ከኤርሚያስ ለገሠ (ቁጥር ሁለት)
ባለፈው ሳምንት “የቴዲ አፍሮ … ተሞክሮ!” በሚል ርዕስ ዘለግ ያለ መጣጥፍ አቅርቤ ነበር። በመጣጥፉ ላይ የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ከቴድሮስ ካሳሁን እና ከእሱ በፊትና በኋላ ከነበሩ (ካሉ) መስዋዕት እየከፈሉ ካሉ አርቲስቶች መቅሰም የሚገባቸውን ትምህርት ለማሳየት ሞክሯል። የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ስራዎቻቸውን ለህዝብ ሲያቀርቡ ራሳቸውን የሚያዩበት መስታዋት ምን ዓይነት ሊሆን እንደሚገባ ተመላክቷል። “የቴዲ አፍሮ ተሞክሮ” በሚለው ማስታወሻው እንደተገለጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ የኪነ -ጥበብ ሙያተኞች በልዩ ሁኔታ ከድምፃዊ ቴዲ አፍሮ ሁለት ትላላቅ ተሞክሮዋችን ሊወስዱ ይገባል። የመጀመሪያው አገራችን በአሁን ሰዓት ያለችበትን ሁኔታ በአግባቡ መገንዘብ ይሆናል። አርቲስቱ እንደገለጸው “ኢትዮጵያዊነት እና ብሄራዊ ስሜት አደጋና ፈተና ላይ ወድቋል ” የሚለው ቀዳሚ ቁም ነገር ይሆናል።
በድምፃዊው አልበምም ሆነ በቃለ መጠይቁ ውስጥ ኢትዮጵያዊ ስሜት እጅግ ፈተና ውስጥ መግባቱን እንድናስብ እና እንድንወያይ ያደርገናል። አርቲስቱ እንደገለጸው በጋራ ጉዞአችን ላይ የገጠመንን ችግር ለመረዳት መፍቀድና መቻል ወሳኝ ጉዳይ ይሆናል። ተያይዘን መራመድ ካልቻልን፣ ተያይዘን እንወድቃለን የሚለውን አባባልም መረዳት መቻል የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ ለመገንዘብ ያስችላል። ማወቅ መሰልጠን ነው። መሰልጠን ደግሞ ወደፊት መራመድ ነው። በእርግጥ ወደፊት ለመራመድ ሁልጊዜ አልጋ በአልጋ ነው ማለት አይደለም። እንዲያውም ወደፊት መውደቅ የተለመደ ክስተት ነው። ዶ/ር ታደሰ ብሩ “የስራ አመራር ጥበብና ተያያዥ ጉዳዮች” በሚለው መጽሃፋቸው ወደፊት የወደቀ ሰው በራሱ ላይ ስቆ፥ አቧራውን አራግፎ፥ እግሮቹን አሻሽቶ፥ ያደናቀፈውን ድንጋይ አንስቶ፥ ሃሳቡን አሰባስቦ በተነቃቃ መንፈስ መንገዱን ይቀጥላል ይሉናል። በእርግጥም ወደፊት መውደቅ ከስህተቶች ተምሮ ከቀድሞ የበለጠ ተጠናክሮ የመገኘት አቅም የሚፈጥር ነው። የቅድሚያ ቅድሚያ መልእክቱ ይሄ ነበር ።
የመጀመሪያ መጣጥፍ ላይ ከአርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን የምንወስደው ሁለተኛ ተሞክሮ ተብሎ የቀረበው ሀገራችን አደጋ የገባችበት መሠረታዊ መንስኤውን እና ምንጩን የተረዳበት ነው። ድምፃዊው እንደገለፀው ባሳለፍነው ሩብ ክፍለ-ዘመን ኢትዮጵያዊነት በሁለት መንትያ መርዞች ሰለባ ሆኗል። አንደኛው በሃይማኖት መከፋፈል ሲሆን ፤ ተከታዩ መንትያ ደግሞ የጎሳ ፓለቲካ እየተስፋፋ መሄድ ነው። እርግጥም ዘረኛና አምባገነን ስርዓቶች ዘወትር ህዝቡን በአካል ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈስም ቀፍድደውና ከሰው በታች አድርገው መግዛት ስለሚፈልጉ ሃይማኖትና የጎሳ ፖለቲካ ላይ ቢያተኩሩ ውጤታማ ይሆናሉ። በመሆኑም ሁለቱ ችግሮች የሚፈጥሩትን መመሰቃቀል አዋህደን ስንመለከት ትክክለኛውን የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር እንገነዘባለን። አለበለዚያ አንደኛው ክፍል ብቻ ነጥለን የምንወስድ ከሆነ የችግሩ ምንጭ፣ ምንነትና ጥልቀት መረዳት አንችልም።
የህወሓት አገዛዝ ሃይማኖት ውስጥ ገደብ የለሽ በሆነ መንገድ አስር ጣቱን በመክተት በአላዋቂነት በመፈትፈቱ ምክንያት በአማኞቹ ዘንድ ከፍተኛ ልዩነት ተፈጥሯል። ጆሮአቸውን በጥጥ የደፈኑት እምነት አልባዎቹ ህወሓቶች የህይወታቸው መመሪያ በሆነው የማኪያቬሊ አስተምህሮ በመመራት የሃይማኖት ተቋማት ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖራቸው አድርጓዋል። የእምነት ተቋማቱ አመራሮች ቤተ-መንግስቱን ከተቆጣጠሩት ጋር በመቆም ኢትዮጵያውያንን በጅምላ ሲታሰሩ ፥ ሲገደሉ ፥ ሲሰደዱ ድጋፍ ሲሰጡ እንጂ አንዲት የእንባ ዘለላ ከአይናቸው ሲወርድ አላየንም ። እነዚህ የሲኖዶሱም ሆነ የመጅሊሱ ቁንጮ አመራሮች የሚያራምዱት አቋም ከሃይማኖቱ ተከታዮች ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰማይ ቤቱ ፈጣሪ ሳይቀር ጦርነት ገጥመዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ኢትዮጵያዊያንን አቻችሎ የያዘው ማህበራዊ ክር በእነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እየተዘመተበት ነው ። በማህበረሰቡ ዘንድ በፍራቻ የታጠረ ዝምታ እየበዛ በመሄዱ የተፈጠሩት ችግሮች እየተጠራቀሙ ከማንወጣው ማጥ ውስጥ እየከተቱን ነው። አሁን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኘው ሲኖዶስ የምንሰማው ጉድ በጣም ያስደነግጣል ። ሰሞኑን እንኳን ከፓትሪያርኩ አንደበት የወጣው ቃል ምን ያህል ሃይማኖታዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ መሔዳቸውን የሚያሳይ ነው ። አቡነ ማቲያስ ከሸገር ሬድዮ ጋር በደረጉት ቆይታ “ ሙስናን ተው ማለት ከአንበሳ አፍ ስጋ እንደመንጠቅ ነው ፥ አቅሙም ጉልበቱም የለንም ” ነበረ ያሉት ። ይሄኛው የፓትሪያርኩ አነጋገር እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የገለጠልኝ ነገር እነዚህ የእምነቱ አባቶች እግዚኣብሄር የሌለባቸው ፥ የሸሻቸውና ሊጠጋቸው ያልፈለገ መሆኑን ነው ። ታዲያ ! በአባቶቻችን ዘንድ እንዲህ አይነት ለስጋ የተገዛ የዲያቢሎስ መንፈስ በወረደበት ሁኔታ በማህበረሰቡ ዘንድ ከባድ ወንጀሎች ቢበራከቱ ለምን ይገርመናል?… ወጣቱ በሚያደነዝዝ እፅና የጫት ሱስ ተጠምዶ ብናይ ለምን ይደንቀናል?… በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሃቀኝነት ፥ ታማኝነትና መልካም ስነ – ምግባር የሚባሉ እሴቶች ድምጥማጣቸው በጠፋበት ሁኔታ በህብረተሰቡ ዘንድ ተንኮል ፥ እርስ በእርስ መጠራጠርና ሌብነት ቢስፋፋ ለምን አዲስ ይሆንብናል ?
ከዚህ በተጨማሪ የጎሳው ፓለቲካ የፈጠረው የህልውና አደጋም በግላጭ መታየት ጀምሯል። እንደ ወራጅ ጎርፍ አደጋው መጣሁ መጣሁ እያለ ነው ። የህወሓት አባላት የሆኑት የበኩር ልጆችና እና የእንጀራ ልጆች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የማራቶን እሩጫውን ጀምረዋል። እርግጥ ድምፃዊው እንዳለው ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተለኮሰ እሳት ተገልብጦ ለኳሹን ማጥፋቱ ታሪካዊ እውነታ ነው። ቢሆንም ግን አሁን ያለውን ተጨባጭ ውስጣዊ ችግር መቃኝት አስፈላጊም ጠቃሚም ይመስለኛል። የውስጣዊ ችግሩ መነሻና መድረሻው መታወቅና የትግሉ ማእቀፍ በአግባቡ መሰመር ይኖርበታል። ከድሮው የተለየ በመሆኑ።
***
ዛሬ ኢትዮጵያ የተጋረጠባት አደጋ በዋናነት ከውስጥ የሚመነጭ ነው። በዋናነት ማለቴን እንድታሰምሩልኝ እፈልጋለሁ ። በዘረኝነት ላይ የተሰነቀረው አምባገነንነት ባለመገታቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላም፣ ሕልውናና አንድነት ዋስትና አጥቷል። የውስጥ ገዢዎቻችን ከየትኛውም ዘመን በከፋ ሁኔታ አገራችንን የሕሊና ህመም በሚፈጥር አስፈሪ ሁኔታ ላይ ጥለዋታል። ኃላቀርና እውቀት አልቦዎቹ ህውሓቶች ተስፍ አስቆራጭ በሆነ መልኩ ሃገሪቱ ዘርን መሠረት ባደረገ መልኩ እንድትከፋፈል አድርገዋል። የጎሳና የዘር ክፍፍሉ ከምድራዊ ሕይወት ተሻግሮ በእምነት ተቋማት ውስጥ ዘልቆ በመግባቱ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ከመንፈሳዊ መላሸቅ ጎን ለጎን ሃይማኖታው ውድቀት ተከስቷል። የተከበሩት ሲኖዶስና መጅሊሶች ለፓለቲካ ስልጣን ምርኩዝ ሆነው የሚያገለግሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፓትሪያሪኩም ሆነ የመጅሊሱ መሪዎች ተጠያቂነት ለህውሓት የደህንነትና ፀጥታ ቢሮ ሆኗል።
የሆነው ሆኖ ኢትዮጵያ የተጋረጠባት አደጋ በወሳኝነት ከውስጥ ነው የተባለበት ምክንያት ይሄ ነው። የመጪውን ዘመን በፍራቻ እንድንመለከተው የሚያደርገው የድሮው ከውጭ ወራሪ ጋር የሚደረግ የብሔራዊ ነፃነት ትግል ሲሆን፤ ይህኛው ደግሞ በሃይማኖትና ጎሳ ከፋፍለው ከሚገዙ የውስጥ ኃይሎች ጋር የሚደረግ የነፃነት ትግል ነው። በዚህም ምክንያት የትግል አውድማው እጅግ ከባድና ቀድሞ ከነበረው ጋር ለየቅል የሚታይ ይሆናል። ዛሬ! ኢትዮጵያን እየከፋፈለ ያለው እንግሊዝ አይደለም። ዛሬ! በቅኝ ግዛት ሊይዘን የፈለገው ጣሊያን አይደለም። ዛሬ! አንገታችንን ሊቆርጡ የሚመጡት ደርቡሾች አይደሉም። ዛሬ! አምስት ኮከብ ስለው ኢትዮጵያን ሊበታትኑ የሚመጡት ሶማሌዎች አይደሉም።
***
ወደ ተነሳንበት ስመለስ የዛሬው መጣጥፌ መዳረሻ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሎም ኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ከድምፃዊ ቴድሮስ ካሳሁን ሊቀስሙት የሚገባ አንድ ተጨማሪ ተሞክሮ ለማከል በማሰብ ነው። ይኸውም ቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” በሚለው አልበምም ሆነ በተከታታይ በሰጣቸው ቃለ-መጠይቆች የገለጠው ሦስተኛ ቁምነገር ይሆናል። ስለ መቆጨት! ሰለመናደድ። አርቲስቱ ርዕቱ በሆነ አንደበቱ “መቆጨት አለብን! መናደድ አለብን! ቁጭት ከሌለ ወደለውጥ ለመሄድ ኃይል አናገኝም” ያለበት ይሆናል። ይህም ወቅታዊውን የአገራችንን ሁኔታ መገንዘብ መቻሉን የሚያመለክት ነው። በሌላ በኩል የሚቀጥለው ጉዞ ካለፈው ምን ያህል የከበደና የሚያስጨንቅ መሆኑን የሚያሳይ ነው። በእርግጥም እንደዚህ አይነት ጠመንጃ ነካሽ ክፉ ስርዓት ለመገላገል በንዴት የተሞላ ተስፋ አስጨራሽ ትግል የሚጠይቅ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነው። እልህ አስጨራሹ የሕዝብ ትግል ማዕከል ከፓለቲካ፣ ከኢኮኖሚና መንፈሳዊ እግረ-ሙቅ የመላቀቅ በመሆኑ በቁጭት መጓዝን ግድ ይላል። አረረም መረረም ሃገራችን የተደገሰላት የእርስ በእርስ እልቂት እየታወቀ ዝምታ ፋንዲያ እንጂ ወርቅ ሊሆን አይችልም ።
እናም አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን “መቆጨት አለብን! መናደድ አለብን! ቁጭት ከሌለ ለውጥ የለም” ብሎ ሲገልጥልን ምን ዓይነት መልዕክት እያስተላለፈልን እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። ሌላው ቢቀር ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገር በቀል ፋሽስቶች የተፈፀመው የጅምላ ግድያ፣ የጭካኔ በትርና ሰጥ ለጥ አድርጎ ለመግዛት የሚካሄደው አፈና ለምን አላስቆጨንም ብለን ከራሳችን ጋር ሙግት መፍጠር ችለናል ወይ? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል። የቅርብ ጊዜ ክስተቱን ብንወስድ እንኳን የመከላከያ እና የፀጥታ ኃይሉ ከህዝብ አብራክ እንዳልወጣ ሁሉ ህዝብን በጅምላ ሲጨፈጭፍ በስሜት ውስጥ ሆነን “ሞት ለገዳይ!” በማለት ህዝቡን አስቆጨን። ታዲያ መስከረም ሳያልቅ ለምን ወደ ሰገባው በፍጥነት ተምዘግዝገን ገባን ብለን ማንሳት ይኖርብናል። አርቲስቶቻችን ባቀነቀኑት የትግል መዝሙር ምክንያት ህዝቡን ከጫፍ እስከ ጫፍ በንዴት ፈንቅለን አስወጥተን ስናበቃ የራሳችንን እግር ለምን ጎተትን ብለን መወቃቀስ ይኖርብናል። እንደኔ እንደኔ ዛሬ የመወቃቀስና የመነቃቀፊያ ጊዜ ነው። ገና አልረፈደም። እንደውም በሃቅ እንነጋገር ከተባለ “እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል” በሚል የእንስሳይቱ ፍልስፍና የሚመራው የህወሓት አገዛዝ ከትላንት እና ዛሬ በከፋ ሁኔታ ነገ ከነገ ወዲያ የሚፈፅመው ወንጀል የከፋ ይሆናል። እናም ተወዲሁ እርምት ወስዶ በቁጭት መራመድ ያስፈልጋል። ዛሬም “ማንነት የራስ ነው፥ አገር የጋራ ነው፥ ቁልፍና ማሰሪያው፥ ኢትዮጵያዊነት ነው!” ከሚለው መዝሙር ጋር በተጓዳኝ “ሞት ለገዳይ” መቀንቀን ይኖርበታል።
እንግዲህ ከላይ በጥቂት የዘረዘርኳቸው ነጥቦች የሚያመላክቱን ነገር በርካታ ጉዳዮች ደም የሚያስተፋና ፀጉር የሚያስነጭ ንዴት የሚፈጥሩብን ሊሆን በተገባ ነበር። ከላይ እንደተገለጠው ባለፈው ሁለት ዓመት ብቻ በኦሮሚያ፣ አማራ፣ ኮንሶ፣ አኝዋክ፣ ሱማሌ ውስጥ የተፈፀመው ግፍ ኢትዮጵያ ውስጥ መወለድን እስከመጥላት የሚያደርስና ዘግናኝ ነው። ገደብ የለሽ የስልጣን ጥማት ተሳክረው በጥይት አርከፍክፈው በገደሉት የልጅ ሬሳ ላይ ወላጅ እናት መቀመጣን ስንሰማ “አናኛቱ (ለእኔ ያድርገው)” ማለት የሚገባ ነበር። ኢትዮጵያዊ አባት ለአሳር ነው የተፈጠርከው የተባለ ይመስል በመከራ ያሳደጋቸውን ሦስት ልጆቹን በአንድ ቀን በጥይት ተደብድበው ሬሳቸውን ሲታቀፍ መመልከት በድጋሚ “አናኛቱ” ያስብላል።…አናኛቱ !…ለእኔ ያርገው !!
***
በነገራችን ላይ ይሄ “አናኛቱ” በሚል ርዕስ የተቀነቀነው የቴዲ አፍሮ ዘፈን በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ምን ያህል ቁጭት እንደፈጠረ ለማወቅ ብዙ መጓዝ አልጠየቀኝም። ጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሠፈረው ለዚህ አባባሌ በምሳሌነት ሊነሳ የሚችል ነው። የጋዜጠኛ በፍቃዱ ሞረዳ ከፊል ጽሑፍ እንደዚህ ይላል።
“… የሌሎችን ስሜት ባላውቅም ቴዲ አፍሮ በሰሞኑ ዘፈኑ በአፋን ኦሮሞ ያዜማት ባለሁለት ስንኝ መልዕክት ቢያንስአስለቅሳኛለች። ሁለት የአፋን ኦሮሞ ስንኞች (“አኩማ ባቴ ሓፍቴ፤ ሙጫኮ በርባደቤ አዱን ዴቢን አቹማ ነፌ”) በእነዚህ የአማርኛ ስንኞች ሊገለፅ ይችላሉ (ትርጉም የእኔ)
“አባትና ልጅ”
ትመጣለች ብዬ ደጅ ደጁን ሳይ፣
ወድቃ ቀረች ልጄ አውራ መንገድ ላይ
ወንድ ልጄም ወጥቶ ሊፈልግ እህቱን
እርሱም ጎዳና ላይ ተቀማ ህይወቱን።
በሠላም ከወላጆቻቸው ተለየተው ወጥተው በጎዳና ላይ በወያኔ ጥይት ወድቀው ለቀሩት እህትና ወንድሞቼ እንደገናእንዳለቅስ አድርጎኛልና!” ይለናል።… አይዞን በፍቄ!… አናኛቱ! … ለእኔ ያድርገው!
***
አርቲስት ቴድሮስ ካሳሁን “መቆጨት አለብን! መናደድ አለብን! ቁጭት ከሌለ ለውጥ የለም” ብሎ ሲገልጥ ሌላ ማስተላለፍ የፈለገው ቁምነገር ያለ ይመስላል። የህወሓት አገዛዝ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለው ንቀት ገደብ የሌለው መሆኑን ማሳየት። እርግጥ የህወሓትን ባህርያት ዘልቆ ለተመለከት አንድ የማይካድ ሃቅ ላይ ይደርሳል። ይኽውም ህወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ የተፈጠረበትን የበታችነት ስሜት ለመደበቅ ከሚጠቀምባቸው ስልቶች አንዱ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያለውን ንቀት ማሳየት ነው። ህወሓት የኢትዮጵያን ታሪክ አናንቆና በመቶ ዓመት ገድቦ ያሳያል። ህወሓት በደማቸውና ባጥንታቸው የዛሬዋ ኢትዮጵያ አውርሰው የሄዱትን ነገስታት የጦር አበጋዞች ያበሻቅጣል። አልፈው ተርፈው የኢትዮጵያን የምስረታ ሂደት እንደወረራና ቀኝ ግዛት በመቁጠር ከታሪክ ሂደትና ከሕብረተሰብ ዕድገት ጋር የሚጋጭ አድርጎ በማሳየት ነገስታትን አመድ አፋሽ ያደርጋል። ዛሬ ዛሬ ስብሃት ነጋን የመሳሰሉ የህወሓት የጡት አባቶች የተለየ አቋም ቢያራምዱም ፓርቲው ደደቢት ላይ ከተመሰረተ ጀምሮ ኢትዮጵያን በቀን ገዥነት የሚከስ ድርጅታው ፕሮግራም ቀርፀው ሲንቀሳቀሱ ነበር። “ያደቆን ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም” እንደሚባለው ዛሬም የአመለካከት ለውጥ ማምጣት አቅቷቸው ሲንቧተሩ የታያል። ለክፋትና ለዘረኛ አላማቸው ያለመታከትና ያለዕረፍት እስከ መጨረሻው ቤተሰብ ድረስ በመዝለቅ ሰንሰለታቸውን “አንድ-ለአምስት” በመዘርጋት ላይ ናቸው። ሌላው ቀርቶ የጫት፣ ካቲካላና ጠላ ቤቶች ወግ ከጊዜ መግደያነት ተሻጋግረው የጎሳ ፓለቲካና ትውልድ መከፋፈያ መድረክ ሆነው እንዲቃኙ ተደርገዋል። በምርቃናና ስካር መንፈስ ውስጥ ተኹኖ እንኳን አገዛዙን መተቸት የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህም ሆኖ በእነዚህ ከይሉኝታ የተሰናበቱ ልበ-ወፍራሞች ድርጊት አንቆጭም። ተራ በተራ ሱሪያችንን ዝቅ አድርገው እየገረፉን በውስጣችን ንዴት የለም ። እየደረሰብን ባለው በትር የሞራል መላሸቁን ተከትሎ የፍርሃት ቆፈን ዙሪያችንን ከቦናል ። የብሎኬት ግድግዳ እያስገፉን “ እኛ ወያኔዎች አንዲህ ነን !” በማለት እያላገጡብን ቢያንስ የየጁን ደብተራ ቅኔና ቀራርቶ ማሰማት አቅቶናል ። እናቶቻችንን ፥ እህቶቻችንንና ሚስቶቻችንን መለ-መላቸውን እያስቆሙና ብልታቸው ውስጥ በረዶ እየጨመሩ እንደሚያሰቃዩ እየሰማን መናደድ አልቻልንም። ኧረ ለመሆኑ! አንዲት የፌስቡክ ጦማሪ “ራቁቴን አቁመው ተሳለቁብኝ” ከማለት ውጭ ምን እንድትነግረን እንፈልጋለን?… አንዲት የፖለቲካ እስረኛ “ጡቴን በኤሌክትሪክ ጠበሱት” ብላ ከመናገር በላይ ምን አይነት ማስረጃ ይገኛል?… ወንድ ልጅ “ብልቴን ስላኮላሹት ወደ ሚስቴና ቤተሰቦቼ አልሄድም ፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ይወቅልኝ” ብሎ ኑዛዜውን ከማሰማት በላይ ሌላ ምን ይጠበስልን? እስቲ ለአንድ አፍታ ቆም ብለን አናስብ! ራሳችንን እንጠይቅ! ለምን መናደድ አልቻልንም?…. ለምን መቆጣት አልቻልንም?…. ለምን መቆጨት አልቻልንም?
***
ይህንን መጣጥፍ ለመቋጨት እፈልጋለሁ። መጣጥፉን እየከተብኩ ያለሁት በኢሳት ቢሮ ውስጥ በሚገኘው የሙሉጌታ ሉሌ መታሰቢያ መጽሃፍት ቤት በመሆኑ በእሱ አስተያየት ልቋጭ። አንጋፋው ብእረኛ በጦቢያ መጽሄት ላይ “ ሰው ስንፈልግ ባጀን “ በሚለው መጣጥፉ በቁጭት የተሞላ መናደድ ለስር ነቀል ለውጥ እንደ-ቅድመ ሁኔታ መታየት እንዳለበት ያስገነዝባል ። እርግጥም መናደድ ትልቅ ነገር ነው ። መናደድ ብንችል አንዱ የዚች ሃገር ማዳኛ የትግል መቅድም ይሆናል። ግን ለመናደድ ለመብሸቅና ከተቻለም እህህ ብሎ ደም ለመትፋት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል ።ታዲያ! ችግሩ አንናደድም ።ከጊዜያዊ ብሽቀት ወጥተን ጨጓራችን እስኪላጥና ቆሽታችን ድብን እስኪል ንዴት የወለደው ቁጭት መፍጠር አልቻልንም ። እንደ መስቀል ወፍ ብቅ ጥልቅ የሚለው ንዴታችንም ወደ ተግባር መቀየር ተስኖታል ። ለምን ይሆን? ራሳችንን እንጠይቅ።
No comments:
Post a Comment