Translate

Tuesday, November 24, 2015

“ገበሬው ነፃነት ካላገኘ ችጋር ሁልጊዜ በኢትዮጵያ ይኖራል” ፕሮፌሰር መስፍን

farmer
* “ችጋር የሰው ልጅ እንደ ማገዶ እንጨት ተለብልቦ የሚያልቅበት የውርደት ሞት ነው”
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (Institute of Development Research) ሥር ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ለ10 ዓመታት ያህል በ102 የኢትዮጵያ አውራጃዎች ላይ ምርምር አድርገው ስለ ድርቅ በእርሳቸው አጠራር (ስለ ችጋር) (Rural vulnerability to famine in Ethiopia 1958-1977) የሚል መጽሐፍ ጽፈዋል። የእንቢልታ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በዛሬው እትማችን ለበርካታ ዓመታት በድርቅ ጉዳይ ያካሄዱትን የምርምር ሥራ መሠረት አድርገን በወቅታዊው የአገሪቱ የድርቅ ሁኔታ ላይ ከጽዮን ግርማ ጋር ቆይታ አድርገዋል። (ዓርብ መጋቢት 26 ቀን 2000 ዓ.ም)

ድርቅን በሚመለከት በርካታ ጥናቶች አድርገዋል። ለምን ያህል ዓመት ነው በጉዳዩ ዙሪያ የሠሩት?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- በመጀመሪያ እኔ ድርቅ አልለውም “ችጋር” ነው። ስሙም እሱ ነው። ያ ማድበስበሻ ቃል ነው። ጥናቱን በሚመለከት እሱን ብቻ ይዤ ለ10 ዓመታት ነው ጥናት ያደረኩት፤ ከዚያም አንድ መጽሐፍ ጻፍኩኝ። ልክ መጽሐፉ እንደወጣ የ1977 ዓ.ም. ከፍተኛ ችጋር ተከሰተ፣ በዚህ ችጋር በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበት ነበር።
ካደረጉት ጥናት ተነስተው ችጋር የሚለውን ያብራሩልኝ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ችጋር ሁላችንም አልፎ አልፎ የምናውቀው ዓይነት ረሃብ አይደለም። ችጋር በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ብቻ ሰዎችን በአንድ ጊዜ የሚያጠቃ የኅብረተሰብ በሽታ ነው። ችጋር ምንም የሚላስ፣ የሚቀመስ በመጥፋቱ ሰዎች በአካላቸው ውስጥ በአከማቹት እየተጠቀሙ፣ ዕለት በዕለት አካላቸውን እየጨረሱ፣ እያወቁት ቀስ በቀስ ወደተረጋገጠ ሞት የሚሄዱበት የኅብረተሰብ በሽታ ነው። ቤተሰብ ይፈርሳል፤ ኅብረተሰብ ይፈርሳል። ባል ለሚስቱ፣ እናት ለልጅዋ፣ ዘመድ ለዘመድ ያለው ፍቅርና ቅን መንፈስ ሁሉ ተንኮታኩቶ እያንዳንዱ ሰው ለብቻው የየራሱን ጻዕር እያብሰለሰለና እያቃሰተ የሚደቆስበት በሽታ ነው። ሕፃን ልጅ የእናቱ ጡት መድረቁን ባለማወቁ እያኘከ የቦጨቃቸውን ጡቶች አይቻለሁ፤ እናቲቱም በባሰ የችጋር ሕመም ተይዛ ከእንደዚህ ዓይነቱ ሕመም ውጭ ነበረች።
ችጋር የሰው ልጅ እንደ ማገዶ እንጨት ተለብልቦ የሚያልቅበትና ቀባሪ እንኳን የማያገኝበት የውርደት ሞት ነው፤ የሰው ልጅ ውርደት ነው፤ የኅብረተሰብ ውርደት ነው፤ የአገር ውርደት ነው። ቁራሽ እንጀራ ወይም እፍኝ ቆሎ የሚሰጥ ዘመድ ወይም ወዳጅ ወይም ወገን ጠፍቶ፣ ለነፍሱም ይሁን ለሰብዓዊ ርኅራሄ ተነሳስቶ፣ የሚረዳ ጠፍቶ በሺህና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በየቤታቸው፣ በየመንገዱና በየገበያው የሚወድቁበት ሁኔታ ነው።
ችጋር የሚመጣው በድርቅ ወይም በተምችና ሌሎች የሰብል ተባዮች ወይም በዝናም ብዛትና በበረዶ ወይም እግዚአብሔር በመቆጣቱ ወይም በእነዚህ ሁሉ ነው ይባላል። እነዚህ ሁሉ ምክንያቶች የሚደረደሩት ሆን ተብሎ በማንም ላይ ኃላፊነት እንዳያርፍ ለማድረግ ነው። ሁሉም ከእውነቱ የራቀ ነው። እውነቱ ነገር እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ችግሮች በብዙ አገሮች ይከሰታሉ፤ ሆኖም በዚህ ምክንያት ሰዎች በችጋር አለማለቃቸው ነው። እውነቱ ነገር ችጋር የአገዛዝ ሥርዓት ውጤት መሆኑ ነው። እውነቱ ነገር ችጋር ኅብረተሰቡ በአገዛዝ ሥርዓት ደንዝዞና በራሱ የኑሮ ትግል ተተብትቦ የመተሳሰብና የመረዳዳት መንፈሱ የተሟጠጠ መሆኑ ነው። እውነቱ ነገር ችጋር የሚጀምረው የድርቅ ወቅት ከመድረሱ በጣም ቀድሞ መሆኑ ነው።
ለመሆኑ ማን ነው በችጋር የሚጠቃው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ለብዙ ሰዎች ግራ የሚያጋባው ነገር በችጋር የሚጠቁት ገበሬዎች በተለይም የምግብ እህልን የሚያመርቱት መሆናቸው ነው። ለምሳሌ የቡና ገበሬዎች በችጋር እምብዛም አይጠቁም። ይህ የሚሆንበት ራሱን የቻለ በቂ ምክንያት አለ።
1ኛ እህል የሚያመርቱ ገበሬዎች አብዛኛውን ጊዜ ለራሳቸው የሚያስፈልጋቸውን እህል ያመርታሉ እንጂ በገበያ የበለጠ ዋጋ ያስገኝልናል በማለትና ከገበያም በርካሽ ዋጋ ሌላ እህል ለራሳችን እንገዛለን ብለው ሂሳብ አስልተው አይደለም።
2ኛ በብዙ ምክንያቶች ምርታቸው ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸውም ከአዝመራ እስከ አዝመራ የሚያደርሳቸው አይደለም።
3ኛ አዝመራውን ጠብቀው የሚመጡና ምርታቸውን የሚሻሟቸው ቀበኞች ብዙ ናቸው። ግብር አስከፋዩ፣ በልማት ስም የማያልቁና ማቋረጫ የሌላቸው የመበዝበዢያ መዋጮዎችና ለገበሬው በአራጣ ያበደሩ ሁሉ ገበሬውን የአዝመራውን ጊዜ ጠብቀው ያራቁቱታል። ገና በልቶ ሳይጠግብ ወጥረው ለሚይዙት ለእነዚህ ቀበኞች መክፈል አለበት፤ አለዚያ መታሰርና መጉላላት የማይቀር ነው። አሁን ደግሞ የማዳበሪያ ዕዳ ተጨምሯል።
በአዝመራው ጊዜ ገበሬው ስለሚወጠር በግድ እህሉን መሸጥ ይኖርበታል። ገበሬው ሁሉ እህሉን በአንድ ጊዜ ወደ ገበያ ያወጣል፤ ዋጋው አሽቆልቁሎ ይጠብቀዋል። ግዴታውን ለመወጣት በርከት አድርጎ መሸጥ ይገደዳል። ከገበሬው የመኖር ግዴታ የቀበኞቹ የጥሬ ገንዘብ ፍላጎት ይበልጣል። ይቀድማል። ችጋርን ጸንሶ የሚወልደው የአገዛዝ ሥርዓት ግፍ ነው። ይህንን እውነት ሳይረዱ ችጋርን እናጠፋለን የሚሉ ችግሩን አልተገነዘቡትም ወይም ሊገነዘቡት አይፈልጉም። ችጋርን ማስወገድ የሚችሉት ገበሬዎቹ ብቻ ናቸው፤ የራሳቸው ባለቤቶች ለመሆን ነፃነታቸውን ሲያገኙ።
ችጋር እንደ ደራሽ ውሃ ወይም እንደ እሳት ቃጠሎ ወይም እንደ መሬት መንቀጥቀጥ በድንገትና ሳይታሰብ የሚመጣ አደጋ አይደለም። ችጋር ሰዎችን ወደ አስከፊ የጅምላ ሞት ለማድረስ ቢያንስ ሰባት ወር ይፈጃል። የገበሬው ኑሮ በተለይ የምግብ ፍጆታው ማሽቆልቆል የሚጀምረው ገና የአዝመራ ወራቱ ሳያልቅ ነው። ይህ የምግብ ፍጆታ ማሽቆልቆል የሚጀምርበት ጊዜ ክረምት ከመግባቱ በጣም ቀድሞና የድርቅ ጉዳይ ገና ሳይሰማ ነው።
በአሁኑ ወቅት በቦረና አካባቢ ድርቅ ተከስቷል፣ ከብቶች ሞተዋል፣ ረሃቡ በሰዎች ላይም እየተከሰተ ነው። ለምንድን ነው ድርቅ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚከሰተው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- የአንድ ችግር መነሻ እስኪታወቅ ድረስ ነው ችግር የሚሆነው። ከታወቀ በኋላ እንዴት ችግር ይሆናል፣ ለምሳሌ ድርቅን እንውሰድ፤ ተምች ወይም አንበጣ መጣና ችጋር አስከተለ እንበል። ይኼ በመጣ ቁጥር ችጋር ያስከትላል ማለት ነው። ድርቅ የሆኑባቸው የተለያዩ የዓለም አገራት አሉ። ለምሳሌ የዓረብ አገሮች ዘላለም ድርቅ ናቸው፤ ግን ችጋር የለም። በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ አልፎ አልፎ ድርቅ ይመጣል፤ ነገር ግን ችጋር የለም። ቻይናና ሕንድ በዱሮ ጊዜ የችጋር አገር ነበሩ፤ ዛሬ በእነዚህ አገሮች ችጋር የለም። ስለዚህ ያ የተፈጥሮ ምክንያት አንድ ጊዜ ሳይታወቅ መጥቶ ከሆነ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ ግን ማሰብና ለዚያ መዘጋጀት ያስፈልጋል። ያንን እንግዲህ እያንዳንዱ ገበሬ ነፃነት ቢኖረው ራሱ ያደርገዋል። አለዚያ ደግሞ በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መንግሥት፣ የሕዝቡን ፍላጎት የሚፈጽም፣ ነገ ይኼ ሕዝብ ከሥልጣን ያወርደኛል ብሎ የሚሰጋ መንግሥት ካለ አስፈላጊውን ሁሉ አድርጎ ችጋሩን ማስወገድ ይችላል። ግን አገር አስተዳዳሪው መንግሥት ለጉዳዩ ግድ የሌለው ከሆነ ያ ገበሬ እንዴት ብሎ ነው ከችጋር ሊወጣ የሚችለው፣ አቅሙ የለውም፣ ነፃነቱ የለውም። ነፃነት፣ አቅም፣ ችሎታና ወኔ የሌለው ገበሬ ሁል ጊዜም ሞት አፋፍ ላይ ነው ያለው፤ አንድ ትንሽ ነገር ሲደርስበት ክንብል ብሎ ይወድቃል።
የገበሬ “ነፃነት” ሲሉ ከምን አንፃር ነው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ከሁሉም አንፃር፤ ሰው እኮ ከጉንዳን አያንስም፤ ጉንዳን ትሰበስብና ለክፉ ቀን ብላ ጉድጓድ ውስጥ ትጨምራለች። ዱሮ የኢትዮጵያ ገበሬ እንደዚህ ያደርግ ነበር። አሁን ለምንድን ነው የማያደርገው፤ ግብር እና የማዳበሪያ ዕዳ ክፈል፤ ካልከፈልክ ትታሰራለህ በሚል ተወጥሮ ይያዛል፣ ያለችውን ነገር ሸጦ ለራሱ ሳይሆን ለአስገባሪዎቹ ይከፍላል። ካለው በጎቹንም ሆነ እህሉን ይሸጣል። አልፎ አልፎ ደግሞ ለተለያዩ ነገሮች መዋጮ ይጠየቃል። ይህ እንግዲህ በገንዘብ በኩል የሚከፈል ግብር ነው። በጉልበቱም የሚከፈል ግብር አለ እርሱ አርሳለሁ ብሎ ሲዘጋጅ ጥሩንባ ተነፍቶ መንገድ ሥራ፣ ድንጋይ ፍለጥ ወይም እዚህ ቦታ ስብሰባ አለና ተሰብሰብ ይባላል። ጊዜውም ገንዘቡም የሱ አይደለም የአስተዳዳሪዎቹ ነው። ይኼ ነው ነፃነት የሌለው የሚያደርገው።
ከተፈጥሮ የድርቅ አደጋ ውጪ የድርቅ መንስኤ ተብለው የሚጠቀሱ ነገሮች ምንድናቸው?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ድርቅ አንድ ጊዜ ያጠቃል። ሁለተኛ ጊዜ እንዴት ያጠቃል? ለምን ዝግጅት አይደረግም? ለገበሬው ነፃነቱ ተሰጥቶት እንዲዘጋጅ አናደርግም። ጥሪት እንዲያካብት፣ ገንዘብ እንዲኖረው ማድረግ ለምን አይቻልም? ለምሣሌ እዚህ ከተማ ያለን ሰዎች አይርበንም፤ ችጋርም አይነካንም፣ ለምንድነው ችጋር የማይነካን? ገንዘብ አለን፣ ገዝተን እንበላለን። ገበሬው በችጋር የሚሰቃየው ለምንድ ነው ገንዘብ የለውም። ገንዘብ የሌለው ለምንድን ነው? በየጊዜው እያራቆቱት፣ እያደኸዩት ስለሚሄዱ ነው። ለምሣሌ የሚከፍለውን ግብር ሃምሳና መቶ ኩንታል እህል የሚያመርት ገበሬ በዚያው መጠን ክፈል ቢባል ሊገባን ይችላል። ግን አሥር፣ አሥራ አምስትና ሃያ ኩንታል የሚያመርት ገበሬ ምኑን ነው ከዚያች ላይ የሚከፍለው። ደረጃ መኖር አለበት። ደረጃ ወጥቶለት፣ ከዚህ በታች የሚያመርቱ ገበሬዎች ከግብር ነፃ መሆን አለባቸው። በጣም እንዲያመርቱ ከተፈለገ ሌላ ዓይነት ዘዴ መፈጠር አለበት። እነሱን ለማነቃቃት፣ ለማትጋትና እንዲሠሩ ለማድረግ ዘዴ መቀየስ አለበት።
አነስተኛ ኩንታል የሚያመርተውን ታክስ ክፈል ማለት አትብላ፣ በችጋር አፋፍ ላይ ቁጭ በል ማለት ነው። እንደዚህ ዓይነቱ ሰው ድርቅም ይሁን ተምችም ይሁን ምንም ይሁን፣ ሲመጣ እሱ አፋፍ ላይ ነው ያለው ክንብል ይላል። አፋፍ ላይ ያደረገው ማነው ነው? ጥያቄው አፋፍ ላይ ያደረገው አገዛዝ ነው። ነፃነት ማጣት ነው። ኃይል ማጣት ነው። ጉልበት፣ አቅም ማጣት ነው። ተገፍቶ፣ ተገፍቶ አፋፍ ላይ የደረሰው ገበሬ የተፈጥሮ መጥፎ መልኩ ሲመጣ ክንብል ይላል። ብዙውን ጊዜ የሚታየውና የሚሰማው ታዲያ ይኼ አፋፍ ላይ የደረሰው ገበሬ ክንብል ሲል ተፈጥሮ፣ ድርቅ፣ ተምች፣ አንበጣ እና የመሳሰሉት ናቸው ችጋሩን ያመጡት ይባላል። ገበሬውን እዚያ አፋፍ ላይ ገፍቶ ያደረሰው ግን ተፈጥሮ ሳይሆን አገዛዝ ነው።
ድርቅ ተከስቷልና ከጥናትዎ በመነሳት መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ነፃነት ነው። ገበሬው ነፃ መሆን አለበት። የራሱ ባለቤት መሆን አለበት። የሀገሩ ባለቤት መሆን አለበት። ይኼ ድሮ እንኳ ይደረጋል። እኔ ጐረምሣ በነበርኩበት ጊዜ ክፍለ ሀገሮች ሄጃለሁ። እዚያ ስሄድ ብዙ ገበሬዎች አራት፣ አምስት፣ አስር ጐተራ እህል የነበራቸው ነበሩ። በጐተራ እህል ያስቀምጣሉ። አሁን የለም፣ በጐተራ እህል የሚያስቀምጥ ገበሬ የለም። የታለና ይወስዱታል። ወዲያው እና ለክፉ ቀን ማሰብ የሚችልበት ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው። እያራቆቱት፣ እያደኸዩት ነው ያለው።
በኢትዮጵያ ከተከሰቱት ድርቆች ምን ያህሉን በጥናትዎ አካተዋል?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- አንድ ሁለት ተብሎ የሚቆጠር አይደለም። ጥናቱን ሳደርግ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩትን ችጋሮች በሦስት መንገድ ነው የከፈልኳቸው። አንደኛው ጥቂት ወረዳዎች አካባቢ የሚደርስ ችጋር አለ። ይኼ ትንሽ ነው፣ ብዙም ሰው አይሞትም ምክንያቱም ዙሪያውን ብዙ እህል አለ። ተለማምኖም፣ ተዟዙሮም ሠርቶም ከዚያ ለመውጣት ይቻላል። ከዚያ ደግሞ ክልላዊ ችጋር አለ። ብዙ አውራጃዎች ወይም ክፍለ ሀገሮች የሚያጠቃልል፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን የሚነካ ይሆናል። ይኼ ጠበቅ ይላል። እህል የማጣቱ ሂደት ሰፊ ነው የሚሆነው። ሦስተኛውና ትልቅ ደረጃ ያለው ብሔራዊ ችጋር ነው። ብሔራዊ ችጋር ሲባል አብዛኛውን የሀገሩን ክፍል ይይዘዋል። በአብዛኛው በሀገሩ ክፍሎች ውስጥ ምርት ስለሌለ እህል ከውጪ መጥቶ ወይ በእርዳታ አሊያም በነፃ መሰጠት አለበት። ለመሸጥ አይቻልም።
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም
በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ወሎ ችጋር ነበር። መንግሥት ወደ 20 ሺ ኩንታል ስንዴ ይመስለኛል በርካሽ ዋጋ እንዲሸጥ ለተራበው ሰው ተብሎ ለተለያዩ የወሎ አውራጃዎች ተላኩ። ላስታ፣ ወድላደላንታ፣ ወረኢሉ፣ ወረሂመኑ፣ ደሴ ተላከ። ገበሬው ግን ገንዘብ የለውም። በጣም ርካሽ አድርገው ነው ያቀረቡት። ከየት አምጥቶ ይግዛው፤ ገበሬው እየሞተ ነበራ። አገዛዝ ለዚያ እህል ቤት ተከራይቶ አስቀምጦት ነቀዝና አይጥ እየበላው ወደ አራት ዓመት የሚሆን ጊዜ ተቀምጦ ብትንትን ብሎ ዋጋ የሌለው ነገር ሆኖ በኋላ አንድ ሰው ዳቦ መጋገሪያ ብሎ በጣም በርካሽ ዋጋ ገዛው። እርሱ እየሸጠ ግን ከብሮበታል። ገንዘብ ለሌለው ሰው በርካሽ ዋጋም ቢሆን ግዛ ብሎ ማቅረብ ያለማሰብ ነው። ከዚያ በኋላ እንግዲህ ሌሎች ነገሮች መጥተዋል፤ በደርግ ጊዜም በአሁኑም ጊዜ “ምግብ ለሥራ” የሚባል ነገር መጣ። ምግብ ይሰጧቸዋል፣ ገበሬዎቹን ያሠሯቸዋል፤ ይኼም ራሱ ሥራን ማሳጣት ነው። ገበሬው ነፃነት እንደሌለው ነው የሚሰማው ይኼንን ሥራና 20 ኪሎ ስንዴ፣ ዘይት እሰጥሃለሁ እየተባለ ስንት ዓመት ነው እንደዚህ የሚኖረው። አሁን እኮ ወደ ሃምሳ ዓመት እየተጠጋን ነው። ከ1951 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ይኸውና አንድም ዓመት የችጋር ወሬ ሣይሰማ የቀረበት ጊዜ የለም። ዛሬ ቦረና ይሆናል፣ ነገ ደግሞ ሌላ ቦታ እንሰማለን። በኦጋዴን፣ በትግራይ፣ በምሥራቅ ጐጃም፣ በምሥራቅ በጌምድር፣ ጐንደር፣ ደቡብ ወሎ ብቻ በየዓመቱ ችጋር ይከሰታል።
በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ በትግራይ በደረሰው ከፍተኛ ረሃብ ላይ ተገኝተው ነበር። በወቅቱ ያዩትን ቢነግሩን?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- እሱን እግዚአብሔር አያሳይሽ፣ በጣም መጥፎ ነገር ነው። ሰው መሆንሽን የሚያስጠላ፣ የሚያንገፈግፍ ነገር ነው። እንደዚህ ዓይነት ቦታ አንዴ ከሄድሽ በድጋሚ ለመሄድ አቅም አይኖርሽም። ሰዎች የሚላስ፣ የሚቀመስ አጥተው ቅጠሉ ሁሉ ደርቆ፣ አካባቢው ምድረ በዳ ሆኖ፣ ዝም ብሎ፣ ቁጭ ብሎ፣ የራስን ሰውነት መብላት ነው። ያከማቹትን ሰውነታቸውንና አካላቸውን እየተጠቀሙ እያለቀሱ፣ ዕለት በዕለቱ ወደ ሞት ሲሄዱ ማየት ማለት ነው። የሚደረገው እርዳታ በቂ አልነበረም። በቂ ካለመሆኑም በላይ ይሰጣቸው የነበረው 25 ኪሎ ስንዴ ነው። ያንን ምን ያደርጉታል? መሬት ላይ የወደቀች ስንት ቀን እህል ያልበላች አንዲት እናት እንዴት ብላ መሸከም ትችላለች? ተሸክመው ቢወስዱት እንኳ ምን አድርገው ይመገቡታል? በችጋር በጣም የደከሙ ሰዎች ነበሩ። እርዳታው ለይስሙላ የግብር ይውጣ ዓይነት ነው፡፡ ያስፈልግ የነበረው የበሰለ እህል ነው። ሲሆን እንደ ሾርባ ዓይነት እንደው ሣያኝኩት ሊውጡት የሚችሉት ነገር እያዘጋጁ መስጠት ነው። ግን ይኼ አልታሰበም እህሉም ቢሆን እኮ ከውጪ የመጣልን ነው የኛው አይደለም። በእርዳታ የተገኘ ነው። ያን ጊዜ የአሜሪካኖች እርዳታ ነው።
በደርግ ጊዜ በተከሰተው ድርቅስ ተገኝተው ነበር?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- አንድ ጊዜ ካየሽው በኋላ ሁለተኛ ማየት አትፈልጊም። የመጀመርያውን በአካል ተገኝቼ ካየሁ በኋላ ሁለተኛ ጊዜ በአይኔ ማየት አልፈለኩም። ግን ሰዎች እየላኩ የሚሆነውን ነገር ዕለት በዕለት እከታተል ነበር። ጀማሪ መምህራኖችን እየላኩ ዕለት በዕለት መረጃ አገኝ ነበር።
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ድርቁ መሻሻል አላሳየም?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ምንም የተሻሻለ ነገር የለም። በርግጥ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በ76ቱና በ77ቱ ችጋር ብዙ የዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ገቡ። እነዚህ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እህል እያመጡ ለገበሬው በያለበት ያድላሉ፣ ምግብ ለሥራ እንደዚህ እያሉ ከ77 ጀምሮ እስካሁን ድረስ እንደቀጠለ ነው። እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ችጋር ሥራቸው አድርገው ዋና ሥራቸውን እዚሁ ተከሉ። እንደውም ትንሽ የዝናብ እጥረት ያለ እንደሆነ እሪ ይላሉ። በዓለም አቀፍ ደረጃ ቶሎ ይወጣል። ስለዚህ ወደ ሞት ደረጃ ሳይደረስ እህል እያመጡ እነዚሁ ያከፋፍላሉ። ሌላው በደርግ ጊዜና በወያኔ ዘመን የተለመደ ነገር ምንድን ነው፣ አንዳንዶች የዚህ ኃላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች አሉ። የመንግሥት ለማኞች በያቸው። አንድ የእርዳታ አስተባባሪ ድርጅት ወይ ሌላ ስም ይሰጠው የልመና ድርጅት ተቋቁሟል። አንዳንድ ጊዜም ከውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርም ቢሆን አምስት ሚሊዮን፣ ሰባት ሚሊዮን፣ አሥር ሚሊዮን ሕዝብ ለመራብ ተቃርቧል እያሉ የዓለም አቀፉን ሕዝብ ያስጠነቅቃሉ። እነሱ ኃላፊነታቸውን ከራሣቸው ወደ ዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ያሸጋግሩታል። እና እነዚያ እስካሁን ድረስ እህል፣ እነዚህም እዚህ ያሉት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እህል ያስመጣሉ፣ ያከፋፍላሉ፣ ይሰጣሉ። በዚህ ምክንያት በሰፊው የሞት አደጋ የደረሰበት ችግር ከ1977 ዓ.ም. ወዲህ አልተከሰተም። ግን ችጋር የለም ማለት አይደለም። እስካሁንም ድረስ አለ። እነዚያ ሲያቆሙት፣ እነዚያ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች በመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወይም እነ አሜሪካ እና እነ አውሮፓ መስጠቱን ሲያቆሙ ችጋሩ በከፋ መልኩ ድሮ እንደነበረው ገበሬው መርገፍ ይጀምራል። አሁን ያለው በኛ በኢትዮጵያ ሳይሆን በውጪ እርዳታ ኃይል ነው።
እሱ መቋረጥ የለበትም ነው የሚሉት? ሰው ሁልጊዜ እየተደጐመ መኖር የበለጠ አያባብሰውም?
ፕሮፌሰር መስፍን፡- ወያኔ ሲጀምር እኛ ይኼንን እርዳታ ብቻ አንፈልግም፣ ገበሬው እንዲሠራ ለማድረግ እሱን ለማነቃቃት፣ የበለጠ ምርታማ እንዲሆን ለማድረግ እርዳታውን በገንዘብም እያደረጋችሁ ለኛ ስጡን፣ ብዙ ዘዴ አለ ብሎ ነበር። ግን መፍትሄ አልተገኘም። የችጋር መፍትሄ የገበሬ ነፃነት ብቻ ነው። ነፃነት እኮ ኃላፊነትን ይወስዳል። ነፃ ከሆንሽ ሕይወትሽ፣ ኑሮሽ በእጅሽ ነው። ኃላፊነቱ ያንቺ ነው ከተባልሽና ሌላ መጥቶ ቢበዘብዝሽስ፣ ነጋ ጠባ ይኼን አምጪ፣ ይኼን መዋጮ አምጪ፣ ይኼን ግብር ክፈይ እያለ የሚበዘብዝሽ ከሌለ አንቺ ራስሽን መቻል አያቅትሽም። እንደ ሰው ትዘጋጃለሽ።
ለክፉ ጊዜ ያለው ነፃነት ኃላፊነትን በእያንዳንዱ ሰው ላይ ያሳድራል። አሁን ኃላፊነቱ መንግሥት የሚለውም አይደለም። ኃላፊነቱ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሆኗል። እኔ ከ3ዐ ዓመት በላይ ችጋርን ለማጥፋት ነፃነት ስል ቆይቻለሁ። እስካሁን ድረስ እነሱ ያመጡት ነገር ሁሉ ምንም መፍትሄ አላስገኘም። ሊያስገኝም አይችልም። በተለይ ገበሬው ነፃ ካልሆነ የራሴ ባለቤት ነኝ ካላለ፣ ለመሬቱ ለምርቱ ባለቤትነቱን የሚያረጋግጥበት ሕጋዊ መሠረት ከሌለው ማንም እየመጣ እንደፈለገ የሚጫወትበት እስከሆነ ድረስ ችጋር ሁልጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖራል።

No comments:

Post a Comment