ከበትረ ያዕቆብ
እርግጥ ነዉ ነገሩ ትንሽ የሚያስገርም ነዉ፡፡ ወጣቱ የሄደበት እርቀት ግራ የሚያጋባና ድፍረቱ የሚያስገርም ነዉ፡፡ ሌላዉን ትተን በሀገር ዉስጥ የሚገኙትን ዩንቨርሲቲዎች ስም ደጋግሞ እያነሳ ይህንን ሸለሙኝ ፣ ይህንን ሰጡኝ ፣ የረዳት ፐሮፌሰርነት ማዕረግ ተበረከተልኝ ወዘተ ማለቱ በእርግጥም ከማሰገረም አልፎ ብዙ ያስብላል፡፡ ያም ሆኖ ግን እኔን ይበልጥ ያስገረመኝ ጉዳዩ የዚያን ያልህ እንደ ተዓምር የመታየቱ ነገር ነዉ፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ እየተደረገ ያለዉን ዉይይት ስመለከት እንዴ ነዉ ነገሩ ብየ መደነቄ አልቀረም፡፡
በዚህ ወጣት የተፈፀመዉ አሳፋሪ ተግባር ዛሬ የተከሰተ አዲስ ክስተት አይደለም ፤ የነበረና አሁንም እየተፈፀመ ያለ ነገር ነዉ፡፡ እዉነቱን መነጋገር ካለብን መሰል ማጭበርበር ቤተ-መንግስት አካባቢ በጣም የተለመደ እና ብዙዎች የተጨማለቁበት ተግባር ነዉ፡፡ ይታያችሁ ፣ ቤተ-መንግስት ነዉ ያልኩት፡፡ ይህንን ስናይ ወጣቱ የፈፀመዉ ተግባር የሚደንቅ አይመስለኝም፡፡ እንዴትስ ያስደንቃል፡፡
ዛሬ ሳሙኤልዘሚካኤልእድል ጥሎት ሁሉም ተረባረበበት እንጅ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የትምህርት ማስረጃ ቢመረመር ስንት ከሱ የባሰ ጉድ ይገኝ ነበር፡፡ እንግዲህ ሀገርን ያህል ትልቅ ነገር እንመራለን የሚሉ ግለሰቦች መሰል ተግባር በሚፈፅሙበት አገር የዚያ ወጣት ተግባር ጉድ የሚያስብልበት ምክንያት አይታየኝም፤፤ እንዴትስ ሊያስብል ይችላል፡፡ ከዚህ ይልቅ ቤተ-መንግስት ተቀምጠዉ አገርን የሚዘዉሩ ግለሰቦች ፣ በያንዳንዳችን እጣ ፈናታ ላይ የመወሰን ስልጣን በጉልበት የጨበጡ ባለስላጣናት የሀሰት ማስረጃ ሊያስደንቀን ፣ ሊያበሳጨን ፣ ሊያስደነግጠን ይገባ ነበር፡፡
ዛሬ በርካታ የኢህአዴግ/ህወሀት ጉምቱ ባለስልጣናት እንከዋን ትምህርት ቤት ገብተዉ ሊማሩ በበሩ እንኳን ሳይልፉ ባለሁለተኛ እና ሶስተኛ ድግሪ የመሆናቸዉ ጉዳይ ለብዙዎቻችን ሚስጥር አይመስለኝም፡፡ ዛሬ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲት ድግሪና ማስትሬት በቀጭን ትእዛዝ እንዳሻቸዉ የሚሰበስቡት ተራ ነገር ነዉ፡፡ ሲያሻቸዉም ከዉጭ በገንዘብ ይሸምቱታል፡፡ ሲልም እድሜ በሙያዉ ለተካኑ የቻይና እና የህንድ ዜጎች እንደፈለጉት አሳምረዉ አዘጋጅተዉ ኮንግራ ይሏቸዋል፡፡ከዛም ከለታት አንድ ቀን ብቅ ብለዉ ይህ አለን ይላሉ፡፡ ይህ ነዉ ለኔ አሳፋሪዉ ፣ አስደንጋጩ፡፡
በእንዲህ አይነት መልኩ በርካታ ትልልቅ ባለስልጣናት የሀሰት የክብር ካባ ለመደረብ ሞክረዋል፡፡ አሁንም ብዙዎች ይህንን መንገድ ቀጥለዉበታል፡፡ ከብዙ ወራት በፊት አንድ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዉስጥ የሚሰራ ወዳጄ ሲያጫዉተኝ “ዩንቨርስቲዉ በካድሬ መመራት ከጀመረበት እለት አንስቶ በርካታ የኢህአዴግ መኳንንቶችን በማዕረግ” አመርቋል” ነበር ያለኝ፡፡ ይታያችሁ እርሱ ያለዉ “በማዕረግ” ነዉ፡፡ ይህ ማለት ሳይማሩ ፣ ሳያጠኑ ፣ ሳይፈተኑ ኤ በ ኤ ይሆናሉ ማለት፡፡ ለኔ ይሄ ነዉ አስደንጋጩ ጉዳችን፡፡ ይህ ወዳጄ እንደነገረኝ አልፎ አልፎም በዉጭ ዩኒቨርስቲ መማር የሚፈልጉ ከተገኙም የሚፈልጉትን የትምህርት መስክ መርጠዉ የመዓረግ ተመራቂ ተብሎና ሁሉም ነገር ተሟልቶለት ይሰጣቸዋል፡፡ እኒህ ሰዎች ናቸዉ ዛሬ ሀገሪቱን የሚመሩት ፤ ከእኛ በላይ አዋቂ የለም የሚሉን ፣ የጭቆና ቀምበር ጭነዉ ፍዳችንን የሚያሳዩን፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሁለት ግለሰቦች ማንሳት እዉዳለሁ፡፡ ይህ ለምሳሌ ያህል ብቻ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ በአንድ ወቅት እንደ ምሁር ለመፈላሰፍ ሲቃጣዉ የነበረዉ የቀድሞዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ነዉ፡፡ ሰዉየዉ ትምህርቱን ከዩንቨርሲቲ አቋርጦ በረሀ እንደ ወረደ እና ከ17 አመት የትጥቅ ትግል በኋላ በለስ ቀንቶት ቤተ-መንግስት እንደገባ ነዉ ነበር የምናዉቀዉ፡፡ ሆኖም ከእለታት በአንዱ ቀን አቶ ምን ይሳነዋል ባለሁተኛ ድግሪ ምሁር ነዉ ሲባል ሰማን ፣ ያም አልበቃ ብሎ ሌላም እንዳከሉበት የቀብሩ እለት ተነገረን፡፡ የአቶ ሳሞራ የኑስም ታሪክ ተመሳሳይ ነዉ፡፡ 11ኛ ክፍል አቅርጠዉ በረሀ ገብተዉ እንደታገሉ እንጅ ሌላ የምናዉቀዉ ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም እርሳቸዉ ከ11 ክፍል በአቋራጭ ከፈለጉት ቦታ ላይ ጉብ አሉ፡፡ በሀዉልታቸዉ ላይም ባለ ሁለተኛ ድግር ምሁራ ናቸዉ ተብሎ ተፃፈ፡፡ እንዴት ብሎ የጠየቀም አልነበረም፡፡ እስከማዉቀዉ ድረስ በጉዳዮ ላይ ጥያቄ ያነሳ ብቸኛ ሰዉ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ብቻ ነዉ፡፡ ዛሬ “ለእዉነት ቆሜያለሁ” የሚለዉ ሬድዮ ፋናም ያኔ አዳች ነገር ትንፍስ አላለም ነበር፡፡ ይህ ብቻ አይደለም በቅርቡ ብዙ አፍሪካዊ ጋዜጠኞች የተሳለቁበት በሀሰት የትምህርት ማሰረጃ በመንግስት ሴራ የአፍሪካ ህብረት አካል በሆነ ድርጅት ዉስጥ ትልቅ ስልጣን እስከመጨበጥ የበቃዉ የኢህአዴግ ካድሬም በምሳሌነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡
እንግዲህ ይታያችሁ እነዚህ ሰዎች ሀገር መሪ ነን ይላሉ፡፡ እነዚህ ናቸዉ የሀገሪቱን ፖሊሲና እስትራቴጅ ቀራፂያን ፣ እነዚህ ናቸዉ ሀገሪቱ እና እኛን ወክለዉ ከሌሎች ጋር የሚደራደሩት ፣ እነዚህ ናቸዉ ዛሬ በእያንዳንዳችን ህልዉን ላይ ወሳኝ ሆነዉን የሚገኙት፡፡ ይህ ነዉ እኔን ይበልጥ የሚያሳፍረኝ ፣ የሚያሰገርመኝ፡፡ ይህ ነዉ ለኔ ትልቁ ጉድ፡፡ እንዴት ነዉ እንዲህ አይነት የሀገር መሪዎች ባሉበት ሀገር አንድ ከደሀ ቤተሰብ የወጣ ልጅ የፈፀመዉ የማጭበርበር ተግባር የሚደንቀዉ፡፡ ነዉ ወይስ አላዉቅም ልንል ነዉ፡፡
ከባለስላጣናቶቻችን እና ከእኛ ዜጎች አልፎ ተርፎ እንኳ በየዩንቨርስቲዉ በዶክተር እና ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ስም የሚያጭበረብሩት የዉጭ ዜጎች በርካታ አይደሉም? የመጀመሪያ ድግሪ ይዘዉ በዶክተር ስም የነገ ሀገር ተረካቢ በሆኑ ወጣት ልጆች ላይ ሲቀልዱ አላየንም ፣ አልሰማንም ? ለምሳሌ እንኳን በቅርቡ ወደ አንድ የዉጭ ዩንቨርስቲ ሁለተኛ ድግሪዉን ለመማር ያቀና ወጣት ዶክተር ነኝ ብሎ ካስተማረዉ የዩንቨርሲቲ መምህሩ ጋር በአንድ ክፍል ዉስጥ ለትምህርት እንደተገናኙ ሲተረክ ሰምተናል፡፡
በጥቅሉ እንነጋገር ከተባለ በርካታ ጉድ በዙሪያችን አለ፡፡ ዘርዝረን አንጨርሰዉም፡፡ በመሀከላችን በርካታ የቀበሮ ባህታዊያን እንዳሉ ልብ ልንል ያገባል፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት አገር የሳሙኤልተግባር ለኔ ብዙ የሚያስደንቅ ነዉ ብየ አላስብም፡፡ እንዴዉም በአንድ ግለሰብ የማጭበርብር ተግባር ላይ ብቻ ማፍጠጡ ችግሩ እንደሌለ ያስመስለዋል ፤ ወደ መፍትሄም አይወስድም፡፡ ስለዚህም ችግሩን ሰፋ አድርጎ ማየትና አፍረጥርጦ መነጋገር ተገቢ ነዉ እላለሁ፡፡ ሬድዮ ፋናም ቢሆን “ለእዉነት ቆሜያለሁ” የሚል ከሆነ በአንድ ግለሰብ ተግባር ላይ ብቻ ከማንባረቅ በዘለለ የሌሎችንም በተለይም ሀገር እንመራለን በሚሉ የኢህአዴግ/ህወሀት አምባገነን ባለስልጣናት እየተፈፀሙ ያሉ ማጭበርበሮችን ሊያጋልጥ ይገባል፡፡ እርግጥ ኢህአዴግ አምጦ ከወለደዉ ተቋም ይህን መጠበቅ ሞኝነት ነዉ፡፡ ለሁሉም ቸር እንሰንብት !
No comments:
Post a Comment