Translate

Friday, October 4, 2013

ከሙስና ተጠርጣሪው የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበር ሃላፊ ጋር በተያያዘ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ተያዘ

ከሙስና ተጠርጣሪው የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበር ሃላፊ ጋር በተያያዘ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ተያዘ

 በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበር ሃላፊ ከነበሩት ተመስገን ስዩም ጋር በተያያዘ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ጥሬ ገንዘብ ሲያዝ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ዶዘር ደግሞ ማሳገዱን የፌዴራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ገለፀ፡፡
የፌዴራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአቶ ተመስገን ስዩም ላይ ያካሄደው ተጨማሪ ምርመራ እንደሚያመለክተው ግለሰቡ በሃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት 12 የነዳጅ ማመላለሻ ቦቴዎችን በሌላ ሰው ስም ገዝተው ለተገዙት መኪኖች ውክልና በመውሰድ መኪኖቹን ለሌሎች ሰዎች ሸጠዋል፡፡
ከሽያጩ በተገኘው ገንዘብ ደግሞ ሁለት ዶዘሮችን ለመግዛት ከ15 ሚሊዩን ብር በላይ ለአንድ ድርጅት ክፍያ ፈፅመዋል፡፡

ግለሰቡ ክፍያ ከፈፀሙባቸው ዶዘሮች መካከል አንዱን በ7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በመረከብ ለአንድ ድርጅት ያከራዩ ሲሆን ሌላውን 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የሚያወጣውን ዶዘር ለመረከብ በዝግጅት ላይ እንደነበሩ የምርመራ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
ግለሰቡ ይህን ያደረጉት ምንጩ ያልታወቀ ገንዘብ በመያዝ ከሚመጣ ተጠያቂነት ለማምለጥ እና በሙስና የተገኘን ህጋዊ አስመስሎ ለማቅረብ እንደሆነ በጉዳዩ ዙሪያ እስካውን የተደረገው ምርመራ ያመላክታል፡፡
እነዚህን የተጠቀሱትን ገንዘብና ንብረት ህጋዊ በማስመሰል ሂደት ተሳትፎ ነበራቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሁለት ነጋዴዎች ከ14 ቀን በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ፥ ነጋዴዎቹ አቶ ተመስገን ስዩምን ለመርዳት የፈለጉት ቀደም ሲል ግለሰቡ በሃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ነጋዴዎቹ በህገ ወጥ መንገድ ዕቃዎችን እንዲያስገቡ ይጠቅሟቸው ስለነበር እንደሆነ ምርመራው ያስረዳል፡፡
በመሆኑም ገንዘቡና ንብረቱን ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው በሚል ጥርጣሬ ግለሰቡ አንድ ዶዘር የገዙበት 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ከተገዛበት ድርጅት እንዲመለስ ተደርጎ ኮሚሽኑ የተረከበው ሲሆን ፥ ሌላው 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚያወጣው ዶዘር እንዲታገድ ተደርጓል ፡፡
በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የአዳማ ጉምሩክ የህግ ማስከበር ሃላፊ የነበሩት አቶ ተመስገን ስዩም ባለፈው ሰኔ በርካታ የገቢዎችና ጉምሩክ የስራ ሃላፊዎች ፣ ነጋዴዎችና ትራንዚተሮች በሙስና ተጠርጥረው በህግ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት ሲፈለጉ ከአዲስ አበባ ወደ ጋምቤላ በመሸሽ ደቡብ ሱዳን ለመግባት ሲሉ መያዛቸው ኢሬቴድ በዘገባው አስታውሷል ።   

No comments:

Post a Comment