ዋዜማ ራዲዮ- ከኦሮሚያ የጨለንቆ ነጋዴዎች ተነስቶ ጊንጪ፣ አምቦና ወሊሶን ያዳረሰው የግብር በዛብን ስሞታ መልኩን እየቀየረ ባለፉት ሦስት ቀናት ወደ አዲስ አበባ ኮልፌ፣ ታይዋንና አጠና ተራ ተዛምቶ ቆይቷል፡፡ ኾኖም የግብር እምቢታ አመጹ በዚህ ፍጥነት ታላቁን የገበያ ስፍራ መርካቶን ያዳርሳል ብሎ የገመተ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ለብዙ ነጋዴዎች ያልጠበቁት ክስተቱ ኾኖ መገረምን የፈጠረው ይህ አመጽ ለመንግሥት ሹማምንትም ዱብ እዳ ሆኖባቸዋል፡፡
ከትናንት ጀምሮ ግምገማ የተቀመጡ የአስሩ ክፍለ ከተማ የድርጅት ኃላፊዎች አመጹን ማን አስተባበረው በሚለው ጥያቄ ላይ ከረር ያለ ግምገማ ያካሄዱ ሲሆን አዝማሚያዎችን ዐይቶ ማስቆም ሲቻል ይህ አለመደረጉ ትልቅ የመንግሥት ድክመት ሆኖ ተነስቷል፡፡
ትናንት ከቀትር ጀምሮ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና የኢህአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በአንድነት በማዘጋጃ ቤት የካቢኔ አዳራሽ፣ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የድርጅት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪዎች ራስ ኃይሉ ሜዳ በሚገኘው ቢሯቸው እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በስብሰባ ተሰንገው ማምሸታቸውን የዋዜማ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
የማዘጋጃ ቤቱን ስብሰባ ከተካፈሉ ምንጮች ዋዜማ እንደሰማቸው አመጹ ገፍቶ ከቀጠለ ቁርጥ ግብሩን የመክፈያ ጊዜ በተራዘመ ዓመታት እንዲሆን ከማድረግ ጀምሮ ሙሉ በሙሉ እስከማንሳት የሚሄድ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ከኃላፊዎች ፍንጭ መሰጠቱን ነው፡፡ ኾኖም እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ መንግሥት ሁኔታዎችን መቆጣጠር እየተሳነውና እየተዳከመ የመጣ ስለሚያስመስል የመጨረሻ አማራጭ እንደሚሆንና አሁን ዋናው ሥራ የእምቢታ አመጹን አስተባባሪዎች የመለየት ሥራ እንደሚሆን አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡ የዚህ ሥራ መጀመርያ የሚሆነው ደግሞ ነጋዴዎች ስሜታቸውን የሚተነፍሱባቸው መድረኮች በየወረዳው እንዲመቻቹላቸው ማድረግ፣ ቅሬታ አቅራቢዎችን በፍጥነት ማስተናገድ፣ በእምቢተኝነት የሚጸኑትን መለየት እንደሚሆንና ይህንንም የየክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች በአስተባባሪነት እንዲያስፈጽሙ ተወስኗል፡፡
የማዘጋጃ ቤቱን ስብሰባ የመሩ አንድ ባለሥልጣን “ትልልቅ አሶችን በቀጣይ መያዝ እንጀምራለን፤ይህንን ስል ከኛም ከነጋዴዎችም ይሆናል” ሲሉ መናገራቸውን የዋዜማ ምንጭ መስክሯል፡፡ ይህን የተናገሩት መንግሥት ለምን ትልልቅ ነጋዴዎች ላይ ትኩረት እንደማያደርግ ሐሳብና ጥያቄ በመነሳቱ ነው፡፡
በየወረዳው የሚገኙ ደንብ አስከባሪዎች በፖሊስ እየታጀቡ “ሱቃችሁን ካልከፈታችሁ እናሽግባችኋለን” የሚል ማስፈራሪያ ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ ማሰራጨታቸውንና ዛሬ ጠዋትም ይኸው ቀጥሎ እንደነበር ታዝበናል፡፡
የነጋዴ አመጹን ማን አስተባበረው የሚለው ለመንግሥት ብቻም ሳይሆን ለአመጹ ተካፋዮችም ግራ ሆኗል፡፡ ትናንት የዋዜማ ዘጋቢ በተዘዋወረባቸው የመርካቶ አካባቢዎች ነጋዴዎች ሱቆቻቸው ላይ ሆነው የሚሆነውን በመጠባበቅ ላይ እንደነበሩ ታዝባለች፡፡ “በርግጥ ጭምጭምታ ሰምቻለሁ፡፡ ጠዋት ስመጣ ግን ብዙ ሱቆች አልተከፈቱም ነበር፣ እኔም ዘግቼ ዋልኩኝ” ትላለች በብርድልብስና አልጋ ልብስ ንግድ የተሰማራች አንዲት ነጋዴ፡፡ “በፌስቡክ ተነግሯል ሲባል ነው የሰማሁት፤ እኔ ፌስቡክ የለኝም” ያሉ ሌላ በእድሜ የገፉ የኤሌክትሮኒክስ ነጋዴ “ሰው የሚሆነውን መሆን ነው እንግዲህ፤ ይሄ ሁሉ ሰው ዘግቶ እኔ አልከፍትም” ብለዋታል ለዋዜማ ዘጋቢ፡፡
ኾኖም በእሚቢታ አመጹ ቀጣይነት ላይ ሁሉም የአመጹ ተሳታፊዎች ሳይቀር ጥያቄ አላቸው፡፡ “ሳንበላ እስከ ስንት ቀን ሱቅ ዘግተን እንውላለን?” ከሚሉት ጀምሮ “ንግድ ፍቃዳችን ሊነጠቅ ይችላል” የሚል ስጋት ያላቸው ነጋዴዎች በርካታ ናቸው፡፡
“በእርግጠኝነት የምነግርህ ይህ አመጽ ነገ አይቀጥልም፡፡ አሁን ራሱ ሁሉም ሰው እርስበርሱ ተፈራርቶ ነው ያለው፡፡ አስተባባሪ የለውም፡፡ በዚህ ላይ መሐላችን መንግሥትን በዚህ መልኩ መቃወም የማይፈልጉ አሉ፡፡ ሱቁን ያልከፈተ ንግድ ፍቃዱን ይቀማል እየተባለ እየተወራ ነው፡፡ ነገሩ አስቸጋሪ ይመስለኛል” ይላል ሚሊቴሪ ተራ ብትን ጨርቃ ጨርቅ ንግድ ላይ የተሰማራ ጎልማሳ ነጋዴ፡፡
ዋዜማ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በደረሳት ያልተጣራ መረጃ ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ሱቅ ያለመክፈት እንቅስቃሴ በመርካቶ በተለምዶ ወንበር ተራ በሚባለው አካባቢ እንደሚኖር የሚጠቁም ቢሆንም ነገሩ አመጹ ትናንት እንደሆነው መላው መርካቶንና አካባቢውን የሚያዳርስ ይሆናል ተብሎ አልተጠበቀም ነበር፡፡ ኾኖም አብዛኛው ነጋዴ በግብር ዉሳኔ ከፍ ያለ ቅሬታ የተፈጠረበት በመሆኑ እድሉን ሲያገኝ አመጹን ፈራ ተባ እያለም ቢሆን ለመቀላቀል ድፍረት እንዳገኘ ተገምቷል፡፡
“በአሁኑ ሰዓት ንግድ ፍቃዴን መልሱልኝ ማለት እንኳን በአመጽ የሚያስከስስ ሆኗል እኮ፡፡ ታምናለህ! የቀን ሽያጭህ 90 ሺህ ብር ነው ብለውኛል፡፡ ለምን ብዬ ነው ከእንግዲህ መንግሥትን የምፈራው? ለምን ብዬ ነው ሱቅ የምከፍተው?” የሚለው አቶ አያሌው በሰሀን ንግድ ችርቻሮ ላይ የተሰማራ ነጋዴ ነው፡፡ “እኔ ከዚህ በኋላ በንግድ ላይ ብዙ አልቆይም፡፡ ግን እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ይህ መንግሥትም ብዙ ዓመት በሥልጣን ይቆያል ብዬ አልገምትም” ይላል በልበ ሙሉነት፡፡
“ነጋዴ ፈሪ ነው፡፡ ለአንድ ቀንም ቢሆን ሱቅ መዝጋቱ ቀላል ዉሳኔ አይምሰልህ፡፡ ነገሮች ካልተስተካከሉ እመነኝ የዚህ መንግሥት እድሜ እያጠረ ነው የሚሄደው” ሲል ሀሳቡን ያጠናክራል፡፡ አቶ አያሌው ከባንክ ሠራተኝነት በቤተሰብ እገዛ ወደ ንግድ ከገባ አምስት ዓመት እንኳን አልሞላውም፡፡ “የዚህ ዓመት የቁርጥ ግብር ግምት ዉሳኔ በመንግሥት የተመራ የለየለት ዘረፋና ዉንብድና ነው” ብሎ ያምናል፡፡
የዋዜማ ዘጋቢ ትናንትና በመርካቶ ዙርያ ባደረገው ሀሰሳ ከተክለሀይማኖት እስከ በርበሬ ተራ የሚገኙ ብረት ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች አብዛኛዎቹ ማለት ይቻላል ሱቆቻቸውን ከፍተው በሥራ ላይ ሆነው ታይተዋል፡፡ ሲኒማ ራስ ዙርያ አርከበ ሱቆች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን ሚስማር ተራ ዙርያ፣ ሳህን ተራ፣ ምናለሽተራ፣ ድር ተራ፣ ሚሊቴሪ ተራ፣ ወንበር ተራ በአብዛኛው በአመጹ ተካፋይ ነበሩ፡፡ የአንዋር መስጊድና ራጉኤል ቤተክርስቲያን አጥሮችን ታከው የተገነቡ ሱቆች በስፋት አመጹን ሳይቀላቀሉ በንግድ ላይ እንደነበሩ ለማየት ችለናል፡፡ ጎንደር ተራም በከፊል በሥራ ላይ ነበር፡፡
ወትሮ ለመኪና እጅግ አስጨናቂ የነበረው የመርካቶ መንገድ ትናንት የእረፍት ቀን እስኪመስል ድረስ ጭር ብሎ ታይቷል፡፡ ለመርካቶ ትልቁ የመኪና ማቆምያ የሆነው ጣና ገበያም የፓርኪንግ አገልግሎቱን ዘና ብሎ ሲያከናውን ተመልክተናል፡፡ ይህ ስፍራ በሌሎች ቀናት ከፍተኛ መጨናነቅ የሚታይበት ነበር፡፡
በዱባይ ተራና ሳጥን ተራ አካባቢ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ሁኔታውን በካሜራ በመቅረጽ ላይ ሳሉ ” ዉሸታሞች፣ ሌቦች፣ ማታ የምትሉትን እንሰማለን…፣ አንድ ጊዜ እንኳን እውነት ተናገሩ እስቲ…” የሚሉ ተቃውሞዎች በአካባቢው ቆመው ከነበሩ ነጋዴዎች ተሰንዝረውባቸዋል፡፡ ሱቆቻቸውን የከፈቱ ነጋዴዎች በበኩላቸው በካሜራ ላለመቀረጽ ጀርባቸውን ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡
ዛሬ ጠዋት ላይ የዋዜማ ዘጋቢ በተዘዋወረባቸው የመርካቶ ሰፈሮች ነጋዴዎች ሱቆቻቸውን ላለመክፈት ሲያመነቱና እርስበርስ ሲጠባበቁ የተመለከትን ሲሆን ብዙዎች የሚሆነውን ለማየት ከሱቆቻቸው አቅራቢያ ቆመው በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡ በሰዓቱ መጠነኛ ዝናብ እየጣለ ከመሆኑ ጋር ማለዳው ጭጋጋማ ስለነበረ ብዙዎች ሱቆቻቸውን የከፈቱት ዘግይተው ነው፡፡ አብነት አዲሱ ሱማሌ ተራና ቁልፍ ተራ እስከ ረፋድ ድረስ ሱቆቻቸውን ባለመክፈት ጸንተዋል፡፡ ደንብ አስከባሪዎች የተዘጉ ሱቆችን መዝግቡ ተብለዋል፤ እርምጃም ይወሰዳል የሚል ወሬ በስፋት ከተሰማ በኋላ በርካቶች ሱቃቸውን ገርበብ አድርገው ታይተዋል፡፡
ምዕራብ ሆቴል አካባቢ የሚገኙ ከ10 የማይበልጡ ሱቆች ትናንት ማምሻውን ‹‹ደንብ በመተላለፍ ታሽጓል›› የሚል ወረቀት ተለጥፎባቸው አድረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment