መልካም ዜጋ ማለት ምን ማለት ነው?
መልካም ዜጋ ኢፍትሃዊ ተግባር ሲፈፀም “እኔ ምናገባኝ?” አይልም። መልካም ዜጋ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ”፤ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶም አይብቀል”፤ “እያለህ ካልሆነ ከሌለህ የለህም” እና በርካታ መሰል ምሳሌዎችን አይሰማም። መልካም ዜጋ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከነፃና ቅን ህሊናው ጋር ታርቆ ይኖራል።
የህወሓት አገዛዝ፣ መልካም ዜጋ ማለት የመንግሥት ሥልጣን የያዘን ማንኛውም አካል ማክበርና በታማኝነት ማገልገል ተደርጎ እንዲተረጎምለት ይሻል። ፍትህ የሚያዛባ መንግሥትን መቃወም የመልካም ዜጋ አቢይ ተግባር መሆኑ የዘመናችን ወጣት እንዳይገነዘብ ያደርጋል። በተለይ ባለሙያዎች የሚያገለግሉትን አገዛዝ ባህርይ እግምት ውስጥ ሳያስገቡ የተቀጠሩበትን ሥርዓት በታማኝነት ማገልገል የዜግነት ግዴታቸው አድርገው እንዲወስዱት ይወተውታል።
ኦስካር ግሮኒንግ ( Oskar Groening)የዘጠና አራት ዓመት ሽማግሌ ጀርመናዊ ነው። በጀርመን የሂትለር አገዛዝ ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ንፁሃን የተፈጁበት አሽዊትስ ካምፕ ውስጥ የሂሳብና ጽህፈት ሠራተኛ ነበር። ኦስካር ግሮኒንግ አንድም ሰው አልገደለም፤ አንድም ሰው አልገረፈም። እሱ ሂሳብ ነው የሠራው። ሆኖም በደል ሲፈፀም አይቶ “ምናገባኝ” ብሎ አልፏልና ከብዙ ዓመታት በኋላ ተከሶ በቅርቡ የ4 ዓመታት እስር ተፈርዶበት በሁለት እግሮቹ መቆም በማይችልበት በ 94 ዓመቱ በእርጅናውና በመጦሪያው ዘመን ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ፊት ተዋርዶ እስር ቤት ወርዷል።
በአንፃሩ ኦስካር ሽንድለር (Oskar Schindler) በጀርመን ናዚ ወቅት ሂትለር ይመራው የነበረው የናዚ ፓርቲ አባልና ሰላይ ነበር። ሆኖም ግን የሥርዓቱን ኢሰብዓዊነት ሲረዳ እዚያው የናዚ ፓርቲ ውስጥ ሆኖ አለቆቹ ያዘዙትን ሳይሆን ቅን ህሊናው ያዘዘውን በምስጢር መሥራት ጀመረ፤ በዚህም የ 1200 ሰዎችን ሕይወት ታደገ። ከጦርነቱ በኋላ ኦስካር ተከብሮ የኖረ በርካታ የክብር ስሞችና ሽልማቶች የተሰጠው በመልካም አርዓያነቱ የሚጠቀስ ሰው ሆነ።
በአገራችንም በአምስት ዓመታቱ የፋሽስት ወረራ ወቅት ስመ ጥር የውስጥ አርበኞች ነበሩ። ከነፃነት በኋላ ባንዶች እንኳን በውስጥ አርበኝነት ለመጠራት ያደርጉት የነበረውን እሽቅድድም ልብ በሉ።
በህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴግ፣ ደህዴግ እንዲሁም አብዴፓ፣ ቤጉህዴፓ፣ ጋህአዴን፣ ሀብሊና ኢሶዴፓ ያላችሁ ወገኞች ኦስካር ግሮኒንግን ወይንስ ኦስካር ሽንድለርን መምሰል ትፈልጋላችሁ? በህወሓት ፋሽስታዊ አገዛዝ የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውስጥ ያላችሁ ወገኖቻችን ነገ የምትዋረዱበትን ሥራ መሥራት ነው የሚበጃችሁ ወይስ ዛሬ ከህሊናችሁ ጋር ታርቃችሁ እየኖራችሁ ነገ ደግሞ ልጆቻችሁና የልጅ ልጆቻችሁ የሚኮሩበትን ተግባር መፈፀም ትፈልጋላችሁ? በአገዛዙ የስለላ ድርጅቶች ውስጥ ያላችሁ ወገኖች ስማችሁን በመልካም ማስጠራት አትሹምን?
ልቦና ያላችሁ ወገኖቻችን ሆይ! መልካም ዜግነት ሎሌነት አይደለም። መልካም ዜግነት ለቅን ህሊና ታማኝ መሆን ነው። መልካም ዜግነት ሲመች በገሀድ፤ ሳይመች በምስጢር ኢፍትሃዊነትን መዋጋት ነው።
አርበኞች ግንቦት 7 የአንድነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ በማናቸውም መንገድ በአገዛዙ የፓለቲካ፣ የጦርና የፓሊስ ተቋማት፤ በስለላም ይሁን በሌላ የሲቪል ሙያ የተሰማራችሁ ወገኖቻችን የታዘዛችሁትን ሳይሆን ቅን ህሊናችሁ የሚጠይቃችሁን በመሥራት ኢፍትሃዊ፣ ፋሽስታዊና ዘረኛ የሆነውን የህወሓት አገዛዝን እንድታዳክሙ ጥሪ ያቀርብላችኋል። በአገዛዙ ውስጥ ሆናችሁ እያለም የምትሠሩት ለሀገርና ለትውልድ የሚጠቅም በርካታ ሥራ አለ። የአገዛዙን ምስጢራዊ ሰነዶች ለአርበኞች ግንቦት 7 እንዲደርስ ማድረግ፤ አሊያም በማኅበራዊ ሚዲያዎች (ለምሳሌ ፌስ ቡክና ቱተር) ማሰራጨት ትልቅ ዋጋ ያለ ሥራ ነው። የህወሓት ፀረ-አገር እና ፀረ-ሕዝብ ፕሮጀክቶችን ማሰናከል ሌላ ትልቅ ሥራ ነው። በነፃነት ታጋዮች ላይ የሚደረጉ ዱለታዎችን ማክሸፍ ሕይወት አድን ሥራ ነው። ድርጅቶቹ ውስጥ ሆኖ ድርጅቶቹን ማዳከም የመልካም ዜግነት ግዴታ መወጣት ነው።
በሥርዓቱ ውስጥ ሆነው ኢፍትሃዊነትን ለማጋለጥ እና ሥርዓቱን ለማዳከም ለሚጥሩ ወገኞች አርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ ክብር አለው፤ ደህንነታቸው እንዲጠበቅም የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ፀረ ኢትዮጵያ እና ፀረ ሰው የሆነውን የህወሓትን ሥርዓት ለመጣል እና በምትኩ ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነትና የሀገር አንድነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን ለማጽናት ከሥርዓቱ ውስጥም ውጭም የሚደረገውን ትግል እናፋፍም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment