Translate

Wednesday, June 25, 2014

ለጂቡቲ በነፃ የተሰጠው ውኃ የሁለቱ አገሮች ስትራቴጂካዊ የውህደት አካል መሆኑን መንግሥት አስታወቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በጠረፍ አካባቢ ለጂቡቲ በነፃ ለውኃ ቁፋሮ የሚውል መሬት መስጠቱ፣ ኢትዮጵያና ጂቡቲ የጀመሩት ስትራቴጂካዊ የመዋሀድ አካል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሰኔ 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኢትዮ-ጂቡቲ የጋራ ኮሚሽን 12ኛ ስብሰባውን ያካሄደ መሆኑን፣ ሁለቱም አገሮች የጀመሩትን የልማትና የውህደት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ለማፋጠን የሚያስችሉዋቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡ አምባሳደሩ እንዳሉት ፍትሕ፣ ኢምግሬሽን፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የሠራተኞች ልውውጥ፣ ንግድና ኢንቨስትመንትና የድንበር ንግድ የስብሰባው ዋነኛ አጀንዳዎች ነበሩ፡፡ 
አምባሳደር ዲና በቅርቡ ለጂቡቲ በነፃ የተሰጠው የውኃ ቁፋሮ ከወዳጅነት በዘለለ ለኢትዮጵያ ምን ጠቀሜታ ይሰጣል በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ውሳኔው ቀደም ሲል ስምምነት ላይ የተደረሰበት የስትራቴጂካዊ የውህደት ዕቅድ ሒደት አካል መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በ‹‹ስትራቴጂክ ኢንትግሬሽን›› ዕቅዱ ስምምነት መሠረት ሁለቱም አገሮች በኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት የተደገፈ የፖለቲካ ውህደት ለማምጣት በኢትዮጵያ በኩል ለጂቡቲ ዜጎች የተለየ ጥቅም (Preferential Treatments) ለማስጠበቅ የተወሰነ መሆኑን፣ ለጂቡቲ በነፃ የተሰጠው የውኃ ቁፋሮ የዚሁ ውሳኔ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንደ ኢምፔርያል ዘመን አንድ አገር ሌላ ሉዓላዊ አገር በኃይልና በጦር ወደ ግዛቱ ማስገባት አይችልም፡፡ የጂቡቲ ዜጎች ግን ወደውና ፈልገው ወደ ቀድሞ ቤታቸው የሚመጡበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤›› ብለዋል ዓላማውን ሲያብራሩ፡፡

ጂቡቲ ኤሌክትሪክና ውኃ ከኢትዮጵያ እንድታገኝ መደረጉ የዚሁ የውህደት አካል መሆኑንም አክለዋል፡፡ ‹‹ጂቡቲ አንድም ሌሊት ከኢትዮጵያ ውጪ ማሰብ አትችልም፤›› በማለት፡፡ ‹‹ጂቡቲን እንደ አንድ የኢትዮጵያ አካል አድርጋችሁ አስቡ›› በማለት፣ ጂቡቲ ያላት የሕዝብ ቁጥር በጣም ትንሽ መሆኑንና የአገሪቱ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ የሚረጋገጠው ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚና በፖለቲካ መተሳሰር ስትችል ብቻ እንደሆነ በአገሪቱ መንግሥት ደረጃ መታመኑን ገልጸዋል፡፡
ሌሎች የኢጋድ አባል አገሮች የሕዝብ ቁጥር ተደምሮ የኢትዮጵያን ያህል እንደማይሆን የጠቀሱት አምሳደር ዲና፣ ኢትዮጵያ አካባቢውን የማስተሳሰር ተነሳሽነትን ወስዳ ተግባራዊ እያደረገች መሆኗን ተናግረዋል፡፡ ተግባራዊነቱም በኢትዮ-ጂቡቲ ስትራቴጂካዊ ውህደት እንደሚጀምር አያይዘው በመግለጽ፣ ባለፈው ዓመት በጂቡቲ መንግሥት የቀረበው የስትራቴጂካዊ ውህደት ሰነድ በኢትዮጵያ ተቀባይነት ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ሰነድ በኢጋድም ዕውቅና ተሰጥቶት በሁለቱ አገሮች የጋራ ኮሚሽን ተግባራዊነቱ እንዲረጋገጥ ወስነው መለያየታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ 
    

No comments:

Post a Comment