Translate

Friday, January 24, 2014

ሌንጮ ከኦነግ እስከ ኦዴግ


በዘሪሁን ሙሉጌታ
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ) የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ መሆኑ በሰፊው ሲዘገብ ቆይቷል። አቶ ሌንጮ ከኦሮሞ ሊሂቃን አንዱ ከመሆናቸው ባለፈ “ትግሉን ወደ ሀገር ቤት ማስገባት” በሚል መርህ ከኦነግ ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት አቋቁመዋል።
አቶ ሌንጮ ያቋቋሙት ድርጅት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) የሚባል ነው። ድርጅቱ በውጪ ሀገር ቢመሰረትም በኢትዮጵያ ውስጥ ሕጋዊ እውቅና ሊኖረው የሚችለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ሲመዘገብ ብቻ ነው። አቶ ሌንጮ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፣ አልመጡም የሚለው ጉዳይ ለጊዜው ግልፅ አይደለም። ግልፅ የሆነው ጉዳይ አቶ ሌንጮና የመሠረቱት ድርጅት ወደ ኢትዮጵያ የመምጣት ሀሳብ ያለው መሆኑ ብቻ ነው። ይሄም የተረጋገጠው የድርጅቱ መሪ አቶ ሌንጮ ለታም ሆኑ፤ የድርጅቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሌንጮ ባቲ በግልፅ “ትግሉን ወደ ሕዝቡ እናስገባለን” ማለታቸው ነው። 
አቶ ሌንጮም ሆኑ ጓደኞቻቸው “ትግሉን ወደ ኢትዮጵያ እናስገባለን” ከማለት ባለፈ እንዴት? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ አልመለሱም። ይሄው መሠረታዊ ጥያቄ ባለመመለሱም በብዙዎች ዘንድ መላምታዊ አስተያየት እንዲሰጥ አስገድደዋል። የኦዴግ ቃል አቀባይ “ስንገባ ሁሉንም እንናገራለን” ከማለት ባለፈ የአገባባቸውን እንዴትነት “ሾላ በድፍን” አድርገውታል። 
የኦዴግ አገባብ ለጊዜው ምስጢራዊ ቢመስልም፤ አንድ ነገር መገመት ይቻላል። እሱም ኦዴግ [የአቶ ሌንጮ ድርጅት] ኢህአዴግ ሁልጊዜ በቅድመሁኔታነት የሚያስቀምጠውን “ሕገ-መንግስቱን መቀበል” የሚለውን ቅድመ ሁኔታ መቀበል፤ በሌላ በኩል ደገሞ እነ ሌንጮ ለታ በኢትዮጵያ ፓርላማ “ሽብርተኛ” ከተባለው ኦነግ በይፋ ጋብቻቸውን በመቅደዳቸው ሕገ-መንግስቱን “በቅድሚያ ተቀበሉ” የሚለውን የኢህአዴግን ቅድመ ሁኔታ ላይቀርብላቸው እንደሚችል መገመት ይቻላል። ይሁን እንጂ ጉዳዩ በቅድመ ሁኔታ ቀረበም፣ አልቀረበም አቶ ሌንጮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎአቸው እስከቀጠለ ድረስ ሕገ-መንግስቱን አክብረው፣ በሰላማዊ መንገድ መቀጠል የውዴታ ግዴታቸው ይሆናል ማለት ነው። 

ሌንጮ ለምን አሁን?
አቶ ሌንጮ ለታ እና ኦነግ፤ ኦነግና ሌንጮ ለታ በአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታነታቸው የሚታወቁ ናቸው። ሌንጮ ኦነግ እያሉ ኢትዮጵያዊ ለመባል ድርድር እስከመጠየቅ የደረሱ ፖለቲከኛ ነበሩ። ኦነግ ለሁለትና ቀጥሎም ለሦስት እስከተከፈለበት ድረስ ከድርጅቱ ዓይን አመራሮች አንዱ ነበሩ። ነገር ግን ኦነግ የያዘው ዓላማ በመዳፉ ላይ መሟሸሹና የአመራሩም ሽኩቻ በፈጠረው ትርምስ ለሦስት ለመከፈል ተገዷል። 
ለሦስት ከተከፈለው ኦነግ መካከል አስመራ “በቁም ታስሯል” የሚባለው አንዱ ነው። ይህ ኦነግ በዳውድ ኢብሳ የሚመራ እንደሆነ ይነገራል። ሁለተኛው ኦነግ ደግሞ በብርጋዴል ጄኔራል ከማል ገልቹ የሚመራው ሲሆን፤ ይህ አንጃ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ወደሚመሩት ግንቦት ሰባት ጋር መግባቱ ሲዘገብ ከርሟል። በሦስተኝነት ሲፈረጅ የነበረው የእነ ሌንጮ ለታ ኦነግ ነው። ይህ ቡድን በኦነግነቱ መቀጠል ባለመቻሉ ወይም ባለመፈለጉ “ኦዴግ” በሚል ጥላ በመሰባሰብ ወደ ሀገር ቤት መመለሱን መርጧል። 
ኦነግ እንደ ኦነግ ለ40 ዓመታት ያህል የኦሮሞን ሕዝብ “ነፃ ለማውጣት” በሚል መርህ ሲንቀሳቀስ ቢቆይም ውጤቱ የማታ ማታ ከአንድነት ወደ ሦስትነት እንዲለወጥ አስገድዶታል። የኦነግ ዓላማና የትግል ግብ ውጤታማ አለመሆኑ የገባቸው እነ ሌንጮና በውጪ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጅ ምሁራንም የኦሮሞ የውይይት መድረክ (Oromo Dialogue Forum) የተባለ ከፖለቲካ “ነፃ” የሚመስል መድረክ በማቋቋም ለመሰባሰብ ጥረት አድርገዋል። ይህም ስብስብ በበርካታ የፖለቲካ ጥያቄዎች ወዲያና ወዲህ ሲላጋ በመቆየቱ በተፈለገው መጠን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል። 
ለኦሮሞ የውይይት መድረክ (DDF) መመስረት የኦነግ መሰነጣጠቅ በር የከፈተ ጉዳይ ነው። ጄነራል ከማል ገልቹ አንድ መቶ የሚሆኑ ወታደሮችን ወደ ኤርትራ ይዘው ከኮበለሉ በኋላ ከኦነግ በመውጣት ‘Jijiirama Koree Yeroo’ በግርድፍ ትርጉሙ “ጊዜአዊ የለውጥ ኮሚቴ” የሚል ነገር ማቀንቀን ጀመሩ። ይህንን ተከትሎ ሌላኛው የኦነግ ቁልፍ አመራር ኦነግን እየተው በJijiirama (ለውጥ) ስብሰባዎች ላይ መታየት ጀመሩ። ሌንጮ ለታ ደግሞ ሁለቱንም ያለመሆን ጠርዘኛ አቋምን ማራመድ ቀጠሉ። ሌሎች አመራሮች ደግሞ ኦነግን በቁሙ እንደ ምስጥ ሊበላው ነው ብለው በማሰብ የነጄነራል ከማልን የለውጥ (Jijiirama) አካሄድ በህቡዕ ለማፍረስ ማሴር ጀመሩ። በዚህ ወቅት በቦረና በኩል ሲንቀሳቀስ የነበረን 100 የኦነግ ታጣቂ የያዙ አንድ ከፍተኛ የኦነግ አመራር በመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ቀርበው እጅ መስጠታቸውን አወጁ። 
በ2002 ዓ.ም ኦነግ በውስጥና በውጪ፣ በሲቪሉና በወታደራዊ አደረጃጀቱ ትርምስ ውስጥ የገባበት አጋጣሚ እንደነበር ተገለፀ። ይባስ ብሎም እነ ጄነራል ከማል ገልቹ እና ኮሎኔል ኃይሉ ጎንፋ እየታገሉ ያሉት ለኦሮሞ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ አወጁ። ይህን ተከትሎ የJijiirama ቡድን ወደተለያዩ አንጃዎች ተከፈለ። እነ ጄኔራል ከማል “ከግንቦት 7” ጋር አዲስ ፍቅር ውስጥ ወደቁ። ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያዊነታቸውን ከሚያራምዱት (Ethiopianist) የኦሮሞ ተወላጆች ኦሮሞ ነን የሚሉ አንጃዎች እያኮረፉ መውጣት ቀጠሉ። 
እ.ኤ.አ በ2011 ጠርዝ ጠርዙን ሲጓዙ የነበሩት አቶ ሌንጮ ለታ ከዲስፒሊን ጋር በተያያዘ ከኦነግ አመራርነታቸው ተባረሩ። ከተባረሩ በኋላ ቀደም ሲል በእነ ጀነራል ከማል ገልቹ ተጠንስሶ ወደነበረው የኦሮሞ ውይይት መድረክ (ODF) ስር ተሰባሰቡ። ODF ከኦነግ አኩርፈው በወጡ ወይም በተባረሩ ሌንጮ ለታ፣ ሌንጮ ባቲ፣ ዲማ ነገዎ፣ ሀሰን ሁሴን እና በያን አሶቦ እንደገና መንቀሳቀስ ጀመረ። ይሄው ቡድን ነፃ ማኅበርነቱ በማጠራጠሩ አንዳንድ ወገኖች ጥያቄ ማንሳታቸውም አልቀረም። “ነፃ” ነኝ የሚለው ይሄው የኦሮሞ የልሂቃን ቡደን ቀደም ሲል ኦነግ ከያዘው “የኦሮምያ ሪፐብሊክ” ከሚለው የመገንጠል ጥያቄ በተቃራኒ የኦሮሞ ሕዝብ የነፃነት ትግል በኢትዮጵያዊነት አጠቃላይ ቅኝት ውስጥ መታየት አለበት የሚልን (Ethiopianist) አቋም ይንፀባረቅበት ጀመር። 
ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ አቶ ሌንጮ ለታ የእራሳቸውን ፓርቲ መሰረቱ አቶ ሌንጮ (አንበሳው) ቋሚ ኑሮአቸው ኖርዌይ ቢሆንም፤ በአሜሪካና ካናዳ የሚገኙ የብሔሩን ተወላጆች በማሰባሰብ ፓርቲው መመስረታቸው እየተነገረ ነው። 
የአቶ ሌንጮ ፓርት መስርቶ ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ጉዳይ ከኦነግ መዳከምና የአመራር ሽኩቻ ጋር በተገናኘ ተስፋ ለቆረጡ ለክልሉ ተወላጆች ጥሩ አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም እየተገመተ ነው። 
የአቶ ሌንጮ መምጣት በኦህዴድ ላይ የሚኖረው ጫና 
የአቶ ሌንጮ ለታ ፓርቲ መስርቶ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ካሉት አንደምታዎች አንዱ በኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ላይ የሚፈጥረው ጫና ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ነው። የአቶ ሌንጮ አሰላለፍ ለጊዜው ግልፅ ባይሆንም በማንኛውም ሁኔታ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም። አንዳንዶች የአቶ ሌንጮን አመጣጥ እጅ እንደመስጠት ቢቆጥሩትም ከጀርባው ግን ያልተጠበቀ የፖለቲካ ሴራ (Political Conspiracy) መፍጠሩ አይቀርም። 
ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ያነጋገርናቸው አንድ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራር የእነ ሌንጮ ወደ ሀገር ቤት መምጣት በድርጅቱ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ የለም ይላሉ። እንዲያውም መምጣታቸው እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር በሰላማዊ መንገድ የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከር ጠቃሚ ናቸው። “እነሱ ድንጋይ እንወርውር እስካላሉ፣ ሕዝብ ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ እስከታገሉ ድረስ በሆደሰፊነት እንቀበላቸዋለን” ብለዋል ስሜ አይጠቀስ ያሉ የኦህዴድ አመራር። 
“ፍርዱ የኦሮሞ ሕዝብ ነው። የኦሮሞ ሕዝብ የሰራለትንና ያልሰራለትን ያውቃል። እነ ሌንጮ የኦሮሞ ሕዝብ አጀንዳ ቢይዙም እስካሁን ምን አይነት ውጤት እንዳመጡ የኦሮሞ ሕዝብ ያውቃል” የሚሉት አመራሩ ከፖለቲካ ትግል አንፃር የእነ ሌንጮ መምጣት መልካም ዕድል (Opportunity) ነው ይላሉ። እነሌንጮ ከሕዝብ ተነጥለው የትም እንደማይደርሱ አውቀው ወደ ሕዝቡ መምጣታቸው ጥሩ ነው። በእኛ በኩል ማንም መጣ ማንም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እስከሆነ ድረስ ምንም ስጋት የለብንም ብለዋል። 
“ኦነግ አሜባ ሆኗል። የአሜባ ሴል በየቀኑ ሲበጣጠስ ይውላል። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ጽኑ አላማ ካለው እንደዚህ አይሆንም። ኦነግ የፀረ-ዴሞክራሲ ድርጅት በመሆኑም እርስ በርስ ሲታገሉ ቆይተዋል እንጂ ለኦሮሞ ሕዝብ አልታገሉም” የሚሉት አመራሩ ኦነግ ያነገበው የመገንጠል አቅጣጫና ዓላማን በኃይል የማስፈፀም እንዲሁም ተነጥሎ ለብቻ የመኖር ፍላጎት ያከተመበት ጊዜ ስለሆነ የወደፊት ተስፋቸው ጨልሟል ሲሉ ተናግረዋል። 
ለኦህዴድ አሁን አደጋው ኦነግ ሳይሆን የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካ እንደሆነ የሚጠቅሱት አመራሩ ኦህዴድን የሚያሰጋው ከራሱ የሚመነጭ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የበላይነት ነው። የስርዓቱም አደጋው ይሄ ነው። ይሄንንም እነ ኦነግ ነግረውን ሳይሆን በራሳችን ላይ ባደረግነው ፍተሻ ነው። ኦህዴድ በውስጥ ጥራቱ ላይ ትኩረት አድርጓል። ግንባርቀደሞችንም በማሰልጠን እያበቃ ሕዝቡም ሙስናን መሸከም እንደማይችል አምኖ እየተፋለመ ነው። የድርጅት፣ የሕዝብና የመንግስት ክንፍ በማዋቀር ድርጅቱ እራሱን እያነጠረና እያጣራ ነው። ድርጅቱ እያበቃቸው ያሉ ግንባር ቀደም አመራሮች ለእኛ እንደተዋጋ ሰራዊት ናቸው። በተመሳሳይም የልማት ሰራዊት ናቸው በማለት የድርጅቱ አደጋ የውጪ ሳይሆን የውስጥ አደጋ ነው ብለዋል።
ኦህዴድ በኦሮሞ ሕዝብ ተወልዶ እያደገ ያለ ድርጅት መሆኑን የጠቀሱት አመራሩ ድርጅቱ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ ለፍትሐዊ የሐብት ክፍፍልና የብሔር ጭቆና ለማስወገድ የታገለ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰዋል። በአንፃሩ ኦነግ ፈረንጆች እንደሚሉት ኦነግ የተግባር ባዶ የቃል ጩኸት (Vocal Forca Pary) ሆኖ የቆየ ስልቱም በጩኸትና በማናጋት ላይ የተመሰረተ ድርጅት ነው። ከዚህ ባሻገር የኦሮሞ ሕዝብ ተገንጥሎ መኖር አለበት የሚለው የተረትተረት ድርጅት እንደነበር ማሳያ ነው ሲሉ የኦነግን አስተሳሰብ አጣጥለዋል። 
የሌንጮ አመጣጥ በሌሎች የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች እይታ 
የሌንጮ ለታ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት በአዎንታዊ ጎኑ ካዩት መካከል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንዱ ናቸው። አቶ ቡልቻ የተበታተኑ የኦሮሞ ድርጅቶች አንድ ላይ መታገል ይኖርባቸዋል ብለዋል። “ኦሮምያን መገንጠል” የሚለው የኦነግ ዓላማ ጊዜው ያለፈበት ይመስልዎታል ተብለው ለተጠየቁት “መቼም ጊዜ አልነበረውም። ፖለቲካ የሚባል ነገር በጆሮዬ ከሰማሁ ጊዜ ጀምሮ እንደዚህ አይነት የተሳሳተ አስተሳሰብ ሰምቼ አላውቅም። ኦሮሞ የሆነን ሁሉ ብትጠይቅ ማንም ሰው ሀገሩን ትቶ ሌላ ሀገር እፈልጋለሁ የሚል አታገኝም። ኢትዮጵያ ማን ሆና ነው ኦሮሞ የሚገነጠለው። እኛ ኩሩ ኢትዮጵያውያን ነን” ብለዋል። 
እነ ሌንጮ መጥተው ኦህዴድ ስር የሚገቡ ከሆነ የኦህዴድ መንገድ የትም እንደማያደርስ ማወቅ አለባቸው የሚሉት አቶ ቡልቻ እውነተኛ ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉ ከሆነ በአጭር ጊዜ ጠንካራ የኦሮሞ ፓርቲ መመስረት ይችላሉ። ከዚህ ውጪ የኦህዴድ መስመር የትም አያደርስም ብለዋል። “የኦሮሞ ሕዝብ የሀብት፣ የፖለቲካና ወታደሪዊ ተሳትፎው በሕዝቡ ብዛትና በቆዳ ስፋት ልክ ተግባራዊ መሆን አለበት። በአሁኑ ወቅት የብሔር የበላይነት ባይኖርም፤ ኢህአዴግ የሚባል የቡድን የበላይነት ነው። ይህ ቡደን መልኩ በደንብ ግልፅ ሆኖ የማይታወቅ ደብዘዝ ያለ ቡድን ነው። ይህ ቡድን ደግሞ የኦሮሞንም የኢትዮጵያንም ሀብት የተቆጣጠረው” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የእነ ሌንጮ መጥተው የሚሰሩት ስራ ሳይታይ አስተያየት መስጠት አስቸጋሪ ነው ይላሉ። የእነ ሌንጮ ለታ መምጣት ትልቅ የፖለቲካ ውሳኔ አይደለም። ትልቁ ውሳኔ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ምህዳር ይኖራል አይኖርም የሚለው ነው ብለዋል። የእነሌንጮ አመጣጥ መንግስትን ለማጠናከር ወይስ ተቃዋሚ የሚለው መለየት አለበት ብለዋል። እነ ሌንጮ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት ብዙ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት ሁኔታ ነው ብለዋል። 
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም የእነ ሌንጮ መምጣትን በአወንታዊ ጎኑ ተመልክተዋል። “እንገንጠል ወይም አንገንጠል” የሚለው የኦነግ አመለካከት በሕዝብ ውሳኔ የሚታወቅ ቢሆንም፤ እንደ ድርጅት ይሄንን አቋም ይዞ መሄዱ ውጤታማ አለማድረጉንም አስረድተዋል። ያም ሆኖ የእነ ሌንጮ መምጣት ኦህዴድ፣ የኢትዮጵያ ብሔረተኞችንና ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶተን ሊያስደነግጥ ይችላል ብለዋል። በኦነግ አስተሳሰብ ውስጥ ለቀሩት ደግሞ የቁጭት ስሜት ሊያሳድር እንደሚችልም ተናግረዋል። 
የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑት ኢንጂነር ዘለቀ ረዲ በበኩላቸው አቶ ሌንጮ ለታ በሰላማዊ ትግል ለውጥ ይመጣል ብለው ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው የሰላማዊ ትግል ደጋፊዎችን የሚያስደስትና የሚበረታታም ነው ይላሉ። ሌላው የአቶ ሌንጮ መመለስ “እገነጠላለሁ” የሚለው የኦነግ አመለካከት እየመሸበት መምጣቱን የሚያመለክት እንደሆነም ተናግረዋል። “የኦሮሞ ብሔር የዚህ ሀገር ባለቤት መሆኑና ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተባብሮ ይህቺን ሀገር መገንባቱን አምነው ወደዚህ ሀገር መምጣታቸው የሚያስመሰግናቸው ተግባር ነው” ሲሉ ተናግረዋል። የእሳቸው መምጣት የሀገር አንድነተን ደጋግመው ለሚሰብኩ ኃይሎች ጥረታቸው አዎንታዊ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል። 
“ኢትዮጵያ የኦሮሞ ብቻ አይደለችም። ኦሮሞም ከኢትዮጵያ ተነጥሎ ብቻውን የሚኖር ሕዝብ አይደለም” የሚሉት ኢንጂነር ዘለቀ ለሁሉም የምትሆን ጠንካራ ኢትዮጵያን ከመፍጠር አንፃር የእነ ሌንጮ መምጣት ተገቢና የሚበረታታ ነው ብለዋል። 
ኦነግ ከጅምሩ ሲነሳ ግንድን የመገንጠልን አቅጣጫ ይዞ በመነሳቱ አስተሳሰቡ ተዳክሟል የሚሉት ኢንጂነር በደም የተሳሰረን ሕዝብ ለመለያየት መነሳቱ ድርጅቱን ዋጋ እንዳስከፈለው ይገልፃሉ። አሁንም “Ormo First” በማለት ተነስተው መልሰው “Muslem First” በማለት ከኦነግ በባሰ ስህተት ውስጥ በመግባት በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ የሃይማኖት ክፍፍል በመፍጠር ሲጣጣሩ ይታያል ብለዋል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ የመነጣጠል አጀንዳ ይዞ የተነሳ ድርጅት ውጤታማ ሲሆን እንዳልታየም ገልፀው በዚህ ረገድ እነ ሌንጮ እውነታውን ዘግይተውም ቢሆን በመቀበላቸው ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ አጠቃለዋል።

No comments:

Post a Comment