“የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል”
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ በዝዋይ እስር ቤት ለወራት ስቃይ የተፈፀመበት
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ይባላል፤ አርሲ አርባ ጉጉ ተወልዶ አዳማ/ናዝሬት አድጎ፣ በ1998 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሲዮሎጂ ተመርቋል፡፡ በ2000 ዓ.ም በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር በሲኒየር ካልቸራል ኤክስፐርትነት የስራ መደብ እስከ ሚያዝያ 2003 ሰርቷል፡፡ ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በግልፅ ባልተረዳው ምክንያት የመንግስት ደህንነት ሀይሎች ተያዞ ለ23 ወር በዝዋይ እስር ቤት ከፍተኛ ስቃይ እየተፈፀመበት መቆየቱን ይናገራል፡፡ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም ከእስራት ሲለቀቅም አንድ ጊዜም እንኳን ፍርድ ቤት እንዳልቀረበ ለፍኖተ ነፃነት አስረድቷል፡፡ ከወጣት ተስፋዬ ተካልኝ መኮንን ጋር ያደረግነውን ቆይታ ተከታተሉን፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- ማን ነበር ያሰረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም በማለዳ ቤቴ ተንኳኳ፤ ተነስቼ ከፈትኩኝ፡፡ የማላውቃቸው ሰዎች ናቸው፡፡ “ና ውጣ፤ ልብስህን ለብሰህ ውጣ” አሉኝ፡፡ እኔ እናቴ ሞታ ሊያረዱኝ የመጡ መስሎኝ “ምነው ቤተሰብ ደህና አደለም? የተፈጠረ ችግር አለ?” አልኳቸው “ዝም ብለህ ናውጣ” አሉኝ፡፡ ልብሴን ለበስኩኝና ወጣሁ፤ አንቀው መኪና ውስጥ ከተው ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝና 3 ወር አሰሩኝ ከዛም አንድ አመት ከ8 ወር ዝዋይ ማረሚያ ቤት፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- መታሰርህን ለቤተሰብ ተናግረሀል?
ወጣት ተስፋዬ:- ለማንም ሰው እንድናገር አልፈቀዱልኝም፤ መስሪያ ቤቴ አልጠየቀኝም፣ ደሃዋ እናቴ ያለችው ናዝሬት ነው እሷም የምታውቀው ነገር አልነበረም፡፡ አባቴ አቶ ተካልኝ አስተማሪ ነበር አርባ ጉጉ ላይ ነው በ1985 ዓ.ም በነበረው ግጭት ነው የተገደለው፡፡ ማንም ሳይጠይቀኝ፣ፍ/ቤት ሳልቀርብ 23 ወር ታሰርኩ ልብስ ምግብም የሚያመጣልኝ ሰው አልነበረም፡፡ እናቴም መታሰሬን እንኳ አታውቅም መስሪያ ቤቴም ስኮላርሽፕ አግኝቷል፤ ወደ ውጪ ሃገር ሊማር ሊሄድ ነው የሚባል ነገር ስለነበረ አልጠየቁኝም፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የት ነበር ስኮላርሺፕ ያገኘኸው?
ወጣት ተስፋዬ:- የዛሬ 2 ዓመት አካባቢ የራስመስ ሙንደስን ስኮላርሽፕ አግኝቼ ነበር፡፡ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያና ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶክዮ ባሉ ምሁራን ሪኮመንድ ተደርጌ በጣሊያኑ ፌራሪ ዩኒቨርሲቲ ለመማር ተዘጋጅቼ ነበር፡፡ እንደተፈታሁ ሄጄ ስጠይቃቸው ብዙዎቹ ጓደኞቼ በጣም ደነገጡ፡፡ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ቅማል ተወርሬ … ባካችሁ ተውኝ … ምንም የሌለ ነገር የለም በጣም ተጎድቻለሁ፡፡ ከማረሚያ ቤት እንደወጣሁ እናቴ ጋ ስሄድ በጣም ደነገጠች፣ በሕይወት ያለሁ አልመሰላትም 23 ወር ሙሉ ከቤተሰብ ስለተለየሁ ግራተጋባች፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- በእስር ወቅት የደረሰብህ ድብደባና ማሰቃየት ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- ከፍተኛ ጉዳት ደርሶብኛል፡፡ በኤሌክትሪክ ጀርባዬ ላይ አቃጥለውኛል፣ በብልቴ ላይና በኩላሊቴ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስላደረሱብኝ ሽንት ችዬ አልሸናም፣ ሽንቴን መቆጣጠርም አልችልም፡፡ ኩላሊቴንም በጣም ያመኛል፡፡ ውሃ ውስጥ እየነከሩ በጣም ደብድበውኛል፡፡ አሁን ስናገር ያመኛል ብዙ አይነት የድብደባና የስቃይ መአት ደርሶብኛል፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደው ስታስበው ለእስር ያበቃህ ወይም ከመንግስት ጋር ያጋጨህ አጋጣሚ ነበር?
ወጣት ተስፋዬ:- መስሪያ ቤቴ ውስጥ የኢህአዴግ አባላት ነበሩ፤ በጣም ይከታተሉኛል፡፡ በቢ.ፒ.አር ላይ ስብሰባ በተደጋጋሚ ይጠራ ነበር፡፡ እኔም ሠራተኛ ላይ ተፅእኖ የሚያደርሱ ነገሮች ሲመጡ እኔ አልቀበልም በግልፅ እናገር ነበር፤ ሠራተኛውም እኔን ይደግፋል፡፡ ከመታሰሬ ጥቂት ጊዜ በፊት ገነት ሆቴል ስብሰባ ነበረን፡፡ በዛ ስብሰባ ላይ በጣም ተከራከርኩ፤ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር አቶ ፀጋዬ ማሞ የሚባሉ አሰልጣኝ፣ ከውጭ ጉዳይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲና ከንግድና ኢንዱስትሪም የመጡ ነበሩ ስማቸውን የማላስታውሳቸው ባለስልጣን ነበሩ፤ እዛ ላይ ሀሳብ አንስቼ ተከራክሬ ነበር፡፡ “የሠራተኛን ሀሳብ ዳይቨርት ያደርጋል” ይሉኝ ነበር፡፡ መቼም ግን ሀሳቤን በመናገሬ ይህን የመሰለ ስቃይ ይደርስብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ “አሸባሪ፣ ግንቦት ሰባት” እያሉ እኔ በማላውቀው ነገር 23 ወር ሙሉ ፍርድ ቤት ሳልቀርብ ያለምንም ፍርድ በርሜል ውስጥ ውሃ ጨምረው እያስተኙ አሰቃዩኝ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- እንደዚህ ያሰቃዩህ ምን አይነት ምንም አይነት መረጃ ሳያገኙ ነው?
ወጣት ተስፋዬ:- እኔን ጥፋተኛ የሚያስደርግ ምንም መረጃ አላገኙም፣ እኔን አስረው ወደ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ይደውሉ እንደነበር ይነግሩኝ ነበር፡፡ የኢሜይል አድሬሴንም ተቀብለው በርብረዋል ግን ምንም አላገኙም፡፡ እኔ ከማንም ጋር ሊንክ የለኝም ኢሜሌ ላይ የስኮላርሺፕ መልዕክት ካልሆነ በስተቀር ምንም የለውም፡፡ በመስሪያ ቤቴ ሪሰርቸር ነበርኩ፣ በሶሲዮሎጂ ነው የተመረኩት፡፡ ሉሲ የተገኘችበት ሣይት ላይ አፋር፣ ጋምቤላ ብዙ ሳይቶች ሰርቻለሁ፡፡ ከአለቆቼ ጋር ያለኝ ግንኙነት ሰላማዊ ነው እነሱ ናቸው ስኮላርሽፕ ሪኮመንድ ያደረጉኝ፡፡ አንደኛው ፕሮፌሰር 25 ዓመት ሙሉ እዚህ አገር ሰርቷል፣ አርዲን ያገኘው እሱ ነው፡፡ ሄነሪ ጊልበርት ይባላል፤ እሱም ሪኮመንድ አድርጎኛል፡፡ እኔ በጣም የሚቆጨኝ ደሃዋ እናቴ አረቄና ጠላ ሸጣ ነው ያስተማረችኝ ምን ብዬ ልንገራት እንደዚህ አትጠብቀኝም ከበደኝ፣ አሁን እሷ የምትሰጠኝ ምግብ ራሱ ደምደም አለኝ… (ረጅም ለቅሶ)፡፡ ልጄ በደህናው አይደለም የጠፋው ሞቷል ወይም መኪና ገጭቶታል ብላ ነበር የምታስበው፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- የከመታሰርህ በፊት ፖለቲካ ተሳትፎ ነበረህ?
ወጣት ተስፋዬ:- 1997 ዓ.ም የቅንጅት ደጋፊ ነበርኩ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነበርኩ በ97 የነበረው ሁኔታ ስንት ሰው አለቀ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነበር ታውቃላችሁ ምንም የምናደርገው ነገር አልነበረም ፡፡ በምርጫ አሸንፎ ሥልጣን መያዝ እንደማይቻል ተረዳሁኝ፡፡ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የማንም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አልሆንኩም፡፡ ከዚህ በኋላ ከምንም ነገር የተገለልኩ ሆኛለሁ፡፡ አንድ ብርጭቆ ሳትሰብር አሸባሪ ስትባል አስብ እንግዲህ አንድ ብርጭቆ እንኳን ሰብሬ አላውቅም ባለኝ እውቀት እንደውም ለእውቀት ነው የምጓጓው እውቀቴን አሳድጌ አገሬን ለመለወጥ ነው የማስበው እኔን ምንም የሚመለከተኝ ነገር የለም አሸባሪም ግንቦት ሰባትም አይደለሁም፡፡ስትደበደብ፣ ስትሰቃይ ያላደረከውን አድርጌያለሁ ትላለህ፤ በርሜል ውሃ ሞልተው ይከቱሃል ያሰቃዩሃል፡፡ አያሳዝንም ይሄ? እንዴት አድርጎ እዚህ አገር ይኖራል? 23 ወር ሙሉ አስረው ማሰቃየታቸው ሳያንስ የደረሰብኝን ስቃይ ለማንም ብናገር ቤተሰቦቼን በሙሉ እንደሚፈጁ አስጠንቅቀውኛል፡፡ እኔ ግን ከዚህ በላይ ሞት የለም ብዬ ነው የነገርኳችሁ፡፡
ፍኖተ ነፃነት፡- አሁን የት ነው የምትኖረው?
ወጣት ተስፋዬ:- መኖሪያ የለኝም … (ረጅም ለቅሶ)
ወጣት ተስፋዬ ተካልኝን ለመርዳት የምትፈልጉ አንባብያን ከፍኖተ ነፃነት መረጃ ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ (ምንጭ ፍኖተ ነጻነት)
No comments:
Post a Comment