በኤፍሬም ማዴቦ
ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። አዎ! ማተቡን ላጠበቀና በአምላኩ ለሚታመን በእርግጥ ቃል የዕምነት ዕዳ ነዉ። ሰዉ ነኝና እንደ ፈጣሪ ቃሌ ሁሉ እዉነት ነዉ ብዬ አለተፈጥሮዬ አላብጥም። ግን ሰዉ ብሆንም ፈጣሪዬን የምፈራ ሰዉ ነኝና ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ስል ልቦናዬ እያወቀዉ እንደነ ጋሼ እንደልቡ ዉሸት ደርድሬ ለአንባቢ የማቀርብበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ቀጥሎ የማስነብባችሁ እያንዳንዱ ቃል እንደ ዳያስፖራ ተረተኞች የምተርተዉ ‘ሰዉ ሰዉ’ የማይሸተት ተረት ሳይሆን ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በየግንባሩ የተሰለፉትንና በስልጠና ላይ የሚገኙትን የኢትዮጵያ አርበኞች ስጎበኝ በአይኔ ያየሁትንና በጆሮዬ የሰማሁትን ቃል ነዉ።
ቨርጂኒያ ወደሚገኘዉ “Dulles” አዉሮፕላን ማረፊያ የሄድኩት ከልጄ ጋር ነበር። ከቤቴ Dulles የግማሽ ሰዐት መንገድ ነዉ። ያቺን ግማሽ ሰዐትና አዉሮፕላን ማረፊያ ደርሼ ሻንጣዬን እስካስጭን ድረስ አይኔ እያንዳንዷን ደቂቃ ከልጄ ከቢኒያም አልተለየም። መለየቱን ስላልወደደዉ ልቤ ደንግጧል። ከወያኔ ጋር ለመፋለም በረሃ የሚጓዘዉ ኤፍሬም ከአንድ ልጁ መለየት አቃተዉ። ምነዉ ብዬ እራሴን ጠየኩት- እኔዉ መልሼ ምንም አልኩ። ልጄን አቀፍኩት፤ አሁንም ደግሜ ደጋግሜ አቀፍኩት። እምባ ፊቴን ሞላዉ። ቀና ብሎ ተመለከተኝና ሲከፋዉ ታየኝ።