የኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሔ መድረክ
የኢትዮጵያውያን የውይይትና ምክክር መድረክ (ኢውምመ) (EDF) በአገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የተመሰረተ መድረክ ሲሆን በኢትዮጵያ መሰረታዊ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የፖለቲካዊ ችግሮች ዙሪያ ምርምሮችን እያካሄደ ለተፈላጊ ለውጦች የሚታገል ድርጅት ነው። የዚህ ድርጅት አመራር አባላት በቅርቡ በሚንስትሮች ምክር ቤት የወጣውን የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚተነትነውን ረቂቅ አዋጅ በጥልቀት ተወያይቶበታል።
ተወያይቶ የሚከተለው መደምደሚያ ላይ ደርሷል በEDF እምነት በመጀመሪያ ደረጃ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው መሰረታዊ ችግር ከብሄር ፖለቲካ የመነጩ አንዳንድ የህገ መንግስቱ አንቀጾች ናቸው። ለዚህ ለአሁኑ የሚንስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ አዋጅ መነሻውም ይሄው ህገ-መንግስቱ ላይ የተቀመጠው አንቀጽ 45 ንኡስ አንቀጽ 5 ነው። ህገ-መንግስቱ ከብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ በመነጨ የተቀረጸ በመሆኑ መግቢያው ላይ ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች አገር መሆኑዋን ሲገልጽ ለዜግነት ቦታ አልሰጠም። በአንጻሩ የብዙ ዴሞክራት ሃገሮች ለምሳሌ የተባበረችውን አሜሪካንን፣ አውስትሬሊያን፣ ህንድን ብንመለከት “እኛ” በሚል ይጀምራል። የአንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ የተባበረ ማህበረሰብ እንደመሰረቱ በቃል ኪዳናቸው ላይ አስፍረዋል። ይህ መሰረታዊ እምነትና ቃል ኪዳን ለአንድ ሃገር ህልውና በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ፖሊሲዎችና ህጎች ሁሉ ከዚህ ከህገ መንግስቱ የህግ ምንጮች የሚቀዱ በመሆናቸው ህገ መንግስቱ የአንድን ሃገር ህዝብ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ወጥነት ማረጋገጡ ቁልፍ ነገር ነው።
ህገ መንግስቱ የያዛቸው አንዳንድ አንቀጾች በራሳቸው ችግር መሆናቸው ሳያንስ ከነዚህ አንቀጾች የሚቀዳው ህግ ሲመጣ ደግሞ እንዴት አንድነታችንን እኩልነታችንን እንደሚጎዳ የሚንስትሮች ምክር ቤት መግለጫውን ሲያወጣ ተምረናል። የሚንስትሮች ምክር ቤት መግለጫ የኢትዮጵያውያንን መሰረታዊ መብቶች እንደ ልዩ ጥቅም አይቶ አዋጅ ማውጣቱም ሌላ ችግር ሆኖ አይተነዋል። ከሁሉ በላይ ደግሞ አዲስ አበባ ብቻ ሳትሆን ቡድኖች ተሰባስበው የሚኖሩባቸውን የክልል ከተሞች ማለትም እንደነ አዋሳ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላና አንዳንድ ዞኖችም እንዲሁ የልዩ ጥቅም ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አግኝተነዋል። ይህ ጉዳይ የሚያመጣው ዋና ችግር የልዩ ጥቅም አስተሳሰብ ሲስተማችንን እስከ ታች ሊያበላሸውና ከእኩልነት ይልቅ በተፈጥሮ ሃብትና ኢኮኖሚ ጉዳዮች የይገባኛል ጥያቄዎችን እየፈጠረ አንድነታችንንና የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄዎቻችንን ያበላሻል። ዛሬ በዚህ በወጣው አዋጅ ዙሪያ ኢትዮጵያውያን የሚያዝኑት አዲስ አበባ ኣካባቢ ያለ ገበሬ አይጠቀም ከሚል ሳይሆን የአዋጁ ስሜት ብሄርን መሰረት ያደረገ በመሆኑ፣ መሰረታዊ የዜጎችን ጥያቄዎች ከመፍታት ይልቅ ልዩነትን ለማጉላት የተጨነቀ ሆኖ ስላዩት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያውያን የቸገራቸው ነገር እንዴት ከድህነት እንደሚወጡ፣ እንዴት ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንደሚያድጉ ነው እንጂ የቀበሌ ስሞች የመቀያየር ጉዳይ አይደለም። የሚንስትሮች ምክር ቤትን ያሳሰበው ጉዳይ በከተሞች መስፋፋት ጊዜ የሚመጣውን ችግር በተመለከ ቢሆን በመላ ሃገሪቱ ወጥነት ባለው ሁኔታ በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ገበሬዎችን ህይወት በሚመለከት አንድ ወጥ አሰራር ሊፈጥር ይችል ነበር። ነገር ግን መንግስትን ያሳሰበው ጉዳይ ይህ ባለመሆኑ በብሄሮች መካከል ያለውን ልዩነት ለማጉላት ሲጥር ይታያል። ወጥነት ያለው ኢትዮጵያውያንን በብሄር በሃይማኖት ሳይነጥል የሚንከባከብ ህግ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሞገስ ያገኛል። የመንግስት ስራ ከዚህ ፍጹም ተጻራሪ በመሆኑ መላው የሃገራችን ህዝብ ለተፈላጊ ለውጥ ትግሉን እንዲቀጥል ጥሪ እያደረግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የኢትዮጵያ ለጋሽ ሃገራት ሁሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ጥብቅ ርምጃ እንዲወስዱና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ እናደርጋለን።
No comments:
Post a Comment