Translate

Sunday, November 23, 2014

ኤሌክትሪክ በየሰዓቱ ይጠፋል “የእጃችንን አገኘን” -10 ቢ.ብር ሲባክን ዝም ብለናል


15 ቢ. ብር የፈጁትን የነፋስ ተርባይኖች፤ በ5 ቢ.ብር የውሃ ግድብ መተካት ይቻላል
ከ10 ቢ. ብር በላይ ሃብት በከንቱ ባከነ፤ እንደ ዘበት በነፋስ ተወሰደ ማለት ነው
በረሃብተኛ ድሃ አገር፣ ይሄ ሁሉ ብክነት እብደት ነው? ወንጀል ነው? ወይስ ምን?
ግን፤ ወይ ነገሬ አላልነውም፤ ወይ አብረን አጨብጭበናል፤ ወይ በዝምታ ፈቅደናል
የግድብ ግንባታን የሚቃወሙ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች፣ መጫወቻቸው አድርገውናል
ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ፤ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችን፤ “የድህነት ጠበቃ” ብለዋቸው ነበር

አገር    አመት    የነፋስ ተርባይኖች አቅም (ሺሜዋ)    በአመት ያመነጩት ሃይል (ሺ ጊዋሃ)    የተርባይኖቹ ብቃት
ጀርመን    2005    31    50    18%
ፈረንሳይ    2005    7.6    15    22%
ፖላንድ    2005    2.5    5.6    25%
ብሪታኒያ    2005    8.7    19    25%
ስፔን    2005    23    49    24%
ጣሊያን    2005    8    13.6    19%
አሜሪካ    2001    4    6.7    19%
በውሃ ግድብ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ጣቢያዎች ብቃትስ?    ከ40 – 50%
መንግስት ባለፈው ወር የተፈራረመውን ውል ጨምሮ፣ በነፋስ ተርባይን ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ሶስት ጣቢያዎችን ለማቋቋም 770 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ሃብት አፍስሷል። ቀላል ገንዘብ አይደለም። ከ15.4 ቢሊዮን ብር በላይ ነው። የሶስቱ ጣቢያዎች ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ተደማምሮ ስንት እንደሆነ ደግሞ ተመልከቱ – 325 ሜጋዋት ብቻ ነው። በቃ፡፡ እና …ለዚህ ነው ያ ሁሉ ገንዘብ እየፈሰሰ ያለው? በገንዘብ መጫወት ይሉሃል፣ ይሄ ነው።
ለንፅፅር ያህል የህዳሴ ግድብ፤ ከነፋስ ተርባይኖቹ ጋር የሚመጣጠን የማመንጨት “አቅም” ለመፍጠር ምን ያህል ገንዘብ እንደሚፈጅበት ማስላት እንችላለን። ከግልገል ጊቤ ጣቢያዎች ጋር፣ አልያም ከተከዜ ወይም ከጣና በለስ ግድቦች ጋርም ማነፃፀር ይቻላል። የግድቦቹ አማካይ የግንባታ ወጪ፣ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለአንድ ሜጋዋት 1.2 ሚሊዮን ዶላር አይደርስም። በዚህ ሂሳብ፣ ባለ 325 ሜጋዋት ማመንጫ ግድብ ለመገንባት፣ ቢበዛ ቢበዛ በአማካይ 390 ሚሊዮን ዶላር ቢፈጅ ነው (ማለትም፣ ከስምንት ቢሊዮን ብር በታች)። ለነፋስ ተርባይ ሲሆን ግን፣ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ!
ታዲያ፤ በአነስተኛ ወጪ፣ ከውሃ ሃይል ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ግድቦችንና ጣቢያዎችን መገንባት እየተቻለ፣ ያ ሁሉ ገንዘብ ለምን በነፋስ ተርባይን ይባክናል? እንዴ! ከሰባት ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ልዩነትኮ፣ በጣም በጣም ብዙ ነው። በየእለቱና በየሰዓቱ መብራት እየተቋረጠ ስራ የሚስተጓጎለው፣ ፋብሪካዎች የሚከስሩት፣ ጨለማ ውስጥ የምናድረው፤ የኤሌክትሪክ ማሰራጫና ማከፋፈያ ተቋማት በማርጀታቸውና በማነሳቸው ነው ተብሎ የለ! በከንቱ የሚባክነውን ገንዘብ፣ ለዚህ ለዚህ ማዋል ይቻል ነበር።
“መቼም፣ የበርካታ ቢሊዮን ብር ሃብት በከንቱ እንዲባክን አይደረግም፤ አንዳች አሳማኝ ምክንያት መኖር አለበት” የሚል ሃሳብ ይመጣላችሁ ይሆናል። ‘ሃሳብ’ ሳይሆን፣ ‘ምኞት’ ብትሉት ይሻላል – ለዚያውም የማይጨበጥ ምኞት። አንዳችም አሳማኝ ምክንያት የሚያቀርብላችሁ አታገኙም። በነፋስ ተርባይን አማካኝት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት፣ በጣም ከፍተኛ ወጪ እንደሚፈጅ…፣ በይፋ የሚታወቅ፣ በቁጥር የተሰላ፣ ማንም ጤናማ ሰው ሊክደው የማይችል ሃቅ ነው።
አስገራሚው ነገር፣ የነፋስ ተርባይኖች ችግር፣ ብዙ ገንዘብ መፍጀታቸው ብቻ አይደለም። ለካ አንዳንዴ የአገራችን ሰዎች “የባሰ አታምጣ” የሚሉት ወደው አይደለም! በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ነው። በብዙ ወጪ የተተከሉት የነፋስ ተርባይኖች፣ የታቀደላቸውን ያህል ውጤታማ አይደሉም። ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው አነስተኛ ነው። የአቅማቸውን 30 በመቶ ያህል እንኳ ብቃት የላቸውም። በውሃ ግድብ አማካኝነት ኤሌክትሪክ የሚያመነጩ ጣቢያዎች ግን፣ የአቅማቸውን 48 በመቶ በሚደርስ የላቀ ብቃት ኤሌክትሪክ እንደሚያመነጩ የኢትዮጵያ የበርካታ አመታት መረጃ ያሳያል። ይህን ለማረጋገጥና የአምና መረጃዎችን ለማየት፤ ብሔራዊ ባንክ በየሶስት ወሩ የሚያወጣቸውን ሪፖርቶች ተመልከቱ። አልያም ከአስር አመታት በፊት የነበረውን መረጃ፣ ከኤሌክትሪክ ሃይል ኮርፖሬሽን ሪፖርቶች ታገኛላችሁ።
በአጭሩ፣ የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችን እና የውሃ ግድብ ጣቢያዎችን ስናነፃፅር፣ የነፋስ ተርባይኖች ኪሳራና ብክነት እጥፍ ድርብ መሆኑን በማያጠራጥር መንገድ መገንዘብ እንችላለን። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፣ የግንባታ ወጪ በግማሽ ያህል ቅናሽ ነው። ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው ደግሞ ከነፋስ ተርባይኖች በ70 በመቶ ያህል ይልቃል።
እንዲያውም፣ ወደ ፊት የነፋስ ተርባይኖቹ ብቃት ይባስ እየቀነሰ መሄዱ አይቀርም። ለምን በሉ። አንደኛ ነገር፣ የነፋስ ተርባይኖች እድሜ በጨመረ ቁጥር፣ ብቃታቸው እየወረደ ይሄዳል። ሁለተኛ ነገር፣ ለነፋስ ተርባይኖች እጅግ በጣም ተስማሚ የሆኑ ነፋስ የሚበዛባቸውና የሚዘወትርባቸው ቦታዎች ናቸው አሁን ጥቅም ላይ የዋሉት። ወደ ፊት ተመሳሳይ ቦታ ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። እናም የነፋስ ተርባይኖች ብቃት ከ25 በመቶ በታች መውረድ አይቀርለትም።
የነፋስ ተርባይኖች ብቃት 30 በመቶ እንኳ መድረስ ያልቻለው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። በሁሉም የአውሮፓ አገራትና በአሜሪካ ጭምር፣ ላለፉት በርካታ አመታት በተጨባጭ የተመዘገበ መረጃ ነው። የነፋስ ተርባይን አፍቃሪ ተቋማት ራሳቸው የሚያቀርቡትን መረጃ ብቻ ልጥቀስላችሁ። የነፋስ ተርባይኖችን ለማስፋፋት መንግስታት ተጨማሪ ድጎማ መስጠት ይኖርባቸዋል እያለ ዘመቻ የሚያካሂደው የጀርመን ተቋም HSH NORDBANK፤ ባለፈው መስከረም ወር Sector Study WIND ENERGY በሚል ርዕስ ካቀረበው አመታዊ ሪፖርት የተወሰዱ ጥቂት መረጃዎችን እነሆ።
ከአመት በፊት በ2005 ዓ.ም፤ ጀርመን ውስጥ የሚገኙ ባለ 31ሺ ሜጋዋት የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች፣ 50ሺ ጊዋሃ ሃይል አመንጭተዋል ይላል ሪፖርቱ። ይህም ማለት የተርባይኖቹ ብቃት 18% ገደማ እንደሆነ ያረጋግጣል። የአሜሪካም ተመሳሳይ ነው። በ2001 ወደ አራት ሺህ ሜጋዋት የሚጠጋ አቅም ያላቸው የነፋስ ተርባይኖች በ19% የብቃት ደረጃ 7ሺ ጊዋሃ የኤሌክትሪክ ሃይል እንዳመነጩ፣ የአሜሪካ የኢነርጂ መስሪያ ቤት ገልጿል – እየተገባደደ ባለው የፈረንጆች አመት ባወጣው ሪፖርት።
የብሪታኒያ ትንሽ ይሻላል። የ8.7ሺ ሜጋዋት አቅም ያላቸው የነፋስ ተርባይኖች፣ በአመት ውስጥ ያመነጩት የሃይል መጠን 19 ሺ ጊዋሃ ነው። (ማለትም ተርባይኖቹ የሚሰሩት በ25% ብቃት ነው)። ምን አለፋችሁ? በየትኛውም የአውሮፓ አገር፣ በየትኛውም ጊዜ፣ የነፋስ ተርባይኖች ብቃት 30% ደርሶ እንደማያውቅ፤ HSH NORDBANK ያወጣው ሪፖርት ያስረዳል። ከተርባይኖቹ እድሜ ጋርም፣ ብቃታቸው ወደ ሃያ በመቶ ይወርዳል።
ነፋስ ተርባይኖች ብቃት፣ በአንዳንዶቹ አገራት ከ20 በመቶ ሊበልጥ የቻለው አንዳች ተአምረኛ ዘዴ ስለፈጠሩ አይደለም። በመሬት ላይ ሳይሆን በባህር ላይ የተተከሉ ተርባይኖችን ስለሚጠቀሙ ነው ልዩነት የተፈጠረው። ምድር ላይ ከሚተከሉት ተርባይኖች ይልቅ የባህር ላይ ተርባይኖች፤ በጥቂቱም ቢሆን የላቀ ብቃት አላቸው። እንዲያም ሆኖ፤ ብዙም ለውጥ የለውም። አንደኛ፣ የባህር ላይ ተርባይኖች ያን ያህልም የሚያስመካ ልዩነት አያመጡም። ሁለተኛ ነገር፤ ባህር ለሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ለመሳሰሉ አገራት፤ ትርጉም የለውም። ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ነጋ ጠባ የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖችና አጨብጫቢዎች ከሚለፍፉት ስብከት በተቃራኒ፤ የነፋስ ተርባይኖች ብቃት ውሎ አድሮ በተጨባጭ 20% ገደማ እንደሚሆን ለመግለፅ ፈልጌ ነው።
በውሃ ግድብ አማካኝነት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ጣቢያዎች ግን፣ ከብዙ አመታት አገልግሎት በኋላም በአማካይ 48 በመቶ ገደማ መሆኑን ደግሞ አትርሱ። ለዚህ ማረጋገጫ፣ ከኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽንና ከብሄራዊ ባንክ የ2006 ዓ.ም ሪፖርቶች በተጨማሪ፣ ሌላ መረጃ ትፈልጉ ይሆናል። Study on the Energy Sector in Ethiopia በሚል በጃፓን ኤምባሲ የተዘጋጀውን የጥናት ሰነድ መቃኘት ትችላላችሁ፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ በነበረው መረጃ መሰረት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ግድቦች በድምር “ባለ 670 ሜጋዋት” እንደነበሩ በማስታወስ፤ በአማካይ በአመት 2.84 ጊዋሃ ሃይል ያመነጩ እንደነበር ጥናቱ ይገልፃል። (የግድቦቹ ብቃት ከ48% በላይ ነበር ማለት ነው።) የአምና መረጃዎችን ብንመለከትም፣ ተመሳሳይ ውጤት እናገኛለን።
የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችና የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፤ ኤሌክትሪክ የማመንጨት ብቃታቸው እንዲያ የሚራራቀው ያለምክንያት አይደለም። የመኪና ሞተርን እንደ ምሳሌ በመውሰድ ልዩነቱን ለማሳየት ልሞክር። ሞተሩ የአቅሙን ያህል ለመስራት ነዳጅ ያስፈልገው የለ? የነፋስ ተርባይኖች፣ መንቀሳቀሻ ነዳጃቸው “ነፋስ” ነው። ለውሃ ግድብ ጣቢያዎች ደግሞ፤ ነዳጃቸው ውሃ ነው። እንዲህ የየራሳቸው “ነዳጅ” ቢኖራቸውም፤ የነዳጅ አጠቃቀማቸው ግን ይለያል። የነፋስ ተርባይኖች ነዳጃቸውን (ነፋስን) መቆጣጠርና ማጠራቀም አይችሉም። የነዳጅ መቆጣጠሪያና ማርሽ እንደ ሌለው መኪና ቁጠሩት – ለአቀበቱም ለቁልቁለቱም፣ ሲቆምም ሲጓዝም ነዳጁን ይጠቀማል። ነዳጅ ሲቋረጥበት፣ ከማጠራቀሚያ አውጥቶ መጠቀም አይችልም። ነዳጅ ሲያልቅበት በጀሪካን እስኪመጣለት ድረስ መኪናውን አቁሞ እንደሚጠባበቅ ሾፌር ማለት ነው። የውሃ ግድቦች ግን፤ የነዳጃቸው (የውሃ) መጠንን እየተቆጣጠሩ መልቀቅ፤ ብዙ የኤሌክትሪክ ሃይል በማያስፈልግበት ወቅትም ውሃውን ይዘው ማቆየትና ማጠራቀም ይችላሉ። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች፤ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት ብቃታቸው ከፍተኛ የሚሆነው በዚህ ዋና ምክንያት ነው።እዚህ ላይ፤ አንድ ቀላል ጥያቄ ቢነሳ አይገርምም። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች ብቃት በእጥፍ የሚበልጥ ከሆነ፤ ወጪያቸው ደግሞ በግማሽ ያህል ቅናሽ ከሆነ ለምንድነው የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎችን ለመገንባት ሃብት የሚባክነው? ወጪያቸው እጥፍ ነው፤ ብቃታቸው ደግሞ በግማሽ የወረደ መሆኑ እየታወቀ!
በነፋስ ተርባይኖች ምትክ 325 ሜጋዋት የሚያመነጭ ግድብ ቢገነባ ኖሮ፣ ወጪው በ7.6 ቢሊዮን ብር ያነሰ ይሆን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፣ የግድብ ሃይል ማመንጫ ብቃት 48% ገደማ ስለሆነ፤ በየአመቱ 1300 ጊዋሃ ሃይል ማመንጨት በቻለ ነበር። የነፋስ ተርባይኖች ግን፤ ወጪያቸው በእጥፍ ቢበልጥም፤ በየአመቱ የሚመነጩት ሃይል 800 ጊዋሃ ገደማ ብቻ ነው።ልዩነቱ እጥፍ ድርብ ነው። የነፋስና የግድብ ማመንጫ ጣቢያዎቹ “ባለ 325 ሜጋዋት” የሚል ስያሜ ቢለጠፍባቸውም፤ ወጪያቸውና ብቃታቸው በጣም ይራራቃል። የነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች፤ ወጪያቸው ከፍተኛ፣ ብቃታቸው ደግሞ ዝቅተኛ ነው። የውሃ ግድብ ጣቢያዎች ደግሞ ወጪያቸው ዝቅተኛ፣ ብቃታቸው ግን ከፍተኛ። እንዳያችሁት፣ “ባለ 325 ሜጋዋት” የተሰኙት የነፋስ ተርባይኖች በአመት 800 ሜዋሃ ገደማ ብቻ ነው ማመንጨት የሚችሉት። የዚህን ያህል የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨትማ፤ ባለ 190 ሜጋዋት የግድብ ማመንጫ ጣቢያ መገንባት በቂ ነው – ለዚያውም ወጪው 230 ሚሊዮን ዶላር አይሞላም – ከ5 ቢሊዮን ብር በታች መሆኑ ነው። እንግዲህ አስቡት፤ ይህችኑ የሃይል መጠን ለማመንጨት ነው ከ15 ቢሊዮን ዶላር በሚበልጥ ወጪ ለነፋስ ተርባይን ጣቢያዎች  እየፈሰሰ ያለው። በሌላ አነጋገር፤ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ሀብት በከንቱ እንዲባክን ተደርጓል። እብደት፣ ወንጀል ወይስ ምን? የጊዜ ጉዳይ እንጂ፤ በዚህ ብክነት ላይ የተሳተፉና የተባበሩ ሃላፊዎች ውሎ አድኖ ተጠያቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ እስከዚያው ግን መብራት በየሰዓቱ እየተቋረጠብን እንቀጥላለን፡፡ ለነገሩ፤ አስር ቢሊዮን ብር በከንቱ ለነፋስ ሲበተን እያየን ዝምታን የመረጥን ሰዎችስ፤ መብራት ሲቋረጥብን ቢውል ቢያድር ይገርማል፡፡ የእጃችንን ነው ያገኘነው፡፡

No comments:

Post a Comment