Translate

Thursday, August 21, 2014

መለስን ቅበሩት!(ተመስገን ደሳለኝ)

ከኢትዮጵያ ሀገሬ የደቀቀ ኢኮኖሚ ላይ በማን አህሎኝነት ወጪ ተደርጎ፣ ቅጥ ባጣ መልኩ በመላ አገሪቱ እየተከበረ ስላለው የቀድሞ አምባገነን /ሚኒስትር ሁለተኛ ሙት ዓመት ዝክርም ሆነ ሰውየውን ዛሬም በአፀደ-ህይወት ያለ ለማስመሰል እየሞከሩ ላሉት ጓዶቹ አንዲት ምክር ብጤ ጣል ማድረጉ ተገቢ ነው ብዬ ስለማስብ በአዲስ መስመር እንዲህ እላለሁ፡-


አብዮታዊው ገዥ-ግንባር ግንቦት ሃያ፣ የህወሓት ምስረታ፣ የብአዴን አፈጣጠር፣ የኦህዴድና የደኢህዴን ውልደት፣ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል፣ የባንዲራ ቀን፣ የመከላከያ ሳምንት፣ የፍትሕ ሳምንት፣ የሕዳሴ ግድብ መሰረት ድንጋይ የተጣለበትጅኒ-ቁልቋል እያለ ዓመቱን ሙሉ በማይጨበጥ ተራ ፕሮፓጋንዳ ማሰልቸትን መንግስታዊ ኃላፊነት አድርጎታል፡፡ ይህ እንግዲህ ለቁጥር የሚያታክቱ፣ በነጭ ውሸት የታጨቁ እና በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቅኝት የተንሸዋረሩዶክመንተሪ ፊልሞቹ ረስተንለት ነው፡፡

ይህ ሁሉ ያልበቃው ‹‹ጀግናው›› ኢህአዴግ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ፣ ወርሃ-ነሐሴንም እንደ ግንቦት ሃያው ሁሉ የሟቹን ታጋይነትና አብዮታዊነት፤ ሕዝባዊነትና አርቆ አስተዋይነት፤ የርዕዮተ-ዓለም ተራቃቂነትና የአየር ንብረት ተካራካሪነት፤ በፖለቲካ ቢሉ በኢኮኖሚ ቁጥር አንድ ጠቢብነትና ባለራዕይነት፤ ፍፁም ፃድቅነትና ሰማዕትነት…. የሚተረክበት ሲያደርገው ቅንጣት ታህል ሀፍረት አልተሰማውም፡፡ ሰሞኑን ‹‹ኢትዮጵያ›› ቴሌቪዥን ግድ ሆኖብን ተመልክተንና ሰምተን በትዝብት ካሳለፍናቸው ‹‹መለስ፣ መለስ›› ከሚሉ የከንቱ ውዳሴ አደንቋሪ ድምፆች በተጨማሪ፣ የኦሮሞን ባሕላዊ ልብስ ሲያለብሱት፣ ሐረሪዎች ጋቢ ሲደርቡለት፤ በደቡብ የሚገኙ ብሔሮች የየራሳቸውን ባሕል የሚወክሉ አልባሳት ሲሸልሙት፣ ስለወላይታነቱ ሲመሰክሩለት

ደጋግመን ለመመልከት ተገደናል፤ ይሁንና ድርጅቱ ስለ ቀድሞ ሊቀ-መንበሩ አልፋና ኦሜጋነት ለመስበክ ዙሪያ ጥምዝ ከዳከረለት ከእንዲህ አይነቱ የተንዛዛ ፕሮፓጋንዳ ይልቅ፣ በዚሁ የቴሌቪዥን መስኮት የቀረበ አንድ ጎልማሳ ‹‹መለስ ሁሉም ማለት ነው›› ሲል የሰጠው አስተያየት፣ ቅልብጭ አድርጎ ይገልፅለት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ የዚህ አይነቱ ምጥን አስተያየትም በጥራዝ ነጠቅነት ዘላብዶ የኋላ ኋላ በሀፍረት ከማቀርቀር ያድናል፡፡ ለምሳሌ እናንተ የግንባሩ ካድሬዎች ስለመለስ ምሁርነት ለመናገር ስትዳዱ ሁሌ የምትደጋግሙት፣  ያንኑ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አርቃቂነቱ እና የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ኀልዮት አዋቃሪነቱ ነው፡፡ ግና፣ ይህ ‹‹ንድፈ-ሃሳብ›› ተብዬ ራሱ በርዕዮተ-ዓለምነት ለመጠራት የማይበቃ የተውሸለሸለ ጭብጥ ስለመሆኑ በርካታ ምሁራን በጥናቶቻቸው ከማስረገጣቸው ባሻገር፣ አገሪቷን ለከባድ ኢኮኖሚያዊ ድቀት፣ ሕዝቧን ደግሞ ለጥልቅ ድህነት መዳረጉን ብቻ ማስታወሱ በቂ ይሆናል፡፡ ስለልማታዊ መንግስት አዋጭነት በብቸኝነት እንደተከራከረ ተደርጎ የሚለፈፈውን እንኳን ንቆ መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ከታንዲካ ማካንደዋሬና መሰል የፅንሰ-ሃሳቡ አበጂዎች የዘረፋቸውን መከራከሪያዎች ማን ዘርዝሮ ይዘልቀውና፡፡መለስን ቅበሩትየምለውም፣ እንዲህ ያሉ አስነዋሪ ማንነቶቹን ማስታወስ ስለሚያም ነው፡፡

እናም እውነት እውነት እላችኋለሁ፡- ስለሰውዬው የምትነግሩን እና የምታስቀጥሉትሌጋሲ ሆነ የምትተገብሩት ረብ ያለው አንድም ራዕይ የለምና ዝም፣ ፀጥ ብላችሁ የምራችሁን ቅበሩት፡፡ እስቲ! ኦጋዴንን ተመልከቱ፤ ካሻችሁም ወደ አኝዋኮች ተሻገሩ፤ ያን ጊዜ እናንተ በአርያም የሰቀላችሁት ሰው፣ ለነዚህ ሁለት ብሔሮች የቀትር ደም የጠማው ጨካኝ መሪ እንደነበር፣ በክፋት ትዕዛዞቹ ጥፋት ከተረፈ ጠባሳ ትረዱታላችሁ፡፡ ለአቅመ-ሔዋን ያልደረሱ ህፃናት በሰልፍ የሚደፈሩባት፣ ወጣቶች እንጀራ ፍለጋ በተስፋ-ቢስነት ጥልቁን ውቅያኖስ ሰንጥቀው ለመሰደድ የማያመነቱባት፣ የጤና ኬላ ማግኘት ተስኗቸው በልምሻ የሚባትቱ ብላቴኖችን በአቅም-የለሽነትና በቁጭት የምናስተውልባት ደካማ አገር አስረክቦን እንዳለፈ ከወዴት ተሰወረባችሁ? ከቀዬዎቻቸው በጉልበት ለተፈናቀሉ ወገኖች በመቆርቆር ‹‹ሕግ ይከበር!›› ባሉ በየጉራንጉሩ ወድቀው እንዲቀሩ የተፈረደባቸው ጎበዛዝትን ሬሳ እንድንቆጠር ያደረገን ደመ-ቀዝቃዛመሪእንደነበረስ ስንት ጊዜ እያስታወስን እንቆዝም? ቀደምት አባቶች ወራሪውን ፋሽስት ለማንበርከክ የተዋደቁባቸው ጢሻና ኮረብቶች በዚህ ዘመን የዜጎች ወደሞት አገራት መሸጋገሪያ ጽልማሞቶች የሆኑት በማን ሆነና ነው? ከሕግ ተጠያቂነት ቢያመልጥ፣ ከታሪክ ተወቃሽነት ልትታደጉት የምትችሉ ይመስላችኋልን?


ይልቅ እመኑኝ! ፀጥ ብላችሁ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍራችሁ ቅበሩት! ላይመለስ በመሄዱም እንደ ግልግል ቆጥራችሁት እርሱት!! መቼም በገዛ ራሱ ሕዝብ ላይ ትውልዶች ይቅር ሊሉት የሚሳናቸውን ይህን መሰሉ መከራ ላዘነበ ሰው በአፀደ-ስጋ ሳለም ሆነ በበድን የሙት መንፈሱ ስር በየዓመቱ ለአምላኪነት መንበርከክ፣ የናንተን አልቦ ማንነት እንጂ ሌላ አንዳች የሚነገረን ቁም ነገር ጠብ ሊለው አይችልም፡፡ ይህም ሆኖ ለመለስ አምልኮ እጅ መስጠት አሳፋሪነቱ፣ ለካዳሚዎቹ ብቻ መሆኑን መስክሮ ማለፉ የቀሪዎቻችን ዕዳ እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡

No comments:

Post a Comment