Translate

Tuesday, March 17, 2015

የህወሃት ታሪክ የመሻማት ሩጫ

ዘሪሁን ተስፋዬ
ላለፈው ሁለት ወር በህወሃት መሪነትና ባጋፋሪዎቹ ርብርብ የህወሃትን 40ኛ አመት ምስረታ ለማክበር በሚል የብዙ ሚሊዮን ብሮችን ወጪ የጠየቀ ታሪካዊ ጉብኝት፣ ስብሰባዎችና ተጓዳኝ ፈንጠዝያ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገሮች ሲካሄድ ሰንብቷል።Tigray people liberation front, tplf
ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ገነት፣ ለብዙሃን የህብረተሰቡ ክፍል ደግሞ ሲኦል እየሆነች ባለችው ሀገራችን ለአንድ ብሄር ድርጅት ምስረታ በአል በሚል በብዙ ሚሊዮን ብሮች ወጪ የተካሄደው ፈንጠዚያ በራሱ እጅግ አሳፋሪ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም።
ይህ ሰማእታትን ለመዘከር፣ የትግል ታሪክንና ተመክሮዎችን ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ. . . ወዘተ የሚሉ ማደናገሪያዎችን በመጠቀም፣ ህወሃት ውዥንብር ሊፈጥርበት ቢሞክርም፣ በቅጡ ላጤነው ግን የድርጅቱንና የመሪዎቹን ገድል እንደ ቀድሞ የሀገራችን የተወደዱ ጀግኖች፡ [ዳር ድንበር ሲያስከብሩ፡ለነጻነትና ለሰው ልጆች እኩልነት ሲታገሉ እንደወደቁት ሁሉ] እንዲወደሱ፣እንዲተረክላቸው፣ እንዲዘፈንላቸው፣ እንዲተረትላቸውም ለማባበልና ለማስገደድ የሚደረግ ሙከራ ነው። ባጭሩ የታሪክ ሽሚያ ነው።

ህወሃት ታሪክን የሚያይበት የተንሸዋረረ መነፅሩ ሁልጊዜ ከጊዜያዊ ጥቅሙ አንጻር እንዲመለከት ግድ ስለሚለው የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ መቶ አመት ዝቅ ያደረገበት ወቅት እንደነበረ ሁሉ፣ ከኢትዮጵያም አልፎ ለአለም ጥቁር ህዝቦች አኩሪ የነበረውን የአድዋ ድል ሲመቸው አንኳሶ፣ ሲመቸው የትግራይ ብቻ ድል አርጎ ሲለፍፍ፣ እንደ ዘንድሮ ደግሞ ከ40ኛ አመት ፈንጠዚያው ጋር ስለሚጋጭበት በመቀሌ፣ ቀኑ እንኳን ታውሶ እንዳይከበር ሲያደርግ የቆየ ድርጅት በመሆኑ የ 66ቱን የካቲትን ለመሻማት የሚያደርገው መውተርተር ሊገርመን አይገባ ይሆናል።
ቢሆንም ግን፣ 40ኛ የምስረታ በአል በሚል ወርሀ የካቲትን አስመልክቶ የሚደረግ የታሪክ ስርቆሽ፣ ብዙ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች አገራዊ ራእይ አንገበው ውድ ህይወታቸውን የከፈሉበትን ልፋት ብቻ ሳይሆን ትውስታውን ጭምር ዋጋ ሊያሳጣ የታቀደ እኩይ አላማ ያነገበ በመሆኑ ማጋለጥና እምቢኝ ሊባልበት የሚገባ ይመስለኛል።
የካቲት ሲባል፣ በማንም ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ የሚያጭረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር የተሳተፈበት፣ የቀድሞውን የፊውዳል ስርአት ከስሩ መንግሎ ለመጣል ቆርጦ የተነሳበትና “የየካቲት አብዮት” ተብሎ የሚታወቀው የ1966 ዓመተ ምህረቱ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ ነው።
ወቅቱ ተራማጆች ሀይላቸውን አሰባስበው ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች በመመስረት ግብታዊ በሆነ መንገድ የተቀሰቀሰውን አብዮት፣ አቅጣጫ በመስጠት ለዘመናት በጭቆና ቀንበር ሲማቅቅ ለነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍትህና ብልጽግናን እንዲጎናፀፍ ያስችላል በሚል የቀየሱትን የትግል መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ቀና ደፋ የሚሉበት ነበር።
ህወሃትን የመሰረቱትና አሁንም በአመራር ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ መሪዎች በወቅቱ በተማሪው እንቅስቃሴ ተሳታፊ የነበሩ ቢሆኑም፣ ከአብዛኛው የትግራይ ተራማጅ ሀይል ተነጥለው ከሀገራዊ ራእይ ይልቅ በጠባብ ብሄርተኝነት የታወሩ ስለነበሩ፣ ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶችን በመቀላቀል የትግሉ አካል ከመሆን ይልቅ ጎጠኛ ድርጅት መስርተው ወደ ትግራይ ያቀኑ ነበሩ።
ይሄ ብቻም አይደለም፣ ለተወሰነ ጊዜ ቢሆንም፣ በመሀላቸው አላማችን “የትግራይን ነፃ ሪፑብሊክ መመስረት” ነው የሚል ቅዠትም የነበራቸው አመራር አባላትም ነበራቸው። (አሁንም በአንዳንድ የህወሃት አመራር አባላት ዘንድ ኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የበላይነት ከተቀሙ ሊተገብሩት እንደሚያስቡ ሲያምኑ፡ እንደ ተስፋጽዮን መድሀኔ ያሉ ኤርትራውያን ምሁራን ደግሞ “ትግራይ ትግሪኝ” ከሚል ህልም ጋር ያዛምዱታል)
ከዚህም አልፎ፣ ከዚህም በመነሳት በትግራይ ምድር የነበሩ ህብረ ብሄራዊ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ “ታግሎ የማታገል” መብት ሊኖራቸው አይገባም በሚል እንኚሁኑ ኢትዮጵያንን በጦር ሀይል ጭምር ገፍቶ ያስወጣ የጠባብ ብሄርተኛ ቡድን ነው።
ይሄ ብሄርተኛ ቡድን በወቅቱ በተፈጠረ የታሪክ አጋጣሚ ደርግን አሸንፎ ኢህአዴግ የሚል ጭምብል ለብሶ ኢትዮጵያን ላለፉት 24 አመታት ሲያስተዳድር ቢቆይም፣ አነሳሱና አደረጃጀቱ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያተኮረ ስለነበር በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ያለው ቅቡልነት ውሱን መሆኑን ስለሚገነዘብ ወደ ታሪክ ተሻሚነት እንዲገባ ተገዷል።
ማናቸውም ስብስብ የተመሰረተበትን ወቅት አመት እየቆጠረ ማክበሩ ያለ ቢሆንም፣ የህወሃት 40ኛ አመት በሚል ሰበብ ግን ታሪካዊውን የ የካቲት1966 የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮትን፣የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት በሚል ተደራጅቶ በነበረ ቡድን ምስረታ ታሪክ ለማስረሳትና ብዥታ ውስጥ ለመክተት መሞከር ግን አስነዋሪ ነው።
ምንም እንኳን በ 66 የታገሉ፣ የተሰዉም ወገኖቻችን አገራዊ ራእያቸው በሚገባው ተግባራዊ ሊሆን ባይችልም ፣ በህይወት ያለነው፣ እኛ፣ግን ታሪካቸውንና ትዝታችንን ከብሄርተኛ ስርቆሽ ልንከላከልላቸው ይገባል።

No comments:

Post a Comment