Translate

Wednesday, August 13, 2014

የ”ብርቱው ሰው” መልዕክት – ከቃሊቲ እስር ቤት (በኤሊያስ ገብሩ)

1044303_169829796523576_1916727500_n
‹‹ለእውነት መቆም ካልተቻለ ስብዕና ይወርዳል፣ ሕሊናህም ይሞታል››
‹‹የክስ እና የእስር መብዛት … የድል ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ያሳያል››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ (ከቃሊቲ እስር ቤት)
‹‹እ… እስክንድር “The Iron man’’?››
የቃሊቲ ጠባቂ ፖሊስ

————————————–
ጥቁር ሰኞ (Black Monday) ከሚሉት ወገን አይደለሁም፤ በአባባሉም አላምንም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በሁሉም ቀናቶች ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ሁነቶችን ሊያስተናግድ ይችላል፡፡ ይህንን ማለት የወድድኩት ዛሬ ሰኞ በመሆኑ ነው፡፡ ብዙዎች ዕለተ ሰኞ እንደሚከብዳቸው እና እንደሚጫጫናቸው ይናገራሉ፡፡ በቀናት መጥቆር እና መንጻት ማመናችንን ትተን፣ እያንዳንዱ ቀናቶችን ለሥራ እና ለመልካም ነገሮች በአግባቡ ብንጠቀምባቸው መልካም እያልኩ ወደዋናው ርዕሰ ጉዳዬ ላምራ፡-
18 ዓመት ተፈርዶበት በቃሊቲ ወህኒ ቤት ታስሮ የሚገኘውንና እጅግ የማከብረውን ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን በቃሊቲ ከጠየኩት አንድ ወር ገደማ ሆኖኝ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት ልጠይቄው አስቤ፣ በአዲስ የጋዜጣ ሥራ ተጠምቼ ስለነበር ሳልችል ቀረሁ፡፡ ዛሬ ግን፣ ከመኝታዬ እንደተነሳሁ የናፈቀኝን እስክንድርን ለመጠየቅ ወደቃሊቲ ማምራት እንዳብኝ ወሰንኩና ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡
ሳሪስ አቦ አካባቢ የመኪና መንገድ ተጨናንቆ ተዘጋግቷል፡፡ ከአዝጋሚው የመኪና ጉዞ በኋላ ቃሊቲ ደረስኩ፡፡ ለመግቢያ ሰዓት (6፡00) የቀረው አስር ደቂቃ በመሆኑ ከታክሲ ወርጄ መሮጥ ግዴታዬ ሆነ፡፡ ቃሊቲ በታችኛ በር ከገባሁ በኋላ መዝጋቢ ፖሊስ እስኪመጣ ድረስ እስረኛ ጠይቀው የሚወጡ ጠያቂዎችን ማየት ጀመርኩ፡፡ የእስረኛ ቁጥር ብዙ፣ የጠያቂውም እንደዚያው! ‹‹መቼ ይሆን! የታሳሪ እና የጠያቂዎች ቁጥር በሀገራችን የሚቀንሰው?›› ስል ራሴን ጠየኩ፡፡ በወቅቱ ግን መልስ አላገኘሁለትም፡፡
የጥዋት ጠያቂዎች እየወጡ ሳለ የድምጻዊ ኤፍሬም ታምሩ የቀደምት ሥራዎቹ የሆኑ ለስላሳ ዘፈኖች በተከታታይ በትልቅ ስፒከር ሲንቆረቆሩ ነበር፡፡ ለስለስ ያሉ የሀገራችን ድምጻውያን የቀደምት ሥራዎች ከሚከፈትባቸው ቦታዎች መካከል አንዱ ቃሊቲ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያቶች እነእስክንደርን፣ ርዕዮት ዓለሙንና ውብሸት ታዬን ለማጠየቅ ስሄድ አድምጬ አውቃለሁ፡፡
****‹‹እ… እስክንድር “The Iron man’’››****
ከምዝገባ በኋላ የተለመደውን ፍተሻ አልፌ ጭር ወዳለው የቃሊቲ ግቢ ዘለኩኝ፡፡ አንድ ጠባቂ መጣና ‹‹ማንን ልጥራልህ?›› አለኝ፡፡ ‹‹እስክንድር ነጋን›› አልኩት፡፡ ወዲያው ፈገግ እያለ ‹‹እ… እስክንድር “The Iron Eskidner-NEgaaman’’ (ብርቱ ሰው)›› በማለት ሊጠራልኝ ሄደ፡፡ የጥበቃው ፖሊስ እንዲህ ማለቱ ትንሽ አግራሞትን ፈጥሮልኝ ነበር፡፡ ‹‹እስክንድር ብርቱ መሆኑን እነሱም ያውቃሉ ማለት ነው?›› በማለት ለራሴ ፈገግ አልኩ፡፡ [ብርቱ ሰው! በሚል ርዕስ ‹‹ፋክት›› መጽሔት ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአንድ ወቅት ስለእስክንድር ጽፉ ነበር፡፡ ኢቲቪም ባሳላፍነው ሳምንት የፍትህ ሚኒስቴር አምስት መጽሄቶችንና አንድ ጋዜጣን በወንጀል ክስ መከሰሱን ተከትሎ ባስተላለፈው ዜና እና በ‹‹ሕትመት ዳሳሳ›› ፕሮግራም ላይ ይህ ርዕስ እና የእስክንድር ፎቶግራፍ ያለበት የመጽሔቱን የፊት ገጽ በተደጋጋሚ ሲታይ ነበር] ፖሊሱም ይህን አይቶ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አደረብኝ፡፡
ወዲያው እውነተኛ ፈገግታ የማይለየው እስክንድር ፈገግ እያለ ወደእኔ መጣ፡፡ በአጋጣሚ በር ጋር ስለጠበኩት በአካል በደንብ ለመገናኘት ዕድሉን አገኘን፤ ጠባቂዎቹም ዝም ስላሉን ተቃቅፈን ሰላምታ ተለዋወጥን፡፡ ከሰላምታው በኋላም እስክንድር ትንሽ ጎንብስ ብሎ፣ አንገቴ ላይ የጠመጠምኩትን ስካርፍ ጫፍ ላይ የነበረውን የኢትዮጵያ ባንዲራ በሁለት እጆቹ ይዞ ሳመው፡፡ የእስክንድር ትህትና መቼም ተነግሮ አያልቅ ብዬ ዝም አልኩ፡፡
*****‹‹ሰርካለም እንዴት ነች?››******
ሁለት ጥበቃዎች ከግራና ከቀኝ ሆነው ማውራት ጀመርን፡፡ ‹‹ስለመጣህ ደስ ብሎኛል?›› አለኝ፡፡ ‹‹እስኬው እኔም ናፍቀኸኝ ነበር፤ ሥራ ስለበዛብኝ ነው መምጣት ያልቻልኩት›› አልኩት፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ቅድሚያ ለሥራ! ብዬሃለሁ›› አለኝና ‹‹አሁን ላይ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ከየቱ እንጀምር? በኋላ ይሄንን ሳልጠይቀው? ይሄንን ሳልነግረው? ብዬ እንዳላስብ›› በማለት ጥያቄውን በፈገግታ አስከተለ፡፡
‹‹አንተ ደስ ካለህ ነገር ጀምር›› አልኩት፡፡ ፈጠን ብሎ ‹‹ሰርካለም እንዴት ነች? ታገኛታለህ?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ደህና ነች፡፡ አልፎ አልፎ በማኅበራዊ ሚዲያ አገኛታለሁ፡፡ ነፍቆትም ማደጉን በፎቶፍራፉ ተመልክቻለሁ፡፡ የእሷንም የቅርብ ጊዜ ፎቶፍራፍ ፌስ-ቡክ ላይ አይቼዋለሁ፤ ደህና ናቸው›› በማለት መለስኩለት፡፡
‹‹በጣም ናፍቀውኛል›› የእስክንድር ምላሽ ነበር፡፡ …በእሱ ቦታ ራሴን ሳስቀምጠው እጅግ የሚከብድ ነገር ነው፡፡ ግን የእስክንድር በጣም ጠንካራ ነው፤ መንፈሱም ጭምር፡፡ …
‹‹አቤል (ዓለማየሁ) ደህና ነው?›› ሲልም በድጋሚ ጠየቀኝ፡፡ ‹‹ደህና ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት ሊጠይቅህ መጥቶ በር ተዘግቶበት መመለሱን ነግሮኛል›› አልኩት፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ›› በለው፡፡ [ጓደኛዬ ጋዜጠኛ እና መጽሐፍ ጸሐፊ አቤል አለማየሁ ያለ ማንም ቆስቋሽ፣ በራሱ ተነሳሽነት የታሰሩ ጋዜጠኞችን እና ፖለቲከኞችን ከሚጠይቁ የተወሰኑ ሰዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ በአሁን ወቅት በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት በፍቃዱ ኃይሉ (በፍቄ) እና ተስፋለም ወልደየስ፣ እንዲሁም በቃሊቲ የምትገኘዋ ማህሌት ፋንታሁን (ማሂ) በራሳቸው ተነሳሽነት የታሰሩትን በመጠየቅ አውቃቸዋለሁ፡፡ ይህ እስከዳር ዓለሙ (ቹቹ)ን፣ መሳይ ከበደንና ኢዩኤል ፍስሐንም ይጨምራል]
ከሰሞኑ ፍትህ ሚኒስቴር በአምስት መጽሄቶችና በአንድ ጋዜጣን አቀረብኩት ስላለው ክስ እስክንድር ሰምቷል፡፡ ‹‹ክሱ ለሚዲያዎቹ ደረሳቸው እንዴ? ‹‹ዕንቁ›› መጽሄትም በክሱ ላይ ስላለበበት አንተን አስቤህ ነበር?›› አለኝ፡፡
‹‹ከፍቄ (የዕንቁ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር) ጋር ተደዋውለን ነበር፡፡ እስከአሁን ባለኝ መረጃ መሰረት ክሱ አልደረሳቸው …ሕግን አክብረን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሰርተናል፤ አሁንም በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በመስራት አምናለሁ፤ ከዚህ ባለፈ ግን በግሌ የሚመጣብኝ ነገር ካለ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ፡፡ ጋዜጠኝነት ከፍርሃት ጋር አብሮ አይሄድም፡፡ እየፈሩ ጋዜጠኝነት የለም፤ ይህ የግል እምነቴ ነው›› በማለት ብዙ ጊዜ ለቅርብ ጓደኞቼ በጨዋታ አጋጣሚ የማካፍላቸውን ሀሳብ ለእስክንድርም ነገርኩት፡፡
‹‹ዴሞክራሲ እንዲሁ አይመጣም፡፡ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ሰዎች ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ አንተም ዋጋ መክፈል ካለብህ መክፍል አለብህ፡፡ ግን ጨካኝ አትበለኝ፡፡ ጨካኝ ሆኙም አይደለም፤ መሆን ያለበት ግን ይሄ ስለሆነ ነው፡፡ (እስክንድር ያመነበትን ፊት ለፊት ነው የሚናገረው) ….ለተከሰሰሱት ሚዲያዎች በሙሉ አንድ ከልቤ ውስጥ ያለ አንድ መልዕክት አስተላልፍልኝ? በማለትም ጥያቄውን አስከተለ፡፡
‹‹እሺ››
እስክንድር ቀጠለ፡- ‹‹በክሱ መምጣት ልትደነግጡ አይገባም፡፡ ኢህአዴግ ሊከስስና በፍ/ቤት እንድትቀጡም ሊያደርጋችሁ ይችላል፡፡ ይሄንን ከዚህ በፊትም አይተነዋል፡፡ እናንተ ግን በታሪክ፣ በሕዝብና በህሊናችሁ ፊት ነጻ ናችሁ፡፡ የክስ፣ የእስርና የስደት መብዛት ሰላማዊ ትግል መኖሩንና ትግሉም እየሰራ መሆኑን ያሳያል፡፡ ሰላማዊ ትግል እና የመብት ጥያቄዎች ሲኖሩ እስር እና ክስ ይኖራሉ፡፡ አንዳንዴም ሞት ይኖራል፡፡ ክሱን ተከትሎ እኔ በግሌ ሁለት ዓይነት ስሜት አለኝ፡፡ ሰዎች ሲከሰሱ እና ሲታሰሩ አዝናለሁ፣ ይሰማኛል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰላማዊ ትግል እየተሰራ እና ውጤት እያመጣ አድርጌ እቆጥረዋለሁ፡፡ እስር እና ክስ በበዙ ቁጥር የድል እና እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈጠርበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ አይዟችሁ! ኢህአዴግ ሊፈርድባችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ በታሪክ ፊት ነጻ ናችሁ፡፡ መንግሥቱ ንዋይ እኮ ያለአግባብ ተፈርዶበታል፤ በታሪክ፣ ሕዝብና በህሊናው ፊት ግን ነጻ ነው፡፡››
አያይዞም፣ ስለማርቲን ሉተር ኪንግ አንድ የግል ታሪክን አስታውሶ አወጋኝና ‹‹ኤልያስ፣ ለእውነት መቆም አለብን፡፡ ለእውነት መቆም ካልተቻለ ስብዕና ይወርዳል፣ ሕሊናህም ይሞታል፡፡›› በማለት ምክሩን ለገሰኝ፡፡
ሁለቱ ፖሊሶች ‹‹በቃችሁ!›› የሚል ድምጻቸውን አሰሙ፡፡ ከእስክንድር ጋር በ30 ደቂቃ ውስጥ ብዙ ቁም-ነገሮችን ተለዋውጫለሁ፤ መቼም ሁሉም አይጻፍ? ከእስክንድር ጋር ልለያይ ስል ባለቤቱ ሰርካለም ፋሲል እስክንድር 18 ዓመት የተፈረደበት ዕለት ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፒያሳ ድረስ አብረን ስንሄድ ደጋግማ የነገረችኝ ቃል ይበልጥ በውስጤ አቃጨለ፡፡
‹‹እስክንድር ማለት ላይብረሪ ነው፡፡ እሱን ማሰር አንድ ቤተ-መጽሐፍት እንደመዝጋት ይቆጠራል››
ሰርኬ፣ እውነትሽን ነው፡፡ ይሄንን ትናንትም በማወቅ አምን ነበር፣ ዛሬም ይበልጥ አውቄያለሁ፡፡
በመጨረሻ እስክንድር ‹‹እገሌ እገሌ አልልህም፤ ሁሉንም አከብራችኋለሁ፣ እወዳችኋለሁ›› በልልኝ ብሎ ተሰናበተኝ! እንግዲህ የእስክንድርን ሰላምታ አድርሻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ አምላክ ከህሊና እስረኞች ጋር ይሁን!

No comments:

Post a Comment