በዘራፊ አገር ወንጀለኛው ተራ ሌባ ነው። ዘራፊው ደግሞ ዳኛ። ዘራፊዎች የሚሰርቁት ህንፃ ነው። ዘራፊዎች የሚሰርቁት ሚሊዮን ነው። ቢሊዮን ነው። ይህም ሆኖ ዳኞች ናቸው። የጨዋታው ህግ አርቃቂ። የዘረፋ ህግ አዋቂ።
ዘራፊዎች ህንፃ እየሰረቁ፣ ኪስ አውላቂን አባረው ይዘው ያስራሉ። መቶ ብር የሰረቀ የጎዳና ልጅ በፍርድ ቤት ክስ ሲቀርብበት ያስቃል። የሚቀርብበት ክስ ” ያለ አግባብ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት” ይላል። የጥቃቅን ሌቦች፣ የተቸገሩ ሌቦች መክሰሻ። ዘራፊዎች ቀድመው በልፅገዋል፣ መበልፀግ አለባቸው ያሉትንም አበልፅገዋል። የሰረቀ የሚያስቀጣው ለድሃ ነው። መቶ ሚሊዮን ሳይሆን መቶ ብር ለሚሰርቀው። ሌብነት የሚያስቀጣው ለመኖር ለሚሰርቀው ነው።
ዘርፎ፣ ዘርፎ ከራሱም አልፎ ለወገኖቹና ለወዳጆቹ በመቶ ሺዎች ለሻይ ብሎ ለሚደጉም፣ በሚሊዮን የሚረዳ ዘራፊ እያለ የመቶ ብር ሌቦች ይከሰሳሉ። መቶ ሚሊዮን ፣ ቢሊዮን የዘረፉ፣ እነሱን አይተው፣ የዘረፋ ህጉን ሀ ሁ ቆጥረው መቶ ሽህ የሰረቁትን ያስራሉ። ይከሳሉ። ጅብ በሬ ጥሎ ያልከሰከሰውን አንጀት የምትለቅመውን ቀበሮ እንደሚያባረው፣ ውሻ ድመትን እንደሚያሳድደው!
No comments:
Post a Comment