Translate

Thursday, September 11, 2014

2007 ወሳኝ የትግል ዓመት!!!

2007 ወሳኝ የትግል ዓመት!!!

Untitled g7
ሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት ለኛ ለኢትዮጵያዊያን በአብዛኛው በመጥፎ የሚታወስ ዓመት ነው። 2006፣ በመካከለኛው ምስራቅም ሆነ በአፍሪቃ በስደት ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ስቃይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት ዓመት ነበር። 2006፣ ቀደም ባሉ ዓመታት አገራቸዉን ለቅቀዉ የተሰደዱ ሳይደላቸው በርካታ አዳዲስ ስደኞች ከአገር ወጥተው በበረሃዎችን ቀልጠው፤ በባህር ሰጥመው ያለቁበት አሳዛኝ ዓመት ነው። 2006፣ ጥንቃቄ በተሞላበትና በተቆጠበ መንገድም ቢሆን የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ወገኖቻችን ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006፣ በአምቦ፣ በለቀምት፣ በጅማ በሀረር በርካታ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተገደሉበት፤ በአስር ሺዎች የሚገመቱት ደግሞ የታሰሩበት ዓመት ነው። 2006፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላ፣ በአዲስ አበባና አካባቢው በ100 ሺዎች የሚገመት ኢትዮጵያዊ የተፈናቀለበት ዓመት ነው። 2006 ቁጥራችው ቀላል ያልሆኑ የነፃነት ታጋዮች ከጎረቤት አገራት ታፍነው ወደ እስር ቤቶች የተጋዙበት ዓመት ነው። 2006 የንቅናቄዓችን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በጉዞ ላይ እያለ በትራንዚት አውሮፕላን ለመቀየር ባረፈበት በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ በየመን መንግሥት ወንበዴዎች ታፍኖ ለሸሪካቸው ህወሓት በህገወጥ መንገድ አስተላልፈው ለስቃይ እንዲዳረግ የተደረገበት ዓመት ነው። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ነው 2006 “ጥቁር ዓመት” የሚል ስያሜ ያገኘው።

ጭንቅላት የሚባል ነገር ያልፈጠረባቸው ድኩማን ሰላዮችና ፈንጋዮች የመጨረሻውን የመንግሥት ሥልጣን የያዙበትና ውሳኔያቸው “እሰረው፣ ክሰሰው፣ ግረፈው፣ ግደለው …” ብቻ የሆነበት ዓመት መሆኑ የ2006 ልዩ መታወቂያው ሆኖ ይቆይ ይሆናል። ይሁን እንጂ በ2006 ጨለማ ውስጥ የታዩ የብርሃን ጨረሮችም እንደነበሩና እንዳሉም መርሳት አይገባም።
በሁለት ሺህ ስድስት ዓመተ ምህረት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቸውም በላይ በህወሓት አገዛዝ አምርሯል፤ በሁለገብ ትግል የህወሓትን አገዛዝ ለመፋለም የቆረጡ ወገኖች ትብብር ተጠናክሯል። በ2006፣ ኢትዮጵያ ዉስጥም ከኢትዮጵያም ውጭም የንቅናቄዓችን የግንቦት 7 ድርጅታዊ መዋቅር ተጠናክሯል። በ2006፣ ከህወሓት አገዛዝ ጋር ያለው መፋጠጥ ከሯል። እነዚህ ሁኔታዎች 2007 አገራችን በለውጥ ማዕበል የምትናጥበት ዓመት ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ።
በአዲሱ ሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የግንቦት 7 አባላትና ደጋፊዎች ትልቁ ሥራ ድርጅታዊ አቅምን ማጎልበት ነው። በተለይ ወጣቶች በአምባገነን ሥርዓቶች ውስጥ ሕዝባዊ የትግል ድርጅቶችን እንዴት መመሥረት እንደሚቻል ማጥናት እና መፈተሽ ይኖርባቸዋል። ትናንሽ የግንቦት 7 ድርጅታዊ ቋጠሮዎች በመላው አገሪቱ መሠራጨት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች ትናንሽ ኢ-መደበኛ ስብስቦችን ቶሎ መፍጠር እና አደጋ ሲያጋጥም ቶሎ ማፍረስ መልመድ ይኖርባቸዋል። ይህንን ክህሎት ደግሞ በቀጥታ ከሌሎች አገራት ከመዋስ ሀገር በቀል ቢሆን ይመረጣል።
በሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የጽዋ ማኅበሮች፣ መድረሳዎችና ጀማዎች፣ የስፓርት ቡድኖችና ደጋፊዎች፣ የመንደር ደቦዎችና የቡና ተርቲቦች፣ ስም ያላቸውም፣ ስም የሌላቸውም ስብስቦች የግንቦት 7 አባላት መገናኛዎች ይሆናሉ። በ2007 የግንቦት 7 አባል መሆን የምርጥ ዜግነት ምልክት መሆኑ በስፋት ተቀባይነት የሚያገኝበት ዓመት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በ2007 በህወሓት ካድሬዎች “ሽብርተኛ” መባል የሚያስደስትና እንደ ሽልማት ተደርጎ የሚወሰድበት ዓመት ይሆናል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን። በ2007 እስር ማስፈራሪያ መሆኑ ያከትማል። በ2007 የኢትዮጵያ ወጣቶች በአርበኝነታቸው ይታወቃሉ። በ 2007 እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የህወሓት ሹማንምትን ዘረፋ የሚያጋልጥበት ዓመት ይሆናል። 2007 ዳኞች “እንቢ፣ በሀሰት አንፈርድም”፤ የመንግሥት ጋዜጠኖች “እውነቱን ደብቀን አንዋሽም”፤ ፓሊሶች “ወገናችንን አንደበድብም፣ አናስርም፣ አንገርፍም”፤ ወታደሮች ደግሞ “በወገናችን ላይ አንተኩስም” የሚሉበት ዓመት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
በዚህም ምክንያት 2007ን የምንቀበለው በታላቅ ተስፋና ዝግጅት ነው። በ 2007 ነፃነትና አምባገነንነት፤ ዘረኛነትና አንድነት፤ እውነትና ውሸት፤ አድርባይነትና አርበኝነት፤ ዝርፊያና ንጽህና፤ ድህነትና ብልጽግና የሚፋጠጡበት ዓመት ይሆናል ብለን እንጠብቃለን። በአጭሩ 2007 የወሳኝ ትግል ዓመት ይሆናል።
ሁለት ሺህ ሰባት ዓመተ ምህረት፣ የኢትዮጵያ መፃዒ እድል የሚወሰንበት ዓመት በመሆኑ ሁላችንም በተነሳሳ የአርበኝነት መንፈስ እንድንቀበለው ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪ ያደርጋል።
መልካም አዲስ ዓመት!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ !

No comments:

Post a Comment