ነገረ ኢትዮጵያ
ከአመታት በፊት የገዥው ፓርቲ አባል ሳይሆን በመንግስት ስራ ላይ ተሰማርቶ ይሰራ ነበር፡፡ 1997 ዓ.ም በኋላ ግን በዚህ አቋሙ አልቀጠለም፡፡ ‹‹አንዴ ቅንጅት ሌላ ጊዜ ደግሞ ኦነግ እያሉ ስም ሲለጥፉብኝ ‹ከዚህ ሁሉ!› ብየ ኦህዴድን ተቀላቀልኩ›› ይላል ካድሬው ለነገረ ኢትዮጵያ፡፡ ከዚህ በኋላ ባሉት ጊዜያት ደመወዝና እድገት በእጥፍ ተጨምሮለታል፡፡ የትምህርት እድል ተሰጥቶታል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ኦህዴድም ሆነ ኢህአዴግ ህዝብ ላይ የሚፈጽሙትን በደል በቅርብ ርቀት ተገኝቶ ተከታትሏል፡፡
ካድሬው እንደሚለው ከእነ አባዱላና መሰል ፖለቲከኞች ውጭ የኦህዴድ ካድሬዎች በፓርቲያቸው እምነት የላቸውም፣ በህወሓት በደል በእጅጉ ተማርረዋል፡፡ የ‹‹ብአዴኖችም ከእኛ የሚለይ ነገር የለውም፡፡ ተመሳሳይ ነው፡፡›› ይላል ካድሬው፡፡
በበርካታ ጉዳዮች ‹‹ፓርቲዬ›› ከሚለው ኢህአዴግ እንደሚለይ ቢገልጽም በአንድ ጉዳይ ግን ይስማማማል፡፡ ‹‹ጥያቄ የሚያቀርብ ካድሬ አንድም ኦነግ አሊያም የድሮው ቅንጅት አካል የነበረ ፓርቲ ወይንም ትምክተኛ ተብሎ ስም ይሰጠዋል፡፡ ኦነግ ወይንም ‹‹ቅንጅትነት/ትምክተኝነት›› ጥያቄ ማንሳት ከሆነ የኦህዴድ ካድሬዎች ሲገለጡ ኦነጎች ናቸው፡፡ ብአዴኖቹ ደግሞ እንደዛው ቅንጅት/ትምክተኛ ናቸው ማለት ነው››፡፡ በዚህ ጉዳይ ካድሬው የድሮው ጠቅላይ ሚኒስትር ‹‹ኦህዴድ ሲገለጥ ኦነግ ነው!›› በሚለው ይስማማል፡፡