገው የሰላም ድርድር የማይስማሙ ከሆነ የምስራቅ አፍሪካ አገራትን አስተባብረው ወታደራዊ ክንዳቸውን በማሳረፍ እንደሚያንበረክኳቸው አስጠንቅቀው ነበር፡፡ የሙሴቪኒ ሁኔታ መለስ ባይኖሩም ለሁለት እንተካለን ብለው የገቡትን ቴድሮስ አድሃኖምና ስዩም መስፍንን እንዲሁም ሌሎች የህወሃት ኃላፊዎችን “ያስደነገጠ” መሆኑን መናገራቸውን በቀጣናው ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑ ጠቅሶ ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል፡፡
ዋንግ ዪ
ዋንግ ዪ
ቻይናም ግጭቱ እንደተጀመረ በደቡብ ሱዳን ካላት ጥቅም እና በምዕራባውያን ከተቀነባበረባት ጥቃት አኳያ ሁኔታውን ለመቆጣጠር ጥረት ስታደርግ ቆይታለች፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ወደ አዲስ አበባ በመላክ ሁለቱም ወገኖች በአስቸኳይ ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ስትመክር ነበር፡፡ አንዳንድ የሚዲያ መረጃዎች እንዳመለከቱት ሚኒስትር ዋንግ ዪ በግላቸው ሁለቱን ወገኖች ለመሸምገል ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ጥረቱ ባይሳካላቸውም ሁኔታው ቻይና ምን ያህል እንዳሳሰባትና በጉዳዩ ላይ ትኩረት እንደሰጠች በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡
ሥልጣናቸውን ለማስጠበቅና ከምዕራባውያን ጋር “በፍቅር” ዓለም ውስጥ ያሉትን ሳልቫ ኪርን “ዲንኮክራሲ” (የዲንካ ጎሣ የበላይነት) የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ አምባገነን፣ ወዘተ እያሉ ከኑዌር ጎሣ የሆኑት ሬክ ማቻር ቢከሷቸውም፤ እርሳቸውም ከዚሁ የዘርና ለሥልጣን የመስገብገብ ባህርይ ውጭ እንዳልሆኑ የቀድሞ ታሪካቸው ይመሰክራል፡፡ እንዲያውም በትጥቅ ትግሉ ወቅት “የቦር ዕልቂት” እየተባለ የሚጠቀሰውን በመምራት ኑዌሮች ከ2ሺህ በላይ ዲንካዎች ለጨፈጨፉበት ወንጀል ዶ/ር ሬክ ማቻርን የሚከሷቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ቀጥሎም ከአልበሽር ሱዳን ጋር በመስማማት የካርቱምን ስምምነት በመፈረማቸው “በከሃዲነት” የሚወነጅሏቸውም የዚያኑ ያህል በርካታ ናቸው፡፡ ሥልጣን አልያዙም እንጂ ከሚወቅሷቸው ሳልቫ ኪር ባልተናነሰ መልኩ ዘረኛና የሥልጣን ጥማተኛ በመሆናቸው መንበሩን ቢቆጣጠሩ “የተማረ አምባገነን” ከመሆን እንደማያልፉ የደቡብ ሱዳንን ጉዳይ የሚከታተሉ ተንታኞች ይናገራሉ፡፡ ሬክ ማቻር ትምህርታቸውን ስኮትላንድ የተከታተሉ ሲሆን በስትራቴጂክ ዕቅድና ኢንዱስትሪ የዶክትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡
s sudan cease fireቀናትን ያስቆጠረውና “በርካታ ድርድር” ተካሄደበት የተባለው ስምምነት ባፈው አርብ እንደተፈረመ ህወሃቶቹ ስዩም መስፍንና ቴድሮስ አድሃኖም ትጉ ሠራተኞች መሆናቸውን በማስመስከር “መለስ ባይኖርም እኛ አለን” የሚያስብል ታዛዥነታቸውን ለምዕራብ አለቆቻቸው አብስረዋል፡፡ “የባድመ ድል አብሳሪ” አቶ ስዩም በዚህ ብቻ አላበቁም፤ “በመልካም እምነት የሚፈረሙ የሰላም ስምምነቶች በርካታዎች ናቸው፤ ተሳክቶላቸው ተግባራዊ የሚሆኑት ግን ጥቂት፣ በጣም ጥቂቶች ናቸው … በደቡብ ሱዳን ግን ይህ እንዲሆን አንሻም” አሉ፡፡ ምክርም አከሉበት፤ ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን ነጥቦች ጠቀሱ “በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉትን በሺዎች የሚቆጠሩትን መልሳችሁ አቋቁሙ፤ የፖለቲካ ውይይቱን በመቀጠል ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ዕርቅ እንዲሆን እንሠራለን” አሉ፡፡ ከሳዑዲ አረቢያ ከተፈናቀሉት ኢትዮጵያውያን ጋር አብሮ ምሳ በመብላት መልሶ የማቋቋም ችሎታቸውን ያስመሰከሩት ቴድሮስ አድሃኖምም ከልምድ የምክሩ ተካፋይና አካፋይ ነበሩ፡፡
የፊርማ ቀለሙ ገና ሳይደርቅ ሁለቱም ወገኖች መካሰሳቸውን ቀጥለዋል፡፡ በተለይ የሳልቫ ኪር ወታደሮች ስምምነቱን እንደ ጊዜ መግዢያ በማድረግ ኃይላቸውን አጠናክረው መልሶ በማጥቃት በአብዛኛው የነዳጅ ቦታዎችን የተቆጣጠረውን የሬክ ማቻርን ኃይል እየደበደቡ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ የማቻር ኃይሎችም አጸፋ በመስጠት ጥቃቱ በጥቃት በመመለስ ጦርነቱን ቀጥለዋል፡፡ ከናይጄሪያና አንጎላ በመቀጠል ከሰሃራ በታች ካሉት አገራት በነዳጅ ክምችት ቀዳሚ የሆነችው ደቡብ ሱዳን በጎሣ ፖለቲካ እየነደደች ነው፤ ምድሪቱም ዳግም እያለቀሰች ነው፡፡Children displaced by the fighting in Bor county, who have just arrived, are standing on the side of a boat in the port in Minkaman
ቻይናን ለመምታት የተነደፈው የምዕራባውያን ዕቅድም እየሠራ ነው፡፡ በውጤቱም የሌሎች አገራት ነዳጅ ድርጅቶች መራራውን ጽዋ እየጠጡ ነው፡፡ የቻይናው ብሔራዊ የፔትሮሊየም ኮርፖሬሽን ጨምሮ የሕንዱ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ኮርፖሬሽን በራቸውን ቆልፈው ሠራተኞቻቸውን ከደቡብ ሱዳን አስወጥተዋል፡፡
ከዲንካ፣ ኑዌር፣ ወዘተ ጎሣዎች አልፎ ለበርካታ አገራት የሚበቃ ነዳጅ ያላት ደቡብ ሱዳን በጭፍን ጎሠኝነት መርዝ ተነድፋ ለምዕራባውያን መጠቀሚያ ሆናለች፡፡ ነጻነት የናፈቀው ሕዝቧም ለማያቋርጥ ስደትና ሰቆቃ ተጋልጦዋል፡፡ ከጎሠኝነት ወደ ሰብዓዊነት ከማደግ ይልቅ ወደ ቤተሰብ ደረጃ መጥበብ፤ በነጻ አውጪነት ተነስቶ በሆደ ሰፊነት አገር ከመምራት ይልቅ የምዕራባውያን አሽከርና መጠቀሚያ መሆን ውጤቱ ምን እንደሚሆን ደቡብ ሱዳን ጥሩ ትምህርት ትሰጣለች፡፡
እንዲህ ያለውን ውጤት ለማየት እንደ ደቡብ ሱዳን ሁለት ዓመታት ብቻ ሊወስድ ይችላል፡፡ “ይህንን አልፈናል” በማለት ጭንቅላታቸው ላበጠባቸው ደግሞ ሁለት ዓስርተ ዓመታት ይወስድ ይሆናል፡፡ የቱንም ያህል ዘመን ይውሰድ ለአንድ ጎሣ ወይም ዘር የበላይነት መቆም በሌሎች ተበዳዮች ዘንድ ቂም ከማስቋጠር አልፎ የምዕራባውያን አሽከርና መጠቀሚያ የሚደርግ ሲሆን “መብቱ አስከብራለሁ” ያሉትን ዘር መልሶ ለሰቆቃ መዳረግም ነው፡፡
dinka nuerደቡብ ሱዳን ያላትን ሃብት በቅጡ ሳትጠቀም እዚህ ደርሳለች፡፡ ሳልቫ ኪርና ሬክ ማቻር በአምባገነኖችና በምዕራባውያን አስመሳይ ሸምጋዮች አደራዳሪነት ሳይሆን በማንዴላ ዓይነት ሆደሰፊነት የወደፊቱን ትውልድ በማሰብ በእውነተኛ ዕርቅ ላይ የተመሠረተ ሰላም ማምጣት ካልቻሉ የዘረኝነታቸውን ውጤት በገሃድ ያገኙታል፡፡ “መብቱን አስከብራለሁ” ብለው የተነሱለትን ጎሣ/ዘር የሚያዋረድና አንገት አስደፍቶ ለትውልድ የሚዘልቅ ታሪክ ይተዋሉ፡፡ አዲሷ አገር ደቡብ ሱዳንም ኅልውናዋ ከስሞ ዲንካ እና ኑዌር የተባሉ “አገራት” በመሆን የአፍሪካ “ኅብረትን” ይቀላቀላሉ፡፡ የጎሣ ፖለቲካው አዙሪትም ወደ አውራጃና ቤተሰብ ደረጃ እየጠበበ መድረሻ ወደሌለው አዘቅት ይወርዳል፡፡

No comments:

Post a Comment