Translate

Tuesday, September 16, 2014

እነ አባዱላ ፓስፖርታቸውን ተቀምተዋል- ኦህዴድና ብአዴን ይጠይቃሉ፤ ህወሓት ይመልሳል

negereነገረ ኢትዮጵያ

ከአመታት በፊት የገዥው ፓርቲ አባል ሳይሆን በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይሰራ ነበር፡፡ 1997 ዓ.ም በኋላ ግን በዚህ አቋሙ አልቀጠለም፡፡ ‹‹አንዴ ቅንጅት ሌላ ጊዜ ደግሞ ኦነግ እያሉ ስም ሲለጥፉብኝ ‹ከዚህ ሁሉ!› ብየ ኦህዴድን ተቀላቀልኩ›› ይላል ካድሬው ለነገረ ኢትዮጵያ፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ጊዜያት ደመወዝና እድገት በእጥፍ ተጨምሮለታል፡፡ የትምህርት እድል ተሰጥቶታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኦህዴድም ሆነ ኢህአዴግ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በደል በቅርብ ርቀት ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡
ካድሬው እንደሚለው ከእነ አባዱላና መሰል ፖለቲከኞች ውጭ የኦህዴድ ካድሬዎች በፓርቲያቸው እምነት የላቸውም፣ በህወሓት በደል በእጅጉ ተማርረዋል፡፡ የ‹‹ብአዴኖችም ከእኛ የሚለይ ነገር የለውም፡፡ ተመሳሳይ ነው፡፡›› ይላል ካድሬው፡፡
በበርካታ ጉዳዮች ‹‹ፓርቲዬ›› ከሚለው ኢህአዴግ እንደሚለይ ቢገልጽም በአንድ ጉዳይ ግን ይስማማማል፡፡ ‹‹ጥያቄ የሚያቀርብ ካድሬ አንድም ኦነግ አሊያም የድሮው ቅንጅት አካል የነበረ ፓርቲ ወይንም ትምክተኛ ተብሎ ስም ይሰጠዋል፡፡ ኦነግ ወይንም ‹‹ቅንጅትነት/ትምክተኝነት›› ጥያቄ ማንሳት ከሆነ የኦህዴድ ካድሬዎች ሲገለጡ ኦነጎች ናቸው፡፡ ብአዴኖቹ ደግሞ እንደዛው ቅንጅት/ትምክተኛ ናቸው ማለት ነው››፡፡ በዚህ ጉዳይ ካድሬው የድሮው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ኦህዴድ ሲገለጥ ኦነግ ነው!›› በሚለው ይስማማል፡፡
ካድሬው ለነገረ ኢትዮጵያ እንደገለጸው በተለይ የብአዴንና የኦህዴድ ካድሬዎች በህወሓት ጫና ከመቼውም በላይ ተማርረዋል፡፡ ‹‹አዛዡም ናዛዡም ህወሓት ነው፡፡ ትጠይቃለህ፡፡ ስም ይሰጥሃል፡፡›› የሚለው የኦህዴድ ካድሬ፤ የኦህዴድና የብአዴን ካድሬዎችም ሆነ ባለስልጣናት ይህ ነው የሚባል ተጽዕኖ እንደሌላቸው ከተሞክሮው ይመሰክራል፡፡ ‹‹ብአዴንና ኦህዴድ ይጠይቃሉ፡፡ ህወሓት ይመልሳል፡፡ የብአዴንና የኦህዴድ ባለስልጣናት ካድሬዎቹ የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች እንኳን በራሳቸው መመለስ አልቻሉም፡፡ ህወሓት ብአዴንም፣ ኦህዴድም፣ ኢህአዴግም ሆኖ ሁሉም የሚጠይቀውን ጥያቄ ይመልሳል፡፡ እንዲያው እድል ተሰጥቷቸው የሁለቱ ፓርቲዎች ፖለቲከኞች ቢመልሱ እንኳ የህወሓት ተራ ካድሬም ቢሆን የሆነ ነገር ያስተካክላል፡፡ ኦህዴድና ብአዴን ብቁ አለመሆናቸውን ለማሳየት የሚያደርገው ነው፡፡››
ካድሬውን ‹‹ኢህአዴግን ምን የሚያሰጋው ይመስልሃል?›› በሚል ከነገረ ኢትዮጵያ ለቀረበለት ጥያቄም የመጀመሪያው ያደረገው ፓርቲው ውስጥ ያለውን ክፍፍል ነው፡፡ ‹‹አብዛኛው የኢህአዴግ ካድሬ እንደ እኔ ፓርቲው ያደርስብኛል ካለው አደጋ ለመዳን አሊያም ለገንዘብ የተቀላቀለ ነው፡፡ አያምንበትም፡፡ ሁሉም ቀን ነው የሚጠብቀው፡፡ ወደ ህዝብ ሲቀርቡ በመካከላቸው ችግር እንደሌለ ያስመስላሉ እንጅ የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች በመካከላቸው ከፍተኛ ቅራኔ አለ፡፡ ለምሳሌ ያህል በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ የኦህዴድ ካድሬዎችን አስቆጥቷል፡፡ እስካሁን ይመለስላቸው አይመለስላቸው ባላውቅም በወቅቱ እነ አባዱላ ፓስፖርታቸውን እንደተቀሙ ሰምቻለሁ፡፡ ይህ አንድ ቀን የሚፈነዳ ይመስለኛል፡፡››
ሌላው ይላል ካድሬው ‹‹ህዝብ በፓርቲው እምነት እንደሌለው ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ህዝብ ገንፍሎ የሚወጣ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ አሁን ህዝቡ ዝምታን መርጧል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ህዝብን ለማሳመን ወይንም ለማስተማር በሄድኩበት አጋጣሚ ከዝምታው በስተጀርባ ህዝብ ለፓርቲው ጥላቻ እንዳለው ለማየት ችያለሁ፡፡ በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና የተሰጣቸው ተማሪዎች ሰነዱን አቃጥለው ስለ ነጻነት ዘምረዋል፣ ፓርቲው አብጠልጥለዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደማመር አንድ ቀን ህዝብ ገንፍሎ የሚወጣ ይመስለኛል››

-- Ze-Habesha Website may contain advice, opinions, and statements of various information and content providers. The Website neither represents nor endorses the accuracy of information or endorses the contents provided by external sources. All blog posts and comments are the opinion of the authors.--

No comments:

Post a Comment