Translate

Monday, October 7, 2013

መሬት የማን ነው?

ክፍል አንድ - ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

land
የተከሰከሰውና ተፈረካክሶ አፈር የሆነው አጥንትና የወረደው የአያቶችና የቅድማያቶች ደም እየፈሰሰ መሬቱ ላይ በሚገኙ ወንዞች ውስጥ ሁሉ ገብቶአል፤ እንዲያውም እነዚህ ወንዞች ወስደው በቀይ ባሕር፣ በሜዲቴራንያን ባሕርና በሕንድ ውቅያኖስ ጨምረውታል፤
ይህ በአጥንትና በደም የታጠረ መሬት የማን ነው? በመሬቱ ላይ የባለቤትነት መብትን ለማስከበር ከውጭ ኃይሎች ጋር የተጋደሉት ጥንታውያን ነፍጠኞች ቅድሚያን የሚያገኙ ይመስለኛል፤ እነዚህ ጥንታውያን ነፍጠኞች ብቻቸውን አልነበሩም፤ ለምግብ የሚሆናቸውን ሁሉ የሚያመርቱ ገበሬዎች ነበሩ፤ ለልብስ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚፈትሉና የሚሸምኑ ባለሙያዎች ነበሩ፤ ልጆቻቸውን የሚንከባከቡና የሚያሳድጉም ለዘማቹ ምግብ የሚያቀብሉ  እናቶች ነበሩ፤ በአጠቃላይ የሕዝቡን መንፈሳዊ ጤንነት ለመጠበቅ በቤተ ክርስቲያኖችና በመስጊዶች የሚጸልዩ ሰዎች ነበሩ፤ ሰላምን የሚያስከብሩና የሚያስተዳድሩ ሰዎች ነበሩ፤ … አንድ ማኅበረሰብ ለተለያዩ የመደጋገፍ ሥራዎች የሚያስፈልጉት የሰዎች ዓይነት ሁሉ ነበሩ፤ እነዚህ ሰዎች ሁሉ በአንድ ላይ አጥሩን ለመገንባት አስተዋጽኦ አድርገዋል፤ ስለዚህ መሬቱ የእነዚህ ሰዎች ሁሉ ነው።
ታሪካችንን በተግባር በኩል ስንመረምረው ግን መሬቱን እኩል እንዳልተካፈሉት እናያለን፤ ዛሬ ነፍጠኛ የሚባሉት መሣሪያ የታጠቁት ሰዎች ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ እንደሚባለው ሰፋፊ መሬት የመያዝ ዝንባሌ ነበራቸው፤ ነገር ግን ለማረስ የነበራቸው የሰው ጉልበትና የጥንድ በሬ ቁጥር የተወሰነ በመሆኑ ራሱንና ቤተሰቡን ለማስተዳደር ብቻ ለሚፈልገው ገበሬ በቂ መሬት ይደርሰው ነበር፤ ሰፋፊ መሬት የያዙት ጉልበት አጥሮአቸው ሲቸገሩና ትናንሽ ማሳ ያለው ገበሬ ሰብሉ ቀንሶበት ሲቸገር በመጋዞ በማረስ ይረዳዱ ነበር (ገበሬዎችና ከብት አርቢዎችም ላሚቱ ስትወልድ ሴት ከሆነች ለከብት አርቢው፣ የከብት አርቢው ላም ወንድ ስትወልድ ለገበሬው እየተሰጣጡ ይረዳዱ ነበር፤) ሰፋፊ መሬት ያዙትም በጉልበት እጥረት ምክንያት፣ ትናንሽ ማሳ የያዙትም በትንሽነታቸው ምክንያት ከአስፈላጊው በላይ ስለማያመርቱ ትርፍ ምርት ቢኖርም በጣም ትንሽ ነበር፤ ከላይ እሰከታች ያለው ሰው ሁሉ የሚተዳደረው በመሬት ስለነበረ በጣም ጥቂት ለሆኑ ሰዎች (ቀጥቃጮች፣ አንጣሪዎች፣ ሸክላ ሠሪዎች፣ ሸማኔዎች … ወዘተ.) ለጉልበት ዋጋ ከሚከፈለውና ለአስተዳዳሪዎች ከሚከፈለው ግብር በቀር አብዛኛው ምርት ለቤት ፍጆታ ነበር።
እዚህ ላይ በመሬት ጉዳይ ላይ ለመታረም ያስቸገሩ ሁለት ስሕተቶችን ሳላመለክት ለማለፍ አልፈልግም፤ ብዙ ጊዜ እንዲታረሙ ብጥርም ፈረንጆች በብዙ ሰዎች አእምሮ ውስጥ በሙጫ አጣብቀውት ሊፋቅ አልቻለም፤ አንደኛ ገባር ማለት ባለመሬት ማለት ነው እንጂ ጪሰኛ ወይም መሬት የሌለው ሰው ማለት አይደለም፤ መሬት የሌለው ገባር አይባልም፤ መገበር ማለት የባለመሬት ግዳጅ ነው፤ ገባር ማለት ግብር ወይም ታክስ የሚከፍል ባለመሬት ነው፤ ጉዳዩን አጣርተው ያልተገነዘቡት ፈረንጆች በራሳቸው አገር የመሬት ስሪት ዓይነት እንደተረጎሙት ለኢትዮጵያውያን ወጣቶች አስተማሩ፤ እነዚያም ያንኑ እንደገደል ማሚቶ እያስተጋቡ ስሕተቱን አራቡት፤ ‹‹ፊውዳሊዝም›› የሚለው ቃልም ከዚህ ስሕተት ጋር የተያያዘ ነው፤ አውሮፓ የነበረው ፊውዳሊዝም የሚባል ነገር በኢትዮጵያ ኖሮም አያውቅ።
ሁለተኛው ከመሬት ጋር የተያያዘ ቃል ጉልት ነው፤ ጉልት በመሬት ላይ ያለ መብት ሳይሆን በመሬቱ ከፊል ምርት ላይ የተሰጠ መብት ነው፤ ዱሮ ገንዘብ አልነበረምና በጥሬ ገንዘብ የሚከፈል ዋጋ አልነበረም፤ ለወታደሮችም ቢሆን በደመወዝ ፈንታ የሚሰጣቸው ገባሮች ነበሩ፤ ዛሬ ባለመሬቶች በጥሬ ገንዘብ ለመንግሥት ይከፍሉና ገንዘቡ ተሰብስቦ ለወታደሮችም ሆነ ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ይከፈላል፤ ጥንት ግን ግብር ከፋዩን (ማለት ገባሩን) በቀጥታ ከመንግሥት አገልጋዩ ጋር ያገኛኙትና በእህል እንዲቀልበውና በጉልበት እንዲረዳው ይደረግ ነበር፤ ይህ ሥርዓት አልተበላሸም ለማለት አይቻልም፤ ሆኖም የመንግሥት አገልጋዮች በገባሩ መሬት ላይ ምንም መብት አልነበራቸውም፤ እንዲሁም ጉልትየተሰጣቸው የመንግሥት ባለውለታ የሆኑ መሳፍንትና መኳንንት፣ ሴት ወይዘሮዎችም በመሬቱ ላይ ሳይሆን ለመሬቱ በሚከፈለው ግብር ላይ ነበር፤ የጉልት ሥርዓት እያሉ የሚጽፉ ወይም የሚናገሩ ሰዎች አለማወቃቸውን እያራቡ ነው።
የኢትዮጵያን የመሬት ስሪት ውስብስብነት በትንሹም ቢሆን ለመረዳት ሌላ ቢቀር የብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴን ዝክረ ነገር ይመልከቱት፤ የጥንቱን እንተወውና በቅርብ ዓመታት ኢትዮጵያ ከሶማልያ ጋር ቢያንስ ሁለት ጊዜ ተዋግታለች፤ ከኤርትራ ጋር የተደረገውን ጦርነት ደግሞ ብዙ ወጣቶችም የሚያውቁት ነው፤ እነዚህ ጦርነቶች የተደረጉት በመሬት ምክንያት ነበር፤ ምናልባትም ከሶማልያ ጋር ሁለት ጊዜ ከተደረጉት ጦርነቶች ይልቅ ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት የተገደሉት የኢትዮጵያውያን ቁጥር በጣም የላቀ ሳይሆን አይቀርም፤ ከዚያም በላይ ከኤርትራ ጋር ጦርነት የተደረገበት ምክንያት ከሶማልያ ጋር ከተደረጉት ጦርነቶች ምክንያት በጣም ያነሰ ነው፤ በአጠቃላይ አገሪቱን በሙሉ ለመውረር የመጣውንም ሆነ አንዲት ትንሽ መንደር የወረረውን እኩል በመዋጋት ሀብትንና የሰው ሕይወትን ማቃጠል የማሰብ ችግር ውጤት ነው፤ ለጊዜው ዋናው ነጥባችን በነዚህ ጦርነቶች የሞቱት ሰዎች መሬቱ የኛ ነው፤ አንሰጥም፤ በማለት ነው፤ በሌላ አነጋገር የመሬቱ ባለቤት፣ የመሬቱ ባለመብት እኛ በመሆናችን ያለፈቃዳችን ሌላ አይወስደውም በማለት ነው።
ባለቤትና ባለመብት ሆኖ የሞተውና በየሜዳው ላይ ሬሳው ወድቆ ሳይቀበር ለጅብና ለአሞራ ምግብ የሆነው ኢትዮጵያዊ መሬትን እንኳን ለኑሮ ለመቃብርም አላገኘም፤ በሆነው ባልሆነው መጫወቻ የሆነው መስዋእት የሚባል ቃል ትክክለኛ ትርጉሙ ይህ ነው፤ እንግዲህ ይህ ሰው መስዋእት የሆነው ለምን ዓላማ? ለማን ዓላማ ነው? የሚለው ጥያቄ መሠረታዊ ነው፤ ማንም ሰው ለመሞት በቆረጠበት ጊዜ ‹‹የምሞተው ለምን ዓላማ ነው?›› ብሎ መጠየቅ አለበት።

No comments:

Post a Comment