የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ
ደራሲ: ኤርምያስ ለገሰ
ነጻነት አሳታሚ ድርጅት: ቨርጂኒያ:ዩ ኤስ ኤ 2014
408 ገጾች
ግምጋሚ: ቢላል አበጋዝ:: ዋሽግተን ዲሲ
ስለ “የመለስ “ትሩፋቶች” ከመጻፌ በፊት ስለ ነጻነት አሳታሚ ድርጅት በጥቂቱ:: እንደ ታዘብኩት ከሆነ ይህ ድርጅት መረጃ የሚያቀርቡ: የሚያስተምሩ ወደፊት ተኮር ስራዎችን እያቀረበልን የሚገኝ ነው:: ፍጹም አፈና ባለባት ኢትዮጵያ መንግስትና ባለስልጣናትን የሚያጣቅስ ጽሁፍ ይወጣል ማለት አይቻልም:: ነጻነት አሳታሚ ድርጅት ዓላማው ስለ ኢትዮጵያ ሀሳባቸውን: ቁጭታቸውን: ሊሰጡ የሚሹትን ትምህርት በግልጽ ለአገር ወዳዱ አንባቢ ማቅረቡን ላውቅለት እወዳለሁ:: ልንክባከበው ተገቢ የሚሆነው አገር መገንባት ካልን አፈናን መዋጊያ መሳሪያ ሳንይዝ አይሆንምና::
የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ
“የመለስ “ትሩፋቶች” የኢትዮጵያ ዊኪ ሊክስ ነው ማለት ያስችላል:: ዊኪ ሊክስ አንድ ጁሊያን አሳንጅ የተባለ የአርባ ሶስት አመት እድሜ ያለው ኦስትርያዊ ጥብቅ የመንግስታትን (ወያኔን ጨምሮ) ሚስጥሮች በኢንተርኔት የዘረገፈበት ሁኔታ ነው:: በአዲስ አበባው የአማሪካ ኤምባሲ ስለ ቅንጅት የተባለውን ሌላም ሁሉ ሚስጥሮች ይፋ ያወጣ ነው:: ጁሊያን አሳንጅን የታይም መጽሄት በ2010 የዓመቱ ሰው ብሎት ነበር:: አሁን በስደት ይኖራል:: “የመለስ “ትሩፋቶች” ደራሲ ልክ እንደ ጁሊያን አሳንጅ የዋያኔን ሚስጥር የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ ብሎ ይዘረግፋዋል:: በቅርቡም ኤድዋርድ ስኖዴን የተሰኘ አማሪካዊም የመንግስ ሚስጥር ዘክዝኴል:: የኢትዮጵያ ዊኪ ሊክስ ምን ይዟል ?
አሳታሚው የመረጠው የመጽህፉ ሽፋን መለስ ዜናዊ ደንግጦ\ፈዞ ቢታይም አንዳንድ ሰዎች የመለስን ምስል በማየት ብቻ መጽህፉን አንገዛም ብለው እንደነበር አጫውተውኛል ደራሲው አቶ ኤርምያስ ከዳያስፖራው ነዋሪ ሆኑ ወያኔ የሚገዛትን ኢትዮጵያ አናይም ብለው ባእድ አገር ለቀሩ ሁሉ: ኢትዮጵያ ላይ የተሰራውን ግፍ ዘርዝሮ በማቅረቡ ውለታ አድርጔል:: መጽሀፍ በሽፋኑ አይዳኝም ተብሎአልና የአዲሳባን ጉድ ማንበብ ይሻላል:: አንብቦ ለመምክር:: መጭውን ለማሰብ:: አገር ሲፈርስ ዝምታ አይበጅምና::
ክርእሱ እንነሳ ?
ማንም መሪ ትቶት የሚያልፈው የስራ ውጤት አለ:: ባለመልካም ውጤት: ጉድለት ጥፋት ያለበት: በጅምር የቀረ::ትሩፋት ቀሪ ውጤት ነው:: መሪው ካለፈ የሚዘከርበት: የሚመሰገንበት: የሚተችበት:: የመጽሀፉ ደራሲ ትሩፋቶች ብሎ በቅንፍ ለምን ተወው ? መልሱን ጥቂት ምዕራፎች እንዳነበብን እናገኘዋለን:: መጽህፉን ስንጨርስ አፋችንን ምሬት ምሬት ይለዋል ባይ ነኝ::
የህወሃት መሩ መንግስት ዛሬ አጥፍቶ ጠፊ ሽብርተኛ መንግስት በመሆኑ በሱ ላይ የሚገኝ መረጃ በሁሉ መልኩ ያስፈልገናል:: ያወቁትን ጠላት መጋፈጥ ድል ማድረግን ያስረግጣል:: ከቅድመ መለስ ሞት አንስቶ ህወሃት እንዴት አድርጎ እንደ ካንሰር ተስፋፍቶ አዲስ አበባን ብሎም ኢትዮጵያ እንደዘመተባት: ህወሃት መርህ አልባ መንጋ መሆኑን:ያኖረው ደግሞ የመለስ ቆማሪነት: ብቻና ሌላው ሁሉ ፈርቶት አዳሪ በመሆኑ የተቀረው መንጋ መሆኑን በብዙ ምእራፎች ደራሲው ድጋፍ ጨምሮ ያቀርባል:: ይህ አስተያየት ህወሃት የነበሩን መለስን የተጋፈጡትን አይጨምርም::
እንደማንኛውም መጽሀፍ ትችት ይዘቱን አጠር አርጎ: የሚዘይደውን:የሚቀረውን አካቶ በዘልማድ ማቅረብ የዚህን መጽሀፍ ጥቅሙን እንዳይቀንስ: እሰጋለሁ:: የኔ ጥረት ዋናዋና ክፍሎቹን አመላክቼ አንባቢንን መጋበዝ ነው:: ይህን ማድረጌ ከሰመረ አንባቢ መጽሀፉን አሳዶ: አንብቦ: ዳኝነቱን ይሰጣል ብዮ አጥብቄ አምናለሁ::
የደራሲው ዓላማ ምንድን ነው ? መጽሀፉ የሚያካትተውስ ?
ይህ መጽሀፍ ባብዛኛው ህወሃት በአዲሳባና ህዝብዋ ላይ የፈጸማቸውን አሳዛኝ ተግባሮች መተረክ ነው:: ስለ አዲሳባም ቢሆን በከተማዋ ስለተደረጉ ምርጫዎች: ዘረፋዎች: ተንኮሎች: በደሎች እንጂ በመክላክያ ውስጥ: በየሚኒቴሩ መስሪ ቤት: በፖሊስ: በስለላ: በባንኮች ናየክልል አስተዳደሮች ሌሎችምቦታዎች የሆነው አያቀርብም::“ባለቤት አልባ ክተማ” ስላላት አዲሳባ ነው ትኩረቱ:: የስልጣን ማዕክልዋ ናትና ስለአዲሳባ መናገር የሌላው ማመላክቱ አልቀረም::
መጽሀፉ የተደራጀበት መንገድ
መጽህፉ በስምንት ክፍሎችና ሃያ ስምንት ምእራፎች ቀርቧል:: የህወሃት\እህአዴግ ክፍተኛ ካድሬዎችን በተለያዩ ምዕራፎች እያቀረበ ባህሪያቸውን ተግባርና ሃላፊነታቸው ያቀርባል:: ደራሲው የበረከት ስሞንን “የሁለት ምርጫዎች ወግ” አጥብቆ ሲሞግት ይነበባል:: አርክበ እቁባይ: አሊ አብዶ አባይ ጸሀዬ: ህላዌ ዮሴፍ: ተፈራ ዋልዋ ሌሎችም ክፍተኛ ህወሃት\እህአዴግ የስራ ባልደረቦቹ ነበሩ:: ክነዚህ አሳዛኝ ፍጥረታት ጋር ስለ ነበረው ውሎዎች ይተርካል::
መጽሀፉ የት ክፍል ይመደባል ?
የህዝብ ተወካይ ምርጫዎች በተመለክተ ብዙ መጻህፍት ወጥተዋል:: እየወጡም ነው:: የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ ከነዚህ ይዛመዳል በዓላማ በይዘት:: ለምሳሌ የቃሊቲው መንግስት በሲሳይ አጌና: የነጻነት ጎህ ሲቀድ በብርሃኑ ነጋ: የክደት ቁልቁለት በ ፕ\ሮ መስፍን ወ/ማርያም::
በረክት ስሞን ደግሞ የጻፈው ስለምርጫም ቢሆንም የህወሃት\እህአዴግ እንጂ የህዝብ አይደለም:: ክጠቀስኴቸው እንዳልመድበው የመንግስት መግለጫነቱ በሌላ እንዲመደብ ያደርገዋል::ደራሲውም የበረከት ስሞንን መንግስታዊ መግለጫ “የሁለት ምርጫዎች ወግ” ሲሞግት ደጋግሞ ይነበባል:: በቁጭት: በስሜት::
ለምን ጻፈው ?
መጽሀፉን ያነበበ ሰው ደራሲው ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉት ማስተዋል አያስቸግረውም:: እናት አባቱን በተሰቡን: የትውልድ ቀበሌውን:ያስተማሩትን:ለስልጣን ያደረሱትን:ስልጣን የደረሰበት መንገዱን ከህይወቱ ገጠመኞች እያመጣ ተርኳል:: ዋናው ግን ህወሃት\እህአዴግ ላይ ያለውን እምቅ ምሬት ማግለጽ ነው ማለት ይቻላል:: ግለ ታሪክ አይደለም:: ከመጀመሪያው እስክ መጨረሻው የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ ብዙ ክፍል የህዝብ: የበደል ታሪክ ነውና::
ስለህወሃት መሪዎች ከዚህ በፊት ሰምተናል:: ምን አዲስ ይነግረናል ?ቱባ ካድሬ ሆኖ ሲኖር ቆይቶ አሁን ቢያወራ ቢጽፍ ምን ይፈይዳል ? ሌላም ብዙ ማለት ቢቻልም ይህን ማለት ጨለምተኝነትን ማስተናገድ ነው:: ዋናው ነገር ስለህወሃት መሩ መንግስት የሚሰጠን መረጃ : ነው። በጥሞና መስማት: በጥሞና ማንበብና መመራመር የጽናት መሰረት ነውና:: ቸሩ አምላክ ሌሎቹንም ወደ መልካሙ መንገድ ይምራቸው:: ደራሲውንም የሚወዳት አዲሳባን የሚክሳት ያድርገው::
ደራሲው በዚህ አስክፊ ስርአት ለአቅመ አዳም የደረሰ ነው:: የነበረበት ስልጣን ለመድረስ ሌሎች ንጹሃንን ካልበደለ: የተሾመው ባገሩ: እግዜር በሰጠው ችሎታው ነውና: በዚህ ችግር የለም:: የዛሬ ተግባሩ እና መጻፉም እጅግ የሚመሰገንበት ነው:: ብዙ ህይወት የተከፈለበት ድጅት መርተው እንኳ ዝም ብለው ቁጭ ያሉ ሰዎች ያሉባት አገር ናት ኢትዮጵያ:: ደራሲው ሌሎች ማስታወሻዎች አሉኝ ይላልና ለነዚህም ምስጋና ይገባዋል:: ቅር የሚለኝ የዚህ ወጣት ምሬት ማስታወሻውን እስከማስነበብ ብቻ የሆነ እንደሆን ነው:: ይህን ማስታወሻ የያዘ ደጋፊ መረጃዎችን ጨምሮ ይዟል ? ለሚክድም: ሰምቶ አላምንም ለሚል::
መልእክቱ ባጭሩ
ዛሬ የህወሃት መሪዎች ለመጭው “ምርጫ” ሽር ጉድ የጀመሩበት ጊዜ ነው:: በዚህም “የምርጫ” ድራማ ምእራቡን ዓለም ለማማለል ነው:: በዚህ አቢይ ጉዳይ ባለፉት ዙመናት ወያኔ ህወሃት በር ዘግቶ ምን መከረ ? ምን ተንኮሎች ፈጸመ ? እንዴት አድርጎ ሁኔታዎችን ተቆጣጠረ ? የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ ላንባቢም ለታሪክም የጽሁፍ መነሻ (ማጠያየቂያ) ያቀርባል:: በሶስት የአዲሳባ ህዝባዊ ምርጫዎች 1992፣1997: 2000 ዓ ም የሆነውን: መሬት ቅሚያውን: ህግ ጥሰቱን: ሙስናውን እና የህወሃትን ዝቅጠት ማሳየት የመጽሀፉ ይዘት ነው:: ወደፊትም ሌሎች ያክሉበታል ተብሎ ተስፋ ይደረጋል::
መጽሀፉ የሚተርከው ህወሃት\ኢህአዴግ ባንድ በኩል ያዲሳባ ህዝብ በሌላ: ሶስት ዙር ግጥሚያ አድርገው ሁለቱን ቢሸነፍ ሶስተኛውን ብቻው ሮጦ ቀደምኩ ያለበትን ቀልድ ነው:: በዚህ ወዲያ ህወሃት\ኢህአዴግ የምርጫ ወግን ትቶ “ልማታዊ መንግስት” ነኝ ማለት ቀጠለ::
አምባ ገነን መንግስት ይነሳል: ሲያበቃለት: ይደቃል:: እንዴት ተነሳ ? እንዴትስ ለድቀቱ በቃ ተብሎ መወሳቱ : መጻፉ: መነበቡ: መመርመሩ የማይቀር ነው:: የመለስ “ትሩፋቶች” አስተዋጽኦ ክዚ አኴያና ከምስክርነቱ አንጻር ይሆናል::
ስላለፉት ሁለት መንግስታት የዘውድና ወታደራዊ ደርግ ዛሬ መጻህፍት ለንባብ እየበቁ ነው:: የነበረውን እንደነበረ በቅንነት ተከታዩ ትውልድ እንዲያውቀው የሚጽፉ ቢኖሩም:: ዘመናት አልፈውም የሚሸፍጡም ጽፈዋል:: የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ በቁጭት የተጻፈ ነው:: በቃኝ:ከማለትም የተነሳ:: “ንቅዘት የነገሰበትን ስርአት ማገልገል ሰልችቶኛል” (ገጽ 359) ይላል ደራሲው:: የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ እየደረሰው ያለው: የከተማው የመንግስት ሰራተኛ ላይ የደረሰው ከስራ መፈናቀል፡የመሬት ቅሚያው፡ያለፍርድ እንግልቱ በሰፊው ሁሉም ቀርቧል:: የሚያንገሽግሽ በደል::
ከሁሉም በላይ ልክ እንደውጭ ጠላት አዲስ አበባ ላይ የወደቀባት አፓርታድ (የዘር መድልኦ መሰረቱ የሆነ ስርዓት) አሰተዳደር እንዴት ተቌቌመ? የህወሃት ካድሬዎች እንዴት በዞን ተከፋፈሉዋት ? አዲስ አበባ እንዴት በህወሃት ተዘረፈች? መጽሀፉ ዝርዝር አለው:: መጽሀፉ የማያነሳው ይህን ሁሉ ሲሆን የአዲስ አበባ ህዝብ ምን አስቻለው? ዛሬስ ቢሆን ምነው ? እንዴት? ያሰኛል:: በንባብ ወቅት::
ዋናው ጉዳይ ለውጥ እንዴት ይመጣል ነው:: ያለፉት የምርጫ ወጎችና ውጤቶች እንዲህ ከሆኑ ህወሃት\ኢህአዴግ ሰንጎ በያዛት አገር ምርጫ ይታሰባል ? ህዝቡስ ምን ይላል ? የተቃዋሚ መሪዎች ምን ይመክራሉ? ደራሲው ስላለፉት ምርጫዎች እንጂ ስለወደፊቱ ያለውን አስተያየት አናውቅም::ደራሲው ሌሎች ማስታወሻዎቹን ያሳትማል ብዬ እመኛለሁ:: ሊያስተምር ሊያደራጅ:: አገር ቤት ተቷ ቸው ለመጣው ወጣቶች ምሳሌ ሊሆን የሚችልበትን ዕድል በስደት ያግጠመው እላለሁ::
ምርጫን ካነሳን ዘንድ ምእራፍ 18 (ለምን ተሽነፍን ?) “ለምን ተሽነፍን” ብሎ ህወሃት የሚያቀርበውን ትንታኔ ያቀርባል:: ከቀረቡት ምክንያቶች እንቶፈቶው የመለስ ዜናዊ ምእራቡ ዓለም አይወደኝም ማላዘን ነበር:: ማን ላይ ቆመሽ ? አይደል:: በመለስ አባባል ምእራቡ አብዮታዊ ዴሞክራሲን ይጠላል:: ለቅንጅት ጥብቅና ይቆማል:: የመለስ ግብዝነት እንጂ ምእራቡ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲን አያውቀውም:: የሚያውቀው የህወሃትን በሙስና መዘፈቅና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ላካባቢው ሰላም አሳሳቢነት ነው:: እውን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ምንድን ነው ? ከሌብነት ሽፋን መሆን በተረፈ? ከምዕራቡ ተመጽውቶ ለቻይና ሰግዶ: ካአረብ ዶልቶ ? አብዮታዊ ዴሞክራሲ የህወሃት ካድሬዎች የስካር ጨዋታ ነው:: አምልኮ መለስ በነበረክት ስምኦን አእምሮ ተቀብሯል:: ታዲያ ማን ማርሽ ይቀይር? የመለስ “ትሩፋቶች” ባለቤት አልባ ከተማ አንብቦ የዝግ በር መዘላለፉን መገመት ይቀላል::
ምእራፍ 26 (የአክራሪነት ጫካ) ላይ ደራሲው የሚያነሳው ማንንም አገር ወዳድ የሚያሳስበውን ነው::
ገጽ 362 “ስጋቱ በዚህ ዙሪያ የሚነሳ ግጭት(በሃይማኖት) የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የመጣል አቅሙ ነው:: ለማይበርድ ደም መፋሰስና እልቂት ክመዳረጉም ባሻገር ወደ ብሔር ግጭት ሊሄድ ይችላል:: በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የብሔርና ሀይማኖት ጥያቈዎች የሚዛመዱበት ሁኔታ ሰፊ ነው:: የሱማሌ: አፋር:ስልጤ:ሐረሬ የመሳሰሉ ብሔረሰቦች ማንነት ጥያቄ ውስጥ የእስልምና ሀይማኖት አንዱ ገጽታ ነው::” በዚህ መጽሀፍ የተነገረውን ተንኮል:ነውር:ህገ ወጥነት የፈጸሙ ለምንም አይመለሱ ብሎ መጠንቀቁ ይበጃል:: የኔ ሃይማኖት ብቻ ካልን: በብሄር ብቻ ካየን ሊሆን የሚችለው ዘግናኝና የማይረሳ ሊሆን ይችላል::
ትሩፋት ካልን ምእራፍ 28 ላይ የሰፈረው ከአእምሮ አይጠፋም:: ደራሲው ምእራፉን “ያልሞተው እስስት” ብሎ አሊ አብዶን ይጠይቃል:: አሊ አብዶ እንዲህ ይላል “ምን እንደሆነ ባይገባኝም መለስ(ዜናዊ) ስለትላልቅ ፕሮጄክቶች መስማት አይፈልግም:: ዛር እንደያዘው ሰው ያንቀጠቅጠዋል:: አባይ ግንዱን ይዞ ይዙር ቀለበትም ሳይጠለቅ ይቅር::” ብሎ አለ ይላል ስለ ባለራእዩ መሪ(ገጽ 385)
ባንድ ጎሳ ማንቁርትዋን የተያዘች ክተማ እላታለሁ አዲስ አበባን “ባለቤት አልባ” ከምላት:: ባለቤትስ አላት:: ህዝቡ:: መለስ ዜናዊን: “ወደድንም ጠላንም የብሔር ፖለቲካ አዲሳባ ላይ አፈር ልሶ የማይነሳበት ደረጃ ደረሷል” እንዲል ያደረገው::
መልካም ንባብ::
No comments:
Post a Comment