በሳውዲ አረቢያ ውስጥ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሁንምመከራና ስቃይ ላይ ናቸው። የደረጃ ጉዳይ ነው እንጂ ችግሩ በመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የተንሰራፋ ነው። በመላው አለም ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ካለማቋረጥ ያደረገው ወገንና ሀገር አኩሪ ጩኸትና አቤቱታ ችግሩ በአለም ዙሪያ ትኩረት እንዲያገኝ ባያደረግ ኖሮ የወገኖቻችን መከራ ከዚህም በከፋ መልክ ይቀጥል እንደነበር ጥርጥር የለውም። አንድ ቀን እንኳን ለሚገዛው ህዝብ ሀላፊነትና ተጠያቂነት ተሰምቶት የማያውቀው የወያኔ ጉጅሌ መንግስት እግሩን እየጎተተ ቢሆንም ወደ ችግሩ አቅጣጫ እንዲመለከት የተገደደው በዚሁ የወገን ጩኸት መሆኑ ግልጽ ነው።
ወያኔ ስላልቻለ ነው እንጂ ይህንን ከአለም አጽናፍ እስከ አለም አጽናፍ ያስተጋባ የወገን ደራሽ ድምጻችንን አዲስ አበባ ላይ እንደ አደረገው በሃይል ለማፈን ወደኋላ አይልም ነበር።
ሀፍረት የለሾቹ የወያኔ መንግስት ባለስልጣኖች ይህን የተጋለጠ ሀገርና ህዝብ አዋራጅ ተግባራቸውን እና በውሸት የተበከለ ገመናቸውን ለመሸፈን ከዚያም አልፈው የዋሆችን በማታለል የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ የተለመደ ቲያትር መስራቱን ተያይዘውታል። ቴዎድሮስ አድሃኖም ችግሩ ባለበት በሳውዲ መሬት ላይ ሳይሆን የሳውዲ አረቢያ መንግስት በራሱ ወጪ አሳፍሮ ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ባፈሰሳቸው ኢትዮጵያውያን መሃል እየተጎማለለ ያዛኝ ቅቤ አንጓች ቲያትሩን ሲሰራ ትንሽ እንኳን ሀፍረት አይታይበትም።