Translate

Wednesday, February 27, 2013

የጁኔይዲ ሳዶን ወደ ኬኒያ መሰደድ ተከትሎ የፌደራል ፖሊስ ምላሽ ሰጠ


“ጁኔይዲ ሳዶ በወንጀል አልተከሰሱም፤ እንደማንኛውም ዜጋ የመውጣትና የመግባት መብት አላቸው”

የፌዴራል ፖሊስ

junedin
(ሰንደቅ ጋዜጣ) የቀድሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር አቶ ጁኔይዲ ሳዶ በጎረቤት ሀገር ኬኒያ በመሰደድ የፖለቲካ ጥገኝት መጠየቃቸውን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀለኛ ስለመሆናቸው የማውቀው ነገር የለም ሲል ለሰንደቅ ጋዜጣ ገለፀ።
አቶ ጁኔይዲ ሳዶ ባለቤታቸው ወይዘሮ ሃቢባ መሐመድ በሽብር ተግባር ተሳታፊ ናቸው በሚል ጥርጣሬ በፌደራል አቃቤ ሕግ መከሰሳቸውን ተከትሎ በአዳማ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ ላይ ተገምግመው ከስራ አስፈፃሚነታቸው መሰናበታቸው ይታወቃል። ይህን የፖርቲውን ውሳኔ ተከትሎ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውም ተሰናብተዋል። ከዚህ ተከታታይ ውሳኔዎች ጋር በተያያዘ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመከሰስ መብታቸውን በማንሳት ክስ ይመሰርትባቸዋል ተብሎ ይጠበቅ የነበረ ቢሆንም ይህ ሳይፈፀም ሰሞኑን ከሀገር መውጣታቸው ተሰምቷል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የውጪና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ዘሚካኤል አነጋግረናቸው በሰጡን ምላሽ፤ “ጁኔይዲ ከሀገር ሊወጡ ይችላሉ ተብሎ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሲደረግ የነበረ ክትትል አልነበረም። እኛ አቶ ጁኔይዲ የምናውቀው እንደማንኛውም ሰው ነው።”

አያይዘውም፤ “አቶ ጁኔይዲ ከሀገር እንዳይወጣ መከልከል የሚችለው በፍርድ ቤት ነው። ፍርድ ቤት ወንጀለኛ ወይም በወንጀል ይጠረጠራል የሚል ትዕዛዝ መስጠት አለበት። ስለዚህ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እስካልተያዘ ድረስ እንደማንኛውም ዜጋ ከሀገር የመውጣትና የመግባት መብት አላቸው። በሕግ መብታቸው እስካተገፈፈ ድረስ ማንም ምንም ማድረግ አይችልም። ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንም ግለሰቡን የመከታተል ሆነ ከሀገር እንዳይወጡ የሚከለክልበት ሕጋዊ መሰረት የለውም” ብለዋል።
ከወራት በፊት አዳማ በተደረገው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አቶ ጁኔይዲ ተገምግመው (ግለሂስ አድርገው) ጥፋታውን ማመናቸው ነው የሚነገረው። በዚህ ላይ ምን አስተያየት ይሰጣሉ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ኮማንደሩ በሰጡት ምላሽ፤ “አቶ ጁኔይዲ በድርጅቱ መገምገማቸውን አውቃለሁ። ድክመት እንደነበረባቸውም በግምገማው ጊዜ እንደተነገራቸው ይታወቃል። ድርጅቱ የሰጠውን ኃላፊነት በበቂ ሁኔታ አልተወጡም ማለት ግን ወንጀለኛ ናቸው ከሚለው ጋር ፈጽሞ የማይገናኝ ጉዳይ ነው” ብለዋል።
ባለቤታቸው በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩበት ጉዳይ ጋር አቶ ጁኔይዲ እጃቸው አለበት ስለሚባለውም ጉዳይ ኮማንደር አበበ ተጠይቀው፤ “የምናውቀው ነገር የለም። መታወቅ ያለበት ባልና ሚስት አብረው ሲኖሩ ሚስት በመሰላት መንገድ የመኖር መብቷ የተጠበቀ ነው። ስለዚህ የአቶ ጁኔይዲ ሚስት የመረጠችው መንገድ ወይም መብቷን ተጠቅማ ይሆናል። የተከተለችው መንገድ ተገቢ ነው፣ አይደለም የሚለው የፍርድ ቤት ጉዳይ ነው የሚሆነው። አቶ ጁኔይዲ ግን ማድረግ የነበረበት ያላደረገው ነገር አለ ብሎ መከራከር ግን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም የሚስቱ መብት በሕግ የተጠበቀ መብት በመሆኑ ነው። ስህተት የሰራው ግን፣ ከሕግ በፊት ባለቤቴ ነፃ ነች። ፌደራል ፖሊስ ያለመረጃ ነው የያዛት ብሎ መናገሩ ነው። ከአንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ይህ መሰል ተግባር አይጠበቅም። በዚህም ድርጊታቸው ተገምግመዋል። ነገር ግን ጉዳዩ ወንጀለኛ ነው አያስብልም” ሲሉ ኮማንደር አበበ ዘሚካኤል ተናግረዋል።
ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የአቶ ጁኔይዲ የመከሰስ መብት በየተወካዮች ምክር ቤት እንዲሳም ጥያቄ ስለመቅረቡም ጉዳይ ኮማንደር አበበ “የማውቀው ነገር የለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ታህሳስ 18 ቀን 2005 ዓ.ም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ “የአንድ የም/ቤት አባልን የሕግ ከለላ ስለማንሳት የቀረበ የውሣኔ ኀሳብን መርምሮ ስለማፅደቅ” በሚል ለውይይት አጀንዳ ከያዘ በኋላ አፈጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ባልታወቀ ምክንያት አጀንዳው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መደረጉን ለም/ቤቱ አባላት በመግለፅ ም/ቤቱ አጀንዳው ላይ ሳይወያይ ቀርቷል።
ምንጮቻችን እንደገለፁት ይህ አጀንዳ አቶ ጁኔይዲንን የሚመለከት እንደነበር በማስታወስ ም/ቤቱ አጀንዳው ላይ ተወያይቶ ውሣኔ ባለመስጠቱ አቶ ጁኔይዲን ምንም ዓይነት ክስ ሳይቀርብባቸው ከአገር እንዲወጡ ምክንያት መሆኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment