በድርጅቶች ውህደትና ቅንጅት አገርን ማዳን!!!
ኢትዮጵያዊያንን በዘር እና በሀይማኖት ለያይቶን እርስ በርስ እያጋጨን በመግዛት ላይ ያለውን ወያኔን ለማሸነፍ እና ከምትኩም ከራሷ ጋር የታረቀች፤ ፍትህ የሰፈነባት፤ እኩልነት የተረጋገጠባት እና በኃያላን አገሮች እርጥባን ሳይሆን በራሷ አቅም የምትተማመን ጠንካራ ሀገር እንድትኖረን የነፃነትና የዲሞክራሲ ኃይሎት መተባበር እንዳለባቸው ሲነገርና ሲወተወት ቆይቷል። ይሁን እንጂ በህወሓት የከፋፍለህ ግዛው ፓሊሲ እና በፓለቲካ ባህላችን ኋላቀርነት ምክንያት እስካሁን የተደረጉ የትብብር ጥረቶች የተፈለገውን ውጤት ሳያስገኙ ቀርተዋል።
ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ ቀድሞ የተደረጉት ጥረቶች የተጠበቀውን ውጤት አለማስገኘት ተስፋ ሳያቆርጠን ከእያንዳንዱ ጥረት ልምድ እየወሰደን የኢትዮጵያዊያን አንድነት እስኪረጋገጥ ድረስ አዳዲስ የትብብር ጥረቶችን ማድረግ ያለብን መሆኑ ያምናል። በዚህም መሠረት የትብብር መርህ ነድፎ ትግል ውስጥ ካሉ ሁሉም የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ሲነጋገር እና ሲደራደር ቆይቷል። እንደሚታወቀው የንቅናቄዓችን አበይት የትብብር መርሆች ሁለት ናቸው። መርህ አንድ፣ ለውጥ እንዲመጣ የምንታገለው ኢትዮጵያ በምትባል አገር ውስጥ መሆኑ ማመን ነው። መርህ ሁለት ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም እርከኖች የመንግሥት ሥልጣን መያዝ የሚገባው በሕዝብ ነፃ ምርጫ ብቻ መሆኑን መቀበል ናቸው።