Translate

Wednesday, January 1, 2014

አዲሱ 2014 አመት በዱባይ፣ በባህሬንና በሳውዲ

የማለዳ ወግ

ነቢዩ ሲራክ
* ዱባይ በአስደናቂ 400 ሽህ ርችቶች አለምን አስደመመች!
* እፁብ ድንቅ ርችቶች የአለምን ሪኮርድ ሰብረዋልም ተብሏል
* ሳውዲና ባህሬንን በሚያገናኘው ድልድይ ተጨናንቋል
* እኛም እያዘንን ለመደሰት በመሞከር ላይ ነን
ከአመታት በፊት 828 ሜትር እርዝመት ያለው የቡርጅ ከሊፋን ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በመገንባት የአለምን ሪኮርድ የሰበሩት ኢምሬቶች ዛሬ በጀመርነው አዲሱ አመት 400 ሽህ እፁብ ድንቅ በህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ርችቶች ወደ ሰማይ በማጎን በኮዌት ተይዞ የነበረው 77,282 የአለም ሪኮርድ በመስበር በአዲሱ 2014 አመት አዲስ ሪኮርድ ተቀዳጅታለች። በኢምሬት አንብርት በዱባይ ሚሊዮኖች ያየነው የሰማዩን ውብና ድንቅ ርችት ብቻ አልነበረም ። በመላ ከተማዋ በሚገኙት ሰማይ ጠቀስ ፎቆቿና መዝናኛ ቦታወች እየተነሱ በምድር ለምድር በመምዘግዘግ በሰው ሰራሽ ሃይቆችና በሚያምሩት ህንጻዎች ተስፈንጥረው የሚወጡት ዘመነኛ የሌዘር ህብረ ቀለማትን የተላበሱ ርችቶች እና መብራቶች በእርግጥም አረቧ ሃገር ኢምሬት የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ በገሃድ የሚያሳይ ነበር ማለት ይቻላል።
በዘንባባ ቅርጽ በተገነባውና የአለማችን ታዋቂ ሰዎች በከተሙበት የጀማርያህ የባህር ዳርቻዎችና በደሴቶች ፣ ብረት ቀልጦ እንደ ልብስ ጥበብ በአስደናቂ ስነ ህንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ሰማይ ጠቀሱ ቡርጅ ከሊፋ እና የቡርጅ አል አረብ ህንጻዎችም ዛሬ የአለምን አይን አማልለው ማምሸታቸው እውነት ነው። በከተማዋ ዙሪያ ገብ በተሰሩት ህንጻና ሰው ሰራሽ ባህሮች እየተስፈነጠሩ ወደ ሰማይ የሚወረወሩት ፣ ወደ ጎን ፣ወደ ላይ ወደ ታች የሚተጣጠፉት መብራቶች ብቻ አልበሩም ። ውሃው በድቅድቁ ጨለማ ከመብራት ተዋህዶ አይንን ሲያማልል ሲፈስ ፣ ሲለው ዝም ጭጭ ሲል በአረብቸኛ ባህላዊ የካልጅ ዝማሬ ቅላጼ ታጅቦ መሆኑ የሰው ልጅን መዘመን ምጥቀቱን ሲያሳብቅ ውሃና ሌዘር ተወንጫፊ መብራቶች እጥፍ ዘርጋ ሲል ጉድ በዱባይ ያየነው በአዲሱ አመት ዛሬ ነበር ። ግዑዙ ፈሳሽ ውሃ በቧንቧ እየተፈናጠረ ከመብራት ጋር ተዋህዲ እንደ ግብጽ “ረጋሳዎች “ዳንሰኞች ሲያረገርግ መመልከት በእርግጥም “ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ ” አለ ያስብላል!New year 2014 in Dubay, Saudi Arabia
ከእኔ ቢጤው ደካማ ገቢ ካለው እስከ ናጠጠው ሃብታም አረቦች አዲሱን አመት ለመቀበል የኢምሬቷን እንብርት ዱባይን ከአፍ እስከ ደገፏ ጢቅ አድርገው ሞልተዋታል። ዱባይ የፈረንጆችን የዘመን መለወጫ ቀምታ ለራሷ አድርጋው ዛሬ አይተናል። እንዲህ አድርገው እንዲህ ሆነው አጅብ ተያሰኙን የዱባይ ስልጡን አረቦች ሰማይ ምድር ባህሯን በህብረ ቀለማት ርችቶች አድምቃ እና በባህላዊ የከልጅ ጣህመ ዜማ አዲስ ታሪክ ሲያስመዘግቡ የፈረንጆቹን ቴክኖሎጅን በገንዘባቸው ገዝተው ቢሆንም ዛሬ ከሸጡላት ስልጡን ሃገራት ደምቀው ፣ ተውበው ተአምርን ለአለም በማስመስከር “የአረቦች ኒዮርክ !” ተብላ በአረቦች የምትንቆለጳጰሰው ዱባይ አዲሱን አመት እንዲህ ጀመራዋለች!
በሳውዲየከተሙ ፣ ዱባይ መሄዱ ያልቀናቸው ወደ ጎረቤት ባህሬን እየጎረፉ ሲሆን ቀይ ባህርን ሰንጥቆ ሳውዲና ባህሬንን በሚያገናኘው በደማም በኩል የተዘረጋውን ድልድይ አጨናንቀውት ማምሸታቸውን የሳውዲ መገናኛ ብዙሃን ዘግበውታል ። ምክንያቱ ባህሬን ከሳውዲ በውበት ደምቃ አይደለም ! ብዙዎች ሳውዲ የሚከለከሉትን ዳንኪራ ቤትና ፈሳሿን ” ቅብአ ቅዱሷን!” እዚያ በነጻነት እየተጎነጩ ነፍሳቸውን የሚያስደስቱባት ባህሬን ብቸኛ አንጻራዊ ነጻነት የምታስተናግድ የቅርብ ጎረቤት ናትና ነው ብለን እንገምት:)
ብዙሃኑ ሃበሻም ባይሆን እኔ እና መሰሎቸ በየአቅጣጫው የወገንን ጭንቅ ፣ ስጋት ሮሮ እየሰማን ፣ ግማሽ ጎናችን ታሞ ግማሹን በአዲስ አመት ትፍስህት በተስፋ ለመቀበል እያዘንን ለመሳቅ በመሞከር ደመቅመቅ ብለን አዲሱን አመት ” እንኳን ደህና መጣህ!” ብለነዋን! …ህይዎት እንዲህ ናት!
መልካም አዲስ አመት!

No comments:

Post a Comment