Translate
Tuesday, August 12, 2014
ኢንጅነር ይልቃል የአውሮፓ ህብረት እርምጃ እንዲወስድ አሳሰቡ
ዛሬ ነሃሴ 6/2006 ዓ.ም በኢትዮጵያ ተወካይ ያላቸው 20 የአውሮፓ አባል አገራት
ተወካዮች በተገኙበት አዲስ አበባ በሚገኘው የአውሮፓ ህብረት ቢሮ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እንዲያስረዱ የተጋበዙት የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያ ወደባሰ ችግር ሳትገባ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ አሳሰቡ፡፡
የአውሮፓ ሉዑካን ኃላፊ የሆኑት ሚስስ ባርባራ በመሩት ስብሰባ ላይ የተገኙት ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት በአሁኑ ወቅት ገዥው ፓርቲ ስለሚያደርገው አፈና፣ ሰብአዊ መብት ረገጣ፣ በሚዲያው ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ፣ ስለታሰሩት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን አስረድተዋል፡፡
ኢንጅነር ይልቃል ስለ ኢህአዴግ ሁኔታ በተጠየቁበት ወቅትም ‹‹ኢህአዴግ በራሱ ችግር፣ በርዕዮት ዓለም መደናበር፣ በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት ምርጫውን ክፍት በማድረግ ዴሞክራሲን መፍቀድ ዋጋ እንዲሚያስከፍለው ያውቃል፡፡ በሌላ ኩል ምርጫን ማጭበርበርም ጣጣ እንደሚያመጣበት ተረድቷል፡፡ በመሆኑም ምርጫ ማጭበርበርም ሆነ ምርጫውን ክፍት ማድረግ ችግር እንደሚፈጥርበት ስለሚያውቅ ከወዲሁ አፈናን መርጧል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢንጅነር ይልቃል ‹‹በቀጠናው ባላችሁ ጥቅም ምክንያት ኢህአዴግን እየደገፋችሁ፣ ህግና ባህላዊ መሰረት የነበረበት አገር ወዳልሆነ አቅጣጫ እያመራች ነው›› ብለዋል፡፡ ኢንጅነሩ አክለውም ‹‹ኢህአዴግን ስለምትደግፉ፣ ወጣት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን ሲታሰሩና ህዝብ አማራጭ እንዲያጣ ሲደረግ ዝም በማለታችው የኢትዮጵያ ህዝብ የኢህአዴግ እንጅ የኢትዮጵያ ወዳጅ አድርጎ አያያችሁም፡፡›› በሚል በህብረቱ አባላት ተወካዮች ላይ ወቀሳ አቅርበዋል፡፡
የህብረቱ አባላት ‹‹ምን እናድርግ?›› በሚል ላቀረቡላቸው ጥያቄ ‹‹ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ ሙጋቤ ላይ ከወሰዳችሁት እርምጃ መካከል ትንሹን እንኳ ኢህአዴግ ላይ ብታደርጉት ትልቅ ለውጥ ማምጣት ትችሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫ በመሆኗ፣ በአፍሪካ ቀንድም ወሳኝ አፈርና ለቀይ ባህርም ያላት ቅርበት ለዓለም ደህንነት ከዚምባብዌ በላይ ጠቃሚ አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያ ቀውስ ውስጥ በመግባቷ የእናንተም ብሄራዊ ጥቅም ጭምር ነው ችግር ውስጥ የሚገባው፡፡ በመሆኑም ለኢትዮጵያውያንም ለራሳችሁም ሲባል ኢትዮጵያ የባሰ ችግር ውስጥ ከመግባቷ በፊት አንድ እርምጃ መውሰድ አለባችሁ፡፡›› በሚል እርምጃ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡
ምንጭ ነገረ ኢትዮጵያ
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment