ባለጌ ብልግናውን በትምህርት ፣ በሥርዓት በተገመደ ባህል ፣ በቤተሰብ እና በሚከተለው ሃይማኖት ካላረቀ ዱርዬ ይሆናል ። ይህ ዱርዬ ወታደር ከሆነ ደሞ ፣ የጠመንጃው አፈሙዝ እና ብልግናው ጥጋብ ይደርብለት'ና የወጣለት አምባገነን ይሆናል ። የኢትዮጵያ ችግር ይሄ ነው ። አመጸኛ ባለጌ ጀግና ሆኖ ፣ የሚፈራው አጣ ፣ የሚያከብረው አጣ ፣ የሚሰማው አጣ ።
ዛሬ ሀገራችን የገባችበት መከራ ምንጩ ፣ የስድ ጓዶች ፣ የመሃይም ጀነራሎች ፣ የባለጌ ሚንስትሮች ፣ የዱርዬ ጳጳሶች እና የወሮበላ ዳኞች ሀገር ስለሆነች ነው ። ባለጌ ብልግናው እሱ ጋ አይቆምም ፣ የ ባለጌ ትውልድ አባወራ ፣ የባለጌ ልጆች አባት ፣ የባለጌ ስርዓት ባለቤት ይሆናል ። ለዚህም ነው ባለጎችን የሚያግባባቸው እና የሚያመሳስላቸው ነገር ሁሉም አለመግባባታቸው ነው የሚባለው ። በባለጌ ስርዓት ውስጥ ይሉኝታ የለም ፣ ሰው ምን ይለኛል የለም ፣ ሀፍረት የለም ፣ ክብር የለም ፣ ታሪክ የለም ፣ ሕዝብ የለም ፣ እምነት የለም ፣ ነገ የለም !
ሕፍረቱን ያጣ ስርዓት ፣ ስርዓቱን የተነጠቀ ሕዝብ ፣ ጨዋነት የራቀው መንግስት ፣ የመዋረድ እና የማጎብደድ ርካሽነት የሚያይበት አእምሮም ነብስም የለውም ። ስለዚህ በሊቢያ መታረድም ሆነ በሱማሊያ ጦር መማገድ ሃገራዊ ውድቀት ሳይሆን እንደ አንድ የማህበረሰብ የለት ተለት ተራ ክንውን ተደርጎ የሚወሰደው ።