Translate

Saturday, February 23, 2013

ጊዮን ሆቴል የተጠናቀቀው የኦህዴድ ድራማ!!


ግለሰብ የሚጠመዝዘው “የህዝብ” ወኪል

opdo1
የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ወገኛ ድርጅት ነው። “ሲያደርጉ አይታ” እንደሚባለው እንደ ኤፈርት አይነት ታላቅ የንግድ ኢምፓየር ከፈተ። ስሙንም ቱምሳ ኢንዶውመንት አለው። ቱምሳ የድርጅት ቅርጽና መልክ ተበጅቶለት ስራ ጀመረ። በበረሃ ትግል ወቅት በነበረን ሃብት መሰረትነው ለማለት ቀዳሚዎቹ የኦህዴድ ምልምሎች ሳንቲም አዋጡና ወደ ተግባር ገቡ።
ቱምሳ በስሩ ዲንሾ ትሬዲንግ፣ ዲንሾ ትራንስፖርት፣ አግሮ ኢንዱስትሪና የንግስ ድርጅቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን ቢፍቱ ገነማ የሚባል የጫት ንግድ አቋቋመ። የትራንስፖርት ዘርፉን ይመሩ የነበሩት የአቶ ኩማ ደመቅሳ ወንድም እንክት አድርገው በሉትና ከሰረ። ዲንሾ ንግድ ማዳበሪያ እነግዳለሁ ብሎ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ከንግድ ባንክ ተበደረና ታሪኩን በኪሳራ ደመደመው። ዲንሾ አግሮም ከእህት ኩባንያዎቹ እንደተማረው ኪሳራ ተከናንቦ መሬት ብቻ አንቆ ቀረ። መጨረሻ ላይ በገፍ የሰበሰበውን መሬት በሽርክና ስም ለሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲ አስረክቦ እጁን ታጠበ።
ማዳበሪያ ንግድ ሲገባ ለመወዳደር ያሰበው ከጉና ንግድና አምባሰል ከሚባለው የህወሃት ማዳበሪያ አቅራቢ ጉልበተኛ ድርጅት ጋር ነበርና ገበያ ለመሳብ በሚል ማዳበሪያ በዱቤ አደለ። መጨረሻ ላይ “የበተነውን ብር መሰብሰብ አልቻለም” ተባለና ከማዳበሪያ ንግድ ተገለለ። ባንክ ተጨማሪ ብር እንዲሰጠው ቢጠይቅም ተከለከለ። ኤፈርት በላይ በላይ እንደሚፈቀድለት ብድር ቱምሳ ቢጠይቅም ባንክ አልሆነለትም። በክልሉ ማዳበሪያ እንኳ የመነገድ መብቱን አሳልፎ ተመልካች ለመሆን ተስማማ። ከፍተኛ የአክሲዮን ባለቤት ከሆነበት ወጋገን ባንክ እንኳ ብር ወስዶ ንግዱን ማስቀጠል ባለመቻሉ ዲንሾ ትሬዲንግ ሰመጠ። ከሙስናው ጋር ተዳምሮ ስውር ደባና ድንቁርና ገደለው። አሁን የአረም መድሃኒት ይቸረችራል።
(የምስሉ ባለቤት: ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ)
የማዳበሪያ ንግዱ እንዳከተመለት ኦህዴድ “ብልሃት አድርጎ” የወሰደውን አዲስ የንግድ ስልት ቀየሰ። ገጠር በመዝለቅ ኮንጎ /ላስቲክ/ ጫማ ለመነገድ ተስማማ። በገፍ በኮንቴነር አስገባ። አገር የሚመራው ኦህዴድ ኮንጎ ቸርችሮ ሊያተርፍ የንግድ “ፋኖ ተሰማራ” አለ። ብዙም ሳይቆይ ያስመጣውን ኮንጎ ይዞ እጁን አጣጥፎ ተቀመጠ። ድርብ ኪሳራ። አቻ ድርጅቶች መኪና መገጣጠሚያ ሲከፍቱ፣ ሲሚንቶ ማምረት ሲጀምሩ፣ ማዳበሪያ ለማምረት ሲነሱ፣ ትርፋቸውን እያሰቡ ወርቅና ማዕድን ቆፍረው ለማውጣት ሲሰማሩ፣ በትራንስፖርትና በሸቀጥ ንግድ ከብረው ትርፋቸውን በዶላር ሲያሰሉ ኦህዴድ ኮንጎ ጫማ ለመነገድ እቅድ አውጥቶ፤ እሱም ከሽፎበት ይደናበር ነበር።
እንጂ ቀደም ሲል ሽፈራው ጃርሶ፣ ከዚያም ግርማ ብሩ ሲመሩት የነበረው ቱምሳ ኢንዶውመንት እንዳይከስም ተሸክሞ የያዘው የጫት ንግዱ ስለነበር አዲስ ስልት ዘርግቶ ለመክበር ያወጣው እቅድና የበረሃ ላይ ስቃዩ ጊዮን ሆቴል እንዴት እንደተቋጨ የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው።
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ “ቱጃሯ ሱራና ኦህዴድ – ከጫት ንግድ በስተጀርባ ያለው ቁማር” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡ በዚያው ዘገባ ላይ ኦህዴድ ሶማሌ ጫት ንግድ ውስጥ ገብቶ እንዳልተሳካለት እናስከትላለን ባልነው መሠረት በተወሰነ መልኩ ከዚህ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ግመሉ ኦህዴድና የጊዮን ሆቴሉ ድራማ
ዋና ጽህፈት ቤቱን ድሬዳዋ ያደረገው ቢፍቱ ገነማ የጫት ንግድ አትራፊነቱ ከግለሰቦች ባይበልጥም ከፍተኛ የሚባል ነው። በዚሁ አትራፊነቱ የተነሳ “ኢገ ኬኛ” ደማችን ይሉታል። የባለስልጣኖችን ከርስ፣ የተለያዩ ሃላፊዎችንና የበታች ሰራተኞችን ቅርምት ተቋቁሞ አዲስ አበባ ኮሜርስ ፊት ለፊት ህንጻ ለመስራት ችሏል። ብቸኛው የቱምሳ ስኬት መሆኑ ነው።
በጫት ንግድ ውስጥ ያለው የገንዘብ ዝውውርና ትርፉ ያጓጓው ቱምሳ ኢንዶውመንት አዲስ ስራ አስኪያጅ ከመደበ በኋላ ወደ ሶማሌ የሚላከውን ጫት ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር እቅድ ዘረጋ። ወይዘሮ ሱሁራ እስማኤል በብቸኛነት ወይም በከፍተኛ ደረጃ የተቈጣጠሩትን የሶማሌ የጫት ንግድ ለማምከን ኦህዴድ ባሉት ከፍተኛ የፖለቲካ ሃላፊዎች አማካይነት ጡንቻውን ለማሳየት ሞከረ። ወይዘሮ ሱራ ባላቸው ከብረት የጠነከረ ሃይልና ጉንጉኑ ሊበተን የማይችል ሰንሰለት ኦህዴድ የመጀመሪያ ሃሳቡ ቅዠት ሆነ። ከሸፈ!!
የመከላከያ ድጋፍ
ሱሁራ ኢስማኤል (ፎቶ: Philipp Hedemann)
ሁለተኛው አካሄድ ወይዘሮዋ ሃርጌሳን ስለተቆጣጠሩት ሃርጌሳ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ዋጋ በመቀነስ ጫት ማቅረብ ነበር። ሆኖም ኦህዴድ ጫት ወደ ሃርጌሳ የላከ ቀን ሃርጌሳ ጫት በነጻ ታደለ። ኦህዴድ የላከውን ጫት የሚገዛው ታጣ። ጫት በባህሪው ቶሎ ስለሚበላሽ “ተቃጠለ” አስቀድሞ መረጃ የደራሳቸው ሞኖፖሎች ኦህዴድን “አርፈህ ተቀመጥ” በማለት “አይቼሽ ነው ባይኔ ወይስ በቴሌቪዥን” የሚለውን ዘፈን ጋበዙት።
ሶስተኛው መንገድ ተቀየሰ። “ተነሳ ተራመድ፣ ክንድህን አበርታ …” ተዘመረ። በእቅዱ መሰረት ኦህዴድ የጫት አበባ ይዞ ጉዞውን ወደ ፑንት ላንድ አቀና። የፑንት ላንድ ጉዞና የንግድ አላማ በሚስጥር እንዲሆን ተወሰነ። የቱምሳ አመራሮች ስንቅና አገልግል ቋጥረው የኦጋዴንን በረሃ በመኪና ለማቋረጥና ፑንት ላንድ ለመግባት ወሰኑ። በረሃው ለህይወትም አስጊ ስለሆነ የመከላከያ ትብብር አስፈለገ።
ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ እንደሚመሰክሩት የኦህዴድ ሰዎች ፑንት ላንድ ለመግባት በበረሃ የተንከራተቱት አንዴ አይደለም። በተደጋጋሚ ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥሟቸዋል። የመጀመሪያውን ጉዞ አከናውነው ሲመለሱ በረሃው በልቶ ጨርሷቸው ከሰል መስለው ነበር። ከበርካታ ምልልስ በኋላ የፑንት ላንድ አስተዳደር ቀና ምላሽ ሰጠ። በውሳኔው መሰረት የፑንት ላንድ “የፓርላማ አባላት” አዲስ አበባ ተገኝተው በኦፊሴል የንግድ ውል ለመዋዋል ቀጠሮ ያዙ።
በቀጠሮው መሰረት የፑንት ላንድ ወኪሎች አዲስ አበባ ገቡ። በቱምሳ ወጪ ግዮን ሆቴል አረፉ። ምርጥ የአወዳይ ጫት ሆቴል ድረስ እየተላከላቸው “ቃሙት”። ተዝናኑ። ለቀናት ውሎ አበልና ሙሉ ወጪያቸው እየተቻለ ተምነሸነሹ። አዲስ አበባ ያሉ ጓደኞቻቸውንና ወዳጆቻቸውን በመጋበዝ ኦህዴድ የሚያቀርበውን ጫት “በሉት”። “አገር መሪ ነኝ የሚለው” ኦህዴድም የታዘዘውን እያቀረበ ጋበዘ። የቢዝነስ ማባበያ መሆኑ ነው። ይህ ሁሉ ሲደረግ የጫቱን ንግድ የተቆጣጠሩትና ከጀርባ ሆነው ከለላ የሚሰጡት ራዳራቸውን አስተካክለው ይቀርጻሉ።
ጋዜጣዊ መግለጫ
የፑንት ላንድ የፓርላማ ወኪል ናቸው የተባሉት ክፍሎች ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ። ታላቅ የንግድ ስራ ለመስራት ይህ የመጀመሪያ እንደሆነና ወደፊት “ዘርፈ ብዙ” ስራ በጋራ ለመስራት እቅድ እንዳለ ተናገሩ። መርቅነው መግለጫውን አደመቁት። ኦህዴድም ፈነጠዘ። በጫት ንግድ ፑንት ላንድን ሲቆጣጠር ታየው። ዶላር ለመሰብሰብ ጎመጀ። ታላቅ የንግድ ኢምፓየር ዘርግቶ ኢኮኖሚውን ሲዘውር ተመለከተ። የማዳበሪያ ቁጭቱን ሲወጣና ሲረካ ተሰማው። ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑ የታወቀው ግን ሰዎቹ አዲስ አበባ በገቡ በበነጋው እንደነበርና ጉዳዩ ገብቷቸው እናባራቸው ያሉም ነበሩ።
ውለታ ለመፈጸም መጥተው ከዛሬ ነገ እያሉ ከሳምንት በላይ በድሎት ጊዮን ሆቴል ተኝተው ሙሉ እንክብካቤ የተደረገላቸው እንግዶች መግለጫውን አስቀድመው ከሰጡና ውሉን ከፈጸሙ ወደ አገራቸው ስለሚመለሱ ጉዳዩን በማዘግየት ኦህዴድን ያልቡት ነበር። ከነሱ መካከል በጓሮ ከሌሎች ጋር የሚነጋገሩም ነበሩ። እንደምንም ተብሎ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ መጽሃፉም ዝም ቄሱም ዝም ሆነ። ኦህዴድ ከፍ ዝቅ ብሎ ያስተናገዳቸው ሰዎች ደብዛቸው ጠፋ። የሞራልና የስሌት ኪሳራ ተከተለ። መንግስት ሆነው እንደ ሌባ በጓሮ ሲርመጠመጡና ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሲልከሰከሱ ተታለሉ። በግልጽ የሂሳብ ሰነድ ያልተወራረደ ከፍተኛ ገንዘብ በወቅቱ በጉርሻ ስም መሰጠቱን፣ የሽኝት ቀን የኢትዮጵያ ባህል እቃዎች ስጦታ መቅረባቸውም የአደባባይ ምስጢር ነው። የኦህዴድ “ግመሉ” የበረሃ ታሪክ ይኸው ነው። ሰዎቹ ድምጻቸውን አጠፉ። ኦህዴድም “ግመሉ” የሚለውን ስም ይዞ ቀረ።
ፉከራው
የፑንት ላንድ ጉዞ ከድግግሞሽ በኋላ መሳካቱ ሲታወቅ የቱምሳ አመራሮች “ገድላቸውን” በገሃድ ቢሮ መናገር ጀመሩ። ኦጋዴን በረሃ ውስጥ ያጋጠማቸውን መከራና ድካም እንዴት እንደተቋቋሙ በኩራት መተረክ ተያያዙ። በተለይ አዲሱ ሃላፊ የዘመቻው መሪ መሆናቸውን ለማሳየት እጅጌያቸውን ይሰበስቡ ጀመር። ወደ ቢሮ ሲገቡ አረማመዳቸውና አስተያየታቸው ተቀየረ። ሰራተኞችን ሲያዙ “የበረሃ ተሞክሮዬ” ማለት ጀመሩ። ስለቁርጠኝነትና ዓላማ መስበክ አበዙ። “ግመል” በስብሰባ ላይ ቋሚ ምሳሌያቸው ሆነ። አስተዳደሮቹን የሚከቡዋቸው በኩራት ታበዩ። ተወጣጠሩ። ቱምሳ ከክስረቱ አገግሞ በትርፍ የሚተኮስበትን አቅጣጫ ያገኙ ያህል በየቀኑ ይዘሉ ነበር። ወሬያቸውም ሁሉ “ፑንት ላንድ ተኮር” ሆነ። ፑንት ላንድ ለመመደብ ዝግጅት የጀመሩና ትርፋቸውን የሚያሰሉት ባልደረቦቻችን ድርጊታቸው ሁሉ ያሳፍር ነበር።
አገር የሚመራ ድርጅት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ “ወኪል” ነኝ የሚል ድርጅት ክብሩን ጠብቆ ስራውን መስራት እየቻለ፣ እንደ ኮንትሮባንድ ነጋዴ በረሃ ለበረሃ ሲቀበዘበዝ ማየት ያሳፍራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ሆነው ለጥቅም ሲሉ ግለሰብ አንግበው ሲነጉዱ ማየት ያሳዝናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የኦሮሞ ገበሬዎች በራሳቸው መሬት ላይ የተከሉትን ጫት ለፈለጉት እንዳይሸጡ በሞኖፖል ገበያ ተወጥረው እንዲያዙ ሲደረግ ተከራካሪ ማጣታቸው አንገት ያስደፋል። የጫት ኬላ ተነስቶ ክልሉ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢውን ማጅራቱን ሲመታ አቋም የሚይዝ መጥፋቱ በባርነት የመያዝ ያህል ዘግናኝ ነው።
ከሁሉም በላይ አሳፋሪው ደግሞ የክልሉ ገቢና ጥቅም ወደ ግለሰቦች ኪስ እንዲገባ በፊርማቸው ያዘዙት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ውሳኔ የወሰኑበት ምክንያት እየታወቀ የኦሮሞን ህዝብ ለቅሶ ተቀመጥ ማለታቸው ነው። በቱምሳ ቢሮ ውስጥ “ባለራዕዩ መሪያችን ተለየኸን” ተብሎ መለጠፉ በራሱ የውርደቱ ድምር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

No comments:

Post a Comment