ናትናኤል ፈለቀ (ከቂሊንጦ እስር ቤት) – ምንጭ ዞን9 ፌስቡክ ገጽ
ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ ዓላማዬ ማዕከላዊ ያሉ ሥራቸውን አክብረው የኢትዮጵያውያንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የሚሰሩ ጥቂት ፖሊሶችን (ምናልባትም በአንድ እጅ ጣቶች ተቆጥረው የሚያልቁ መርማሪዎችን) ለማበረታታት አይደለም፡፡ ይህን ዓላማ በሌላ ጽሁፍ እመለስበት ይሆናል፡፡ ለነገሩ ሥራቸውን አክብረው የሚሰሩ ባለሙያ ፖሊሶች የኔ ማበረታታትን የሚፈልጉ አይደሉም፡፡ ያሉበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በኃላፊነት ማሰብ የቻሉ ስለሆኑ፡፡
ስለዚህ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ በተቋሙ ውስጥ ኢትዮጵያ የምትተዳደርባቸውን ሕጎች ለማክበር (የተላለፉትን ለይቶ ለማስቀመጥና በስህተት የተጠረጠሩትን ነጻ ለማውጣት) ሳይሆን የአገዛዙን ዕድሜ ለማርዘም የሚሰሩትን አብዛኞቹን ሙያቸውን የማያከብሩ ፖሊሶች ‹‹ምርመራ›› ሴራቸውን እንዴት እንደሚፈትሉ ለማሳየት፣ ቢያንስ ሌላ ስልት እስኪፈጥሩ ድረስ በሀገሪቷ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ኢትዮጵያውያን አንዴ በተቋሙ ውስጥ ከገቡ በኋላ ሊገጥማቸው የሚችለውን የተንኮል መረብ ለማስረዳት እና ቀድሞ ለማዘጋጀት ያሰበ ነው፡፡
እውነት ለመናገር እነዚህ የስርዓቱ ጠባቂ ሎሌዎች የህዝብን ደህንነት ለአደጋ የሚያጋልጥ ወንጀልን እና ወንጀለኞችን ለይተው አውቀው ፍትህ እንዲያገኙ አድርገው ጭራሹንም አያውቁም ማለት አልችልም፡፡ ስለዚህ አሁን የማብራራው ጉዳይ ለወንጀለኞችም መዘጋጃ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ፡፡ ነገር ግን ወንጀለኞች ከፍትህ እንዲያመልጡ ጠብታ ውሃ ማቀበል አልፈልግም፡፡ አንድ ነጻ ሰው ባልሰራው ወንጀል ከሚቀጣ መቶ ወንጀለኞች ቢያመልጡ ይሻላል የሚለው የህግ መርህ የበለጠ አቋሜን ያስረዳል፡፡
ሁለት ማሳሰቢያዎች አሉኝ፤ አንደኛ፡-እኔ ተይዤ ማዕከላዊ እስክገባ ድረስ ልታሰር እንደምችል አስቀድሜ ባውቅም ሊጠብቀኝ የሚችለውን የ‹‹ምርመራ›› ሂደት (የሴራ መረብ የበለጠ ይገልጸዋል) አጽንዖት ሰጥቼ አላሰብኩበትም፡፡ የምርመራው ሂደትን ተንተርሼ የማነሳቸውን ሀሳቦች የተረዳሁት በምርመራ ውስጥ ካለፍኩ በኋላ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን ጽሁፍ የሚያነቡ ሰዎች እኔ በፍርሃት ያላደረኳቸውን ነገሮች እንዲያደርጉ (በምርመራ ሂደት) የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ይህንን ጽሁፍ በሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል የሚል እና ሀሳቡን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች በሚፈቅዱት መሰረት በነጻነት የሚገልጽ ሁሉ ጊዜ ሳይሰጥ ቢያነበው እመክራለሁ፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ሀሳብ የአቃቤ ህግ ምስክር ከተሰማ በኋላ በብይን የተለቀቁ ሙስሊም ወንድሞች መጻፋቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ያ ጽሁፍ የተሻለ የተደራጀ ነው ብየ ስለማስብ እንዲነበብ እጋብዛለሁ፡፡ በተጨማሪም ስርዓቱን የሚደግፉ ሰዎች ይህንን ጽሁፍ በማንበብ ወንጀለኞች ከሚጠቀሙበት ለተሻለ አላማ ያውሉታል ብዬ ስለማስብ ሁለቱም ባያነቡት ይሻላቸዋል፡፡
ወደ ዋናው ሀሳብ ልግባ፤ ከተያዝኩ በኋላ በነበሩ የመጀመሪዎቹ ቀናት ውስጥ የነበሩት‹‹ምርመራዎች›› እውነቱን እና የማውቀውን ብቻ በመናገር እራሴን ነጻ ማውጣት እንደምችል መተማመኛ መስጠትን ያለሙ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ሚያዝያ 18/2006 (በተያዝኩኝ በማግስቱ ቅዳሜ) የነበረውን ምርመራ ም/ሳጅን መኮንን በተረጋጋ ሁኔታ የምርመራው ሂደት በመከባበር እንደሚቀጥል፣ ልክ እኔ የዕለት ስራየን ለማከናወን ሙያ እንደሚጠይቀው ያክል የፖሊስ ምርመራም ተመሳሳይ እንደሆነ፣ በቁጥጥር ስር የዋልኩት ተጠርጥሬ ብቻ እንደሆነ እና በምርመራው ሂደት ወንጀል አለመፈጸሜ ከተረጋገጠ በነጻ ወደቤቴ እንደምሄድ ነበር ያስረዳኝ፡፡ ይንቁናል የሚል ስሜት አስቀድሞ ስለሚያድርባቸው ተቋሙን እና እራሳቸውንም ከፍ የሚያደርግ ነገር በነዚህ የመጀመሪያ ‹‹የምርመራ››ቀናት ይናገራሉ፡፡
‹‹ይህ የወረዳ ጣቢያ አይደለም፡፡ የክልልም አይደለም፡፡ ይህ የፌደራል ወንጀል ምርመራነው፡፡ ሚኒስትር ደረጃ የደረሱ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀር እዚህ ተመርምረዋል›› ነበር ያለኝ ም/ሳጅን መኮንን በአጽንኦት፡፡ ከዚህ ገለጻ በኋላ ነበር ስለህይወት ታሪኬ በመጠየቅ ቃል የመስጠት ሂደቱን የጀመርኩት፡፡
ማስታወሻ- 1. ቃል ያለመስጠት መብት
ቃሌን ያለመስጠት መብት ስላለኝ ቃሌን አልሰጥም ለማለት መጀመሪያ መብቱ እንዳለ ማወቅ ይጠይቃል፡፡ በወቅቱ ይህ መብት እንዳለኝ ማወቄን እጠራጠራለሁ፡፡ አውቅ ከነበረም ግን በፍጹም ትዝ አላለኝም፡፡ ቃል አለመስጠት አንድ ለምርመራ ሂደቱ ተባባሪ አለመሆንን ማሳያ ነው፡፡ ለተቋሙ የጭቆና መሳሪያ ስለመሆኑ በቂ ማስረጃ እንዳለ አምነን ተጨማሪ ማረጋገጫ ዕድል (benefit of the doubt) መስጠት የማንፈልግ ከሆነ ይህ ትክክለኛው አማራጭ ይመስለኛል፡፡ ከግምት መግባት ያለበት ቃል በመስጠቱ ሂደት ውስጥ ፖሊስ በእርግጠኝነት ስህተት መስራቱ አይቀርም፡፡ ይህም የማይቀረው ክስ ሲመጣ ተቋሙን ማጋለጥ እንደ ስልት የሚወሰድ ከሆነ እንደማስረጃ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በኛ ጉዳይ የቀረበብን ክስ የሽብር ቡድን በኅቡዕ አደራጅተዋል በሚል ሲሆን ሁላችንም ቃል ስንሰጥ የተጠየቅነው እና ስናብራራ የነበረው ግን በይፋ ስንጽፍበት እና ዘመቻዎቻችንን ስናካሂድበት ስለነበረው ዞን 9 ነው፡፡
አቃቤ ህግ በክሱ እያለ ያለው የከሰስኳችሁ በመጻፋችሁ እና መብትን የሚጠይቁ ዘመቻዎችን በማድረጋችሁ (በአጠቃላይ ከዞን-9 ጋር በተያያዘ) ሳይሆን ሌላ የህቡዕ ቡድን መስርታችሁ ለሽብር ዓላማ ስትንቀሳቀሱ ስለነበር ነው፡፡ የሰጠነው ቃል እና ክሱን ለመደገፍ የቀረቡት ማስረጃዎች ግን ስለ ዞን-9 አውርተው አይጠግቡም፡፡ በመጀመሪያዎቹ ቀናት የሚነግረውን ‹‹ተቋሙ ገለልተኛ ነው፣ ሰዎችን ወንጀለኛ ለማድረግ ሳይሆን እውነትን ፈልፍሎ አግኝቶ ነጻ ሰውን ወደቤቱ ይሸኛል›› የሚለውን ዕምነት በቀላሉ ማስረጽ ከቻሉ የሚቀጥሉት ጥርጣሬ ወደመዝራት ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ ያሉትን የማያምኑ ከሆነ ግን የተጠርጣሪውን በራስ መተማመን ለመሸርሸር ህገ-ወጥ ተግባራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
‹‹ምርመራ›› በጀመርኩ በአራተኛው ቀን የተከሰተው ይሄው ነው፡፡ ሚያዝያ 21/2006 ዓ.ም ምሽት ድረስ ‹‹በምርመራው›› ሂደት ውስጥ ስሳተፍ የነበረው በሙሉ የራስ መተማመን ነበር፡፡ ለምሳሌ ም/ሳጅን መኮንን፣ ም/ሳጅን እቴነሽ፣ እና ሳጅን ፈይሳ በነበሩበት ታስሬ ‹‹እየተመረመርኩ›› ያለሁት ሀሳቤን በነጻነት ለመግለጽ ባለመፍራት ነው፡፡ ያኔ ‹‹ፖሊስ ለህዝብ የሚሰራ ተቋም ነው የምትሉትንም አላምንም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ፖሊስ እንደ ተቋም እየሰራ ያለው አገዛዙን ስልጣን ላይ ለማቆየት ነው›› ብያቸዋለሁ፡፡
ከላይ በጠቀስኩት ቀን ማታ ግን ሌላ ሊከሰት እንደሚችል የማውቀው፣ ግን ከምር ያልተዘጋጀሁበት ነገር ተከሰተ፡፡ ምሽት 1፡00 አካባቢ የተጀመረው ‹‹ምርመራ›› ቶሎ ኃይለ ቃል ወደመሰንዘር እና ዛቻ ተለወጠ፡፡ በወቅቱ ም/ሳጅን መኮንን፣ የመጀመሪያ ቀን ፍርድ ቤት የወሰደን እና በየመተላለፊያው ሳገኘው ጭምር ቤተሰብ እንዲያገኘን መብት አለን፣ ፍርድ ቤት አዝዞልን ሳለ ለምንድነው የማታገናኙን እያልኩ ስጠይቀው የቆየሁት ሳጅን ምንላርግልህ እና ማዕረጉን የማላስታውሰው ፀጋየ (በቅጽል ስሙ ጥጋቡ) የሚባል መርማሪ ነበሩ፡፡ የ‹‹ምርመራ››ውም ዋነኛ አጀንዳ የዞን 9 ድብቅ ግብ እና የውስጥ የስራ ክፍፍል (መዋቅር)በተመለከተ ነበር፡፡ በሁለቱ ጉዳይ ላይ እውነተኛው የማውቀው መልስ ‹‹መዋቅር የለውም›› የሚለው ነበር፡፡ ዞን 9 ድብቅ ግብም መዋቅርም ኖሮት አያውቅም፡፡ ሳጅን ምንላርግልህ መልሴ አላጠገበውም፡፡ ‹‹እኔ እንደሱ እንዳልመስልህ (የእኔን ጉዳይ በዋነኛነት ወደያዘው ም/ሳጅን መኮንን እየጠቆመ) አለቅህም! ሽባ ነው ማደርግህ! ልብስህን አስወልቄ ሳልለጠልጥህ እውነቱን ብትነግረኝ ይሻልሃል!›› የሚሉ ዛቻዎች ደረደረ፡፡ እኔ ግን መዋቅሩን በተመለከተ ስራ ለማቅናት ሲባል ምክረ ሀሳብ ቀርቦ እንደተወያየንበት፣ ነገር ግን ሀሳቡ ውድቅ እንደተደረገ ከማስረዳት በቀር የምጨምረው የማውቀው እውነት አልነበረም፡፡ ም/ሳጅን መኮንን እና ፀጋየ (ጥጋቡ) በየተራ ክፍሉን ለቀው ከወጡ በኋላ ሳጅን ምንላርግልህ ከወንበሩ በመነሳት ምቾት በሚነሳ ሁኔታ ከተቀመጥኩበት ፊት ተጠግቶኝ ቆሞ ጥያቄዎችን ይደረድር ጀመር፡፡
ጥያቄ፡- ‹‹ለምንድነው እነ ርዕዮትን ብቻ የምትጠይቁት?››
መልስ፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ስለሆኑ እና የታሰሩት በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ነው ብለን ስለምናምን፡፡››
ጥያቄ፡- ‹‹(በቁጣ) ባንክ የዘረፈውስ ኢትዮጵያዊ አይደለም? ለምንድነው ሌላውን ወንጀለኛ የማትጠይቁት?››
በእውነት እዚህ ጋ ሳቄ መጥቶ ነበር፡፡ በርግጥ የታሰረን ሁሉ ከተቻለ መጠየቅ ለህሊና የሚያስደስት ስራ ነው፡፡ እግዜርም ይወደዋል፡፡ ግን ርዕዮትን ስጠይቅ እንዲሰማት የምፈልገው፣ ትግሏ ዋጋ እንዳላጣ እና እንዳልተረሳች ነው፡፡ ይህም ትንሽም ቢሆን ብርታት ይጨምርላታል ከሚል ተስፋም ጭምር ነው፡፡ ተመሳሳይ ነገር የባንክ ዘራፊ እንዲሰማው በፍጹም አልፈልግም፡፡ ጥያቄው ቀጠለ፣
‹‹ዝዋይ ለምን ሄዳችሁ?››
‹‹እነ ውብሸትን ለመጠየቅ››
‹‹አትዋሽ! በቀለ ገርባን ለመጠየቅ ነበር?››
‹‹አዎ በቀለንም ለመጠየቅ ነበር፡፡››
‹‹በቀለ ምን እንደሚል ታውቃለህ? ለምን እንደታሰረ ታውቃለህ? ኦሮምኛ ትችላለህ?››
‹‹አልችልም››
‹‹በቀለ እኮ የሚለው ኦሮምኛ የማይችሉ ሰዎች በሙሉ ይታረዱ ነው፡፡››
ስለ በቀለ ገርባ የማውቀው ጥቂት ነገር ከሚለኝ ጋር ፍጹም የሚጣጣም ስላልነበር የፊቴን መለዋወጥ መቆጣጠር አልቻልኩም፡፡ ፊት ለፊቴ ተደንቅሮ የጥያቄ ዝናብ ሲያወርድ የነበረው ሳጅን ምንላርግልህ አሁን ማድረግ የሚፈልገውን ለማድረግ በቂ ምክንያት አገኘ፡፡ የመጀመሪያዋን ጥፊ ሰነዘራት፡፡ መብቴን እየነካ እንደሆነ ስነግረው ‹‹ይህንን ነው አይደል ፈረንጆቹ ወስደው የሚያሰለጥኗችሁ?›› በማለት ስራውን ቀጠለ፡፡ ድብደባው እዚያ ቤት ከሚፈጽሙት ሰቆቃዎች (torture) አንጻር ትንሽ ቢሆንም አሸነፈኝ፡፡ አሁን የሚጸጽቱኝንም ቃላት ተናገረኝ፡፡ ከውጭ የነበሩት ሁለቱ መርማሪዎች ድብደባ ሲፈጸምብኝ በነበረበት ወቅት በመሐል መጥተው ገላጋይ ሆነው ነበር፡፡ ምንላርግልህ ግን ለያዥ ለገናዥ አስቸገረ፡፡
ማስታወሻ፡-2. መርማሪዎች አንድ አላማ ነው ያላቸው
ሁለትና ከዚያ በላይ ሆነው ሲመረምሩ የትኛውንም ማመን አያስፈልግም፡፡ በኋላ ላይ ከሌሎች ተጠርጣሪዎች ጋር ሳወራ የተረዳሁት ይህ የተለመደ አሰራር መሆኑን ነው፡፡
ሌላ ተጠርጣሪ ሲመረመር ሳጅን ምንላርግልህ ገላጋይ ሌላኛው ደግሞ እምቡር እምቡር ይላል፡፡ ከዚያም ፀጋየ (ጥጋቡ) እኔ ላይ ሲያደርግ እንደነበረው ገላጋይ የሚሆነው መርማሪ ‹‹እኔ ችግር ውስጥ እንድትገባ አልፈልግም፤ ለምን እውነቱን አትነግረንምና ራስህን አትጠብቅም? ደግሞ ዘጠኝ ሆናችሁ ለሰራችሁት ስራ አንተ ብቻህን ለምን ትጎዳለህ? ሌሎቹ እኮ እየተናገሩ ነው፤ አይደለም ዘጠኝ ሰው የሚያውቀው ነገር ይቅርና ለሌላ አንድ ሰው የነገርከው ነገር እኮ ሚስጥር መሆኑ ያበቃል›› የሚሉ ማግባቢያዎች በመደርደር ምስኪን ምስኪን ሊጫወት ይሞክራል፡፡
የዛን ምሽት ምርመራ ሲጠናቀቅ የሁለት ሰዓት ማሰቢያ ጊዜ ተሰጥቶኝ የዞን 9 ግብ ምን እንደሆነ እና የመዋቅራችንን እያንዳንዱን የስራ ዘርፍ እንዳስታውስ የቤት ስራ ተሰጥቶኝ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ተመልሼ እንደምጠራ ተነግሮኝ ነበር ወደ ማረፊያ ቤት ውስጥ የተመለስኩት፡፡
በተለምዶ ሳይቤሪያ የሚባለው ማረፊያ ቤት ባለአንድ ፎቅ ህንጻ ሲሆን የታችኛው ወለል በኮሪደር ተከፍሎ በግራና በቀኝ አምስት አምስት ክፍሎች አሉት፡፡ ኮሪደሩ መሀል ላይ አንድ የግድግዳ ሰዓት ተሰቅሏል፡፡ የመጀመሪያ ሰሞን ልብ ስላልኩት ሰዓት የማውቀው ምርመራ ክፍል ካሉት ሰዓቶች በመነሳት በግምት ነበር፡፡ ከሳጅን ምንላርግልህ በተሰጠኝ የቤት ስራ መሰረት ከምሽቱ አምስት ሰዓት ሲል ተመልሼ ወደ ምርመራ እጠራለሁ፡፡ ከምርመራ ከተመለስኩ ጀምሮ በአዕምሮዬ ሲመላለስ የነበረው ነገር ተጨማሪ መልስ ልሰጣቸው እንደማልችል እና በዚህ ምክንያት ተመልሼ ከሄድኩ በኋላ የሚደርስብኝ ሰቆቃ ማብቂያ ምን እንደሚሆን ማሰብ ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ በምርመራ በማሳለፌ ድካም የነበረብኝ ቢሆንም እንቅልፍ ሊወስደኝ ግን አልቻለም፡፡ ራሴን አረጋግቼ በተሰጠኝ ሁለት ሰዓት እረፍት መውሰድ ብፈልግም ምንም ዓይነት ድምጽ በሰማሁ ቁጥር አምስት ሰዓት የሆነ እየመሰለኝ እባንን ነበር፡፡ እነምንላርግልህ ግን አልፈለጉኝም፡፡ አይነጋ የለም ሌሊቱም ነጋ፡፡ ጠርተው ቢደበድቡኝ ይሻል ይሆን እንደነበር እንጃ!
ማስታወሻ፡- 3. እራስን አረጋግቶ በቂ እረፍት መውሰድ
መርማሪዎቹ መቼም ቢሆን ምርመራ ጨርሰናል ደህና እደሩ ብለው አይሸኙም፡፡ ሁል ጊዜ‹‹በኋላ እንገናኛለን፤ አስብበት›› ብለው ነው የሚጨርሱት፡፡ አንዳንድ ጊዜ በቀጠሮ መሰረት ምርመራው ይቀጥላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የውሃ ሽታ ይሆናሉ፡፡ በቀጠሮ መሰረት ብጠራም ባልጠራም ያለችውን ጊዜ በቂ እረፍት ለማድረግ መጠቀሚያ ማድረግ የሚያዋጣው አማራጭ ነው፡፡ ከድብደባው በባሰ የሚጎዳው የማያቋርጥ ጭንቀት እና የእረፍት እጦት ነው፡፡ ከአሁን አሁን ወደምርመራ ተጠራሁ ብሎ መጨነቅ ጥሪውን የማዘግየትም የማስቀረትም አቅም የለውም፡፡ ‹በኋላ እንገናኝ› የምትለዋ ቀጠሮ እረፍት መንሻ ዘዴ ናት፡፡
በመቀጠል የምርመራው ዓላማ የነበረው ከጓደኞቼ ያገኟቸውን መረጃዎች በመጠቀም ብዙ እንደሚያውቁ ጥያቄ የሚጠይቁትም ከኔ ይምጣ ብለው እንጂ ሁሉ ነገር ላይ መረጃ እነዳላቸው ለማሳመን መጣር ነበር፡፡ በወቅቱ የእኔ ምላሽ የነበረው ሁሉንም የሚያውቁ ከሆነ ለኔ ጥሩ እንደሆነ እና ምንም ጥፋት እንደሌለብኝ ከዛ በላይ ማስረጃ እንደሌለ የሚያስረዳ ነበር፡፡
ማስታወሻ፡-4. አብረው የሚሰሩ ጓደኛሞች ወጥ መልስ ለመስጠት አስቀድመው ስምምነት ላይ መድረስ
ስለ አንድ ጉዳይ ሁለት ጓደኛሞች የተለያየ መልስ ከሰጡ ሰቆቃው ሁለቱም ላይ የጠና ነው፡፡ አንደኛው ወደ ሌላኛው መልስ የሚጠጋ ነገር እስካልተናገረ ድረስ ሁለቱም ይሰቃያሉ፡፡ በኛ ምርመራ ወቅት አስቀድመን ምንም የምንደብቀው ወይንም የምንዋሸው ነገር እንዳይኖር ስንነጋገር ስለከረምን በተነጋገርነው መሰረት የአንዳችን ቃል ከሌላችን የጎላ ልዩነት አልነበረውም፡፡
በጓደኞች መሀከል ክፍተት ለመፍጠር ሙከራ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ ለበፍቄ ‹‹ናትናኤል እኮ እውነቱን ነግሮናል፡፡ በፍቃዱ ነው አብዮት እና አመጽ እንድንጠራ የሚገፋፋን ብሏል፡፡ አንተ ለምንድነው እንዲህ የምትደብቅላቸው እነሱ እውነቱን እየተናገሩ›› ብለውታል፡፡ ቀዳዳ ካገኙ ቅያሜ በመፍጠር ከጓደኛሞች መሀል አንዱን መስካሪ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ ማስፈራሪያዎች በታጨቁበት ምርመራ መሀል እራሴን ነጻ ማውጣት ቀላሉ አማራጭ እንደሆነ ደጋግመው ይነግሩኝ ነበር፡፡ ፀጋዬ (ጥጋቡ)፣ ም/ሳጅን መኮንን እና ኢንስፔክተር አሰፋ እየመረመሩኝ በነበሩበት ወቅት ፀጋዬ ተራ ስድቦችን እና ዛቻዎችን ከሰነዘረ በኋላ በዛው አፉ እኔን ማቆየት እንደማይፈልጉ እና የሚፈልጉትን ካልኩላቸው ወዲያውኑ ወደቤቴ እንደሚሸኙኝ አባቴንም መንከባከብ እንደሚሻለኝ ሲነግረኝ ነበር፡፡ የአባቴ ጤንነት እንዳሳሰበኝ ስለገባቸው ባገኙት አጋጣሚ ለምርመራው ግብአትነት ይጠቀሙበት ነበር፡፡
አብዛኛው የምርመራ ጊዜ በተደጋጋሚ ጥያቄዎች እና ተደጋጋሚ መልሶች የሚያልፍ ነው፡፡ ይህም ምርመራዎችን እጅግ አድካሚ እና አሰልቺ ያደርጋቸዋል፡፡ ዝርዝር ጉዳዮችን በተደጋጋሚ በመጠየቅ ከምሰጠው መልስ ላይ ልዩነት ለማግኘት ይህንንም ተጠቅሞ ሌላ አዲስ ነገር ለማውጣጣት ይጥሩ ነበር፡፡ የተሳካላቸው ግን አይመስለኝም፡፡ በተቻለኝ አቅም ቀዳዳ ሳገኝ የማምንበትን አቋም ከመናገር ወደኋላ አላልኩም፡፡ የማውቀውን ለማካፈልም እንደዚያው፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስት አንቀጽ 39ን የሚቃወም መርማሪ አግኝቼ ለምን ልክ ነው ብዬ እንደማምን አስረዳኋቸው፡፡ በተለያየ ጊዜ የወሰድኳቸው የበይነ መረብ ደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎችንም በተመለከተ ያብራራሁለትም መርማሪ ነበር፡፡
ማስታወሻ፡-5. በተገኘው አጋጣሚ አቋምን ማስረዳት
መርማሪዎቹ በተደጋጋሚ ስለተነገራቸው ብቻ የሚያምኑት ብዙ ነገር አለ፡፡ ኢህአዴግ ትግል ላይ በነበረበት ወቅት ጭራቅ ተደርጎ ይሳል እንደነበረው አሁንም የነጻነት ትግል እያደረጉ ያሉትን ሰዎች እንደ ሰው በላዎች የሚቆጥሯቸው መርማሪዎች ብዙ ናቸው፡፡ በነዚህ መርማሪዎች ይህን ከተማ (አ.አ) ተወልዶ ያደገ ሰው ፖለቲካ ውስጥ ቦታ የለውም፡፡ ተደጋግሞ ሲነሱልኝ ከነበሩት ጥያቄዎች መሀል ይህ መንግስት ምን በድሎሃል (በግል) እንዴት እንደዚህ አይነት አቋም ልትይዝ ቻልክ? የሚለው እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ መልሴ ግን አጭር ነበር፡፡ ነጻነቴን ዋጋ እሰጠዋለሁ!!
ከምክትል ሳጅን መኮንን ጋር በነበረን ጊዜ የተረዳሁት ስለ አቋሞቼ በጥልቀት ማወቅ ቢፈልግም እንደ ጦር እንደሚፈራቸው ነው፡፡ ገና ማስረዳት ስጀምር ቶሎ ብሎ ‹ወደ ጉዳያችን እንመለስ፣ ዳግም ወደ አንተ ልትስበኝ ነው?› ይለኝ ነበር፡፡ ሌሎችም መርማሪዎች ተመሳሳይ ፍላጎት አይቸባቸዋለሁ፡፡ አንድ የማይረሳኝ ምሳሌ ከኢሜሌ ላይ የተገኘውን የዜና መጽሔት በተመስጦ ሲያነብ የነበር አንድ መርማሪ አለቃቸው ድንገት ቢሮውን ከፍቶ ሲገባ ወረቀቱን በድንጋጤ ወርውሮታል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የቻልኩት እነዚህን በአንድ በኩል መረጃ የተደፈኑ ሰዎች ሌላኛውን ጎን ማሳየት በሌላ አማራጭ የማያገኙት መረጃ ምንጭ መሆን ስለሆነ በምርመራ ወቅት እንደ አንድ ዓላማ ሊወሰድ እንደሚገባ ነው፡፡
አልፎ አልፎ ከሌላ ቦታ የሚመጡ (ከደህንነት መስሪያ ቤት) መርማሪዎች ለመመለስ አደጋች የሆኑ ውስብስብ ጥያቄዎችን ከመጠየቃቸው ውጭ የሚጠየቁት ጥያቄዎች እዚህ ግባ የሚባሉ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ጊዜ መርማሪዎች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች ለራሳቸውም ግልጽ አይደሉም፡፡ ጥያቄዎችን የሚያበጁት ከጀርባ ሆነው ምርመራውን የሚመሩት አለቆቻቸው ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ ለመመለስ አደጋች የሚመስሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ፡፡ ለምሳሌ ሚያዝያ 27 ቀን (የአርበኞች ድል ቀን) ኢንስፔክተር አሰፋ እና አንድ የደህንነት ባልደረባ ሆነው ባካሄዱብኝ ምርመራ ወቅት አንድ አስቸጋሪ ጥያቄ ተነስቶ ነበር፡-
የደህንነት ባልደረባው፡- ‹‹ዞን 9 ምን ማለት ነው?››
መልስ ፡- ‹‹ዞን 9 ማለት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን የተነጠቀ ታሳሪ ነው ለማለት የተጠቀምንበት ስም ነው፡፡››
‹‹እኔም የዞን 9 አባል (ነዋሪ) ነኝ ማለት ነው?››
‹‹አዎ!››
‹‹ጥሩ! ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን የተነጠቀ ከሆነ መቼ እና እንዴት ነው ዞን9 ነጻ የሚወጣው?››
ይህ ጥያቄ ትንሽ ለመመለስ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በርግጥ እንደማነኛውም ግለሰብ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጻነቱን መቼ ያገኛል ለሚለው ጥያቄ የራሴ አስተያየት ቢኖረኝም በዚህ ምርመራ ወቅት ሀሳቤን በነጻነት ብናገር የሚያመዝነው አደጋው ነበር፡፡ ስለዚህ ማለት የቻልኩት ዞን 9 የሚለውን ተምሳሌታዊ ስያሜ አምነንበት ብንጠቀምም የዞን 9 ነዋሪዎችን ነጻ ማውጣት ግን እንደ ግብ ያስቀመጥነው እና እንዲሳካም ኃላፊነት ወስደን የሰራንበት ጉዳይ እንዳልነበር ነው፡፡
አጠቃላይ የእስር ቤቱ የአያያዝ ሁኔታና የምርመራው አሰልቺነት በየዕለቱ መርማሪዎቹ ከሚነግሩኝ የራሳቸው እውነት ጋር ተደማምሮ ሊያሸንፈኝ ዳር ዳር ብሎ ነበር፡፡ ነገር ግን በተባራሪ የምንሰማቸው ጓደኞቻችን እና መታሰራችን የሚቆረቁራቸው ሰዎች የሚያደርጉት ሰላማዊ ሰልፍ እና የበይነ መረብ ዘመቻ ተጨማሪ የጥንካሬ ምንጭ ሆነውኛል፡፡ የማታዎቹ ምርመራዎች ለዚህ ምቹ ናቸው፡፡ ካስተዋልኩት የተረዳሁት የማታውን (የሌሊቱን) የምርመራ ጊዜ መርማሪዎቹ ለሚከፈላቸው ተጨማሪ ገንዘብ እና ስላመሹ መ/ቤቱ ለሚያቀርብላቸው ቆሎ እና ውሃ ካልሆነ በስተቀር አይፈልጉትም፡፡
በማታው ምርመራ ወቅት ቶሎ የመሰላቸት እና የኃይል እርምጃ ወደ መውሰድ ይሄዳሉ፡፡ ብዙ ማውራት አይፈልጉም፡፡ ስለዚህ አለቆቻቸው የሰጧቸው ጥያቄዎች ሲያልቁባቸው የተለያዩ ስፖርታዊ ቅጣቶች በማዘዝ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት ጨዋታ (game) ይይዛሉ፡፡ ወይንም ሌላ ክፍል ምርመራ ላይ ካለ ጓደኛቸው ጋር በኢንተር ኮም ወግ ይይዛሉ፡፡ በተመርማሪዎች ላይ ያላግጣሉ፡፡ በማታዎቹ ምርመራዎች ወቅት ለሚነሱ ጥያቄዎች ረዘም ያሉ መልሶችን መምረጥ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ መልሶችንም በህገ-መንግስቱ ስለተፈቀዱ መብቶች፣ ስለ ተቋማት ነጻነት አስፈላጊነት፣ እና መሰል ፖለቲካዊ ጉዳዮች ወደ ማብራራት ማጠጋጋት፣ ከተቻለ የመርማሪዎቹን ቀልብ ለመሳብ እና ከሚወስዷቸው አላስፈላጊ የኃይል እርምጃዎች መከላከል ይቻላል፡፡
ማስታወሻ፡-6. አቤቱታ ማሰማት
የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ፍርድ ቤት በሚወሰዱበት ጊዜ ያለውን አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በተለምዶ ፍርድቤት በፖሊስ የአያያዝ በደል ተፈጽሞብኛል ብሎ የሚያመለክት ሰው ከፍርድ ቤቱ መልስ ተመልሶ ማዕከላዊ እንደሚገባ ስለሚያውቅ የባሰአደጋ ለመቀነስ በሚል አቤቱታ ከማቅረብ ሊቆጠብ ይችላል፡፡ ነገር ግን አቤቱታውን አቀረበም አላቀረበም ሰብዓዊ መብቱን ከመረገጥ አይድንም፡፡ ልዩነቱ የሚሆነው የፍርድ ቤቱ መዝገብ ላይ የመብት ጥሰቱ ተመዝግቧል ወይስ አልተመዘገበም የሚለው ነው፡፡
እዚህ ላይ የምመክራቸውን ነገሮች ያለማድረግ ቁጭት በእኔ ብቻ ሳይሆን ብዙ ታሳሪዎች ላይ ያስተዋልኩት ነው፡፡ ያላደረግሁትን አድርጉ ብሎ የመጠየቅ ይሉኝታም ጽሁፉን ልጻፍ ወይስ ይቅርብኝ ብዬ እንዳንገራግር አድርጎኝ ነበር፡፡ ውስጤ ከሚብላላ ግን ጽፌው አንብቦ ቢያንስ አንድ ሰው የተለየ መንገድ ተከትሎ ጉዳት ቢቀንስ የተሻለ ነው የሚለው ሀሳብ የተሻለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ሌሎቹም ጓደኞቼ ተመሳሳይ መንገድ አልፈዋል፡፡ የነሱንም የምርመራ ሂደት ይጽፉታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እስከዛው ድረስ መታገስ ያልቻለ የሀገር ውስጥ ነዋሪ ግን ወደ ቂሊንጦ ጎራ ብሎ ከራሳቸው አፍ ጠይቆ መረዳት ይችላል፡፡ እኔ ቀረኝ የምለው ነገር ካለኝ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡
ማስታወሻ፡-7. የማዕከላዊ ቤቶችን (ክፍሎች) ይተዋወቁ
በግቢው ውስጥ ሶስት የእስረኛ ማቆያ ቦታዎች አሉ፡፡ በተለምዶ ጣውላ ቤት፣ ሳይቤሪያ እና ሸራተን በመባል ይታወቃሉ፡፡ጣውላ ቤት አምስት ክፍሎችን በተርታ የያዘ ሲሆን የምርመራ ቢሮዎች ያሉበት ህንጻ ጀርባ ምድር ላይ ያሉ ክፍሎች ናቸው፡፡ እኛ ማዕከላዊታስረን በነበርንበት ወቅት ሶስቱ ክፍሎች ለሴት ተጠርጣሪዎች ማቆያ ሲሆኑ ቆርቆሮ መከለያ ተደርጎለት፣ ደግሞ የተቀሩት ሁለቱ ምስክርለመሆን የተስማሙ ወንድ ተመርማሪዎች ማቆያ ነው፡፡ ማሂ እና ኤዶም ከሶስቱ ክፍሎች በአንደኛው ከሌላ ሴት ታሳሪዎች ጋር እንዳይገናኙሁለቱ ብቻ ተለይተው ነበር፡፡ ጣውላ ቤት ፊት ለፊት የክፍሎቹ ወለል ጣውላ መሆኑ ነው ጣውላ ቤት የሚል ስያሜ ያሰጠው፡፡ ይህንንማቆያ ቤት አልፎ አልፎ ሂልተን በማለት የሚጠሩት ሰዎች ገጥመውኛል፡፡
ሳይቤሪያ የሚባለው የእስረኛ ማቆያ በቅዝቃዜው ምክንያት ነው ስሙን ያገኘው፡፡ ይህ ባለአንድ ፎቅ ህንጻ ምድር ላይየሚገኘው ማቆያ ቦታ በረጅም ኮሪደር የተከፈለ ሲሆን በግራና በቀኝ ከ2 ቁጥር እስከ 10 ቁጥር የተለጠፈባቸው አምስት አምስት ክፍሎች አሉት፡፡ 8 ቁጥር ከተለጠፈበት ውጭ ሌሎቹ ወጥ ክፍሎች ሲሆኑ 8 ቁጥር የተለጠፈበትን በር ተከፍቶ ሲገባ ግን ሌሎች ራሳቸውን የቻሉ አራት ክፍሎች አሉት፡፡ የበለጠ ቅጣት እንዲቀጣ የሚፈልጉት ተመርማሪ እነዚህ ሁለት ሜትር በሁለት ሜትር የሆነ ጨለማ ክፍል ውስጥ ያስሯቸዋል፡፡ ሳይቤሪያ የምርመራ ግለቱ እስኪሰክን ድረስ ተመርማሪዎች የሚቆዩበት ቦታ ሲሆን ሁሉም ክፍሎች ከኤሌክትሪክ መብራት ውጭ ምንም አይነት ብርሃን አይደርሳቸውም፡፡ የክፍሎቹ ግድግዳዎች ወለሉና ጣራው ከኮንክሪት የተሰራ ነው፡፡ ቀኑን ሙሉ ከውጭ ተዘግቶ የሚውለው ክፍል በቀን ለሶስት ጊዜ ያክል ይከፈታል፡፡
ሳይቤሪያ ውስጥ ያሉ ክፍሎች ጠዋትና ማታ በተራ በተራ እየተከፈቱ ተመርማሪዎች በጋራ ወደሚጠቀሙት ባለስድስት ክፍል ሽንት ቤት እና መታጠቢያ ቤት እንዲሄዱና ተጠቅመው እንዲመለሱ ለደቂቃዎች ፈቃድ ያገኛሉ፡፡ ለሌሎች ጥቂት ደቂቃዎች ደግሞ የፀሐይ ብርሃን ለማግኘት ይፈቀድልን ነበር፡፡ ፀሐይ የምናገኘው በጣውላ ቤት እና በህክምና ክሊኒኩ መሐከል ባለ ክፍት ቦታ ላይ ነበር፡፡ጣውላ ቤት ያሉት ክፍሎች በር ክፍት ስለሚሆን ከማሂ እና ኤዶም ጋር በዓይን እና በምልክት ብቻ እናወራ ነበር፡፡ የሳይቤሪያ ክፍሎች በየተራ በሳምንት አንድ ቀን የሚጸዱ ሲሆን ባለችን መታጠቢያ ጊዜም የምናገኘው በነዚህ ቀናት ብቻ በሳምንት አንዴ ነው፡፡
ሸራተን ለ12 ሰዓት ፀሐይ የሚገኝበት፣ ቲቪ የሚታይበት እና የሽንት ቤት እና የመታጠብ ፍላጎት ያለው ሰው የፈለገውን ማድረግ የሚችልበት ቦታ ነው፡፡ የምርመራው ሂደት ሲጠናቀቅ ቀለል ባለ ጉዳይ የሚመረመር ሰው ወይንም ደህና ባለስልጣን ዘመድ ያለው ሰው ሸራተን ሆኖ የማዕከላዊ ቆይታውን ያጠናቅቃል፡፡
በመጨረሻም አንድ እብሪተኛ መርማሪ በተናገረኝ ንግግር ማስታወሻየን ላጠናቅቅ፡፡ እንዲህ ነበር ያለኝ፣ ‹‹መንግስት ብዙ ዓይኖች እና ጆሮዎች አሉት፡፡ እናንተ ደግሞ ስታወሩ የነበረው በእኛው ስልክ፣ ከሀገር ስትወጡ የነበረው በእኛው በሀገራችን አየር መንገድ እና በቦሌ በኩል ነበር፡፡ እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችሁን መረጃ አለን፡፡ አንተ አሁን እየደበቅህን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለአንተ አይጠቅምም፡፡ እኛ ምርጫ እንሰጥሃለን፡፡ ሕይወትህን ወደብርሃን መውሰድ የምትፈልግ ከሆነ ወደዚያው እንመራሃለን፡፡ አይ አልፈልግም የምትል ከሆነ ደግሞ መውጣት ወደማትችለው ድቅድቅ ጨለማ እንከትሃለን፡፡ ምርጫው የአንተ ነው፡፡››
No comments:
Post a Comment