ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
የእንግሊዝ ህዝብ መሰረታዊ ህገ መንግስት 800ኛ ዓመት በዓል በማክበር ላይ እገኛለሁ
እንዴት!?
አንዴ በጅ በሉኝ! ጥያቄአችሁን ተገንዝቤዋለሁ!
በአሁኑ ጊዜ በአሜሪካ ሀገር የሚኖር አንድ በአፍሪካ ያውም በኢትዮጵያ የተወለደ ሰው በመካከለኛው ዘመን ከ800 ዓመታት በፊት በእንግሊዝ ሀገር ያመፁ ባለጉልት ባላባቶችና በነጉሳቸው መካከል በተደረገው የስልጣንና የግል ጥቅም ትግልና ስምምነት ለምንድነው የሚያከብረው? ስለነሱ መብትና ነፃነት ምን ግድ አገባው?
ብላቸሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ።
ብላቸሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ።
የፊውዳል ወይም ደግሞ የንጉሳውያንን ስርዓት በፍጹም አልወድም፡፡ ተወልጀ ያደግሁት በፊውዳሏ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ የፊውዳሉን ስርዓት አስከፊነት፣ ስብዕና የለሽነት እና የበሰበሰ መሆኑን በሚገባ አይቸዋለሁ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት የመንግስት ዓይነት ንጉሳዊ የመንግስት ስርዓት ነበር፡፡
የደርግ ወታደራዊ የሆነው የህብረተሰባዊ/socialist ስርዓት ማጭድ ፈላጭ ቆራጭ የነበረውን የንጉሳዊ ስርዓት ከስሩ ቆርጦ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ገነደሰው፡፡ ለእኔ የመሬት ከበርቴው/ፊውዳሊዝም እና የንጉሳውያን/ሞናርኪ ስርዓቶች ለታሪክ ጥናት ካልሆነ ምንም ፋይዳ የላቸዉም፡፡ የመሬት ከበርቴው ስርዓት ለካፒታሊዝም ስርዓት መደላድል ነው የሚለውን የካርል ማርክስን ትንተና ማንበቤን አስታውሳለሁ፡፡ እ.ኤ.አ በ1974 በስሜት የሚነዱ እና ምንም ዓይነት እርባና ያለው ስራ የማይሰሩ ባለዝቅተኛ ማዕረግ የነበራቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች በወታደራዊ ኃይል ክንፍ ስር ሆኖ ሀገሪቱ ካለችበት የመሬት ከበርቴ ስርዓት በቀጥታ ወደ ህብረተሰባዊነት ስርዓት መሸጋገር ትችላለች ብለው አስበው ነበር፡፡ በእርግጠኝነት ለመናገር የእንግሊዞች የመብት፣ ክብር እና ነጻነትን/Magna Carta ህገ መንግስት በዓል የማከብረው ንጉስ ጆን የፈላስፋ ንጉሥ ስለነበሩ አይደለም፡፡ ንጉስ ጆን መጥፎ አርዓያነት ያለው ስራ የሚሰሩ፣ ክብር የማይሰጣቸው እና ለመርህ የማይገዙ ሰው ነበሩ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ ሰው እምነት የማይጥልባቸው ከሀዲ፣ እምነተቢስ፣ ገብጋባ እና ጨካኝ ሰው ነበሩ፡፡ ጆን ሰውን ሲገድሉ እንደ እኛዎቹ ዓይን አውጣ ፈጣጣዎች ለይስሙላም እንኳ ቢሆን ማዘናቸው ቀርቶ መሳቅ የሚቀናቸው ሰይጣናዊ ባህሪ የተጠናወታቸው ንጉስ ነበሩ፡፡ ሰዎች እንዲህ ብለው ነበር፣ “በእርኩሱ ንጉስ ጆን መኖር ገሀነም እራሷ ትጸየፋለች፡፡“ ጆን በቀልተኛ እና አምባገነናዊ ንጉስ ነበሩ፡፡ የእራሳቸውን ሰዎች በእራሳቸው ፈቃድ በቁጥጥር ስር ያውላሉ፣ ወደ እስር ቤት ያግዛሉ፣ ያስራሉ፡፡ የማይሞላ የገንዘብ ካዝናቸውን ለመሙላት በህዝቦች ላይ አስከፊ የሆነ ግብር በመጣል ገንዘብ ይዘርፋሉ፡፡ የስግብግብነት እና የገንዘብ ጥማታቸውን በማርካት እራሳቸውን የበለጠ በሀብት እንዲበለጽጉ ጦርነት ሁሉያደርጉ ነበር። የውትድርና አገልግሎት ላለመስጠት የመሬት ከበርቴዎች የሚሰጧቸው ገንዘብ እና ሰዎችን በገንዘብ በመቅጣት የሚዘርፉት ገንዘብ ዋና ዋና የገንዘብ ማጋበሻ ምንጮቻቸው ነበሩ፡፡
ጆን የእራሳቸውን ሰዎች መሬቶች፣ ፈረሶች፣ ጋሪዎች፣ የበቆሎ ሰብል እና እንጨቶቻቸውን ሳይቀር ከህግ አግባብ ውጭ በመቀማት የሚዘርፉ ገብጋባ ንጉስ ነበሩ፡፡ ከዚህ አንጻር የንጉሳውያንን ደን ዋና የገቢ ምንጫቸው አደረጉ፣ እናም በእርሳቸው የአገዛዝ ዘመን ዋና የሙስና ምሽጋቸው አደረጉት፡፡ በትክክል ለመናገር ጆን ፍትህን ሸጠዋታል፡፡ የንጉሳውያን/ት የፍትህ ስርዓት በጠቅላላ በሚገዙት የወሰን ክልል ውስጥ ሁሉ ሙሉ ቁጥጥር ያለው ስለሆነ ለህግ ጥብቅና የሚቆሙ ሰዎች እና ቡድኖችም ለንጉሳውያን ቤተሰቦች ገንዘብ እንዲከፍሉ ያስገድዷቸው ነበር፡፡ በአንድ በተወሰነ ጊዜ በሚደረግ የገንዘብ ፍሰት ሁኔታ ላይ በመመስረት ጆን የህግ መብት እና ክብርን ሁልጊዜ ከፍተኛ ጨረታ ላቀረበ ሰው ወይም ቡድን በሽያጭ ያቀርቡ ነበር፡፡ ጆን ጦርነቶችን ለማሸነፍ በቅጥር ወሮበላ ነፍሰ ገዳዮች ተከብበው ይኖሩ ነበር፡፡ በኃይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ይገቡ ነበር፡፡ የስልጣን ሀራራ የተጠናወታቸው የስልጣን ቁንጮ ሰው ነበሩ፡፡
ንጉስ ጆንን የምገልጽበት ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ በ21ኛው ክፍለ ዘመን አንድ አማካይ የአፍሪካ አምባገነን ወሮበላ ዘራፊ “መሪዎች ” ከሚያደርገት ጋር ተመሳሳይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከአንዱ የአፍሪካ ጫፍ ወደ ሌላው የአፍሪካ ጫፍ ሲታይ የአፍሪካ አምባገነኖች ተቃዋሚዎቻቸውን በእራሳቸው ስልጣን ከህግ አግባብ ውጭ በቁጥጥር ስር ያውላሉ፣ በየእስር ቤቱ ያግዛሉ፣ ያሸማቅቃሉ እንዲሁም ያስፈራራሉ፡፡ የአፍሪካ አምባገነኖች የይስሙላ ፍርድ ቤቶቻቸውን በመጠቀም ተቃዋሚዎቻቸውን ለማሰቃያነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ደግሞ በግልጽ በአደባባይ ከፍተኛ ገንዘብ ለሚሰጥ ፍትህን ይሸጧታል፡፡ ቀደምቶቻቸው ይዘውት የኖሩትን እና ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የመሬት የባለቤትነት መብት በመንጠቅ ለውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በጣም ርካሽ በሆነ ዋጋ ይሸጡታል፡፡ ምንም ዓይነት የጦር መሳሪያ ሳያነሱ በሰላማዊ መንገድ በሚቃወሟቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጦር በማዝመት እልቂት እንዲፈጸምባቸው ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ አምባገነኖች የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን ያስራሉ፣ ያሰቃያሉ እናም ግዞት እንዲወርዱ ያደርጋሉ፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮችን ከእራሳቸው ህዝቦች በመስረቅ በውጭ ሀገር የሚገኙ የባንክ ሂሳቦቻቸውን በማደለብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በኃይማኖት ላይ ጣልቃ ይገባሉ እናም በስልጣን ወንበሮቻቸው ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ለመኖር የጥላቻ መንፈስን ያራምዳሉ፡፡ በእራሳቸው ህዝቦች ላይ ግድያን የመፈጸም እና እልቂትን የማምጣት ጦርነት ናፋቂዎች ናቸው፡፡ በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ወንጀሎችን የሚፈጽሙ እና የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን የሚተገብሩ ፈጣጣዎች ናቸው፡፡ በሰው ልጆች ላይ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣ ወንጀል በመፈጸማቸው ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ ሁለት የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገር መሪዎች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ክስ ተመስርቶባቸው የክስ ሂደታቸው በመታየት ላይ ይገኛሉ፡፡ እንደ ንጉስ ጆን ሁሉ የአፍሪካ አምባገነን ገዥዎች ሰላማዊ ዜጎችን ሲገድሉ ይስቃሉ፣ ሆኖም ግን እየሳቁም ቢሆን ይገድላሉ፡፡ ገሀነም እራሷ የበሰበሱትን የአፍሪካ አምባገነኖች እና ወሮበላ ዘራፊዎች ትጸየፋቸዋለች፡፡
የእንግሊዝ መብት፣ ክብር እና ነጻነት የጸደቀበትን/Magna Carta (ማግና ካርታ) ጊዜ የማከብረው ለምንድን ነው?
የእራሴን ጥያቄ ለመመለስ በኢትዮጵያ ገና ልጅ የነበርኩበትን ጊዜ ወደ ኋላ 50 ዓመታት ተጉዠ ማስታወስ ይኖርብኛል፡፡ ማንበብን በጣም የምወድ ልጅ ነበርኩ፡፡ የዓለምን የስነጽሁፍ እና ፍልስፍና ስራዎች በማግኘቱ ረገድ በጣም እድለኛ ነበርኩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ለነበሩት የአሜሪካ የስነጽሁፍ ስራዎች ፍጹም እንግዳ አልነበርኩም፡፡ እንደዚሁም ደግሞ የአማርኛ ታዋቂ ስነጽሁፍ የሚባሉትን ሁሉ አነባለሁ፡፡
በህጉ የበለጠ እደነቃለሁ፡፡ ገና ከወጣትነት እድሜዬ ጀምሮ ስለዓለም የህግ ሂደት ተጋላጭነቱ ነበረኝ፡፡ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች እና በሌሎች ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ፍርድ ቤቶች ላይ የሚካሄዱትን የፍርድ ሂደቶች በአንክሮ እከታተል ነበር፡፡
ከፍርድ ቤቶች ግቢ ውጭ ባሉ መንገዶች ዳርቻ በሚገኙ ትናንሽ ቤቶች/ኪዮስኮች ውስጥ ተቀምጠው በግራ እና በቀኝ ለሚደረግ ክርክር የሚሆን ማመልከቻ በአማርኛ በእጅ ጽሁፍ በቢክ እስክብሪቶ ይጽፉት የነበረውን ውብ የሆነ የእጅ ጽሁፍ በግልጽ አስታውሳለሁ፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሰዎችን ሊያሳምን የሚችል አንደበት ያላቸውን የህግ ባለሙያዎችን እና ጥሩ ዳኝነት የሚሰጡ የህግ ሰዎችን በተለይም ደግሞ ስለህግ ጭብጦች በተለይም በፍርድ ችሎቱ ላይ ስለሚሰጠው ፍርድ ሳይሆን ስለህግ ስነስርዓት የሚናገሩትን እና የሚከራከሩትን ዳኞች ማዳመጥ ከምንም በላይ ደስታ ይሰጠኝ ነበር፡፡ አንደበተ ርትኡ የሆነው ንግግራቸው እና ያነጋገር ግልጽነታቸው፣ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ሊያሳምን በሚችል መልኩ የሚቀርበው ንግግራቸው እና በጥቂት የህግ ባለሙያዎች የሚደረገው አዕምሮን የሚገዛው ንግግራቸው እንደዚሁም በህግ ሂደቱ ላይ በሚነሱት የሰሉ ጥያቄዎች እና ነገሮችን ፈጥኖ የመረዳት እና ተገቢ የሆነ ፈጣን መልስ የመስጠት ችሎታቸውን በመመልከት በአዕምሮዬ ላይ የዕድሜ ልክ ትዝታን ጥሎ አልፏል፡፡ እነዚህ ሰዎች ለእኔ ትልቅ ተምሳሌቶች ነበሩ፡፡
በአማርኛ የተዘጋጁትን የኢትዮጵያን የወንጀለኛ መቅጫ እና የፍትሐብሄር ህጎችን በተለይም ደግሞ የህግ ባለሙያዎች እና ዳኞች በእነዚህ ህጎች ላይ ክርክር ካካሄዱ በኋላ ነጥብ በነጥብ እየለየሁ አንብቢያቸዋለሁ፡፡ በተለይም የወንጀለኛ እና የፍትሐብሄር ስነስርዓቶችን ከምንም በላይ እወዳቸዋለሁ፡፡ የፍትሐብሄር ስነስርዓት ህግ ከ245 ገጾች ባነሰ ጥራዝ የተቀነበበ ነው፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ወደ 69 ገጾችን አካትቶ በመያዝ ከፍትሐብሄር ስነስርዓት ህጉ ጋር በአባሪነት እንዲያያዝ ሆኖ የተዘጋጀ ነው፡፡ ማንኛቸውም ቢሆኑ ለማንበብ እና ግንዛቤ ለመውሰድ የሚያስቸግሩ አይደሉም፡፡
የስነስርዓት ህጎችን በመጣስ ረገድ የሚቀርቡ የህግ የክርክር ጭብጦችን መከታተል ከምንም በላይ ያስደስቱኛል፡፡ ፖሊስ የቀረበለትን የወንጀል ድርጊት ተገቢ በሆነ መልኩ መርምሮ ለፍትህ ያቀርባልን? ወንጀለኛ ነው ተብሎ የተጠረጠረን/የተጠረጠረችን ሰው ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ግምታዊ በሆነ ስሌት በመገፋፋት ነውን? ፖሊስ ተሰራ ለተባለው ወንጀል ተገቢ የሆነውን ማስረጃ ይዟልን? ለፍትሐብሄር ስነስርዓት ሕግ ክርክር ጉዳይ የቀረቡት ሰነዶች በትክክለኛነት የተረጋገጡ ናቸውን? በአንድ በሕግ በተያዘ ጉዳይ ላይ ማገጃ ለማውጣት የሕግ መሰረት አለውን? ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት (ከላይ ያሉትን ስዕሎች ይመልከቱ) ተዘጋጅተው እስከ አሁን ድረስ በስራ ላይ እየዋሉ ያሉት የኢትዮጵያ የሕግ ስርዓቶች ዋናዎቹ ሰነዶች በእጀ ላይ ይገኛሉ፡፡ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እና የፍትሐብሄር ስነስርዓት ሕግ ሰነዶች በአሁኑ ጊዜ ካለው ዓለም አቀፍ የሕግ መስፈርት አንጻር ሲገመገሙ እንኳ ከፍተኛ የሆነ እመርታ የነበራቸው መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ በእርግጥ የግማሽ ምዕተ ዓመት እድሜን ከመግፋት አንጻር በሰነዶቹ ጥራዞች ላይ የእርጅና ምልክት ከመታየት ባለፈ ምንም ዓይነት ችግር የለባቸውም፡፡ ወረቀቱ ከጊዜ ብዛት የተነሳ ቀለሙ ወደ ብጫነት ተቀይሯል፡፡ እንደዚሁም በእነዚህ ጥራዞች ዋና መገጣጠሚያ ላይ የነበረው ሙጫ ደርቋል እናም ከብዙ ጊዜ በፊት ተለያይቷል፡፡ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን በጥንቃቄ በማንበብ እና በመመርመር እነዚህ የሕግ ስርዓቶች ምን ያህል ዘመናዊ እና የተሻሻሉ እንደነበሩ በአድናቆት እመለከታለሁ፡፡
ከ30 ዓመታት በኋላ የእራስ ጥፋትን በፍርድ ቤት ማመንን በማስመልከት በተደረገው በ5ኛው የዩ.ኤስ አሜሪካ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ያጎናጸፈውን መብት ከግንዛቤ በማስገባት የስነስርዓት ሂደቱን ለመጠበቅ በዓለም ላይ አንዱ እና ታዋቂ ከሆነው ከካሊፎርኒያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት የመቆም ዕድልን አግኝቸ ነበር፡፡ በዚያ ፍርድ ቤት በሳክራሜንቶ ካሊፎርኒያ ለቃል ክርክር ከፍርድ ቤቱ በር ደረጃ ላይ ስራመድ በዚያ የልጅነት ዕድሜዬ እንደዚያ ያሉትን አስደማሚ የሆኑትን ታላላቆቹን የህግ ባለሙያዎች እና ዳኞችን ለአጭር ጊዜም ቢሆን አስታወስክዋቸው። ደስ ብሎኝም በጣም ፈገግ አልኩኝ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እ.ኤ.አ በ1955 ተሻሽሎ የወጣው የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግስት ነበር፡፡ በማንኛውም ጊዜ ቢሆን ግን በፍርድ ቤት ወይም ከፍርድ ቤት ውጭ ስለሕገ መንግስት የተደረገ ክርክር ተመልክቸ አላውቅም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የተማሩ፣ የበቁ ዳኞች እና የሕግ ባለሙያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ “ሕገመንግስቱ” ሲሉ እሰማለሁ፣ ሆኖም ግን በሕገ መንግስቶቹ ረቂቆችም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዚያት ውስጥ ሁሉ የእነርሱ የተመዘገበ ውይይት ወይም ደግሞ የተናገሩት ንግግር ለመኖሩ በህሊናዬ ላይ የሚያቃጭል አንድም ነገር የለም፡፡
ያንን የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ለበርካታ ዓመታት እንዳጠናሁት የሕገ መንግስቱ ምዕራፍ 3 ከአሜሪካው የሰብአዊ መብት ሕግ ጋር ባልተጠበቀ መልኩ አንድ ሆኖ የመገኘቱ ጉዳይ በጣም አስገርሞኛል፡፡ ምዕርፍ 3 “የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ሕግ” ተብሎ ሊገለጽ ይቻላል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እንደዚህ ያለውን ሰፊ መሰረት ያለውን እና ለህዝባቸው ነጻነትን ሊያጎናጽፍ የሚችል ሕገ መንግስት እንደ ንጉሳዊ ወግ አጥባቂ አስተዳደር ልዩ የሆነ የፖለቲካ ቁጥጥር ባለበት ስርዓት ውስጥ ቢያንስ በመርህ ደረጃ እንኳ ምን ያህል ዘመናዊነትን ለማስፈን ጥረት ያደርጉ እንደነበር ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ጥቂቶቹ ሕገ መንግስቱ ባጎጸፋቸው ነጻነቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በታሪክ እንደምንረዳው እንደማንኛውም ንጉሳዊ አገዛዝ ሁሉ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግስትም ጊዜ አልፎበት አልፏል፡፡
እ.ኤ.አ በ1955 ተሻሽሎ የወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ከጥቂት ነጥቦች በስተቀር እንዳለ የአሜሪካ የሰብአዊ መብት የሕግ ድንጋጌ ጋር እና ከዩ.ኤስ አሜሪካ ሌሎች የሕገ መንግስት ማሻሻያዎች ጋር አንድ እና ተመሳሳይ የሆነ የካርቦን ቅጅ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን መመልከቱ ዋቢነቱን የበለጠ ግልጽ ያደርገዋል፣
ማንም ቢሆን የሕግ እኩልነትን አይነፈግም…ማንም በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ ያለ ሰው ከሕግ አግባብ ውጭ ሕይወቱን፣ ነጻነቱን ወይም ንብረቱን አያጣም…ማናቸውም ሰው በሀገሪቱ ሕግ መሰረት በሕግ አግባብ ካልሆነ በስተቀር ንብረቱን አያጣም…የኢትዮጵያ ሕዝቦች በሰላማዊ መንገድ የመሰብሰብ መብት አላቸው…ማናቸውም ሰው በፍርድ ቤት ማዘዣ ካልሆነ በስተቀር በቀጥጥር ስር አይውልም…ማናቸውም በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው በ24 ሰዓቶች ውስጥ ለፍትህ አካል መቅረብ አለበት…በማናቸውም በወንጀል ጉዳዮች ክስ የተመሰረተበት ሰው የምስክሮችን ማስረጃነት በማቅረብ ጉዳዩ በፍጥነት እንዲያልቅለት ይደረጋል… በጥርጣሬ የተያዘ ወንጀለኛ የሚፈልገውን የሕግ አማካሪ ጠበቃ በመንግስት ወጭ እንዲቀጠርለት እና የሕግ አገልግሎት የማግኘት መብት አለው…የሕግ ጠበቃ ቀጥረው መከራከር የማይችሉ ድሆች በመንግስት ጠበቃ ተቀጥሮላቸው መከላክል እንዲችሉ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ሕገ መንግስት ከጸደቀ እና መተግበር ከጀመረ ከ8 ዓመታት በኋላ እንኳ እ.ኤአ. እስከ 1963 ድረስ በዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ጠበቃ ቀጥረው መከራከር የማይችሉ ደኃ ዜጎች ነጻ የሕግ አግልግሎት ጥቅም የማግኘት መብት አልነበራቸውም፡፡ ማናቸውም በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ጥፋተኝነቱ በፍትህ አካል እስካልተረጋገጠ ድረስ ወንጀለኛ አይደለም…ማናቸውም ሰው በአንድ ዓይነት ጥፋት ሁለት ጊዜ ሊቀጣ አይችልም…ማናቸውም ሰው ጭካኔ የተሞላበት እና ሰብአዊነት የጎደለው ቅጣት ሊፈጸምበት አይችልም…ሁሉም ሰዎች እና የግል መኖሪያ ቤቶች ከህገ ወጥ ምርመራ እና ፍተሻ ነጻ ናቸው…ማናቸውም ሰው በንጉሱ ላይ ክስ የመመስረት መብት ሊኖረው አይችልም…በአሁኑ ጊዜ ተሻሽሎ የተዘጋጀው ሕገ መንግስት በሀገሪቱ ላሉ ግዛቶች ሁሉ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ይሆናል…
እ.ኤ.አ በ1994 በህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ (ሕወሀት) ተረቅቆ በስራ ላይ የዋለው ሕገ መንግስትም ፍትህን እና ነጻነትን በማጎናጸፉ ረገድ በተግባር ሳይሆን በቃላት አጻጻፉ በጣም የተዋበ እና የተሽሞነሞነ የተዋጣለት ሰነድ ነው፡፡ በምዕራፍ 3 “ሰብአዊ መብቶች” ከሚለው ስር የተገለጹት በእርግጠኝነት የአሜሪካንን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እዳለ በመኮረጅ እንዲህ በማለት እንዲካተቱ ተደርገዋል፣
በህግ አግባብ ከተደነገገው ውጭ ማንም ሰው ቢሆን ነጻነቱን አያጣም…ማንም ሰው ክስ ሳይመሰረትበት እና ጥፋተኛነቱ በህግ አግባብ ሂደት ሳይረጋገጥ በቁጥጥር ስር ሊውል ወይም ደግሞ ሊታሰር አይችልም…ማንም ሰው ቢሆን ጭካኔ የተሞላበት እና ኢሰብአዊነት የሆነ ድርጊት ወይም እራስን ሊያዋርድ የሚችል ቅጣት ሊፈጸምበት አይችልም፡፡ ማንም በወንጀል ክስ የተመሰረተበት ተጠርጣሪ ስለተከሰሰበት ክስ ምንነት እና ለክሱ ምክንያት ስለሆነው ጉዳይ ወዲያውኑ እና በዝርዝር የመነገር መብት አለው፡፡ ማንም ቢሆን ስለተከሰሰበት ጉዳይ ምስክርነት ያለመስጠት፣ ወይም ደግሞ ዝም የማለት እና ያለመናገር መብት አለው…ማንም ቢሆን ተጥርጥሮ በቁጥጥር ስር በዋለ ሰው በ24 ሰዓቶች ጊዜ ውስጥ ለፍትህ አካል የመቅረብ መብት አለው፡፡ ማንኛውም በወንጀል የተጠረጠረ ሰው ሕጋዊ ከሆነው የፍትህ አካል የመጥሪያ ደብዳቤ ሊደርሰው እንደሚገባ የመጠየቅ እና የማግኘት መብት አለው…ማንኛውም በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው በዋስ የመለቀቅ መብት አለው…ማናቸውም በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ምንም ዓይነት የመዘግየት ሁኔታ ሳይፈጠር በፍርድ ቤት ድምጹ የመሰማት መብት አለው…ማንም በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው ስለተከሰሰበት ጉዳይ በዝርዝር በጽሁፍ ሊገለጽለት ይገባል፡፡ ማንም በጥርጣሬ በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው በእራሱ የሕግ ጠበቃ አቁሞ መከራከር ወይም ደግሞ የገንዘብ አቅም የሌለው ከሆነ መንግስት ጠበቃ ቀጥሮለት ሊከራከር የሚያስችል መብት አለው… ሕገ መንግስቱ የሀገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነው…
ህወሀት የአሜሪካንን የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች እንዳለ ኮርጆ በሰነዱ ላይ አሰፈረ፣ ከዚያም ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ በመበጣጠስ ወደ ቅርጫት መጣል ጀመረ፡፡
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ በ1955 ተሻሽሎ ስለወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ስለሲቪል ርትዕ እና ስለግለሰብ ነጻነቶች የሚያትተውን ሀሳብ ያገኙት ከየት ነው?
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ስለሲቪል ርትዕ እና ስለግለሰብ ነጻነቶች የሚደነግገውን እና እ.ኤ.አ በ1994 ያረቀቀውን ሕገ መንግስት የመነሻ ሀሳቡን ያገኘው ከየት ነው?
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ስለሲቪል ርትዕ እና ስለግለሰብ ነጻነቶች የሚደነግገውን እና እ.ኤ.አ በ1994 ያረቀቀውን ሕገ መንግስት የመነሻ ሀሳቡን ያገኘው ከየት ነው?
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከላይ የቀረበውን የህገ መንግስት ድንጋጌ እንዳለ ያገኙት እና ገልብጠው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አካል ያደረጉት ከአሜሪካ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ወስደው መሆኑን ምንም ዓይነት ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ አይደለም፡፡
ሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ ስለሲቪል ርትዕ እና ስለግለሰብ ነጻነቶች የሚያትተውን ሕገ መንግስት ሀሳቡን ያገኘው እና የኮረጀው እ.ኤ.አ በ1955 ተሻሽሎ ከወጣው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ነው፡፡
ስለሆነም የ64 ሺ ዶላር ጥያቄ ሆኖ ሊቀርብ የሚችለው፡ አሜሪካውያን ስለእያንዳንዱ ሰው ነጸነት እና ርትዕ የሚያትቱትን ጠቃሚ ሀሳቦች ያገኟቸው ከየት ነው? የሚለው ነው፡፡
አሜሪካኖች እነዚህን ጠቃሚ የግለሰብ መብቶች እና ርትዕ ሀሳቦች ያገኟቸው የእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን/Magna Carta ካስከበረባቸው የሰብአዊ መብት ድንጋጌ መሰረታዊ ሀሳቦች በመነሳት ነው፡፡ በአሜሪካ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ላይ በዝርዝር የተቀመጡት ነጻነቶች (የመጀመሪያዎቹ የዩ.ኤስ አሜሪካ አስሩ የሕገ መንግስት ማሻሻዎች) ቅሬታን የማቅረብ ነጻነት (1ኛው ማሻሻያ)፣ የሕግ የበላይነትን እና አብዛኞቹን ነጻነቶችን ያካተተውን (5ኛው እና 14ኛው ማሻሻያዎች)፣ ስለትክክለኛ ካሳ (5ኛ ማሻሻያ)፣ ከመጠን ያለፈ ዋስትና እና ገንዘብ የማስያዝን (8ኛ ማሻሻያ)፣ ፈጣን የሆነ የዳኝነት ሂደት፣ ከሳሾችን፣ የዳኞችን የችሎት ሂደት እና ከአድልኦ ስለጸዳ የዳኝነት ሂደትን ከመጋፈጥ አንጻር (6ኛ ማሻሻያ)፣ ስለሀገሪቷ የበላይ ሕግ (አንቀጽ 4)፣ የመጥሪያ ወረቀት ስለማግኘት መብት (አንቀጽ 1 ንኡስ አንቀጽ 9) እንደዚሁም የመንቀሳቀስ፣ የግል ነጻነት እና ሌሎች መብቶች ሁሉ መሰረታቸው የእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን ያወጀበት ድንጋጌ ነው፡፡
ቀደም ሲል አቅርቤው ለነበረው ጥያቄ መልሱን አግኝቻለሁ፡፡ የእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን/Magna Carta ያስከበረበትን ጊዜ አከብራለሁ ምክንያቱም ለኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ርትዕ እና ነጻነቶች መሰረቱ የሚገኘው የእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን/Magna Carta ካወጀበት የቀደምት የዘረመልድ/ዲኤንኤ ውህድ ውስጥ ስለሆነ ነው፡፡ ይኸ እውነታ ለጥቂቶች እንደ አስደናቂ ነገር ሊሆን ይችላል፣ ሆኖም ግን የኢትዮጵያ የሕገ መንግስት የነጻነት ድንጋጌዎች የዘረመልድ አፈጣጠር የተወረሱት ከእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን/Magna Carta ለማስከበር ከደነገገበት ትዕዛዞች እና መርሆዎች የመነጨ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ያ ውርስ ወይም ደግሞ የዝርያ ቅብብሎሽ ለኢትዮጵያ ብቻ ልዩ ሆኖ የተተወ አይደለም፡፡ በግልጽ የሚታየው እና የዜጎችን ነጻነት እና ፍትህ በማጎናጸፍ የግለሰቦችን ነጻነት እና ክብር የሚያስጠብቀው ማንኛውም ዘመናዊ የሆነ ሕገ መንግስት ቅርጹ የተለያየ ሊመስል ይችላል ሆኖም ግን ሁሉም በቀጥታ የዘር ግንዳቸው የእንግሊዝን ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን ካስጠበቀበት/Magna Carta ሕገ መንግስት የሚመዘዝ ነው፡፡
የእንግሊዝ ህዝብ መብቱን፣ ክብሩን እና ነጻነቱን ያስጠበቀበት/Magna Carta (ማግና ካርታ) ምንድን ነው?
ማግና ካርታ በተገዥ ህዝቦች የተረቀቀ እና በገዥዎች ላይ እንዲተገበር የተጣለ የመጀመሪያው የሕግ ሰነድ ነበር፡፡ ተገዥ መደቦች ገዥዎቻቸውን አስገድደው የሕግ የበላይነትን እንዲቀበሉ ለማድረግ የተደረገ የመጀመሪያ ጊዜ ድፍረትን የተላበሰ ጥረት ነበር፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገዥዎችን ደህንነት እና የቀጣዩን ትውልድ ሰላም እና ንብረት ሊያስጠብቅ በሚችል መልኩ በእራሳቸው በተገዥዎቹ እጆች ሕጎቹ ተጽፈው በተገዥዎች እና በገዥዎች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ የግዳጅ የፖለቲካ ስምምነት ሰነድ ነው፡፡ በእርግጥ ያ ሰነድ የእንግሊዝ ተራ ህዝቦች በእንግሊዝ ንጉሳውያን እና የመሬት ከበርቴዎች ይደርሱባቸው የነበሩትን የዘፈቀደ ያልተገደቡ ጭቆናዎችን እና በደሎችን ከስርዓቱ በማስወገድ ነጻነታቸውን ለማስከበር ሲሉ ያዘጋጁት ሰነድ ነው፡፡
የማግና ካርታ ሕጎች አስርቱን ትዕዛዞች መተግበር ከመጀመራቸው በፊት ሌሎች ታላላቅ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎች ነበሩ፡፡ ትክክለኛነታቸው ታምኖበት ቀደም ሲል ተሰብስበው የነበሩ ሕጎች እና የሮማን የሕግ ባለሙያዎች የተረጎሟቸው የሕግ ትርጉሞች በዚህ ርዕስ ስር ከሚካተቱት ውስጥ ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሮማውያንም ህጉን ከታች ያሉት ተራ የሆኑት የሮማ ህዝቦች መብቶቻቸውን እንዲያውቁ እና በንጉሳውያን ቤተሰቦች እና በመሬት ከበርቴዎች ሰብአዊ መብቶቻቸው እንዳይደፈጠጡ ለመከላከል በማሰብ ቀደም ሲል ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ451 – 450 የወጡ የፍትሐብሄር፣ የወንጀለኛ እና የኃይማኖታዊ ጉዳይ ሕጎችን ከሮማ ሕጎች ጋር በማጣመር ለሁሉም ዜጎች እንዲዳረስ ያደርጉ ነበር፡፡ በጥንታዊ አቴን የሶሎን ሕጎች የመሬት ባለቤት በሆኑ ንጉሳውያን ቤተሰቦች እና በገበሬዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት ዒላማ በማድረግ ግጭቶችን በሰላማዊ መልኩ ለመፍታት ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ የሶሎን ሕጎች የተሳሳተ እና ትክክለኛ ያልሆነ ቡድን ካልሆነ በስተቀር ለማንኛውም አቴናዊ የህግ ችሎት ስርዓት ለማካሄድ የሚያስችሉ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሆነው ብይን የሚሰጡ ዳኞችን ውሳኔ የሚገመግም ስርዓትን አቋቁመው ለብዙሀኑ ህዝብ ጥሩ የሆነ የህግ አገልግሎት ይሰጡ ነበር፡፡ የጥንታዊ ባቢሎናውያን የሐሙራቢ ህግ በርካታ የሆኑ ጉዳዮችን ያካተቱ ማለትም የቤተሰብ አባወራዎችን እና የቤተሰብ ጉዳዮቸን ጨምሮ እንዲሁም የሲቪል እና ወታደራዊ አገልግሎቶችን በመያዝ 282 ሕጎችን በማውጣት በስራ ላይ አውለው ነበር፡፡ ያ ሕግ በአሁኑ ጊዜ ዓይን ላጠፋ ዓይን፣ ጥርስ ለሰበረ ጥርስ የሚለውን አስከፊ ሕግ ያስታውሰናል፡፡
የማግና ካርታን የሕግ ሰነድ የሚቀድሙ ማናቸውም ዓይነት ሕጎች በሕግ የበላይነት መርህ ላይ የተመሰረተ ሕግ እስከ አሁን ድረስ አልተገኘም፡፡ ማናቸውም ሕጎች ቢሆኑ ተራ በሆነው ህዝብ ሉዓላዊነት ላይ በመመስረት የተረቀቁ እና የጸደቁ አይደሉም፣ ወይም ደግሞ በእራሳቸው በተራ ሕዝቦች የወጡ ሕጎች አይደሉም፡፡ ተራ የሆኑ ሕዝቦች በሌሎች ተረቅቀው እና ጸድቀው በእራሳቸው ላይ ስለሚጫኑባቸውን ሕጎች የሚሉት ነገር በጣም አናሳ ነው፡፡ ለሕጎቹ እንዲገዙ እና እየታዘዙ አስከፊ የሆነ ህይወትን ብቻ ያለምንም ተስፋ እንዲኖሩ ነው የሚፈለገው፡፡ ተራው ሕዝብ በገዥዎቻቸው ስልጣን ላይ ገደብን ለመጣል ድፍረቱ የላቸውም፡፡
ከማግና ካርታ ሕግ መውጣት በፊት ንጉስ ጆን እና የእርሳቸው ቀደምት ንጉሶች በኃይል እና በማስገደድ መርህ ላይ የተመሰረተ የአገዛዝ ስርዓትን ያራምዱ ነበር፡፡ ጆን የፈለጉትን ነገር ያደርጉ ነበር ምክንያቱም እንደ ንጉስነታቸው እርሳቸው ከሕጉ በላይ እንደሆኑ አድርገው ያምኑ ነበር፣ እናም ምንም ዓይነት ምድራዊ ለሆነ ኃይል ተጠያቂ አልነበሩም (ምናልባትም ለቅዱስ ጳጳሱ)፡፡ ለመካከለኛው እንግሊዝ ዘመን ፖለቲካ የእንግሊዝ ንጉሳውያን በጊዜው ባለው የማህበረሰብ ልማድ እና ልማዳዊ ህግ (በፍርድ ቤቶች ዳኝነት እና አዋጆች) እየታገዙ እና በአገዛዙ ዋና አማካሪ እየተረዱ ይሰሩ እንደነበር በአጠቃላይ ሁኔታ ቅቡል ነበር፡፡ በእርግጥ የጆን ቀደምት የነበሩት ሄንሪ 2ኛ ተግባራዊ የሆነ የሕግ ስርዓትን በመተግበር ከሕግ አግባብ ውጭ የንብረት መወሰድን የሚከለክል ህግ አውጥተው ነበር፡፡
ጥያቄ ሆኖ የሚቀርበው ንጉሱ እራሱ ያወጣውን ሕግ እና ከእርሱ በፊት የነበሩ ነገስታት ያወጧቸውን ሕጎች ሳይተግብራቸው የቀረ እና ልማዳዊ ስርዓቶችን በሙሉ የተወ እና ቀደም ሲል የታወጁ አዋጆችን ወይም ደግሞ ሌሎች ነገሮችን ሁሉ አልቀበልም ያለ እንደሆነ ነው፡፡
እ.ኤ.አ በ1215 ተራ የሆነው የእንግሊዝ ህዝብ ከንጉስ ጆን ጋር በተያያዘ መልኩ እንደዚህ ባለ ችግር ውስጥ ነው ወድቀው ሲማቅቁ የነበሩት፡፡ ንጉስ ጆን ደንታ ቢስ እና ተራ ህዝቦችን የሚጨቁኑ ገዥ ነበሩ፡፡ በተራው ህዝብ ላይ ጦርነትን አወጁ፡፡ ምንም ዓይነት ማስረጃ ሳይቀርብ ወይም ደግሞ ጥፋት ለመስራታቸው በማስረጃ ሳይረጋገጥ ሰዎችን እንዲያቀርብ የፍርድ ቤት ዳኛን አዝዘው በመላክ ሰዎችን አምጥቶ እንዲታሰሩ ያደርጉ ነበር፡፡ ንጉስ ጆን ከህዝቦች ላይ የመሬት ከበርቴነት ክፍያዎችን እና ግብሮችን ይጠይቁ ነበር፡፡ ጆን እራሳቸው ላወጧቸው ህጎች ተገዥ መሆን እንዳለባቸው አይቀበሉም ነበር፡፡ እንዲሁም ያሉት የሕግ ሂደቶች በተግባር ላይ እንዳይውሉ ቀስ አድርገው በድብቅ እንዲወጡ ያደርጉ ነበር፡፡
የእንግሊዝ ተራ ሰዎች በጆን የዘፈቀደ ስልጣኖች ላይ ገደብ ለማስቀመጥ ፈለጉ፡፡ ጆን እራሳቸው ላወጧቸው ህጎች እና ለሀገሪቱ ሕጎች እራሳቸውን እንዲያስገዙ ለማድረግ ፈለጉ፡፡ እ.ኤ.አ ሰኔ 1215 በቁጣ የተሞሉ የታጠቁ ተራ ህዝቦች በታምስ ወንዝ ዳርቻ ባለው የውኃ መስክ ቦታ ከለንደን ከተማ በቅርብ ርቀት በሩኒሜድ አካባቢ በንጉስ ጆን ላይ ባሏቸው ቅሬታዎቻቸው ላይ ለመወያየት እና መፍትሄ ለመስጠት ተሰባስበው ታዩ፡፡ በእርግጥ በዚያ ቦታ ላይ የተሰባሰቡት ለንጉስ ጆን እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ነበር፡ አምባገነናዊ የሆነ አሰራርዎን ያቁሙ ወይም ደግሞ ከአማጺያን ጋር የእርስ በእርስ ጦርነት ለማካሄድ እራስዎን ዝግጁ ያድርጉ የሚል ነበር፡፡
ጆን ስምምነት ለማድረግ ዝግጁ አልነበሩም፡፡ ይልቁንም በቅርቡ ፈረንሳይን መውረራቸውን ተከትሎ በደረሰባቸው አሳፋሪ ሽንፈት በመበሳጨት ላይ ነበሩ፡፡ ተራው ህዝብ ለጆን ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ወታደሮች የገንዘብ ክፍያ ዕዳ እንዲከፍሉ እንዲሁም የውትድርና አገልግሎት ላለመስጠት የመሬት ከበርቴዎች ገንዘብ ይከፍሉ ነበር፣ ወይም ለወታደራዊ አገልግሎት ወታደር ያቀርቡ ነበር፡፡ ከፈረንሳይ ንጉስ ጋር የንጉስ ጆንን ጥላቻ በመከተል አብረው ጥላቻ ውስጥ ለመግባት እና ለውጊያው ድጋፍ መስጠት አልፈለጉም፡፡ የእንግሊዝ ተራ ሕዝቦች ለጆን ወታደራዊ ጀብድ ድጋፍ ላለመስጠት መፈለጋቸውን ተከትሎ ንጉስ ጆን የጭቃ ጅርፋቸውን ማጮህ እና መበሳጨት ጀመሩ፡፡ እንደዚሁም ደግሞ እ.ኤ.አ በ1208 ከሮማ ጳጳስ 3ኛ ጋር በነበራቸው ችግር ምክንያት የንጉስ ጆን የድርድር አቋምም እየተዳከመ እና እየተሸረሸረ መጣ፡፡ በጳጳሳት ሹመት ላይ ጣልቃ የመግባት እና እና በቤተክርስቲያን ገንዘብ ላይ ጣልቃ የመግባት ሁኔታ እ.ኤ.አ በ1209 ከጳጳሳት ጋር የግንኙነት ችግርን ፈጠረ፡፡
እ.ኤ.አ ሰኔ 1215 በሩኒምድ ላይ የታዬው ተራው አማጺ ህዝብ ደስተኛ የካምፕ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ከአንድ ወር በኋላ ለንደንን በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ፣ እናም ታላቅ የሆነ መደራደሪያ በእጃቸው እንዳለ አረጋገጡ፡፡ በተራው ህዝብ የተረቀቁ አንቀጾች እንዳሉ እና በአሁኑ ጊዜ የሚፈለገው የንጉስ ጆን ፊረማ እንዲያርፋባቸው ነበር፡፡ ጆን ነገሮችን ሊያወሳስቡ እና ሊያታልሉ የሚችሉበት መንገድ አልነበራቸውም፡፡ ንጉስ ጆን ምንም ዓይነት ትኩረት በሌለው መልኩ የንጉሳዊ ማህተማቸውን በማኛ ካርታ ላይ በማሳረፍ እ.ኤ.አ ሰኔ 15/12115 ስምምነቱ ተፈጸመ፡፡ በዚህምመሰረት ጆን ሊያደርጉት የነበረውን የእርስ በእርስ ጦርነት በመተው ካመጹት ተራ ህዝቦች ጋር ሰላምን በማውረድ ታማኝነታውን እንደገና ለመመለስ በቁ፡፡
ንጉስ ጆን የማግና ካርታን ስምምነት ቢፈርሙም እንኳ የህጉን ዋና ባህሪያት በውል ተገንዝበው እና አጢነው ያለምንም ሰይጣኒያዊ ባህሪ እና ዕኩይ አስተሳሰብ ለመተግበር የሚያስችል ተነሳሽነት አልነበራቸውም (አንቀጽ 63ን ልብ ይሏል)፡፡
በሳምንታት ጊዜ ውስጥ የማግና ካርታ ዉጤታማነት ግልጽ እየሆነ መጣ፡፡ ጆን በተለዬ መልኩ የማግና ካርታን ስምምነት ወደ ተግባር ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት እራሳቸውን ያስጨንቁ ጀመር፡፡ ስለ ህገ መንግስት ማስፈጠም የሚናገረው አንቀጽ 61ን በተለየ መልኩ አስቸጋሪ ሆኖ አገኙት፡፡ በዚያ አንቀጽ ላይ የንጉሳውያንን የተጠራቀመ ስልጣን አሳልፈው የሰጡትን ያህል ተሰማቸው፡፡ ተራዎቹ ሰዎች እራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው ከመካከላቸው 25 የሚሆኑትን በመምረጥ የሰጠናቸውን ሰላም እና ነጻነቶች በሙሉ አቅማቸው እና ኃይላቸው እዲያረጋግጡ እና ለተፈጻሚነታቸውም ክትትል እንዲያደርጉ በማለት ጆን በጥርጣሬም ቢሆን እየኮመዘዛቸው ተቀበሉ፡፡ ጆን በተራ ህዝቦች ቁጥጥር እና ክትትል ስር እንዲሆኑ እራሳቸውን ዝግጁ አደረጉ፡፡ በተራ ህዝቦች የተዘጋጀው አንቀጽ 61 ታላቅ የሆነ ብልሀት የታከለበት ነበር፡፡ ምክንያቱም ጆን በሳር ውስጥ ያለ እባብ መሆናቸውን ያውቁ ነበርና ነው፡፡
ጆን አላዘኑም፡፡ ይልቁንም እ.ኤ.አ በ1215 የበጋ ወቅት የማግና ካርታ ሕግ ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ለጳጳሱ መልዕክት ላኩባቸው፡፡ በማመጽ ለንደንን ከበው ይዘዋት የቆዩት ተራዎቹ ሰዎች ጆን የማግና ካርታን ሕግ ተግባራዊ ካላደረጉ በስተቀር ለንደንን አንለቅም በማለት ተቃውሟቸውን አሰሙ፡፡ እ.ኤ.አ ነሀሴ 1215 ጳጳስ ኢኖሰንት 3ኛ “የጳጳሱ መግለጫ“ በሚል ርዕስ ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ በመጻፍ የማግና ካርታን ህገወጥነት የሚያሳይ እና ትክክለኛ ያለመሆን እንዲሁም ይህ ድርጊት የንጉሳውያን ቤተሰቦችን መብት ለታላቅ ጉዳት የሚያጋልጥ መሆኑን እና ይህ ድርጊትም ለእንግሊዝ ህዝብ ታላቅ አሳፋሪ ነገር እንደሆነ በመግለጽ ይህም መቸውንም ጊዜ ቢሆን ተፈጻሚነት እንደማይኖረው እና መሰረዝ እንዳለበት የሚያስጠነቅቅ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ መስከረም 1215 በንጉስ ጆን እና በተራው ህዝብ መካከል የእርስ በእርስ ጦርነት ተጀመረ፡፡ እንደተለመደው ሁሉ ጆን ተራዎቹን ህዝቦች ለመውጋት በማሰብ ቅጥረኛ ተዋጊዎችን ቀጠሩ፡፡ ተራዎቹ ህዝቦች በበኩላቸው የፈረንሳይ አልጋወራሽ የነበሩትን በመጋበዝ ወደ እንገሊዝ መጥተው በዙፋኑ ላይ እንዲቀመጡ እና ንጉስ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረቡ፡፡ እ.ኤ.አ በ1216 ፈረንሳዮች እንግሊዝን ወረሩ፡፡ በዚያ ጦርነት ወቅት ጆን በተቅማት በሽታ ምክንያት ህይወታቸው አለፈ፡፡
ሄንሪ 3ኛ በ9 ዓመታቸው ጆንን በመተካት በዙፋኑ ላይ ተቀመጡ፡፡ እ.ኤ.አ ጥቅምት 1216 የተሻሻለው የማኛ ካርታ ሰነድ እንዲወጣ እና የንጉሱን ፈቃደኝነት በመሳብ የተራ ህዝቦችን ሀሳብ ደጋፊ እንዲሆኑ ጥረት ማድረግ ጀመሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1217 ፈረንሳዮችን ከእንግሊዝ ካባረሩ በኋላ ሌላ የተሻሻለ የማግና ካርታ ሰነድ ተዘጋጅቶ ቀርቦ ነበር፡፡ ሄንሪ 18 ዓመት ከሞላቸው በኋላ እ.ኤ.አ በ1297 ንጉስ ኤድዋርድ 1ኛ ያዘጋጁትን እና በሰነዱ ላይ የነበረውን ጠቃሚ ነገር በማካተት እንዲታተም አደረጉ፡፡
የ1215 የማኛ ካርታ ሰነድ ውስጥ ያለው ነገር ምንድን ነው?
የማግና ካርታ ዝግጅት ለእንግሊዝ ህዝቦች ነጻነት እና ርትዕ ርቆ የሚያስብ ታላቅ ዕይታ የተንጸባረቀበት ልዩ የሆነ ሰነድ ነው፡፡
ይህ ሰነድ ከመሬት የባለቤትነት ጥያቄ ጀምሮ አስከፍትህ ስርዓቱ፣ ስለግብር አከፋፈሉ (መሬትን ለመጠቀም በየጊዜው የሚደረግ ክፍያ) እንዲሁም ከበርካታ ወንዞች ዓሳን እስከማስወገድ እና በርካታ ሚዛኖችን ደረጃ እስከመስጠት፣ ወዘተ ድረስ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት እንዲካተቱ ተደርጎ የተዘጋጀ ሰነድ ነበር፡፡
በጣም ታዋቂ ከነበሩት አንቀጾች መካከል የማግና ካርታ ሰነድ (አንቀጽ 1) የእንግሊዞችን ነጻነት ዘርዝሮ የሚያቀርብ እና እስከ ዛሬም ድረስ በተለያዩ ዘመናዊ ሕገ መንግስቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ውሎች እና ስምምነቶች ላይ ጉልህ ድርሻን በመያዝ የቀጠለ መሆኑን ያመላክታል፡፡
እ.ኤ.አ በ1215 የማኛ ካርታ ላይ ንጉስ ጆን ለሁሉም ዓይነት ነጻነቶች ዕውቅና እንደሚሰጡ እና ለመቀበልም ዝግጁ እንደሆኑ ሰነዱ እጅግ በጣም ጠቃሚ እና ልዩ እንደሆነ እና በማንኛውም የዕድሜ ክልል ላይ ላለ ዜጋ ሁሉ ጠቃሚ እንደሆነ ግልጽ አድርገው ነበር፡፡ በተለይም በሚከተሉት አንቀጾች ላይ ስምምነትን አድርገው ነበር፣
በእራሳቸው በጆን ፈቃድ እና እምነት ወራሾቻቸውን ለዘላለም የመምረጥ የሚለውን የሰነድ እና ስለነጻነት የተጠቀሰውን እንደገና ማየት እና መመርመር (አንቀጽ 1)፣
በእራሳችን የመንግስት ምክር ቤት እስካልተወሰነ ድረስ ማንኛውንም ግብር የመጣል ድርጊት እንዲቆም (አንቀጽ 12)፣
የተለመዱ የህግ ችሎት ስርዓቶች እንዲካሄዱ የተለዬ ነገር ማድረግ፣ ስለሆነም የእኛን የፍርድ ቤት አሰራር ሳይከተሉ በአንድ በተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ እንዲታዩ ሊደረግ ይችላል (አንቀጽ 17)፣
ለትንሽ ጥፋት ሁሉ ነጻ በሆነ ሰው ሁሉ ላይ የገንዘብ ቅጣት መጣል እንዲቆም… (አንቀጽ 20)፣
በዘውዱ እየታዘዙ በህዝቦች ላይ ችግርን እና መከራን የሚያዘንቡት ሕግ አስፈጻሚዎች፣ መለስተኛ ሕግ አስፈጻሚዎች፣ በጥርጣሬ የሞተን ሰው የአሟሟት ሁኔታ የሚመረምሩ ሰዎች እና የፍርድ ቤት ኃላፊዎች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ (አንቀጽ 24)፣
መለስተኛ ሕግ አስፈጻሚዎች እና የፍርድ ቤት ኃላፊዎች ከተራው ህዝብ ዘንድ የሚወስዱትን የበቆሎ እና ሌሎችንም ምርቶች ወዲያውኑ ገንዘብ ሳይከፍሉ ከመውሰድ እንዲታቀቡ (አንቀጽ 28)፣ ወይም ደግሞ የማንኛውንም ነጻ የሆነ ሰው ፈረስ ወይም ጋሪ ከተጠቀሰው ነጻ ሰው ፈቃድ ውጭ መውሰድ እንዳይችሉ (አንቀጽ 29)፣ ወይም ደግሞ ለቤተመንግስቶቻችን ለሌላ አገልግሎት ሲባል የሌላ ሰውን እንጨት ከመውሰድ መታቀብ (አንቀጽ31)፣
አንድ ነጻ የሆነ ሰው ምንም ዓይነት ከፍትህ አካል የመጥሪያ ወረቀት ሳይደርሰው በፖሊስ ወይም በማናቸውም አስገዳጅ ኃይል ተይዞ ወደ ህግ አካል እንዲቀርብ ሲደረግ የቆየው አሰራር እንዲቋረጥ (አንቀጽ 34)፣
አንድ የሕግ ኃላፊ በእራሱ ፈቃድ እና ስልጣን ታማኝነት ያለው የምስክርነት ቃልን የሚሰጥ እንዳይቀርብ በማድረግ አንድን ሰው በመመደብ በፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲያስረዳ ሲደረግ የቆየው አሰራር ክልክል ነው (አንቀጽ 38)፣
ከሕግ አግባብ ውጭ ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ በቀጥጥር ስር አውሎ ወደ እስር ቤት ማስገባት፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ንብረትን መውረስ፣ ህገወጥነት ድርጊትን መፈጸም፣ ማንኛውንም ነጻ የሆነ ሰው ማውገዝ ወይም ደግሞ ከሕግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ ምንም ዓይነት ወንጀል የሌለበትን ዜጋ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ወይም ለሀገሪቱ ሕግ ተገዥ ያለመሆን ዓይነት የአሰራር ድርጊቶች እንዲቆሙ (አንቀጽ 39)፣
ፍትሕን፣ መሸጥ፣ መካድ ወይም ደግሞ መብትን ወይም ፍትሕን ሆን ብሎ ማዘግየት እንዲቆም (አንቀጽ 40)፣
ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ የሆነ ሁሉ ከሀገሪቱ ግዛት የመውጣት እና በደህና ወደ ሀገሩ የመመለስ መብቱ አስተማማኝ በሆነ መልኩ እንዲጠበቅለት (አንቀጽ 42)፣
የሀገሪቱን ሕግ እና የአሰራር ሂደቱን የማያውቁ እስካልሆኑ ድረስ የፍትህ ዳኞችን፣ መለስተኛ የሕግ አስፈጻሚዎችን፣ የሕግ ኃላፊዎችን ወይም ደግሞ የፍርድ ቤት ዳኞችን መሾም (አንቀጽ 45)፣
ሕገወጥ በሆነ መልኩ ወይም ደግሞ ከሕግ አግባብ ውጭ መሬት፣ ቤተመንግስት፣ ነጻነትን ወይም መብትን እንዲሁም ሌሎች ንብረቶችን ነጥቀው ወስደው ከሆነ በአስቸኳይ እንዲመልሱ እና ተገቢ የሆነ ካሳም እንዲከፍሉ ማድረግ (አንቀጽ 52)፣
ፍትሀዊ ባልሆነ መልኩ ወይም ደግሞ የሀገሪቱን ሕግ በተጻረረ ሁኔታ ሁሉም የቅጣት ከፍያዎች የሕግ አግባብን ባልተከተለ መልኩ ተጭነው ያሉትን ወይም ከሀገሪቱ ህግ በሚጣረስ መልኩ ሲፈጸም የቆየው ክፍያ እንዲቆም ከዚህ ቀደም የተፈጸሙት ሀግወጥ ክፍያዎችም ለባለመብቱ ተመላሽ እንዲደረጉ (አንቀጽ 55)፣
የማግና ካርታን ሕግ በተሳካ ሁኔታ ለማስፈጸም እንዲቻል ነጻ በሆነ ምርጫ አማካይነት 25 ሰዎች ተመርጠው ሁሉንም ዓይነት ስልጣን ተሰጥቷቸው የሕጉን አፈጻጸም እንዲመለከቱ፣ እንዲጠብቁ እና የተጎናጸፍናቸውን ሰላም እና ነጻነቶች ተግባራዊ ለመሆናቸው ክትትል እንዲያደርጉ ስምምነት መፈጸም (አንቀጽ61)፣
ከዚህም በተጨማሪ የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ ነጻነትን የማያጎናጽፉ ሀረጎችንም እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ ለምሳሌም ያህል በባሏ መሞት ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በሌሎች ሰዎች መሞት ምክንያት አንዲት ሴት አቤቱታ ብታቀርብ አቤቱታ የቀረበበት ሰው በቁጥጥር ስር አይውልም ወይም ደግሞ አይታሰርም (አንቀጽ 54)፡፡ አንዲት ባሏ የሞተባት ሴት ምንም ዓይነት ባል ሳይኖራት ለመኖር የፈለገች ከሆነ ባል እንድታገባ የሚያስገድዳት ምንም ዓይነት ኃይል የለም (አንቀጽ 8) ካገባች ግን ለነጉሡ ክፍያ ማረግ አለባት ፡፡ ከ600 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፈላስፋ የነበሩት ጆን ስታውርት ሚልስ እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር፣ “በተፈጥሮ ሕገ መንግስት ማንም ቢሆን ሴቶች ምንድን እንደሆኑ ወይም እንዳልሆኑ፣ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ወይም እንደማይችሉ ለመወሰን የሚሞክር ማንም ሰው ቢሆን በእኔ እምነት በማስረጃ ያልተደገፈ ግምት ነው እየተናገረ ያለው የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡ ሁልጊዜ እስከ አሁንም ድረስ ተፈጥሯዊ ባልሆነ ሁኔታ ግብታዊ እድገት እስከታሰበ ድረስ ተፈጥሯቸው በከፍተኛ ደረጃ በተሳሳተ መንገድ ከመሄድ እና ከመመራት ውጭ በተፈጥሯቸው ላይ ምንም ዓይነት አዲስ ዓይነት ነገር አይመጣም…“ የአሜሪካ ሴቶች ድምጽ የመስጠት መብታቸውን የተጎናጸፉት እ.ኤ.አ በ1920 ነው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሁለተኛው አስርት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ባለንበት በአሁኑ ጊዜ ሴቶች በምርጫ ድምጽ የመስጠት መብት የሌለባቸው ሀገሮች እስከ አሁን ድረስ አሉ፡፡
የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ ስለአይሁዶች የሚሊኒየሙን ታጋሽነት ባሳጣ መልኩ ደረጃ የሚያስይዝ ፍረጃም አቅርቧል፡፡ እንዲህ የሚል ድንጋጌን አስቀምጧል፣ “ማንም ከአይሁድ ሰው ምንም ዓይነት ነገር በብድር ቢወስድ እና ይህ ብድሩን የወሰደው ሰው ብድሩን ከመክፈሉ በፊት ቢሞት እና ብድሩን የወሰደው ሰው ወራሽ ቢሆን ለብድሩ ወለድ ሳይታሰብ የሚከፈል ይሆናል…አንድ ሰው ከአይሁድ የተበደረውን ብድር ሳይከፍል ቢሞት የሟቹ ሚስት የባሏን ውርስ የምትወስድ ሲሆን ምንም ዓይነት ብድር ሊከፈላት አይችልም…(አንቀጽ 10፣ 11)”
እ.ኤ.አ በ1215 የተዘጋጀው እና የጻደቀው የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ በመጀመሪያ ደረጃ ለህዝብ ሲሰጥ 63 አንቀጾችን አካትቶ የያዘ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ በጣም ጥቂቶቹ ሕጎች ብቻ የእንግሊዝ ሕግ አካል ሆነው ቀጥለዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1969 1,225 የሚሆኑ የማኛ ካርታን ህጎችን ከአንቀጽ 1፣ 9፣ 29 በስተቀር ሁሉንም በሚባል መልኩ ተፈጻሚነት እንዳይኖራቸው ሽሯቸዋል፡፡ እንደዚሁም እ.ኤ.አ በ1998 በተዘጋጀው የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ተተክተዋል፡፡
የማግና ካርታ ትሩፋት በእኔ ዕይታ፣
የበቁ ልሂቃን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች እና ሌሎችም እንደዚሁ ለ800 ዓመታት ያህል ስለማግና ካርታ የሕግ ሰነድ ጠቃሚነት እና አስፈላጊነት ላይ ክርክር ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ፡፡ የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ ለእንግሊዝ ህዝብ ወይም ደግሞ ለነጻው ተራ ህዝብ ፍትህን እና ፍትሀዊ ዳኝነትን አጎናጽፏን? ለመሬት ከበርቴ ጌቶቻቸው አቤቱታ ሲያቀርቡ ለነበሩት ነጻ ላልሆኑት ገበሬዎች የሕግ ሰነዱ ጠቃሚነት ነበረውን? የማግና ካርታ ሕግ በሕግ አግባብ በዳኝነት የመታየት መብታቸውን አጎናጽፏቸው ነበርን? የማግና ካርታ ሕግ የሕግ የበላይነትን መርሆዎች በማጠናከር የሕግ የበላይነትን አስገኝቶ ነበርን? ሰነዱ የሕግ የበላይነትን ተቋማዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎ ነበርን? በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመንግስት እና በዜጎች መካክል የሕገ መንግስት ማዕቀፍ (የማህበረሰብ ስምምነት) ስምምነት እንዲኖር አስችሎ ነበርን? ያ የሕግ ሰነድ የግለሰብ ነጻነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ አስችሏልን? በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ ያሉት ማለትም ንጉሶች እና ንጉሳዊ ቤተሰቦች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ፕሬዚዳንቶች፣ የምክር ቤት/ኮንግረስ አባላት፣ የሕዝብ ተወካዮችን፣ ወዘተ… ጨምሮ በሀገሪቱ ባለው የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግስት እንዲገዙ የሚያስችሉት የሕግ መርሆዎች ተቋማዊ እንዲሆኑ አስችሏልን?
በዚህ ጉዳይ ላይ ምሁራን የማይስማሙበት ቢሆንም የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ ለአሜሪካ ሕገ መንግስት አርቃቂዎች (1787) እንደ ዋና እርሾ ሆኖ ያገለገለ ከመሆኑም በላይ እንደዚሁም የሰብአዊ መብት ደንጋጌ [አስርቱ ትዕዛዛት] በ(1791) ሲረቀቁ በግብዓትነት በማገልገል የመንግስትን ስልጣን በዘፈቀደ ከህግ አግባብ ውጭ መጠቀም እንዳይቻል በማድረጉ ሁኔታ ጉልህ ድርሻን አበርክቷል፡፡ ከአፍጋኒስታን እስከ ዙምባብዌ ሁሉም ሀገሮች በሚባል መልኩ እ.ኤ.አ በ1948 በተፈረመው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድንጋጌ/Universal Declaration of Human Rights (UDHR) ሰነድ ላይ የማኛ ካርታ አሻራ እና መንፈስ ተንጸባርቆበታል፡፡ ኤሎኖር ሩዝቬልት የUDHRን ሰነድ አርቃቂ ኮሚቴ በሚመሩበት ጊዜ ለሁሉም ህዝቦች እና ሀገሮች አንድ ዓይነት መስፈርትን በማዘጋጀት እኩልነትን፣ ክብርን እና መብትን በመተግበር ስኬትን መጎናጸፍ እንደሚቻል ወይዘሮ ሩዝቬልት ህልም ታይቷቸው ነበር፡፡ ከእርሳቸው ጋር እኔም እስማማለሁ፡፡ የኢትዮጵያ መብቶች፣ የአሜሪካ መብቶች፣ የእንግሊዝ መብቶች፣ የቻይና መብቶች፣ የግብጽ መብቶች… በሚለው ነገር ላይ ፍጹም አልስማማም…የሰብአዊ መብቶች አሉ በሚለው ላይ ብቻ እምነት አለኝ፡፡
ለእኔ በሙሉ ልብ እና በጽናት ከቆመ የኢትዮ-አሜሪካዊ የሕገ መንግስት የሕግ ባለሙያ እና ልሂቅ ማግና ካርታ ከፍተኛ የሆነ አንጸባራቂ አሻራ አለው የሚል አምነት አለኝ፡፡ ማግና ካርታ የመንግስት ተጠያቂነት እና ግልጸኝነት ለሚሉት ለሁለቱ መንታ መርሆዎች ተግራዊነት በጣም አስፈላጊ የሆነ የሕግ ስርዓት ያለው ሰነድ እንደሆነ ግንዛቤ አለኝ፡፡ ስልጣንን የያዙ ኃይሎች ለሚፈጽሟቸው ጉድለቶች እና ህጸጾች በሀገሪቱ ባለው የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግስት ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ በገዥዎች እና በተገዥዎች መካከል ባለው ግንኙነት በተወሰኑ የሕግ ማዕቀፎች የሚቀነበብ ነው፡፡ ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ ማንም በስልጣን ላይ ያለ ባለስልጣን የዜጎችን ህይወት ሊያጠፋ ወይም ደግሞ ንብረት ሊወርስ አይችልም፡፡ ስልጣናቸውን በዘፈቀደ በመጠቀም የዜጎችን ሰብአዊ መብት ለመደፍጠጥ እና የግለሰብ ነጻነቶችን ከአደጋ ለመጠበቅ እና ስልጣናቸውን በመጠቀም በሙስና የበከቱትን ባለስልጣኖች ከመቅጽበት ከስልጣናቸው ለማስወገድ እና በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማድረጉ ረገድ የማኛ ካርታ ሕግ በታሪክ የመጀመሪያው ሕግ እንደሆነ አምናለሁ፡፡
በ19ኛው ክፍለ ዘመን በተለያዩ 4 አጋጣሚዎች የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊሊያም ግላንድስተን የማግና ካርታን ህግ በማስመልከት እንዲህ የሚል ምልከታን አድርገው ነበር፣ “የእንግሊዝ ሕገ መንግስት ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ከተመሰረተ ተራማጅ ታሪክ ማህጸን ውስጥ አድጎ እና ዳብሮ እንደተገኘ ሁሉ የአሜሪካ ህገ መንግስትም እጅግ በጣም የሚደንቅ እና በአንድ ወቅት ጭንቅላት ባለቸው ሰዎች ለህዝቡ ጠቀሜታ ሲባል ተዘጋጅቶ የቀረበ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡“
እንደዚሁም ሁሉ እንከን ያለበትን ሕገ መንግስት አይነ ስውር የሆነውን ወደ ባርነት የቀየረውን ሕገ መንግስት ያረቀቀው እና ወደ ተግባር እንዲገባ ያደረገውም ልዩ የሆነው የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደሆነ የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም፡፡
ነጻነት የሚለው የእኔ አመለካከት በጣም ቀላል የሆነ ነገር ነው፡፡ ነጻነት መንግስት ከመፈጠሩ በፊት የነበረ መሆኑን አምናለሁ፡፡ መንግስት መብቶችን እና ነጻነቶችን ለዜጎች ይሰጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ መንግስት እራሱ የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን ዋና ስራውም የህዝቦችን፣ ህይወት፣ ነጻነት እና ንብረቶችን ለመጠበቅ ብቻ ሲባል የሚኖር ነው፡፡
በመንግስት እና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመግለጽ የሆነ የአገላለጽ ዘዴን በመጠቀም ሀሳቤን ለመግለጽ ሞክሪያለሁ፡፡ መንግስት ጌቶቹ ለሆኑት ለህዝቦች እንደጠባቂ ውሻ እንደሆነ አድርጌ እገነዘባለሁ፡፡ (የወንዶችን እና የሴቶችን ምርጥ ጓደኛ የሆነውን አካል በዚህ ምሳሌዬ ላይ ከተገለጸው እንስሳ ጋር በማመሳሰሌ ቅር አሰኝቸ ከሆነ ይቅርታ እንድታደርጉልኝ እጠይቃለሁ፡፡) የዚህ የጠባቂ ውሻ ብቸኛው ስራው የአለቆቹን ህይወት፣ ነጻነት እና ንብረቶች መጠበቅ ነው፡፡ ይህ ጠባቂ ውሻ በተፈጥሮው ከዳተኛ ወይም ደግሞ ለመክዳት የሚያስችል ባህሪ የተጠናወተው ስለሆነ በአለቆቹ የጭልፊት ዓይን እና አይነ ቁራኛ በአንክሮ ተመልካች ጌቶቹ ሁልጊዜ መታየት እና መጠበቅ አለበት፡፡ ይህ ጠባቂ ውሻ በአጭር ገመድ ተይዞ በተወሰነ ቦታ ላይ ብቻ እንዲቀሳቀስ ካልተገደደ በስተቀር በተፈጥሮ የተወረሰ፣ ሊቀየር እና ሊወገድ የማይችል የተፈጥሮ ባህሪን የተላበሰ ሁሉንም አካባቢ ካልዞርኩ እና ካልተቆጣጠርኩ የሚል ከንቱ ባህሪ አለው፡፡ በመንግስት የውሻ ጠባቂነት ሕገ መንግስቱ ማሰሪያ ገመድ ሆኖ ያገለግላል፡፡ ማሰሪያው ሰንሰለት ካጠረ ለውሻ ጌቶች ደህንነት እና አስተማማኝነት መልካም ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ይህንን ጉዳይ በማስመልከት ቶማስ ጃፈርሰን እንዲህ የሚል ምልከታን አድርገው ነበር፣ “መንግስት ህዝቡን መፍራት ሲጀምር ነጻነት አለ ማለት ነው፡፡ ህዝቡ መንግስትን መፍራት ሲጀምር አምባገነንነት ተንሰራፍቷል ማለት ነው፡፡“ መንግስት የሚኖረው ህዝቡን ለማገልገል እንጅ ሌላውን ተቃራኒውን ሁኔታ ለመፈጸም አይደለም፡፡ የውሻው ጌቶች በምንም ዓይነት ሁኔታ ውሻውን መፍራት የለባቸውም፡፡
ለዚህም ነው ሁሉም የመንግስት ባለስልጣኖች፣ መሪዎች፣ ተቋማት እና ማንም ስልጣኑን የሚተገብር ሰው ሁሉ የሀገሪቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ በሆነው ሕገ መንግስት ገመድ መታሰር እና ለሚሰራቸው ስራዎች እና ለሚፈጽማቸው ግድፈቶች እና ጉድፎች ሁሉ ተጠያቂ መሆን አለበት የሚባለው፡፡ ያ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግስት ሌላ ምንም ሳይሆን ዜጎች በዘፈቀደ ከህግ እግባብ ውጭ ህይወታቸውን እንዳያጡ፣ ስልጣንን በተቆናጠጡ ሰዎች እንዝህላልነት ነጻነታቸውን እንዳይገፈፉ እና ንብረታቸውን ከህግ አግባብ ውጭ እንዳያጡ የሚከላከለው ሕገ መንግስት ነው፡፡ የአሜሪካንን ሕገ መንግስት ካረቀቁት ታላላቅ ሰዎቸ መካከል አንዱ የሆኑት እና የታወቁት ጀምስ ማዲሰን በአንድ ወቅት እንዲህ የሚል ጽሁፍ አስፍረው ነበር፣ “ሰዎች መላዕክት ቢሆኑ ኖሮ ምንም ዓይነት መንግስት የሚባል ነገር አስፈላጊ አይሆንም ነበር፡፡“ እኔ ደግሞ እዲህ እላለሁ፣ መንግስት ወደ ከፋ እና ሰይጣናዊ ባህሪ ወዳለው አካልነት ባይቀየር ኖሮ የሰው ልጆች የተቻላቸውን ያህል የደግነት ባህሪያት ጥረትን በማድረግ ወደ መላዕክትነት ለመቀየር ከፍተኛ የሆነ ፍላጎትን ያሳዩ ነበር፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ሁለተኛው ፕሬዚዳንት ከነበሩት ከጆን አዳምስ ጋር እንዲህ ከሚለው ምልከታቸው ጋር በሙሉ ልብ እስማማለሁ፣ “ከሁሉም ወንዶች እና ሴቶች ጋ ታላቅ አደጋ አለ፡፡ ብቸኛው የነጻ መንግስት ህግ በስልጣን ላያ ያለ ማንም ወንድ ወይም ሴት የህዝብን ነጻነት አደጋ ላይ የሚጥል ስለሆነ እምነት ሊጣልበት አይችልም፡፡“
ፕሬዚዳንት ዊት. ዲ.ኢሰንሀወር እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር፣ “የሕግ የበላይነት ዕለት በዕለት ህይወታችን ምን ማለት እንደሆነ ለማወቅ በጣም ቀላሉ እና ግልጽ የሆነው መንገድ የህግ የበላይነት ባይኖር ኖር ሊሆን የሚችለውን ነገር ማስታወስ መቻል ነው፡፡“ እኒህ ታላቅ ሰው ይህንን ሲሉ በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ አህጉር እየተደረገ ያለውን ዕጣ ፈንታ አስቀድመው እየነገሩን ነበር ማለት ነውን?
እ.ኤ.አ ሀምሌ 28/2014 ፕሬዚዳንት ኦባማ ለወጣት የአፍሪካ መሪዎች በአንድ ከተማ ላይ በተደረገ ስብሰባ እንዲህ ብለዋቸው ነበር፣ “አንድ ሀገር የፈለገውን ያህል የተፈጥሮ ሀብት ይኑራትም አይኑራትም፣ እንዲሁም የፈለገውን ያህል የተማረ ሰው ይኑራትም አይኑራትም የሕግ የባላይነት መሰረታዊ ስርዓት ከሌለ የሲቪል እና የሰብአዊ መብቶች የማይከበሩ ከሆነ፣ ለህዝቡ ግልጽነትን በተላበሰ መልኩ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ህይወት ውስጥ ያለምንም ተጽዕኖ ተንቀሳቀስው የፈለጉትን ነገር ለማድረግ ታማዕኒነት እና ህጋዊ የሆነ የአሰራር ሂደት ከሌለ፣ መሰረታዊ የሆኑት የመናገር እና የመደራጀት መብቶች የማይከበሩ ከሆነ… አንድ ሀገር በስኬት ጎዳ ላይ ትራመዳለች ማለት እጅግ በጣም የመነመነ አስተሳሰብ ነው፡፡“
ኢትዮጵያ እንደሀገር እና እንደ ህዝብ ስኬታማ መሆን አለባት፡፡ አፍሪካ እንደ አህጉር ስኬታማ መሆን አለባት፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ የጨነገፈ መንግስት ለመሆን በመጨረሻው ጠርዝ ላይ ትገኛለች፡፡ ያለ ምዕራቡ ዓለም እርዳታ እና ብድር አንድም የአፍሪካ ሀገር አይደለም ለሳምንታት ለቀናት እንኳ መቆየት ሳይችል ፍርክስክሱ ሊወጣ እንደሚችል ምንም ዓይነት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያሉት የአፍሪካ ገዥዎች ህልውናቸው አለ ምክንያቱም ኪሳቸው በምዕራብ ሀገሮች ግብር ከፋዮች ዶላሮች ስለሚታጨቅላቸው ብቻ ነው፡፡ ይኸ ነው እንግዲህ ለመዋጥ በጣም የመረረ ክኒን እየሆነ ያለው!
ባለፉት አምስት ዓመታት የታማኝነት አለመኖር እና ጨለምተኛ በመሆን በአፍሪካ የህግ የበላይነት እና ወደ የብዘሁን ፓርቲ ፖለቲካ ሰላማዊ ሽግግር በማድረግ ዴሞክራሲ ይገነባል የሚለው ተስፋዬ እና ህልሜ እየተሟጠጠ ሄዷል፡፡ በየዕለቱ እራሴን እንዲህ እያልኩ በመጠየቅ ላይ እገኛለሁ፣ “የአፍሪካ ተስፋ ሊኖራት ይችላልን?“ ኢትዮጵያስ? የአፍሪካ ዕጣ ፈንታ በተስፋ መለምለም እና በተስፋ መመናመን መካከል ተንጠልጥሎ በመዋዠቅ ላይ ይገኛልን? ወደፊት ሊደረጉ በሚችሉት የእርስ በእርስ ጦርነቶች፣ የዘር ማጥፋት እኩይ ምግባሮች፣ የስርዓተ አልበኝነት ሁኔታ፣ ህገወጥ እና በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ድፍጠጣዎች አፍሪካ ልትወገዝ ትችላለችን? የአፍሪካ ብሩህ ተስፋ ተንጠልጥሎ ያለው በብዙሀን ሀገሮች ብድር እርዳታ ላይ ነውን? አፍሪካ እየተቆለለባት ባለው የዕዳ ተራራ ምክንያት የውጭ መዋዕለ ንዋይ አፍሳሾች በታደሙበት ከዓለም አቀፉ የዕዳ ቁልል ተራራ ስር ልትቀበር ትችል ይሆን? አፍሪካ ለቀሪው ዓለም የተመጽዋችነት፣ የሀዘን እና የትካዜ ማዕከል የመጥፎ ተምሳሌት ሆና ልትቀጥል ትችላለችን? አፍሪካ ችግር እና ምስቅልቅል ያለ ተስፋ በተንሰራፋበት ባህር ውስጥ ተንሳፍፋ ወይስ ደግሞ በተስፋየለሽነት ከውቅያኑ ውስጥ ሰምጣ ትጠፋለች? በአፍሪካ ባህሪ፣ በአፍሪካ አመክኖያዊ አዕምሮ፣ መንፈስ እና በአፍሪካ እርባናየለሽ ትረካ ይህም አፍሪካን ወደ መጥፎ 3 ነገሮች የሚያመራውን ማለትም ጨካኝነት፣ አምባገነንነት እና በሙስና ላይ የተደበቀ ነገር ይኖራልን? አፍሪካ ከዳንቴ ሰይጣናዊ የመድረክ ላይ የአስቂኝ ትወና ደረጃ ላይ ደርሳለችን? በአፍሪካ የምትኖሩ ሁሉ ተስፋችሁ ተሟጧል እና ተውት ማለት ነው ፡፡
የማግና ካርታን በዓል በደስታ በማክበሬ ምክንያት ጥያቄ የሚያነሱ እና ከዚያም ባለፈ ትችትን የሚያቀርቡ ከአንባቢዎቸ መካከል ጥቂት ሊኖሩ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ከሁሉም በላይ የነጮች ሰነድ ነው (እውነቱን መናገር አለብኝ!) የጭራቆቹ ቅኝ ገዥዎቹ እና የሌሎቸም የመሰረት ሰነድ ነው፡፡ የማግና ካርታ ሰነድ ለጥቁሮች፣ ለቡናማዎቹ፣ ለብጫዎቹ እና አዎ ለአረንጓዴዎቹ ህዝቦች ጠቃሚነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ከአረንጓዴ ህዝቦች በስተቀር ሌሎቹ የየእራሳቸውን ሕገ መንግስቶች እንዲመለከቱ በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በአቧራ በተጀቦነው ሕገ መንግስታቸው ውስጥ የሰው ልጆች ነጻነቶች መሰረታቸው ከየት እንደሆነ ልጠይቃቸው እፈልጋለሁ፡፡ ከነጻነት መብቶቻቸው ውስጥ የትኞቹ ለመንግስቶቻቸው ሰለባ እንደሆኑ ለማወቅ በጣም ደስ ይለኛል፡፡
ኤሊ ዊሰል እንዲህ ብለው ነበር፣ “በእርግጠኝነት ማንም ሰው ቢሆን ያለ ሕልም ሊኖር አይችልም፣ እንዲሁም ካለ ተስፋ ሊኖር አይችልም፡፡ ሕልሞች ያለፈውን የሚያንጸባርቁ ከሆነ ተስፋ ደግሞ የወደፊቱን ያመላክታል፡፡” ስለሆነም ስለ ተስፋ መንገድ ለማለም ምርጫ አድርጊያለሁ – ነጻነትን፣ ፍትህ እና እኩልነትን ለማራመድ እንዲቻል ብቃት ባለው እና ነጻ የሆነ የዳኝነት ስርዓት እና የህግ የበላይነት መኖር– ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ አህጉር የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማስወገድ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡
በመላ አህጉሪቱ ውስጥ የአምባገነንነት እና የግፈኞች የጨቋኝነት ደመና በየቦታው አጥልቶ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ያሉትን ተስፋ እና ህልሞች ማሳካት ቀላል የሚሆን አይደለም፡፡ የዚህ ዓይነት የሀዘን ድባብ በተንሰራፋበት ስሜት ነው እንግዲህ እንዲህ የሚሉትን የሄንሪ ፍራንስን የግጥም ስንኞች ማስታወስ ተገቢ የሚሆነው፡፡
ለውስን ዓመታት ለምንቆየው መሬት፣
እርስ በርስ ተባልተን ተቧጭቀን በሀሜት፣
ገሀነምን ሰርዞ ለመግባት ከገነት፣
በማጭበርበር መኖር በሸፍጥ በሀሰት፣
ይህችን ከሀዲ ዓለም እንዴት እናድናት?
እርስ በርስ ተባልተን ተቧጭቀን በሀሜት፣
ገሀነምን ሰርዞ ለመግባት ከገነት፣
በማጭበርበር መኖር በሸፍጥ በሀሰት፣
ይህችን ከሀዲ ዓለም እንዴት እናድናት?
የምጻት ቀን ደርሷል፣
ማዕበሉ ይነጉዳል፣
ወዠቦው ይጥላል፣
እሳቱ ያጋያል፣
ግፈኞችን ሁሉ ጥርግርግ ያደርጋል፡፡
ማዕበሉ ይነጉዳል፣
ወዠቦው ይጥላል፣
እሳቱ ያጋያል፣
ግፈኞችን ሁሉ ጥርግርግ ያደርጋል፡፡
ያልዘሩትን ሰብል በሸፍጥ ለማጨድ፣
አቀበቱን ወርዶ ከማሳው በመሄድ፣
ሀ ብሎ ለማጨድ እጆችን በመስደድ፣
የእርሱ ያልሆነውን የሌላ ለመውሰድ፣
በሰማይም ግፍ ነው አምላክም አይፈቅድ፣
በምድራዊም ዓለም በሰው አይወደድ፡፡
አቀበቱን ወርዶ ከማሳው በመሄድ፣
ሀ ብሎ ለማጨድ እጆችን በመስደድ፣
የእርሱ ያልሆነውን የሌላ ለመውሰድ፣
በሰማይም ግፍ ነው አምላክም አይፈቅድ፣
በምድራዊም ዓለም በሰው አይወደድ፡፡
የመሬት ደስታ ቀስ ብሎ ይጠፋል፣
ዝናዋ ኮስምኖ አቅሟ ይዳሽቃል፡፡
ዝናዋ ኮስምኖ አቅሟ ይዳሽቃል፡፡
ለውጥ እና መበሰበስ ሁለቱም ባንድ ላይ፣
ሰምና ወርቅ ሆነው ፍጹም ባደባባይ፣
ሰምና ወርቅ ሆነው ፍጹም ባደባባይ፣
እኔ እጥል እኔ እጥል ሁለቱም ሲላፉ፤
አንደኛው ለበጎ ሌላኛው ለክፉ፣
ምንም ባልጠበቁት ወድቀውት አረፉ፡፡
አንደኛው ለበጎ ሌላኛው ለክፉ፣
ምንም ባልጠበቁት ወድቀውት አረፉ፡፡
የለውጡ ሐዋርያ የዕድገቱ መሀንዲስ፣
ብስባሽን ቀብሮ መንፈስን የሚያድስ፣
ሀገርን ከካንሰር ከደዌ እሚፈውስ፣
የለውጥ ተሟጋች በህዝብ እሚወደስ፣
እኮ እሱ ማን ይሆን የልብን የሚያደርስ?
ብስባሽን ቀብሮ መንፈስን የሚያድስ፣
ሀገርን ከካንሰር ከደዌ እሚፈውስ፣
የለውጥ ተሟጋች በህዝብ እሚወደስ፣
እኮ እሱ ማን ይሆን የልብን የሚያደርስ?
ትዕዛዝን ተከተል አርማህንም አንሳ፣
መስዋት ሁን ላገርህ ወድቃ እስክትነሳ፣
ታገል ላህጉርህ ለህይወት ሳትሳሳ፣
ዓለምን ለውጣት ቃልህን ሳትረሳ፡፡
መስዋት ሁን ላገርህ ወድቃ እስክትነሳ፣
ታገል ላህጉርህ ለህይወት ሳትሳሳ፣
ዓለምን ለውጣት ቃልህን ሳትረሳ፡፡
በማግና ካርታ አስደሳች ትችት ላይ የሀዘን ስሜትን በሚያንጸባርቅ መልኩ እደዚህ ባለ ሁኔታ ላይ በመደምደሜ የተከበሩ አንባቢዎቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡
ከ800 ዓመታት በፊት የተጻፈውን የእንግሊዝ የነጻነት ሕገ መንግስት በአሁኑ ጊዜ እንኳ ህግ ያልሆነውን በነጻ ማክበር በመቻሌ እና ከ20 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ነጻነት፣ ፍትህ እና እኩልነትን ለማጎናጸፍ በሚል ተረቅቆ የጸደቀውን ሕገ መንግስት ለማክበር አለመቻሌ እንቆቅልሽ የሆነብኝ እና በጣም ያዘንኩበት የቆዘምኩበት ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ተረቅቆ ጸደቀ የተባለው ሕገ መንግስት ወረቀቱ የተጻፈበትን ዋጋ እንኳ ሊያወጣ አይችልም፡!
የኢትዮጵያን የማግና ካርታ የሕግ ሰነድ የማዘጋጃ ጊዜው አሁን ነው!!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም
የካቲት 24 ቀን 2007 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment