Translate

Tuesday, November 12, 2013

በሳዑዲ አረብያ የመከራ ማጥ ውስጥ ላሉት ወገኖቻችን ሲባል ፈጥነን እንነሳ!

ዳኛቸው ቢያድግልኝ

Protest at Saudi Arabia Mission to United Nations!
እንደ ሰው አንድ የሚያደርገን ባሕርይ፣ እንደ ኢትዮጵያዊነትም ሁላችንንም የሚመለከተንና የፖለቲካም ሆነ የሃይማኖት ልዩነት የማይነጣጥለው በደል በሳዑዲ አረብያ ግዛት እየተፈጸመ ነው።
የጥቃት ዒላማዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የጥቃቱ ልክ የለሽነትና አሰቃቂነት ደግሞ ይበልጥ የጎላው በሴት እህቶቻችን ላይ ነው። ይህ ዛሬ በሳዑዲ አረብያ የሚደረገው ጥቃትን ማስቆምና ቁጣችን መቆምያ እንደማይኖረው ማሳየት ለነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሳችን ደህንነትም ጭምር የምናደርገው ነው። ምክንያቱም ነገ ተመሳሳይ ጥቃትና በደል በመላው አለም ይስፋፋል። በአፍሪካ ሀገሮች የተበተኑ ኢትዮጵያን ከሶማሌና ኤርትራ ከሚሰደዱት በተለየ ይዘረፋሉ፣ ይደፈራሉ ይዋረዳሉ። እንደ አገር ልጅ አብረው እንዳይቆሙ በዘር በሀይማኖትና በፖለቲካ አቋም ምክንየት የተበተኑ ናቸው። ለሰላሳና አርባ አመት አምባገነኖች ያደረጉት ጭፈጨፋና በደል ፍርሃትን ሰማይ ጥግ አውጥቶታል። እናም ኢትዮጵያዊ በየተበተነበት ሁሉ ተኛ ሲሉት የሚተኛ አውልቅ ሲሉት እርቃኑን የሚቆም ፈሪ እንዲሆን ተደርጓል። ሲቸግረው የሚጮኸውን ያህል ሲመቸው ለወገን የሚደርሰው ጥቂቱ ነው። ይህ ሊቀጥል አይገባም!
ቀደም ባለው ጊዜ አንድ ኢትዮጵያዊ ጥቃት ቢደርስበት ባገኘው መሳርያ ዘነጣጥሎም ቢሆን ይገድል ስለነበር ማንም አይደፍረውም ነበር። በዘመነ ኮሎኒያሊዝም ኢትዮጵያውያን በሄዱበት ሁሉ አንገት የማይደፉና ክብራቸውን የማያስነኩ ነበሩ። ዛሬ ጠቁመው የሚያስይዙ፣ ወገናቸውን የሚያሻሽጡና የሚሰልሉት ሁሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው። የዚህ ጽሁፍ መነሻም ሆነ መድረሻው የድሮውን አሁን እየሆነ ካለው ጋር ማወዳደር አይደለም። ለዚህ የሚሆን የቅንጦት ጊዜም የለንም። ዓላማው አሁን እየደረሰብን ያለውን በደል በቁርጠኛነት አንታገለው ነው። ይህ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ ከዳር እስከዳር ማስነሳት ካልቻለና ቁጣቸውንም ለመላው አለም ማሳየት ካልቻለ እውነትም አገራችን እያበቃላት ነው ማለት ይቻላል።
የዱር አውሬ እንኳን ከዚህ የተሻለ ክብር አለው። እነዚህ አጅግ ሁዋላ ቀር የሆኑ አረመኔዎች ከእንስሳ እንኳን አንሰው አንዲት በፍርሃት ነብሷን የሳተችን ሴት አስር ሆነው የሚደፍሩትን እያየን የተደፈሩት ህጋዊ ናቸው ህገወጥ የሚል የሕግ አንቀጽ መረጣ ውስጥ ልንገባስ እንዴት ይቻለናል? በመላው አለም ያለ የሳዑዲ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ሊደረግና የሳዑዲ ወሮበሎች በወጣት ሴቶች ላይ እያደረሱ ያለው ግፍ በመረጃም ተደገፎ በበራሪ ወረቀትም ተዘጋጅቶ ለአለም ሕዝብ ሊበተን ይገባዋል። ተፈጥሮ ዘይትን ስትቸራቸው አእምሮ ግን እንደነፈገቻቸው ከዚህ በላይ መረጃስ ከየት ይመጣል?
እንደ ትውስታ ከወሰድነው በኬንያ ያሉ ስደተኞች ላይ በደል ይደርስ በነበረበት ወቅት ያ በጨካኝነቱ የሚታወቀው መንግሥሰቱ ሀይለማርያም አንኳን “ኢትዮጵያውያኑ የተሰደዱት የምናራምደውን ፖለቲካ እንጂ ሀገራቸውን ጠልተው አይደለም…” በሚል ኬንያን ማስጠንቀቁን መስማቴ ትዝ ይለኛል። በየወሩ 40 ሺህ ሴቶችን እንልካለን እያለ እንደ እንቁላል በየአረብ ቤቱ ሲያከፋፍል የነበረው መንግስት ዛሬ ዜጎቹ እንዳይሆን መጫወቻ ሲሆኑ ዝም ብሎ መመልከቱ እጅግ የሚያሳዝን ነው። ኢትዮጵያውያኑ ምናልባትም ኤምባሲውን ራሱን መቆጣጠር የሚገባቸው እስኪመስል ያስቆጣል።
በኢትዮጵያዊነት ላይ የተነጣጠረን ክፋት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ካላስቆምነው በሳዑዲ የተጀመረው መረን የጥላቻ ሰደድ ሊቀጣጥል የሚችልና የየሀገሩ የፖለቲካ ኪሳራ ማስተንፈሻ የሚሆነው አገር አጥቶ የተሰደደው ኢትዮጵያዊው ላይ ሁሉ ይሆናል። ይህንን በአስቸኳይ ለመቃወም ያሉ የትግል መንገዶች ሁሉ ክፍት ሊሆኑ ይገባል። እኔ አዘጋጀሁ እኔ ጠራሁ የሚል ደካማ የፖለቲካ ትርፍ ፍለጋ መንቀሳቀስ ሳይሆን ለሰብዓዊ ክብርና የመከራ ማጥ ውስጥ ሆነው የወገን ያለህ ለሚሉት እህት ወንድሞቻችን የድረሱልን ጥሪ ምላሽ እንስጥ። በጣም የሚያሳዝነው አብዛኞቹ ለስራ የሚሄዱት ወጣቶች የትምህርት ደረጃቸው አነስተኛ የሆነና በድህነት ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት የሆነው ይሁን ብለው ከቤታቸው የወጡ ናቸው። አንዳንዶቹም ግሩም እድል አንደሚገጥማቸው በደላላዎች እየተነገራቸው ከቤት ወጥተው የቀሩ ናቸው። ለኒህ አጋር መሆን ለሀገር እንኳን ደንታ ባይኖረን ለነብስ የሚበጅ ስራ ነው። የኢትዮጵያ ኮሙኒቲዎች፣ በኢትዮጵያ ስም የተቋቋሙ የሀይማኖት ማዕከላት፣ ሲቪክ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ለዚህ ዓላማ ቢቻል አደራጆች ካልተቻለም ዋንኛ ተሳታፊዎች ሊሆኑ ይገባል። ይህ በደል እጅ ለእጅ ሊያስተሳስረንና አንድ ላይ እንድንቆም ሊያደርገን የሚችል የጋራ ጉዳይ ነው። ዛሬ ነገ ሳንል በተደራጀና አለም አቀፍ ትኩረት ሊኖረው በሚያስችል አቅሙ እንነሳ ለወገንም አንድረስ።የመከራ ቀናችንን ለማሳጠር እንደ ሕዝብም ከአንገታችን ቀና እንድንል በያለንበት እንትጋ!
biyadegelgne@hotmail.com

No comments:

Post a Comment