Translate

Wednesday, August 12, 2015

ታሪክ የማይረሳው የኮሚቴዎቹ ስቅየት

ከማዕከላዊ እስከ ቂሊንጦ

muslim leaders
የኢትዮጵያን ቀጣይ እጣ ፈንታ አጨልመን እንድናይ ከሚያስገድዱን ሁነቶች ውስጥ ለእስልምና ሃይማኖት የትኞችም አይነት ጥያቄዎች በአገዛዙ በኩል እየተሰጡ ያሉ አሉታዊ ምላሾች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ላይ ሐምሌ 27/2007 ዓ/ም የተላለፈው “የፍርድ ውሳኔ” ኢሕአዴግ የሚል ገዥ መደብ እስልምናን በምን ያህል መጠን አፍኖ እየገዛ እንዳለ የአደባባይ ማስረጃ ሆኖ ቀርቧል፡፡ በኮሚቴው አባላት ላይ የተላለፈውን “የፍርድ ውሳኔ” ከሃይማኖታዊ መነጸር ባሻገር ጉዳዩን ከፍትህና ከሞራል ልዕልና አኳያ ማየት ተገቢ ነው፡፡ የዚህ አጀንዳ ቀዳሚ ጉዳይ የኮሚቴውን አመሰራረት በማስታወስ የፍርድ ሂደቱን በመጠኑም ቢሆን በመቃኘት የኮሚቴ አባላቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ በተመለከተ ሦስት የሚሆን እድል (Scenarios) በማስቀመጥ ማሳየት ይሆናል፡፡

የንቅናቄው ጅማሮ
አሁን አሁን ከየትኛውም ጫፍ የሚነሳ ማንኛውም አይነት ችግር መፍትሄ ሲሰጠው ከማየት ይለቅ ችግሩ በራሱ ሌላ ችግር ሲወልድ እየታዘብን ነው፡፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ማስፈጸሚያ ከሆኑት ስልቶች አንዱ ለሆነው ሃይማኖታዊ ጣልቃ ገብነት አብይ ማሳያ የሆነው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጉዳይ የበላይ “ተቋም” (መጅሊስ) ውስጥ አንድ ደብዳቤ ታህሳስ 21 ቀን 2004 ዓ/ም በወቅቱ የመጅሊስ አመራር ጀማል መሐመድ ፊርማ ወደ አወሊያ ትምህርት ቤት ተላከ ይሄው ደብዳቤ በሳምንታት ልዩነት ውስብስብ ችግሮችን ፈጠረ፡፡ በወቅቱ የተላከው ደብዳቤ ይዘት በርካታ የመስጂድ ኢማሞች፣ የትምህርት ቤቱ መምህራን እና የአረበኛ ተማሪዎች መባረራቸውን የሚያረዳ ነበር፡፡ ለንቅናቄው መነሻ እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ደብዳቤ መጅሊሱ የአገዛዙ የፖለቲካ ክንፍ መሆኑን ያስረገጠበት እንደሆነ ሦስተኛ ወገን የሆኑ የንቅናቄው ፅሐፈት ይስማማሉ፡፡
ይህ መዘዘ ብዙ የሆነ ደብዳቤ ኢትዮያዊን ሙስሊሞች ለአመታት አፍነው ያቆዩዋቸውን ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄዎች ወደ አደባባይ እንዲያወጡ በር ከፈተ፡፡ የመብት ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዲያገኙ ኮሚቴ ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በጥር/2004 ዓ.ም በመጀመሪያ ሃያ አባላት ያሉት ኮሚቴ በመምረጥ እንቅስቃሴው ቢጀምረም ‹በኮሚቴው ውስጥ ወጣቶች በዝተዋል› በሚል የእምነቱ ተከታይ የሆኑ ሽማግሌዎችም እንዲገቡ በቀረበው ምክረ ሃሳብ መሰረት አስራ ሁለት ጎልማሳና ሽማግሌዎች እንዲሁም አምስት ወጣቶች በድምሩ አስራ ሰባት ሰዎች ሰባት መቶ ሺህ በሚደርሱ የእስልምና እምነት ተከታዮች የድጋፍ ፊርማ “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” በሚል ሕዝበ ሙስሊሙን እንዲወክሉ ተደረገ፡፡ የኮሚቴው አባላት እንዲያስፈጽሙ የተሰጣቸው ተልዕኮዎች “የመጅሊስ አመራሮች በህዝበ ሙስሊሙ በተመረጡ ሰዎች ይተኩ”፣ “ አወሊያ ከመጅሊስ ወጥቶ በቦርድ ይተዳደር” እና “የአህባሽ የግዴታ ጠመቃ ይቁም” የሚሉ ነበር፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች/ችግሮች መፍትሔ ፍለጋ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የደረሱ ደብዳቤዎችን አስከመፃፍ ደርሰዋል፡፡ ለአብነት በመጋቢት ወር 2004 ዓ.ም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፉት ደብዳቤ ላይ “…እንደሚታወቀው የሃገሪቱን ሰላሳ ሦስት በመቶ የሚሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክለው የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ተገቢው ሕጋዊ ሰውነት የለውም…” በማለት መጅሊሱ ህጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ለመንግስት አቤቱታቸውን አሰምተዋል፡፡
በወቅቱ የኮሚቴው አባላት ከመጅሊሱ ደካማነት አኳያ ጥያቄዎቻቸውን ይዘው ለመንግስት ‹አቤት› የማለታቸው ተገቢነት ለክርክር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄዎች በመጅሊሱ በኩል ምላሽ እንዲያገኙ በተለይም መጅሊሱ የሃይማኖቱ አስተምህሮት በሚፈቅደው መልኩ በአዲስ መዋቅር ማደራጀት በሚቻልበት ሁኔታ የወቅቱን የመጅሊስ አመራሮችና ኮሚቴዎችን አቀራርቦ ማወያየት “መንግስት” ነኝ ለሚል አካል ከቀላል በታች ነበር፡፡
ቀላሉ ነገር ሰለምን ከበደ?
አቤቱታ ተቀባይ የነበረው “መንግስት” ቀላሉን ነገር ከፖለቲካ ፍላጎትና የድንገቴ ክስተት ጋር በተያያዘ የተወሳሰበ አድርጎታል፡፡ ይህን ጉዳይ ካወሳሰቡትና ካከበዱት ጉዳዮች አንዱ የገዥውን ግንባር ርዕዩተ አለም የሚንተራሰው ምክንያት ቀዳሚ ሲሆን፣ ፓርቲው በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መመሪያው መሠረት የየትኞቹንም የሃይማኖት ተቋማት ነፃነት የማይፈቅድ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በጊዜው ከተከሰተው ወቅታዊ ጉዳይ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ የኮሚቴ አባላቱ የታሰሩበት ጊዜ ከቀድሞው ጠቅላላ ሚኒስትር ያልታሰበ የህልፈት ዜና ብዙም ያልተራራቀ መሆኑ ቀላሉን ነገር እንዳከበደው ይታመናል፡፡ በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ኮሚቴዎቹ ያቀረቡትን ጥያቄ በመግፋት አባላቱን የፖለቲካ ስልጣን በሻተ ቡድን በመፈረጅ፣ ጸቡ በመጅሊስ እና በኮሚቴው መሀከል መሆኑ ቀርቶ መጅሊሱ ራሱን አግልሎ የመንግስትና ኮሚቴው ጸብ ሊካረር በቃ፡፡ በኋላም ሰባት ወራትን ያልተሻገረው የኮሚቴ አባላቱ የስራ ጊዜ ሐምሌ 10/2007 ዓ/ም ረፋዱ ላይ በእስር ተደመደመ፡፡ ቀላሉን ነገር እንዲከብድ ካደረጉት ሁለት ምክንያቶች ውስጥ ሁለተኛውን ጉዳይ አፍታቶ ማየቱ በነገሩ ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ የሚፈጥር ይሆናል፡፡ የኮሚቴው አባላቱ ከመታሰራቸው በፊት በደህንነት ሠራተኞች ከፍተኛ የሆነ ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር በወቅቱ ይወጡ የነበሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የኮሚቴው አባላት ሰላማዊ በሆነ መንገድ አወሊያ ትምህርት ቤት ውስጥ ካደረጓቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎችና በተደጋጋሚ ጊዜያት በኮሚቴ አባላቱ መኖሪያ ቤት ውስጥ ለጥያቄዎቹ ምላሽ ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ውይይት ከማድረግ የዘለለ የተለየ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳልገቡ የተረዳው “መንግስት” አባላቱን ለማሰር አልደፈረም ነበር፡፡ ምንግዜም ቢሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካ በነባራዊ ሁነቶች ሳይሆን በድንገቴ ክስተቶች መልኩን የሚቀያይር ነውና የኮሚቴ አባላቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ለእስር የተዳረጉበት ጉዳይ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያልታሰበ ህልፈት ጋር የተያያዘ እንደነበረ የብዙዎች ጥርጣሬ ነው፡፡
በወቅቱ አቶ መለስ በህመም ምክንያት ረዘም ላሉ ቀናት ከመንበረ ስልጣናቸው ገለል ያሉበትና ‹ሙተዋል የለም ጣር ላይ ናቸው› የሚሉ ክርክሮች በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባሉ ኢትዮጵያዊያን በኩል ይነሳ የነበረበት ጊዜ ከመሆኑ አኳያ፣ የአረብ አገራት ‹የፀደይ አብዮት› ንቅናቄ ግለቱ ያልበረደበት ጊዜ ከመሆኑ አኳያ፣ በአገር ቤት የሕዝብ ብሶትና የፖለቲካ ነፃነት እጦት…. ወ.ዘ.ተ. የሚሉ ታሳቢ ስጋቶችን ከገዢው ግንባር ድንጉጥ የአፈና ተሞክሮ ጋር አስተሳሰረን ስናጤነው ‹ናዳውን ለመግታት ሁሉንም የስጋት ምንጮች ማድረቅ› በሚል የኮሚቴው አባላት ለእስር ሊዳረጉ ችለዋል የሚለውን ጥርጣሬ፣ የጊዜው ሁነት አጉልቶ ያሳየናል፡፡ በአናቱም በፍርድ ሂደቱ ላይ የታዩ ተለዋዋጭ ክስተቶች ለአብነት፡- የኮሚቴ አባላቱ መጀመሪያ የተከሰሱበት የ”ሽብር ተግባርን ሙሉ በሙሉ መፈጸም”ን የሚመለከተው የጸረ ሽብር አዋጅ 652/2001 አንቀጽ 3 ቀርቶ፣ “የሽብርን ተግባር ማቀድና ማሴር”ን ወደሚመለከተው አንቀጽ 4 መቀየሩን (የተወሰኑ ተከሳሾች አንቀጽ 7 ተጠቅሶ እንደተከሰሱ ሳንዘነጋ) እንዲሁም የአቃቤ ህግ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ከክሱ ጭብጥ ጋር የማይገጥሙ መሆናቸውን ተከትሎ ሲደመጡ ከቆዩ ትችቶች አኳያ የኮሚቴዎቹ እስር የድንገቴ ውሳኔ እንደነበር ለማመን እንገደዳለን፡፡ በወቅቱ እንኳንስ በሃገሪቱ ካሉት ሁለት ግዙፍ ሃይማኖቶች ውስጥ አንዱን የሚወክሉትን የኮሚቴ አባላት ቀርቶ በሦስት ዘመነኛ ወጣቶች እየተዘጋጀች ለንባብ የምትበቃውን “ፍትሕ” ጋዜጣን በመዝጋትና የጋዜጣውን ባለቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን ለእስር እንዳደረጉት በማስታወስ የድንገቴውን እስር ጥርጣሬ ወደ እምነትነት ይበልጥ መግፋት ይቻላል፡፡
የማዕከላዊ ቆይታና የምርመራ ጊዜ
ድንጉጡ ኢሕአዴግ ናዳውን ለመግታት ያደረቃቸውን “የስጋት ምንጮች” ህግን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ የአገር ውስጡንም ሆነ አለማቀፉን ማህበረሰብ ለማሳመን፣ አለቅጥ የሚለጠጠውን የፀረ-ሽብር ህግ (ቀዩ ካርድ) በመምዘዝ በኮሚቴዎቹ ላይ ስቅየት ማዝነቡን ጀመረ፡፡ በየትም አገር ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የኮሚቴው አባላት በፍርድ ቤት ጥፋተኝነታቸው ብይን ባልተሰጠበት ሁኔታ፣ በያኔው የኢትዮጵያ ቴሌቨዥን ባሁኑ ኢቢሲ “ጀሐዳዊ ሐረካት” በሚል ባስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም በአባላቱ ላይ የወንጀለኝነት ብያኔ የሰጠው “መንግስት” የተከሳሾችን ስም በማጠልሸት ለአቃቤ ሕግ ጉልበት፣ ለዳኞች ተፅዕኖ መፍጠሪያ በመሆን እንደገለገለ እሙን ነው፡፡ የዚህ ዘጋቢ ፊልም ውጤትም የሐምሌ ሃያ ሰባቱን “የፍርድ ውሳኔ” ወልዷል፡፡
የኮሚቴው አባላት ወደ እስር ከተጋዙበት ጊዜ (ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ/ም) ጀምሮ ለአራት ተከታታይ ወራት የፍርድ ቤት በር ሳይረግጡ፣ የሃገሪቱ ዜጎች ‹የስቃይ ማማ› በሆነው ማዕከላዊ እስር ቤት በስቀየት የታጀበ ጊዜ አሳልፈዋል፡፡ በእነዚህ የእስር ቆይታ ጊዜቸው በወንጀል መርማሪዎች ይደርስባቸው የነበረውን በደል በተመለከተ ከኮሚቴው አባላት እስር በኋላ የንቅናቄው መሪ የሆነው “ድምጻችን ይስማ” በአንድ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያ በለቀቀው መረጃ “… ማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስነ – ልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ ይደርስብናል፡፡ ከአስራ አራት ሰዓታት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን እስኪላጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና አይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና በድብደባ ብዛት እንቅልፍ በመንሳት፣ ፂማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ ፣‹ልጅህን እንገድለዋለን ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ የውሃ ሃይላንድ በማንጠልጠል መሀን እናደርግሀለን!› እያሉ በማስፈራራት ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ አድርሰውብናል፡፡… በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳ ቅዝቃዜው በማይቻለው ‹ሳይቤሪያ› ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል አጉረውናል፡፡ መቋቋም የሚያዳግተውን የማሰቃያ ስልታቸውን በመጠቀም ያላሰብነውንና ያልሰራነውን ‹እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ!› ብለው አስገድደውናል” በማለት ተከሳሽ የኮሚቴው አባላት ለፖሊስ ቃላቸውን የሰጡበትን ሁኔታ ልብ በሚሰብር የስቅየት ትርክት አስነብቦናል፡፡ ከንባብ በላይ፣ ውሉ ባልታወቀ ምክንያት አንደኛ ተከሳሽ የሆነው አቡበከር አህመድ እጆቹ በካቴና እንደታሰሩ በምርመራ ላይ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተለቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ከላይ የተመለከተውን የስቅየት ትርክት ከተከሳሾች አንደበት የሰማው ፍርድ ቤት ጉዳዩን በዝምታ እንዳለፈው የሚታወስ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ “ፍርድ ቤት” የሚባለው ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት አይመስላችሁም? እውነተኛ ፍርድ ቤት ካለ ማለቴ ነው፡፡
ተከሳሾች ከአንድ መቶ በላይ የሰው ምስክሮችን፣ በብዙ ሺህ ገፆች የሚቆጠሩ የሰነድ ማስረጃዎችን፣ የድምጽና ምስል የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርበው “ፍርድ ቤት” ለተባለው ቢያሰሙም ፍርድ ከዳኞች ሳይሆን ከቤተ – መንግስት በሚተላለፍባት ኢትዮጵያ ነውና ጉዳዩ እየታየ ያለው፣ ተከሳሾቹ ጥፋተኛ ከመባልና “የፍርድ ውሳኔ” ከመቀበል የተሻለ እድል አላገኙም፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ‹ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት ተንቀሳቅሰዋል› በሚል ለተከሰሱ የኮሚቴው አባላት በአቃቤ ህግ በኩል የቀረበው ማስረጃ የተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ላፕቶፖች፣ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሲዲዎች፣ በራሪ ወረቀቶች …. መሆናቸው ነው፡፡ ኢሕአዴግን የሚያህል ባለ ብረት መዳፍ ገዥ መደብ ያውም “ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት” የሚንቀሳቀስ ቡድን እንደምንስ በበራሪ ወረቀትና በሲዲዎች ጋጋታ ሊወድቅ ይቻለዋል? በሞባይል ቀፎዎችና በላፕቶፖች ምን አይነት የጦርነት ስትራቴጂ በንደፈ ሃሳብ ደረጃ ተገኝቶ ይሆን? አገሪቱ ግን በብዙ መልኩ የቧልት ሁናለች፡፡
የሆነው ሆኖ እጅግ የተራዘመ የፍርድ ሂደት ያሳለፈው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የክስ ጉዳይ በሀገሪቱ ታሪክ በፍርድ ቤት ደረጃ “ውሳኔ” ተሰጠባቸው ከሚባሉ ጉዳዮች ውስጥ በአሉታዊ ጎኑ የሚጠቀስ ነው ማለት ይቻላል፡፡
የኮሚቴ አባላቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ…
መንግስት በከሻሽነት ወደ ፍርድ ቤቶች ይዟቸው በሚቀርቡ ጉዳዮች በተለይም በፖለቲካ ነክ ጉዳይ በታሹ መዝገቦች ላይ አንድም ቀን ሽንፈት ደርሶበት እንደማያውቅ የሩብ ክፍለ ዘመን የአገዛዝ ታሪኩ ጮኾ ይነግረናል፡፡ ከዚህ አኳያ በኮሚቴ አባላቱ ላይ የተላለፈው ውሳኔ የሚጠበቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ይመስላል የኮሚቴው አባላት ለፍርድ ቤቱ “እዚህ የቆምነው ፍትህን እናገኛለን በሚል አይደለም፤ ለታሪክ ምስክር ለመሆን እንጂ” የሚል ኃይለ ቃል በፍርድ ሂደት ላይ ሳሉ የተናገሩት፡፡ “የፍርድ ውሳኔ”ው ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ያለበት ጉዳይ ከመሆኑ አኳያ የሚጠበቅ ቢሆንም ብዙዎቹን የጉዳዩ ተከታታዮች ያስደነገጠው ነገር በኮሚቴ አባላቱ ላይ የተላለፈው የረዥም አመታት “የፍርድ ውሳኔ” የመሰጠቱ ጉዳይ ነው፡፡
ከዚህ ውሳኔ አኳያ የኮሚቴ አባላቱ እጣ ፈንታ በሦስት የቢሆን እድሎች የተንጠለጠለ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው የቢሆን እድል የኮሚቴ አባላቱ ጉዳዩን ወደ ፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ብሎም ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት በመውሰድ እስከ መጨረሻው ድረስ ለውን ይግባኝ የመጠየቅ መብታቸውን አሟጦ በመጠቀም “የፍርድ ውሳኔ”ው እንዲቀንስ በማድረግ ራሳቸውን ከተራዛሚ ዓመታት የእስር ቆይታ የሚያድኑበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችል ይሆናል፡፡ ርግጥ ይህን የቢሆን እድል የሚያከሽፉ ሁለት ተያያዥ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት የኮሚቴ አባላቱ “ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣ ወዴት ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል” የሚለው የአዝማሪ ግጥም በተጨባጭ ያጋጠማቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ የቅጣት ማቅለያ ለፍርድ ቤቱ አላቀረቡም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ ይግባኝ የመጠየቅ ፍላጎት አይኖራቸውም የሚለው ጥርጣሬ ሲሆን፣ ሁለተኛው ተያያዥ ምክንያት ደግሞ የመንግስት ረጅም እጅ በክሱ ሂደት ላይ የታየ በመሆኑ የይግባኝ ጥያቄው ቢቀርብ እንኳ “ጽኑ!” የሚል ውሳኔ ይጠብቀዋል የሚል ነው፡፡
በሁለተኝነት የሚጠቀሰው የቢሆን እድል የፍርደኞቹ ጉዳይ በፖለቲካዊ አግባብ ይታይ ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ከኢሕአዴግ “አሸናፊ ነኝ” ባይ ሥነ-ልቦና አኳያ ይህ ጉዳይ እውን የሚሆንበት እድል ሰፊ ይመስላል፡፡ የኮሚቴ አባላቱ ፍላጎት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡
የቀድሞ የቅንጅት አመራሮች ከእስር የተፈቱበት መንገድ ለሁለተኛው የቢሆን እድል የማጠናከሪያ ሀሳብ ይሆናል፡፡ በወቅቱ የነበሩትን የቅንጅት አመራሮች እጅግ አወዛጋቢ በሆነ የፍርድ ሂደት “ጥፋተኛ” በማለት የተላለፈው “ውሳኔ” ‹እኔ ልክ ነበርኩ› ከሚለው የኢሕአዴግ ድንፋታ በኋላ ጉዳዩ በ”ይቅርታ” አማራጭ መዘጋቱ የሚታወስ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹ከተራዛሚ የእስር ቆይታ ይልቅ የእርቅና የይቅርታ አማራጭን መከተል› የሚለው መንገድ በኮሚቴ አባላቱ ከተመረጠ ጉዳዩ በፖለቲካ አግባብ የሚፈታ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው የቢሆን እድል ለኮሚቴ አባላቱ ተመራጭ ባይሆን እንኳ ከተወሰነ አመታት የእርስ ቆይታ በኋላ ቅጥፈት የማይሰለቸው ኢሕአዴግ ‹ራሳቸውን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት እያሉ የሚጠሩ ግለሰቦች ሃይማኖታዊ መንግስት ለመመስረት የሄዱበት መንገድ ጸጽቷቸው መንግስትን ይቅርታ ጠየቁ፣ መንግስትም ሆደ ሰፊ በመሆኑ ይቅርታቸውን ተቀብሎ ከእስር ፈቷቸዋል› የሚል ነጭ ውሸት በመፈብረክ የኮሚቴ አባላቱ ከእስር ይፈታ ይሆናል የሚለው ቅድመ ግምት በሁለተኛው የቢሆን እድል የሚጠቃለል ይሆናል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የሚጠቀሰው የቢሆን እድል ደግሞ ከሦስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ጋር ተያይዞ የሚቀርብ ጉዳይ ይሆናል፡፡ ብዙዎች የኢትዮጵያ ፖሊቲካ ተከታታዮች እንደሚያምኑት አገዛዙ እያሳየ ባለው አምባገነናዊ ባህሪ የተነሳ አገሪቱን ወደ ሕዝባዊ አብዮት እየገፋት ይገኛል፡፡ ይህን ተከትሎ የየትኛውም ማህበረሰብ የመብት ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው በሦስተኛው የኢትዮጵያ አብዮት ማግስት እንደሆነ የሚሞግቱ ዘመነኞች ተፈጥረዋል፡፡ ሰኞና ማክሰኞ ይመጣል ብለን ቀጠሮ ልንይዝለት የማይቻለን ሕዝባዊ አብዮት መምጣቱ አይቀሬ ነውና በአብዮቱ ማግስት የኮሚቴ አባላቱም ሆነ ሌሎች የህሊናና የፖለቲካ እስረኞች አዲሲቷን ኢትዮጵያ በነፃነት የሚቀላቀሉበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል፡፡ በአንድ ነገር ግን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል! ‹በምን?› ከአገዛዙ መላ ቅጡ የጠፋው ባህሪም ሆነ አገሪቱን ሊወጣት ከቀረበው የህዝቡ የለውጥ ፍላጎት አኳያ ኮሚቴዎቹ የተላለፈባቸውን ተራዛሚ የእስር ውሳኔ በእስር ቤት ውስጥ አያሳልፉም፡፡ ተወደደም ተጠላም ተውጡ አይቀሬ ክስተት ነው፡፡
እንደ መውጫ
እስልምና አሁን ባለው ተጨባጭ ዓለም ለአሻሚ ትርጉም የተጋለጠ ሃይማኖት ነውና ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ በጎረቤት ሀገር ሱማሌ፣ በናይጄሪያ፣ በማሊ እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ላይ ሃይማኖትን መሰረት ያደረጉ ትርምሶች መፈጠራቸው እና በአንዳንድ አካባቢዎች ችግሩ ዛሬም ድረስ ባለማባራቱ፣ ሀገራቱ ካሉበት ቀጠና አልፎ የአለም አጀንዳ እስከመሆን ደርሷል፡፡ እስልምና ሃይማኖት የሙስሊሞች ነው፡፡ እስልምናን ተከትሎ የሚፈጠረው ጣጣ ግን ሁሉን የሚጎዳ ጉዳይ ነው፡፡ እናም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እየጠየቁት ያለው የእምነት ነፃነት ጥያቄ በማያዳግም መልኩ መመለስና ሕገ-መንግስቱ ላይ በነቢብ የሰፈሩ መብቶችን በተግባር ማዋል የአለም አጀንዳ የሆነውን አክራሪነት ለመከላከል ብቸኛ መንገድ ነው፡፡ ከመስከረም አስራ አንዱ የአሜሪካ ጥቃት በኋላ የምዕራቡ አለም ተፅዕኖ ታክሎበት “የአክራሪነት ምንጭ እስልምና ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ መደረሱ አሳዛኝ አረዳድ መሆኑን ሳንዘነጋ እንደሆነ ልብ ይባል፡፡
ብዙዎቹ ተራማጅ የእምነቱ መምህራን እንደሚሉት እስልምና አለም አቀፍ ነው፡፡ በሁሉም ሀገራት ተመሳሳይ ነው፡፡ እስላማዊ እንቅስቃሴዎች ግን ከሀገር ሀገር ይለያያሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች በነቢብ ደረጃ በህገ-መንግስቱ ላይ የሰፈረው የሃይማኖት ነፃነት በትክክል ቢተገበር እንዲሁም እንደ አቻው ኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት እምነቱን የሚያሳድጉና የሚያበለጽጉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቢኖሩት ለባእዳን ትምህርት ክፍተት የማይሰጥ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ማነፅ ይችላል፡፡ ችግሩ የሰፈር ጎረምሳ ፀባይ ያለው “መንግስት” ለዚህ መሰል ጉዳይ ምቹ መደላደል ከመፍጠር ይልቅ እንቅፋት መሆን ይቀለዋል፡፡ ግድ የለም! ዘመን ሲፈቅድ እንቅፋቱ መነቀሉ አይቀሬ ነው፡፡ ያኔ ታሪክ የማይረሳው የኮሚቴዎቹ ስቅየት ቁስሉ ይጠግጋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
(የዚህ ጽሁፍ ባለቤት ጋዜጠኛ ሙሉዓለም ገ/መድህን ይባላል፡፡ ጋዜጠኛው በቅርቡ “የኢሕአዴግ ቁልቁለት” የሚል መጽሀፍ እንዳሳተመ የሚታወስ ሲሆን፤ በዚሁ መጽሐፉ ላይ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ጉዳይ በስፋት ዳስሶታል፡፡ ለበለጠ ግንዛቤ መጽሀፉን ማንበብ ይቻላል)

No comments:

Post a Comment