Translate

Sunday, June 1, 2014

የኢትዮጵያ መሰረታዊ የልማት ችግር የት ነው እንዴትስ ይፈታል?

ገለታው ዘለቀ

Ethiopian opinions forum
ስለ ልማታዊ መንግስት (developmental state) ስናወራ ልማታዊ የሚለው ቅጽል ስም ገላጭ በመሆኑ መጀመሪያ “ልማታዊ” ሲባል ምን ማለት ነው? ብለው ሰዎች እንዲጠይቁን ያደርጋል። ኣንዱ የዚህ ጥያቄ ምንጭ በኣሁኑ ዘመን ልማት ለሚለው ስያሜ ሰፊ ትርጉም ስለተሰጠው ሲሆን ኣንድ መንግስት ዛሬ ላይ ሆኖና ብድግ ብሎ “ልማታዊ መንግስት ነኝ” ሲል ማን ልማታዊ ያልሆነ ኣለ ብለው ሰዎች እንዲነሱ ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሹ የሚያደርግ ጥያቄ ለማኝ ጉዳይ ነገር ያንጠለጠለ በመሆኑ ነው።
ሁሉ እንደሚያውቀው በኣሁኑ ጊዜ ልማት ለሚለው ጽንሰ ሃሳብ የተሰጠው ትርጉም ሰፊ ሲሆን የሰው ልጆችን ሁለንተናዊ ኣዎንታዊ እድገት ይጠቀልላል። የኢኮኖሚ እድገት፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ዴሞክራሲና መልካም ኣስተዳደር፣ ወዘተ. ይሸፍናል። በመሆኑም ኣንድ መንግስት በዚህ በኣሁኑ ጊዜ ልማታዊ ነኝ ሲል ማንም መንግስት ለነዚህ ጉዳዮች ቆሚያለሁ ይላልና ምን የተለየ ነገር መጥቶ ነው ልማታዊ የሚያሰኛችሁ በሚል ያስጠይቃል ወይም ለፖለቲካ ትርፍ ከሆነ ደግሞ ህዝብ መቀለጃ ያደርገዋል ማለት ነው።

ባለፉት ዘመናት በተለምዶ ልማታዊ መንግስታት ይባሉ ለነበሩት የተሸለመው ይህ “ልማታዊ” የተሰኘ ቅጽል ስም የሚገልጸው እንዲህ እንዳሁኑ ልማትን በሰፊው ኣይቶ ሳይሆን የኢኮኖሚ እድገትን የሚመለከት ጠባብ ጉዳይ ነው።የልማታዊ መንግስትነት ኣንዱ ልዩ መገለጫውም ይሄው ነበር። በኢኮኖሚ እድገት ላይ ከፍተኛ ዝንባሌ ያለው መንግስት ማለት ነው።የኢኮኖሚ እድገት ከመጣ ውስብስብ የሆነው የሰው ልጆች ችግርም ኣብሮ በዝግታ ይፈታል ስለዚህ መጀመሪያ ኢኮኖሚው ላይ እናተኩር የሚል ነገር ከደጋፊዎች ይደመጣል።
በሌሎች ተቃዋሚዎች ዘንድ ደግሞ ልማታዊ መንግስት የሚለው ጉዳይ ስሙ ራሱ ኣደናጋሪ ነው። ልማት ከተባለ ዴሞክራሲንም ማቀፍ ኣለበት ኣብሮ ነው ሁሉም ማደግ ያለበት ይላሉ። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሄ ጉዳይ ቀን የጣለው (outdated) ነው። የዛሬው ትውልድ ስለ መብቱ ይጨነቃል ከኣምሳ ኣመት በፊት እንደነበረው ኣባቱ ኣያስብም የሚል ነገርም ይነሳል።እንደነዚህ ዓይነት ተቃውሞዎች ከማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ኣካባቢ የሚቀርቡ ናቸው።
ዋናው ክርክር ግን ለምን የኢኮኖሚ እድገት ላይ ታተኩራለህ ኣይደለም። በርግጥ ኣንድ ጎበዝ መንግስት ኣገሩን ከድህነት ለማላቀቅ የኢኮኖሚ ጥርመሳ(breakthrough) ውስጥ የሚያስገባውን ስራ መስራት ኣለበት። ነገር ግን ልማታዊ መንግስትነትን የሚተቹ ሰዎች ለኢኮኖሚ እድገት ጠንክሮ መስራትን ሳይሆን ልማታዊ መንግስት ነኝ የሚለው መንግስት ለኢኮኖሚው ጥርመሳ ኣንድ ዋና መንገድ ኣድርጎ የሚያየው የመንግስትን በገበያ መሃል ጣልቃ መግባትና ኢኮኖሚን በከፍተኛ ሁኔታ መቆጣጠር ከሆነ ነው። ተቃዋሚዎች ይህን ኣስተሳሰብና ዝንባሌ ከምን እንደመነጨ የፍልስፍናው መሰረት ምን እንደሆነ፣ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ማወቅ በጥብቅ ይፈልጋሉ። በመንግስት የገበያ ጣልቃ ገብነት ወይም በመንግስት ነጋዴነትና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ምን ኣይነት ሳይንሳዊ ግንኙነት ኣለ ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ። የመንግስት ጣልቃ ገብነት የሚገለጽባቸው ቅርጾች የተለያዩ ሲሆኑ በኢትዮጵያ ሁኔታ መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን ጣልቃ ገብነት የምንገልጸው ራሱ መንግስትና ፓርቲዎች በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የያዙዋቸውን የንግድና የኣገልግሎት ተቋማት በማየት ነው። ለዛሬው ውይይታችን የመንግስት ጣልቃ ገብነት በገበያው መሃል እያልን ስናወራ ጣልቃ ገብነቱን ከዚህ ክብ ውስጥ እያየን ነው።
በተለምዶ እንደሚታወቀው የኢኮኖሚ እድገት የሚመጣው ወይም ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ከጂዲፒ ማደግ፣ ከምርት መጨመር ጋር የተያያዘ ሲሆን በርግጥ ምርት እንዲጨምር የሚያደርጉ እምቅ ጉዳዮች (potential factors) ደሞ ኣሉ። እነዚህ ጉዳዮች መሬት (land) ፣ የሰው ሃይል፣ ካፒታል እና ኢንተርፕሩነርሺፕ ናቸው። በርግጥ እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ ኖረው የፖለቲካው ከባቢ ምቹ ካልሆነ ምርት ላይጨምር ይችላል። ይሄ የታወቀ ነው። ነገር ግን የመንግስት ጣልቃ መግባትና ያለ መግባት ከኢኮኖሚ እድገት ጋር የሚያያይዛቸው ቀጥተኛ ሳይንሳዊ ግንኙነት የለም። ብዙ ኣገሮች መንግስት በገበያ ጣልቃ ሳይገባ ወይም ጣልቃ ገብነቱን ሲያቆም ኣድገዋል ጥቂት ሃገሮች ደግሞ መንግስት ጣልቃ ገብቶ ኣድገዋል። ኣንዳንድ ኣገሮች መንግስት ጣልቃ ባይገባም ኣላደጉም፣ ብዙ ኣገሮች መንግስት ጣልቃ ገብቶ ኣላደጉም። ይህ የሚያሳየው በመንግስት ጣልቃ ገብነትና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ኣለመኖሩን ነው። ኣንዳንድ ወገኖች ቻይናንና ኣሜሪካንን ይጠቅሳሉ።እነ ኣሜሪካና እንግሊዝ ኢኮኖሚያቸውን ደብል ለማድረግ ሃምሳና ስልሳ ኣመት ሲፈጅባቸው ቻይና ደግሞ በኣንድ ኣስርት ውስጥ ደብል ማድረግ የቻለችው መንግስት በማክሮና ማይክሮ ኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ በመግባቱ ኢኮኖሚውን በመቆጣጥሩ ነው ሊሉ ይዳዳቸዋል። ለምን የኢኮኖሚውን ፈጣን እድገት ከመንግስት ጣልቃ ገብነት ጋር ፈጥነው እንደሚያያይዙት ኣይታወቅም። ለቻይና ጂዲፒ እድገት ብዙ ፋክተርስ ኣስተዋጾ ኣድርገዋል። ኣንዱና ትልቁ ኢንቨስትመንት የመሳቡዋ ጉዳይ ነው። ቻይና ውስጥ በግል ከተያዙ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶች መካከል ሰማኒያ በመቶ የሚሆኑት በውጭ ኢንቨስትመንት የተያዘ እንደሆነ ኣንድ ጥናት ያሳያል። ይህ ግዙፍ ኣሃዝ የሚያሳየው ኢንቨስትመንቱ ምን ያህል እድገቱን እንዳፋጠነው ነው። እነ ኣሜሪካ፣ እንግሊዝና ሌሎች የዘመናዊነት ቀዳሚ ኣገሮች እድገት መነሻው ከባድ ነበር።እነዚህ ኣገሮች ኢኮኖሚያቸውን በጥንድ ቁጥር ለማሳደግ ስልሳና ኣምሳ ኣመት ከዚያም በላይ ሲፈጅባቸው በኣሁኑ ሰዓት ለማደግ ምቹ ሁኔታ ያገኙ ኣገሮች ግን ያን ያህል ጊዜ የማይፈጅባቸው ኣንዱ ምክንያት የውጭ ንግዱ ያደገበት ጊዜ መሆኑ፣ ኣጠቃላይ የግሎባል ዲማንድ የጨመረበት ጊዜ ላይ መሆኑ፣ሳይንስና ቴክኖሎጂ ያደገበት ጊዜ መሆኑ ሲሆን ኣሁን በርትተው የተነሱ ኣገሮች በጥንድ ቁጥር የማደግ እድላቸው ከሃምሳ ኣመት በፊት ከነበረው እድል ይሰፋል።ለዚህም ነው የምስርቅ እስያ ኣገሮች በየኣስር ኣመቱ ደብል ማደግ የቻሉት።
ሌላው እንደ ኮርያ ያሉ እርዳታን በትክክል ለእድገት የሚጠቀሙ ሃገሮች ደግሞ መነሻ ስለሚያገኙ ለመስፈንጠር እና ኢኮኖሚያቸውን በጥንድ ለማሳደግ መሰረት ይኖራቸዋል።ሰፊ የፋይናንስ እርዳታዎችን እያገኙ ማደግ ከባዶ ተነስቶ ከሚታደግ ጋር ሊወዳደር ኣይችልም። ዛሬ ብዙ የኣፍሪቃ ሃገራት የተለያየ ብድርና እርዳታን እያገኙ ኣንዳንዶቹ ጋናን መጥቀስ ይቻላል ሲያድጉ ኣንዳንዶቹ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሚሰጠውን እርዳታ ያክል በየኣመቱ ያባክናሉ። ከዚህም የተነሳ ከድህነት ሳይወጡ ይቆያሉ።
ኮርያና ኣንዳንድ የምስራቅ እስያ ኣገሮች በመጀመሪያው የእድገት ወራታቸው ከፍተኛ የሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ ዝንባሌ ያሳዩ ሲሆን በዚህም ኢኮኖሚያቸው በፈጣን ሁኔታ ሊያድግ ችሏል።ስለ ኮርያ ከተነሳ ኣይቀር ጥቂት ማለቱ ተገቢ ነው። ኮርያ የኢኮኖሚ ጥርመሳ የጀመረችው በ1970 ዎቹ ነበር። በዚህ ጊዜ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዚደንት ፓርክ ዲክቴተር የሚባሉ ኣይነት ነበሩ። የኮርያ ኢኮኖሚ ማንሰራራት የጀመረው በእኚሁ መሪ የስልጣን ዘመን ቢሆንም ለኮርያ መነሳት(economic takeoff)ግን ብዙ ፋክተርስ ኣሉ። ከነዚህም ውስጥ ምን ኣልባትም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቀዝቃዛው ጦርነት ጉዳይ ነው። እንደሚታወቀው ደቡብና ሰሜን ኮርያ በወቅቱ ዓለምን ለሁለት በከፈለው የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ከተለያዩ በሁዋላ ደቡብ ኮርያ የካፒታሊስቱን ስርዓት ኣጥብቃ የያዘች ሲሆን ይህ ኣቋሟ ከተባበረችው ኣሜሪካና ከምእራብ ሃያላን ኣገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራት ኣደረገ። በተለይ የተባበረችው ኣሜሪካ በሰሜንና በደቡብ ኮርያ ጦርነት ወቅት 34 ሺህ ወታደሮቿን የሰዋችባት ኣገር ናት ኮርያ። በጦርነቱ ወቅት ከሞተው ሌላ የቆሰለውን ቤቱ ይቁጠረው። ለጦርነቱ ያወጣችው ወጪ በብዙ ቢሊየን ዶላር የሚቆጠር ነው።ይህ መስዋዕትነቱዋ ኣሜሪካ የኮርያን እድገት እንድትፈልግ ኣድርጓታል። ኣሜሪካ ብቻ ሳትሆን በሁለቱ ኮርያውያን ጦርነት ጊዜ በወቅቱ ደቡብ ኮርያ ከተባበሩት ህዝቦች ድርጅት(UN)እርዳታ በመጠየቋ ከራሺያና ከቻይና ውጭ ዓለም በሙሉ ከደቡብ ኮርያ ጋር የቆመበት ታሪካዊ ወቅት ነበር። UN በኣራቱም ማእዘናት ኮርያን ለመታደግ ጥሪ ሲያስተላልፍ በሊግ ኦፍ ኔሽንስ ምስረታ ወቅት ጉልህ ሚና የነበራቸው ኣጼ ሃይለስላሴም ለጥሪው ፈጣን ምላሽ በመስጠት በሺህ የሚቆጠር ጦር በመላክ ኢትዮጵያም ኮርያን ኣግዛለች።
ከፍ ሲል እንዳልነው ጦርነቱ ከቆመ በሁዋላ የተባበረችው ኣሜሪካም ሆነች የዓለም ህዝቦች ይህቺ ኣገር ተቋቁማ፣ በኢኮኖሚ ጠንክራ ማየቱ ኣስፈላጊ ሆኖ የታያቸው ይመስላል። ከዚህ በተጨማሪም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የነበረው የሁሉቱ ጎራዎች ፉክቻ ከኮሚኒስቱ ኣካባቢ በኣብዛኛው የቃላትና የስድብ ውርጅብኝ ሲሰነዘር ከምእራቡ ዓለም ኣካባቢ ደግሞ ከቃላቱ ጦርነት ይልቅ በኢኮኖሚ እድገትና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምጥቀት በልጦ ለመገኘት እልህ ውስጥ የመግባት ሁኔታ ይታይ ነበር። በመሆኑም የኮሚኒስት ደጋፊ የነበረችውን ሰሜን ኮርያን ለማስቀናትም ጭምር የተባበረችው ኣሜሪካና ምእራባውያን ለደቡብ ኮርያ በመለገሳቸው ለኮርያ የኢኮኖሚ ጥርመሳዋ ከፍተኛ የሆነ ጥሩ ከባቢ ፈጥሮላታል።ኮርያ በዚያን ጊዜ እርዳታና ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ያገኘች ሲሆን በርግጥ የኮርያ ትልቅ ምሳሌነቱዋ የሚሰጣትን እርዳታ መጠቀም መቻሏ ነው። ብዙ ኣገሮች እርዳታ እያገኙም ማደግ ያልቻሉ ሲሆን ደቡብ ኮርያ ለዓለም ያስተማረችው ትልቁ ጉዳይ እርዳታን ለእድገት መጠቀም መቻሏ ነው። በዚያው በ1970ዎቹ የኮርያ ወርቃማ ዘመናት ጊዜ ፕሬዚደንት ፓርክ ያቋቋሙት ሴማእል ኡንዶንግ የተባለው ድርጅት በተለይ ለገጠሩ ክፍል እድገት ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣድርጓል። ይሁን እንጂ ሴማእል ኡንዶንግ (ኣዲስ ንቅናቄ)የተሰኘው የልማት ድርጅት በገጠሩ ወይም በእርሻ ላይ ያተኮረ ስራ የቱንም ያህል ቢሰራ ሃገሪቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሊለውጣት ኣይችልም ነበር። ምክንያቱም ኮርያ በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገች ኣገር ኣይደለችም። እስካሁንም በከፍተኛ ሁኔታ የጥራጥሬ እህሎችንና ጥሬ ሃብቶችን ከውጭ ነው የምታስገባው። ካላት ዝቅተኛ የተፈጥሮ ሃብት የተነሳ ለማደግ ኣቅጣጫዋን ወደ ኢንዱስትሪው እንድታዞር ኣድርጓታል። በርግጥ ሴማእል ኡንዶንግ በገጠር ያለውን ማህበረሰብ በማህበራዊ ኣገልግሎት ኣቅርቦት፣ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ስራ በኣጠቃላይ የእርሻውን ስራ በከፍተኛ ሁኔታ የለወጠው ሲሆን ከሁሉ በላይ የፈጠረው የህብረተሰብ መነሳሳት(community mobilization)ወዲያው ወደ ኢንዱስትሪው ኣካባቢም መንፈሱ በመዛመቱ ከፍተኛ የሆነ ለእድገት የመነሳሳት ሁኔታን ፈጥሮ ነበር። በዚያው በ1970ዎቹ ጊዚያት የመሰረተቻቸው ኢንዱስትሪዎች መንቀሳቀስ ሲጀምሩ እድገቷን የናፈቁ የዓለም ህዝቦች የመጀመሪያ ምርቶቿን በመግዛት በማበረታታት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ሲሆን ኣሜሪካ ከፍተኛ ድጋፍ ኣድርጋለች። ከዚህ በተጨማሪም 1970ዎቹ በዓለም ታሪክ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገቶች የተመዘገቡበት ኣስርታት በመሆኑ ኣጠቃላይ ከባቢው ለእድገት ኣስተዋጾ ነበረው። ከሁሉ በላይ ደግሞ የህዝቡ ጠንካራ ሰራተኝነት ለኮርያ የኢኮኖሚ ጥርመሳ ከፍተኛ ኣስተዋጾ ኣድርጓል። በዚያ ጊዜ ኮርያውያን በተመቸ የኣስተዳደር ስርዓት ውስጥ ስለ ነበሩ ዓይደለም ያደጉት። ወይም ዲክተተርሺፕ ለኮርያ እድገት ኣስተዋጾ ኣላደረገም። የሆነው ምንድነው ኮርያውያን በኣንድ በኩል ኢኮኖሚውን እያሳደጉ ጠንክረው እየሰሩ በሌላ በኩል ደግሞ ዲክቴተርሺፕን ይቃወሙ ነበር። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኣጠቃላይ ህዝቡ ለዓመታት ታግለው በመጨረሻም ኣምባገነናዊ ስርዓትን ለመገርሰስ ችለዋል። ኣምባገነኑን መንግስት ጥለው ወደ ዴሞክራሲ ጎዳና ከገቡ በሁዋላ የሚያስገርም የኢኮኖሚ እድገቶችን ማስመዝገብ ጀምረዋል። በኣጠቃላይ የኮርያን እድገት መነሻዎች ስናይ በብዙ መልካም ከባቢዎች ውስጥ የታጀበ መሆኑን እንረዳለን።ለዴቨሎፕመንታል ስቴት ምሳሌ ከሆኑት የምስራቅ እስያ ኣገሮች መካከል የኮርያ የእድገት ሁኔታ እዲህ የሚታይ ሲሆን ሌሎቹንም ብናይ በርግጥ ዲክተተር መሆን ኣላሳደጋቸውም ወይም መንግስታቱ በገበያው መሃል ጣልቃ በመግባታቸው ኣይደለም እድገት ያመጡት። ለኢኮኖሚ እድገት ቀጥተኛ ኣስተዋጾ ያላቸው ጉዳዮች በመገጣጠማቸውና ጠንክረው በመስራታቸው ከሁሉ በላይ ደግሞ ኢንቨስመንት በመሳባቸው የተመቻቸ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመንደፋቸው ነው።
ለኣንድ ኣገር የኢኮኖሚ እድገት ጥርመሳ መንግስት ኢኮኖሚውን መቆጣጠር ኣለበት የሚሉ ወገኖች ከሚያነሱት ኣሳብ መካከል ኣንዱ መነሻ ላይ ግለሰቦች ታላላቅ የሆኑ ኢንቨስትመንቶችን ለማንቀሳቀስ ኣይችሉም፣ ዜጎች ለብዝበዛ ሊጋለጡ ይችላሉ፣ ከግለሰቦች ኣካባቢ የኣቅም(capacity) ችግር ስለሚኖር መንግስት የተደራጀ ነውና ኢኮኖሚውን ቢቆጣጠር ኣመርቂ ውጤት ያመጣል የሚሉ ዋና ዋና ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ የሊብራል ኣስተሳሰብ ያላቸው ወገኖች ከፍ ሲል እንዳልነው በመንግስት ጣልቃ ገብነትና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት የለም እንዴውም የመንግስት ጣልቃ ገብነት ለኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ ኣስተዋጾ ያለውን ኣንዱን ኢለመንት ማለትም ኢንተርፕሩነርሺፕን ያጠፋና እድገቱን ያዘገየዋል ከሁሉ በላይ የእኩልነት የብዝበዛ ጉዳዮችን መንግስት የሚያስተካክልበትን ሜካኒዝም ሊፈጥር ይችላል። በገበያ መሃል መግባቱ መፍትሄ ኣያመጣም የሚሉ ናቸው። ከሁሉ በላይ ያለው ስጋት ደግሞ መንግስት በኢኮኖሚ እየበረታ ሲሄድ የራሱን መደብ ፈጥሮ የተጠራቀመውን ገንዘብ መጨቆኛ ሊያደርገው ይችላል። ግለሰቦችን እያደኸዩ መንግስትን ማደለብ ኣደጋ ኣለው። ኣሳቡ ራሱ ኣንድ ፓርቲ በስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ እንዲቆይ የሚያበረታታ ኣዝማሚያ ስላለው ሃብት መጮቆኛ ሊሆን ይችላል ብለው ይሰጋሉ። መንግስት በገበያ መሃል ጣልቃ በመግባቱ እድገት የሚመጣ ቢሆን የደርግ መንግስት ከማምረቱ ጀምሮ EDDC (Ethiopian Domestic Distribution Corporation) መስርቶ እስከ ማከፋፈሉ ተቆጣጥሮት ኣልነበረም ወይ? እድገት መቼ መጣ? ጎረቤት ኣገሮች ሁሉ ኢትዮጵያን ጥለዋት ኣልሄዱም ወይ? የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ይልቁን መንግስት የግል ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ የውጭ ንግድን መሳብ የሚገባ ሲሆን፣ ሊከሰቱ ይችላሉ ተብለው የሚፈሩትን ችግሮች ለመግታት መንግስት ለኢንቨስተሮች ከፍተኛ የምክርና የሰለጠነ የሰው ሃይል ድጋፍ ሊያደርግ ነበር የሚገባው።ጣልቃ ገብነቱ በዚህ መንገድ የሚገለጽ ቢሆን ይመረጣል ለማለት ነው። ኢንቨስተሮች ለትርፍ ብቻ የሚነሱ ስግብግብ ኣድርጎ ማሳብ ትክክል ኣይደለም። የኣገልግሎት ሰጪነት ስሜት ያላቸው፣ ከትርፍ ይልቅ ኣገልግሎት በመስጠት ልባቸው የሚረካ ዜጎች ኣሉ። በቅርቡ እንኳን ኣቶ ብርሃነ መዋ ሲናገሩ ልብ የሚነካ ነገር ነው። እኚህ ሰው ሚሊየነር ሆነው ቤት እንኳን ኣልሰሩም። ይደክሙ ይሰሩ የነበሩት ውስጣቸው ለተቀመጠው የህዝብ ኣገልጋይነት ጸጋ ነበር። እንዲህ ኣይነት ዜጎች ስላሉ መንግስት ራሱን የተለየ ኣድርጎ ሃላፊነት የሚሰማው እሱ ብቻ እንደሆነ ኣድርጎ ማሰቡ ከመነሻው የተሳሳተ ነው።ሌላው ጉዳይ በተለምዶ ልማታዊ መንግስት የሚለው ጉዳይ በርግጥ ቀን የጣለው ነው። ከለውጥ ጋርና ከሰው ልጆች እድገት ጋር ኣብሮ መሄድ ኣይችልም። ዛሬ በግሎባላይዜሻን ዘመን፣ የሰው ልጆች ስለ ሰብዓዊ መብትና ስለ ዴሞክራሲ በነቁበት ዘመን የዛሬ ኣምሳ ኣመት የነበረውን ኣሰራር ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ኣስቸጋሪ ነው። መንግስት ኣንዱ ትልቁ ጥራቱ ለውጥን የተረዳ ሲሆን ነው። የቴክኖሎጂ እድገትና የሰው ልጆች የማህበራዊ ሳይንስና የተፈጥሮ ሳይንስ እውቀት እየጨመረ መሄድ ኣለምን ወዴት እየወሰዳት እንዳሆነ መገመት ተገቢ ነው። ቴክኖሎጂው እና ንግድ እንዴት ኢንተር ዲፐንደንሲን እየፈጠረ እንደሚመጣ ማየትና መተንተን ብሎም ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ነው። የዓለም ህዝቦች ግንኙነት እየጠበቀ እርስ በርስ የመተዋወቁና የመቀራረቡ ጉዳይ እየገፋ ነው የሚሄደው። የብዙ ያላደጉ ኣገሮችን ውስብስብ ችግር መፍቻ ከሆኑት ቁልፎች መካከል ኣንዱ ኣለማቀፋዊ ትብብር መሆኑን መረዳትና ክፍትነት(oppennes) በጣም ኣስፈላጊ ነው። ራሺያን ከገባችበት ኣዘቅት የታደጋት የሚካኤል ጎርቫቾቭ የውጭ ፖሊሲ መሻሻልና ለሌላው ዓለም ክፍትነትን ማሳየት በመቻሉ ነው።
የሊብራል ፖለቲካል ኢኮኖሚ ዋና መነሻ ዜጎች ገበያውን ይምሩት፣ ኢንተርፕሩነርሺፕን እናበረታታ የሚል ሲሆን ይህ ኣሳብ የሚፈልቀው ከጽኑ የዴሞክራሲ ኣስተሳሰብም ነው። ዜጎች የሚመሩት ገበያ እርስ በርሱ የሚያጫርስ ኣድርጎ ማሰቡ በዜጎች የሃላፊነት ስሜት ላይ መረማመድ ነው።ወይም ከባለፈው የኮሚኒዝም ትምህርት የመጣ፣ የቀዝቃዛው ጦርነት ፕሮፓጋንዳ የወለደው ማስፈራሪያ ሊሆን ስለሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ተገቢ ነው። ወደድንም ጠላንም ኣለም ነጻነትን (liberty) በሁሉም የህይወት ኣቅጣጫዋ እያስከበረች ነው። በዚህ ጊዜ ከውጪያዊና ውስጣዊ ለውጥ ጋር ተጋጭቶ ለመኖር መሞከር እድገትን ይጎዳል።
የዴቨሎፕመንታል ስቴትስ ችግራቸው በገበያው ጣልቃ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ለኢኮኖሚ እድገት ቅድሚያ ለመስጠት ሌሎች ጉዳዮችንም መጎተታቸው ነው። ከነዚህ ጉዳዮች መካከል የፕሬሱን ጉዳይ እንይ። ፕሬሱን ልማታዊ ሁን በማለት ትኩረትን ወደ ኣንድ ኣቅጣጫ በመሳብ በመንግስት ላይ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ሂሶችን ለመገደብ ይሞክራሉ። ይህ ዝንባሌ በርግጥ ለኢኮኖሚ እድገት ይጠቅማል ከሚል ሳይሆን በስልጣን ላይ ለመቆየት ይጠቅመኛል ከሚል ስሜት ነው። ፕሬሱን ማቀዝቀዝ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችንም ይዘጋል። በተለይ በሰባዊ መብትና በመልካም ኣስተዳደር ኣካባቢ የሚሰሩትን እያባረረ ለኢኮኖሚ እድገት ቅድሚያ ሰጥቻለሁ “ልማታዊ ነኝ” በሚል ሽፋን የዴሞክራሲን እድገት ያቀጭጫል።
ከሆነስ ሆነና ኢትዮጵያ የልማታዊ መንግስት ኣገር ናት ወይ?
ኣጠቃላይ የሆነን በልማታዊ መንግስት ላይ ያለውን ያልጠራ ጉዳይ ሁሉ ትተነው እንደሚባለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይኑር እንኳን ቢባል ኢትዮጵያ ከባቢው ኣላት ወይ? ብለን እንጠይቃለን። ይህንን ጉዳይ ስንመረምር በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ጠንካራ ብሄራዊ ስሜትን እየገነባች ያለች ኣገር ኣለመሆኗ ብቻ ሳይሆን ያላት የፖለቲካ ስሪት የጋራ ሃብትን በመንግስት ካዝና ለማፍራት እምነት የሚጣልበት ስርዓት ኣልገነባችም። በሌላ በኩል በኢንዱስትሪው ንግድ ውስጥ የጦፈ ነጋዴ የሆነው መንግስት ሳይሆን ፓርቲዎች ሆነው ነው የሚታየው። ለዚህ ኤፈርትን መጥቀሱ ይበቃል። ኤፈርት በህወሓት የተመሰረተ ኣሁንም በህወሃት ማእከላዊ ቢሮ ኣባላት የሚመራ ንብረትነቱ የቡድን የሆነ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ድርጅቶች ሁሉ የሚበልጥ ሲሆን ወደ መቶ የሚጠጉ ድርጅቶችን የሚያንቀሳቅስ የንግድ ተቋም ነው። ኢትዮጵያዊያን ይህ ድርጅት እየደለበልን ነው ኣንድ ቀን ችግራችንን ይፈታል ብለው ተስፋ ኣያደርጉም። ምክንያቱን ራሱ የፖለቲካው ተፈጥሮ ለዚህ ከባቢ እምነት (trust) የሚፈጥር ባለመሆኑ ነው።በኣጠቃላይ ኢትዮጵያ ባላት የፖለቲካ ኣሰላለፍ ልማታዊ መንግስት ለመሆን ኣትችልም። ዘውጌ የፖለቲካ ኣስተሳሰብን ይዞ ዴቨሎፕመንታል ስቴት መገንባት ኣይቻልም ለማለት ነው። ይህን ያመጣሁት እንዴው ሌላውን ሁሉ ትተነው ዴቨሎፕመንታል ስቴት የሚባለው ከለውጥ ጋር የማይሄድ መሆኑን ሁሉ ትተነው በመንግስት ጣልቃ ገብነት የኢኮኖሚ ጥርመሳ እናመጣለን ለማለት የሚያስችል የፖለቲካ ቅርጽ እንኳን ኢትዮጵያ የላትም ለማለት ነው።
ከዚህ በፊት በ 2009 “Unbalanced growth strategy a potential for conflict in Ethiopia” በሚል ኣርቲክል ላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው የሙስና መስፋፋት፣ የእምነት(trust) መውረድ የተቋማት ነጻ ኣለመሆን ከፍተኛ የሆነ ተስፋ ማጣትን (uncertainity about the future) ስላመጣ ኢትዮጵያ ዴቨሎፕመንታል ስቴት ለሚባለው ጉዳይ የማትመች ኣድርጓታል። ይልቁን መንግስት ልማታዊ መንግስት ነኝ የሚልበት ትልቁ ምክንያት ዴሞክራሲን ለማስረሳትና በኢኮኖሚ እድገት ለመደለል ብሎም በስልጣን ለመሰንበት ነው። ይህ ኣዝማሚያ ግን የሚያዋጣ ባለመሆኑ ዛሬ የልማታዊ መንግስትነት ስያሜ ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ መቀለጃ ኣድርጎታል።
የኢትዮጵያ መንግስት ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ ለልማታዊ መንግስትነት ኣብነት ኣድርጎ የሚጠቅሳቸው ኣገሮች ሁሉ ለእድገታቸው የተለያዩ ፋክተርስ ያለ ሲሆን ኣምባገነን በነበሩበት ሰዓት እድገት የጀመሩትን ከዓለም ላይ ስማቸውን እየነቀሱ እያወጡ ኣምባገነን መሆን፣ ነጻነትን ነፍጎ በገበያ ጣልቃ ገብነት እናድጋለን ማለት ስህተት መሆኑን ነው። ሌላው ኣንዱ የመንግስትን ጣልቃ ገብነት የሚደግፉ ሰዎች የሚሉት ጉዳይ ደግሞ ሃብትን ለመቆጣጠር ይረዳል ይላሉ ነግር ግን ኣፍሪካ በየዓመቱ ሃምሳ ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ ታጣላች ሲሉ የቀድሞው የደቡብ ኣፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦን ቤኪ በቅርብ ጊዜ ተናግረዋል። ሃብት በኣንድ ሃገር በሚገባ ሊጠበቅ የሚችለው በግል ነው። ዜጎች ሁሉ ሃብታቸውን ነቅተው ይጠብቃሉ። በተግባር እንደሚታየው በከፍተኛ ሁኔታ ዝርፊያ ያለው በግሉ መስክ ሳይሆን በመንግስት መስሪያ ቤቶች ኣካባቢ ነው።
የኢትዮጵያ መሰረታዊ የኢኮኖሚ ችግር የት ነው እንዴትስ ይፈታል?
የሚያሳዝነው ችግሮቻችን ከባድ ኣልነበሩም። የከበደን የኢትዮጵያ መንግስታት ኣልሰማ ማለታቸው፣ ቅድሚያቸው ለራሳቸው የስልጣን ጊዜ በመሆኑ ነው። ኢትዮጵያ በኣሁኑ ሰዓት ትልቅ ችግር ሆኖባት ያለውና በኣስቸኳይ ሊፈታ የሚገባው የምግብ ዋስትናና የድህነት ጥግ (extreme poverty) ጉዳይ ነው። ይህ የሚፈታው ደግሞ እነደነ ኤፈርት ኣይነቱ ድርጅት ከተማ ከተማውን ስላውደለደሉ ኣይደለም። ብዙ ኢኮኖሚስቶች እንደሚያምኑት ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ጥርመሳ ውስጥ ለመግባት ግብርናውን የመለወጥ ስራ መሰራት ኣለባት።ኣንዳንድ ወገኖች ግብርናው ላይ ያተኮረ ስራ መስራት ያስፈልጋል ሲባል ከተማው ችላ የተባለ ይመስላቸው ይሆናል። ግን ኣይደለም። ኣጠቃላይ የሃገሪቱን ምርት ከፍ ለማድረግ የትኛው መንገድ ይመረጣል ለማለት እንጂ ከእድገቱ ተጠቃሚው ሁሉም ዜጋ ነው። ዓላማው የሃገሪቱን ጂዲፒ ከፍ በማድረግ ያንድን የህብረተሰብ ክፍል ከመጥቀም ጋር የተያያዘ ኣይደለም።
ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የሚገልጻትን ኑሮዋን እንመልከት። ለምሳሌ ኣንድ ገበሬ ገብስ ያመርታል እንበል። ይህ ገበሬ በሬውን ተጠቅሞ፣ ኣነስተኛ መሬት ላይ ኣብቅሎ፣ በኣብዛኛው በጥንታዊ መንገድ ኣርሞ፣ ኣጭዶና ወቅቶ ወደ ጎተራው ካስገባ በሁዋላ ለሚፈልጋቸው ኣንዳንድ የኑሮው ጉዳዮች ማለትም እንደ ጨው፣ ጋዝ የመሳሰሉትን ለመግዛት ሲሻ ካለችው ላይ ይቀንስና በኣህያ ጭኖ ወደ ከተማ ይዞ ይወጣል። ከተማ ውስጥ ሜዳ ላይ በተኮለኮሉ ገበያዎች ላይ ይዘረጋና ከተማ ላሉት ሰዎች እየሰፈረ ይሸጣል። የቀረችውን ገብስ ደግሞ ግማሹን እየቆላ ግማሹን ወይ ሚስቱ በድንጋይ ፈጭታ ወይ በባቡር ወፍጮ ኣስፈጭቶ ዱቄትና ውሃን ኣገናኝቶ እየጋገረ ይበላል። ከተማ ውስጥ ያለው ሰውም ልክ ገበሬው እንዳደረገው ኣስፈጭተው እየጋገሩ ይበላሉ።በገበሬውና በከተሜ መካከል ያለው መስተጋብር ድሮ ጊዜ እንደነበረው ቀጥታ ግንኙነት ነው። ከተማ ወይም ገጠር ያለው ሰው ገብሱን ጠላ ማድረግ ከፈለገ ኣንድ ኩንታል በእሳት ኣቃጥሎ ኣሻሮ ኣድርጎ ጥቂት ጠላ ይወጣውና በዚያ ለመደሰት ይሞክራል። ገበሬው በገብስ ውስጥ እስካሁን ያየው ኣቅም(potential) ጥቂት ሲሖን በነዚያ ዙሪያ ብቻ በጥንታዊው መንገድ እየተጠቀመ ይኖራል። የኢትዮጵያ የግብርና ችግር ያለው እዚህ ጋር ነው። በተጠቃሚውና በኣምራቹ መካከል መሃል ላይ ሰንጥቆ የገባ ሳይንስ የለም። ገበሬውና ከተሜው ቀጥታ እየተገናኙ በዱሮው የኣኗኗር ዘይቤ እየተጠቀሙ ስለሚኖሩ በምግብ በኩል ያለን ዋስትና ሳይሻሻል ቆየ። በመሃል የመጣው ክፍተት(gap) የግብርናው ኢንዱስትሪ ኣለመስፋፋቱ ሲሆን ይህ ኢንዱስትሪ ቢስፋፋና ምርቱን በቴክኖሎጂ ሂደት ውስጥ ኣስገብቶ ኣባዝቶ፣ ኣክሞ፣ ፕሪዘርቭ ኣድርጎ ወደ ተጠቃሚው ቢያደርስ የምግብ ዋስትናቸን ይረጋገጥና በዚያ በኩል የኢኮኖሚ ጥርመሳ ውስጥ ለመግባት ይቻላል። የኢትዮጵያ የዘመናት የምግብ ዋስትና ኣለመረጋገጥ ችግር የመጣውና ኣሁን ድረስ ፈተና የሆነብን በቂ ምርት ስለማናመርት ብቻ ኣይደለም። ኣልፎ ኣልፎ ተረፈ ምርትም ይገኛል። በልግ ወይም መኸር ሲሰጥ ምርት የሚትረፈረፍበት ጊዜ ነበር ። ይሁን እንጂ ምርት በሰጠ ሰዓት ገበሬው ለጋስ ይሆንና ወደ ከተማ ሄዶ ሲሸጥ ከተሜው የሚገዛው ሁል ጊዜም በሚፈልጋት በወር ቀለቡ ልክ ብቻ ነው። ኣንድ ጊዜ በ1990 ዎች ኣካባቢ በቆሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተመርቶ ነበር። የኣንድ ኩንታል በቆሎ ዋጋ እስከ ሃያ ብር ድረስ ወርዶ ገበሬው የሚገዛው ኣጥቶ ሲንከራተት ነበር። ያቺ ሃያ ብር የገበሬውን የትራንስፖርት እንኳን ኣትሸፍንም። ትንሽ ኤክስፖርት ለማድረግ የተሞከረ ቢሆንም ግን ገበሬውን ገዝቶ ፕሪሰርቭ ለማድረግ እንኳን ኣልተቻለም ነበር።ይህ ችግር የመጣው በመሃል የተፈጠረ ክፍተት ስላለ ሲሆን ይህ ክፍተት የግብርናው ኢንዱስትሪ ኣለመስፋፋት ነው። ይህንን ምርት እየገዛ ፕሪዘቭ ቢያደርግ በቆሎን በተለያየ መንገድ እያዘጋጀ ወደ ተጠቃሚ ቢያደርስ ኣክሞ ኣባዝቶ ቢሸጥ ምርቱ ይበዛል ገበሬውም ለፍቶ ለፍቶ የልፋቱን ዋጋ ያገኘል። ጃፓኖችና ኮርያዊያን ቻይናዎች በሩዝ ውስጥ ያለውን ኣቅም በሚገባ እየተጠቀሙበት ነው። የሩዝ ቅባት፣ የሩዝ ዳቦ፣ የሩዝ ኣይብ የሩዝ ብስኩት፣ የሩዝ ፓስታና ማኮረኒ የሩዝ ዘይት፣ የሩዝ ኬክ፣ ስንቱ ተዘርዝሮ። በኢትዮጵያ ውስጥም የግብርናው ኢንዱስትሪ መጠናከሩ የሚጠቅመው ያሉንን እጅግ ብዙ ኣዝርእት እያባዛን ብዙ ነገር ኣድርገን እየሰራናቸው የምግብ ዋስትናችንን ለማስከበር ያስችለን ነበር።የግብርናው ኢንዱስትሪ ጣልቃ መግባት ያለበት ብዙ ለማምረት የሚያስችሉ ግብዓቶችን መጠቀሙና ማቅረቡ ላይ ለመስራት ብቻ ሳይሆን የተመረተውን ምርት ማከም፣ ማባዛትና መጠበቅ የሚያስችል ሂደት ስለሚያስፈልግ ነው። በኣሁኑ ጊዜ ዘይት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ይሰማል። ዘይትን ከኑግና ከሰሊጥ ብቻ መጠበቃችን እና የኑግና የሰሊጥ ምርት ደግሞ ለውጭ ምንዛሬ ትንሽ ደለብ ያለ ገንዘብ ስለሚያስገኝ መንግስትም ወደ ውጭ በመላኩ የሚያገኘው ዶላር ስላጓጓው ዘይት በሃገራችን ኣልቀመስ ኣለ። የሚገርመው ግን ይህንን የዘይት ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት ከሌሎች ኣዝርእት ለምን በስፋት እንደማይሰራ ነው። ለምን የገብስ፣ የስንዴ፣ የበቆሎና የሌሎች ኣዝርዕቶች ዘይት ኣይመረትም? ብለን ብንጠይቅ ዞሮ ዞሮ ያው ቅድም ያነሳነውን ክፍተት ማለትም የግብርናውን ኢንዱስትሪ ኣለመጠናከር ነው የሚነግረን። እነዚህ ኣዝርዕቶች ሁሉ ለምግብ ዘይት ለመሆን የሚችል እምቅ ሃይል ኣላቸው ነበር። በፍራፍሬም በኩል ያለው ችግር ይሄው ነው። ኣንዴ በኣንድ ወቅት የሚመረትን ፍራፍሬ በሁዋላ ቀር መንገድ ስለምንጠቀምበት ሳይባዛ ይቀርና የፍራፍሬ ፍላጎታችንን ሳያሙዋላ ቀረ። በስጋ በኩል ደግሞ ምንም እንኳን ብዙ የቀንድ ከብት ቢኖረንም በስጋ ምርት በኩል በጣም ዝቅተኛ የሆነ ኣቅርቦት ነው ያለን። ብዙ ከብት መኖሩ በኣንድ በኩል ከፍተኛ ማስጋጥ(over grazing) ስለሚያመጣ መሬቱን በማራቆት በኩል ከፍተኛ ችግር ያመጣል። ለስጋ የሚሆኑ ከብቶችን ሰብሰብ እያደረጉ የማድለብ ስራ ለብቻው መስራት ከባድ ኣልነበረም።ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ኣመጋገብ ባህል ያለን በመሆኑ እንደየ ባህሉ በኣጭር ጊዜ በብዛት ሊራቡ የሚችሉ የእንስሳት ዓይነቶችን ማርባት ለስጋ ምርት ኣቅርቦት ይረዳል። ከዚህም በላይ ገበሬውን ከሁለገብ የእርሻ ባህል እያወጡ ወደ ኣንድ የግብርና ስራ እንዲያተኩር የማድረግ ስራም መስራት ያስፈልጋል። ለዚህ ሁሉ የግብርናው ኢንዱስትሪ መስፋፋት በኢትዮጵያ ውስጥ ወሳኝ መሆኑን ያሳያል።ሌላው ጃፓኖች ይጠቀሙበት የነበረ ኣንድ መንደር ኣንድ የተለየ ምርት(one village one special product) ለኢትዮጵያ ትልቅ ትምህርት ይሆን ነበር። በዝንጅብል የሚታወቀውን ኣካባቢ ሌላን ችላ ብሎ ዝንጅብል ላይ እንዲያተኩር፣ ሁለገቡን ችላ ብሎ ሃይሉንና ጉልበቱን ወደ ኣንድ ኣቅጣጫ እንዲያዘነብል ማድረግና ገበያ መፍጠር ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ሚና ኣለው። ሌላው ደግሞ የገበሬውን ኣሰራር ለመቀየር በሁሉም ገበሬ ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ከማቃመስ ይልቅ ኣንድ ፐርሰንት ሊሆን የሚችልን ገበሬ ይዞታውን በማስፋት ወይም በማስፈር ይህንን ኣነስተኛ ቁጥር ያለውን የለውጥ ሃዋርያ ኣድርጎ ሜካናይዝድ በማድረግ በነዚህ ጥቂት ገበሬዎች የኢትዮጵያን የምግብ ኣቅርቦት ማሻሻል ይቻላል። የኢትዮጵያ ገበሬ የማይሞክረው የለም። ቅይጥ እርሻ (mixed farming) የሚባለውን እርሻ እየሰራ ሁሉንም እየሞከረ የሚኖር ነው። ይሄ የሚበረታታ ኣይደልም።ይህን ገበሬ ከእንዲህ ዓይነቱ ኣሰራር እያወጡ በኣንድ የግብርና ስራ ላይ እንዲያተኩር ማድረጉ ምርት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል ለሺህ ዓመታት በበሬ የሚያርሰውን ገበሬ ኣራትና ኣምስት እየሆነ በቡድን ኣንድ ትራክተር እንዲገዛ ማድረግ ይቻላል። ይህ ገበሬ ይህን ለማድረግ የበሬው ዋጋ ይበቃዋል። ይህን ማድረጉ ጥቅሙ ኣንደኛ ከፍተኛ ማስጋጥን ስለሚቀንስ የመሬቱን መሸርሸር ይቀንሳል። በሌላ በኩል በሬ በመጠበቅ ስራ ምክንያት ከትምህርት ያስቀረውን ልጁን ወደ ትምህርት ቤት ይልካል። በኣመት ሁለቴና ሶስቴ ለማረስ ሲል በየቀኑ የሚቀልበውን በሬ ወጪ ስናየው ብዙ ስለሆነ ከወጪም ይተርፋል። በሌላ በኩል የማድለብ ዝንባሌ ያለው ገበሬ ይህን ስራ በዘመናዊ መንገድ ኣድልቦ እንዲሸጥ እድሉን ያሰፋለታል። መሬት የግል መሆኑ ኣንዱ ጠቀሜታው ኣንዳንድ ገበሬዎች መሬታቸውን ሸጠው ወደ ሌላ የግብርና ስራ እንዲሰማሩ እድል ስለሚሰጥ ነው። መሬቱን የሸጠው ገበሬ ለምሳሌ የእርባታ፣ የወተት ምርት ወይም ሌሎችን ስራዎች ሊሰራ ሲችል ኣነስተኛ መሬት የነበረው ሰው ደግሞ ሌላ ገዝቶ መሬት ሲጨምር የተሻለ ምርትን ማምረት ይጀምራል። የመሬት ባለቤትነት ሲረጋገጥ ገበሬው መሬቱን እየሸጠ ጥሎ ይሄዳል ብሎ ማሰብ ተላላነት ነው። ገበሬው ሞኝ ኣይደለም። ከሸጠም ሾጦ ሊሰራ ላሰበው ጉዳይ መነሻ እንዲሆነው ነው። ኣንዳንዴም የራሱን መሬት ሸጦ ሌላ መሬት ሊገዛም ሊያስብ ይችላል። ኣንድ ስለ ልጆቹ ስለ ራሱ የሚያስብ ገበሬን ሸጦ ከተማ ይገባል ወይም ገበሬው ሁሉ እየተነሳ ይሸጥና የድሮው የፊውዳል ጊዜ ይመለሳል ማለት የኢትዮጵያን ገበሬ ኣለማወቅ ነው። ይልቅ ከፍ ሲል እንዳልኩት የመሬት ባለቤትነት መብት ሲረጋገጥ ገበሬው ከኣንድ የእርሻ ስራ ወደ ሌላ የእርሻ ስራ ለመዛወር መነሻ ሊሰጠው ይችላል።
ሌላው ጉዳይ ኣንዳንድ የገበሬ ልጆች ወደ ከተማ የመፍለሳቸው ጉዳይ መንግስትን ሊያሳስበው የሚገባ ጉዳይ ኣልነበረም። ይሄ ሂደት የለውጥ ሂደት ውጤት ነው። በተግባር እንደሚታየው ባደጉ ኣገሮች ሁሉ የገበሬው ቁጥር እየቀነሰ ነው የሚሄደው። ይሄን ማቆም ኣይቻልም በጎም ነው። ከተሜነት ሲጨምር ኣንዱ የእድገት ነጂ የሆነው የፍላጎት ሃይል (Demand force)እንዲጨምር ስለሚያደርግ ለእድገት ኣስተዋጾ ኣለው። ኣሜሪካንን ብናይ የገበሬው ቁጥር ሁለትና ሶስት ፐርሰንት ነው። ጃፓንን ብናይ ከኣንድ ፐርሰንት በታች ነው። ግማሽ ሚሊዮን እንኳን የማይሞላ ገበሬ ነው ያላት። በመሆኑም ኢትዮጵያም የገበሬው ቁጥር እየቀነሰ የመሬት ይዞታ እየሰፋ መሄዱ መልካም ሲሆን ከገጠር ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ገበሬ ኣዳዲስ በሚፈጠሩ የግብርና ኢንዱስትሪዎች ላይ የማሰማራት ስራ መስራት ኣስፈላጊ ነው።ሌላው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በዝናብ ላይ ብቻ ጥገኛ የሆነውን ገበሬ ለምን በኣካባቢው ያሉትን ወንዞች እንዲጠቀም እንደማይደርግ ኣይገባም። ከወንዝ የሚገኝን ውሃ በርቀት ማሳ ላይ ወስዶ ማፍሰስ እንዴት ይሳነናል። ለዚህ ከባድ የሆነ የመስኖ ልማት ስራም ኣያስፈልግም። ቢያንስ እዚያው ኣገር ቤት ሊመረት የሚችል የሸራ ቧንቧ ሰርቶ ማኑዋል በሆነ የውሃ መግፊያ መሳሪያ ውሃን ኣስፈንጥሮ ማሳን ማጠጣት በጣም ቀላል ስራ ሲሆን ይህን በስፋት ኣናይም። በከፍተኛ ወጪ የሚሰሩ የመስኖ ግድቦችን እያቀድን ገበሬውን ሳንደርስለት ሳናሳየው በመቅረታችን ያሳዝናል። የሸራ ቧንቧ ቢሰራና የእርሻ ተማሪዎች ኣንድ ማኑዋል ማሽን ቢፈጥሩ ገበሬው ከወንዙ ራቅ ያለ ቦታ ሳይቀር ደርሶ ሊያለማ ይችል ነበር። ባለፈው ጊዜ ኣንድ የሚገርም ዜና ተሰማ። በመላው ኣገሪቱ ገበሬው ውሃ ኣቁር ተብሎ ጉድጓድ ሲቆፍር ከረመ። ሁዋላ ላይ ዝናብ ሲመጣ ጉድጓዱ ውሃ ይሞላና ሲያበቃ ክፍቱን ስለሆነ ኣንዳንዴ ጥጆች ኣልፎ ኣልፎም ህጻናት ገቡ ተብሎ ከላይ በመጣ ትእዛዝ የተቆፈረው ጉድጋድ እንዲደፈን ተደርጓል። ሌሎች የተፈጥሮ ምንጮችና ጉድጓዶች ይህ ኣዋጅ ሲመጣ ምን እንደዋጣቸው ኣልታወቀም። በስንት ወጪ የተቆፈርን ጉድጓድ እንደገና ጥጃ ኣለቀ ተብሎ የወባ መራቢያ ሆነ ተብሎ ድፈኑ ተባለ። እንዴት መክደኛ ማበጀት ይሳነናል? የሚለው ይገርማል።ገበሬውስ ኣይታዘብም ወይ? ነገ የምናስተምረው ትምህርት ላይ እምነት ኣያጣም ወይ? ብለን ማሰብ ያስፈልጋል።ለዚህ ስህተት ይቅርታስ የጠየቀ ኣካል ይኖር ይሆን? ይሄ በሃገሪቱ የግብርና ኤክስቴንሽን ስራ ላይ ከፍተኛ ኣሉታዊ ተጽእኖ ኣለው። ገበሬው እምነቱ እንዲሳሳ ስለሚያደርግ ሌላ ኣዲስ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ለማስረጽ ከባድ ፈተና ያመጣል። ከመነሻውም ቢሆን የሆነ ፓይለት ሙከራ ሳይደረግ በሙሉ በሃገሪቱ ጉድጓድ እንዲቆፈር መደረጉ ምናልባትም ከሙያተኞች ኣካባቢ ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔም ይመስላል።ሌላው ድርቅን ለመቋቋም የሚረዳን ደግሞ የከርሰ ምድር ውሃን በተገቢው መንገድ መጠቀም ነው። ዋናው ለማለት የፈለኩት ጉዳይ ችግሮቹ ከባድ ሆነው ሳይሆን ቀለል ያሉ መፍትሄዎችን ያለማየት ነገር ይንጸባረቃል። ኣንድ ጊዜ ኣንድ መንፈሳዊ ሰው ሲያስተምሩ የሰማሁት ታሪክ በምናቤ ሲታየኝ ይኖራል። እኚህ ሰው ያስተምሩ የነበሩት ስለ ኣጋር ነበር። ኣጋር በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተጠቀሰው የኣብርሃም እና የባለቤቱ የሳራ የቤት ሰራተኛ ነበረች። ሁዋላ ላይ ከኣብርሃም ጋር በነበራት ግንኙነት ምክንያት ልጅ ትወልዳለች። ሳራ ጠልታት ነበርና ከእለታት ኣንድ ቀን ከቤት ኣስወጥታ ኣባረረቻት። ኣጋር ረጅም ጉዞ ተጓዘች።በቤርሳቤህ ምድረ በዳ ተንከራተተች።የኣብርሃም ሚስት ሳራ የሰጠቻት ኣንዲት ኣቁማዳ ውሃ ኣለቀች። እሷና ልጇ በውሃ ጥም ተቃጠሉ። በተለይ ልጁ በውሃ ጥም ምክንያት ሊሞት ደረሰና ማቃሰት ሲጀምር የልጁዋን ሞት እንዳታይ ብላ ፈንጠር ብላ ታለቅሳለች። ሁዋላ ላይ የእግዚኣብሄር መልዓክ ተገለጠላትና የህጻኑን እንባና ልቅሶ ሰምቻለሁና ኣይዞሽ በውሃ ጥም ኣትሞቱም ኣላት። ዓይኑዋን ከፈተላትና ዘወር ብላ ስታይ የውሃ ጉድጓድ ኣየች። የሚገርመው ውሃ ጥም ይዙዋት የምትሰቃየው በኣካባቢው ውሃ ሳይኖር ቀርቶ ሳይሆን ኣካባቢዋን ስላልቃኘች ነው። የውሃ ጉድጓድ ስር ቁጭ ብላ ነው ታለቅስ የነበረው:: ኣጋር ምንጩ ኣደናቅፎ ካልጣላት ወይም ፊት ለፊት ካልተደቀነባት ግራና ቀኝ የማታይ ነበረች ብለው ኣስተማሩ። ርግጥ ነው ኣንዳንዴ በቀላሉ በኣካባቢያችን ልናያቸው የሚገቡ መፍትሄዎችን ሳናይ እየቀረን እንዲሁ ከድህነት ሳንወጣ ቆይተናል።
የደን ሃብታችንን በሚመለከት ድንጋይ ያለቀብን ይመስል ብዙ ያዘንን ሲሆን ከዚህ ይልቅ መትከሉ ይሻላል። ሌላው እየተከልንም መቆረጡ መጨፍጨፉ ኣይቀርምና ገበሬውን ከማስተማሩ ጎን ለጎን ኣማራጭ ሃይል መፈለግ ነው። የሶላር ኤነርጂን ጨምሮ ሃይልን ማቅረብ ካልተቻለ ጭፍጨፋው ኣይቆምም።ገበሬው ደን የሚጨፈጭፈው ዝንባሌ (hobby) ስለሆነው ኣይደለም። ኑሮው ሁሉ በከፍተኛ ሁኔታ ከዛፍ ጋር ስለተቆራኘበት ነው። መስራት ለፈለገው ነገር ሁሉ እንጨትና ገመድ ወሳኝ ሆነውበት ነው። ሞፈር ቀንበሩ፣ቅትርትና ድግሩ፣ ቤቱ መቀመጫው፣ የከብቶቹ ቤት፣ ምርኩዙ የሚበላበት ገበታ፣ የሚተኛበት ኣልጋ እግር፣ ምግቡን የሚያበስልበት ሃይል ከዛፍ ጋር የተያያዘ ነው። እነዚህን ጉዳዮች ብረት እንኳን ቢከብድ ከፕላስቲክ የሚሰሩ የገበሬው መገልገያ እቃዎች እንደልብ መገኘት ቢችሉ ጭፍጨፋውን ይቀንሰው ነበር። የፕላስቲክ ቀንበርና ቅትርት መስራት፣ ኣንዳንድ ወደ ፕላስቲክ ሊቀየሩ የሚችሉ የገበሬውን የመገልገያ እቃዎች መቀየር ብዙ ከባድ ስራ መሆን ኣልነበረበትም። ሌላው ደግሞ ከተሜው ራሱ ከተማ ይኑር እንጂ የሃይል ኣቅርቦቱ ተመጣጣኝ ስላልሆነ ከፍተኛ የከሰል ምርትን ከገበሬው ይጠብቃል። ይህ ደግሞ ለገበሬው ትንሽ የኢኮኖሚ ኢንሴንቲቭ ስለሰጠው ደን እያጠፋ ወደ ከተማ ከሰል ጭኖ ይመጣል። ይህ ጉዳይ የሚቀንሰው ከሰልን በመከልከል ሳይሆን ኣማራጭ ሃይል ለከተሜው በማቅረብ ነው። ኣብዛኛው የከተማ ነዋሪ ለምግብ ማብሰያው የሚጠቀመው እንጨት በመሆኑ በከተሜውና በገጠሩ ነዋሪ በኩል ከፍተኛውን የሃይል ክፍተት የሞላው እሱ በመሆኑ ጭፍጨፋው ቀጥሎኣል።
የኣፈርና ውሃ ጥበቃችን ትልቅ ችግር ያለበት ነው። የኢትዮጵያ ገበሬ በስራ በታታሪነት የማይታማ ጀግና ሲሆን በኣፈርና ውሃ ጥበቃ በኩል ያለው ግንዛቤ፣ ለኣፈር መሸርሸር የሰጠው ዋጋ ግን ዝቅተኛ ሆኖ ይታያል። ይህ ችግር በርግጥ ኮንሶን ኣይመለከትም። የኮንሶ ህዝብ ከባህል ጋር ተያይዞ የዳበረ ግንዛቤ ስላለው የኣፈር ዋጋው ውድ ነው። በሰሜን ኣካባቢ በኣንዳንድ ግብረሰናይ ድርጅቶችና በግብርና የልማት ሰራተኞች መሪነት የሚሰራው የመቀልበሻ ቦይ፣ ክትር፣ ግማሽ ጨረቃና እርከን የላይኛውን ኣፍር ለመጠበቅ የሚጠቅም ነው። ከሁሉ በላይ ግን የጎልማሶች ትምህርት በገበሬው ኣካባቢ መሰጠቱ ወሳኝ ነገር ነው።ማንኛውም ዜጋ በውዴታ ግዴታ መማር ኣለበት። ኣለበለዚያ ኣዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን ገበሬው የመቀበል ኣቅሙ ዝቅተኛ ይሆናል።ሌላው ደግሞ ገበሬውን ለውጭው ኣለም የማጋለጥ ስራና የቅስቀሳ ወይም ኣኒሜሽን ስራ በሰፊው ቢሰራ ኣካባቢውን ሊለውጥ ይችላል። ኣርብቶ ኣደሩ የእርባታ ስራውን ወደ ዘመናዊነት እንዲቀይር ሞባይል ትምህርት ቤቶች ጠንክረው ማስተማር ካልቻሉ፣ የረጋ ኑሮ እንዲኖር ካልታገዘ ህይወቱ ሳይለወጥ የዚህን ዓለም ብርሃን ሳያይ ይኖራል።
በቅርብ ቀን የግብርና ሚንስትሩ እንደገለጹት ግብርናው በዓመት በዓማካይ በስምንት በመቶ ምርቱ እያደገ ነው የመጣው ብለዋል። ይህ ከሆነ የህዝብ ብዛት የሚያድገው በሶስት በመቶ ሲሆን የኢትዮጵያን ህዝብ ሳይራብ ሊያቆይ የሚችል እድገት ኣለ ማለት ነው።በሌላ በኩል መንግስትም በየዓመቱ የእለት ደራሽ ርዳታ ሲለምን ነው የሚታየው። ግብርናው በዚህ ከፍታ የሚያድግ ከሆነ ምርቱ የት ሄደ? ተብሎ ይጠየቃል። በዓማካይ እስከ ሶስት ሚሊየን ህዝብ በየዓመቱ ርሃብ ኣለ:: በቅርቡ እንኳን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው ስድስት ነጥብ ኣምስት ሚሊየንን ህዝብ ለመመገብ ዝግጅት ተደርጓል ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከገበሬው ይልቅ የከተሜው ችግር እጅግ ውስብስብ ነው። በኣቅርቦትና በዲማንድ መካከል ሰፊ ልዮነት የሚታይበት የህብረስተሰብ ክፍል ያለው ከተማው ኣካባቢ ነው።የከተሜውን ችግር እንደ ገበሬው ችግር በኣንድ ወጥ እይታ ለማስቀመጥ ይከብዳል። የገበሬውን ችግር በማጠቃለል የጋራ መፍትሔ ለመፈለግ በኣንጻራዊነት የሚቀል ሲሆን የከተሜው ግን ሲበዛ ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ በተጠቃለለ መልኩ ችግሩን ለማስቀመጥ ይከብዳል። የትናንሽ ከተሞች ነዋሪው፣ የመካከለኛ ከተሞች ነዋሪው፣ የከፍተኛ ከተሞች ነዋሪው፣ የመንግስት ሰራተኛው፣ የነጋዴው፣የጎዳና ተዳዳሪው፣ የኣነስተኛ ንግድ ሰራተኛው የሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግር የሚገናኝበት የጋራ ባህርይ ቢኖረውም ደግሞ ይለያያል። የቤት ችግር መፍታት ደግሞ ከመንግስት የሚጠበቅ ቢሆንም እስካሁን ችግሩ እየከፋ ሲሄድ ነው የሚታየው። :: የዚህን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት ግብርናውን መሰረት ያደረገ የጂዲፒ ጭመራ ስራ ነው የሚሻለው። ኣጠቃላይ የሆነው እድገት ከግብርናው ገፍቶ ሲመጣ የከተማውን ህዝብ ጓዳ ሁሉ ቀስ እያለ ይለውጠዋል። ይህ ማለት ኢንዱስትሪው ይቀራል ማለት ኣይደለም። ግብርናው ይደግ ሲባል ግብርናው ኢንዱስትሪያላይዝድ ይሁን እያልን ነው። ይህ ማለት የኢንዱስትሪው ስራ ኣለ:: የሚለየው የሚቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች በኣብዛኛው ግብርናውን በገፍ የሚያስመርትና የተመረተውን የሚያክም የሚያበዛ የሚያከማች ከዚያም ወደ ኤክስፖርት የሚሄድ ለማለት ነው።
ሌላው ኣገራችን እስካሁን ድረስ የዓለም ንግድ ድርጅት ዓባል ኣለመሆኗና የዓባልነት ጥያቄው መጓተቱ የሚያሳየው የመንግስትን ትልቅ ድክመት ነው። ኢትዮጵያ ቶሎ ቶሎ ብላ ፎርማሊቲውን ኣሙዋልታ መግባት ነበረባት። በተለምዶ የዚህ ድርጅት ኣባል መሆን ጨቅላ የሆኑ ኣገር በቀል ድርጅቶችን ሊያቀጭጭ ይችላልና ለኣዳጊ ኣገሮች ኣስቸጋሪ ነው የሚለው የሚሰራ ኣይመስልም። በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ምን ጨቅላ የሆነስ ኢንዱስትሪ ኣላት? ብለን መጠየቅ እንችላለን። ሁልጊዜም ኤክስፖርት የሚደረገው የግብርና ውጤቶች ማለትም የቅባት እህሎች፣ ቆዳና ሌጦ ቡናን የመሳሰሉትን ነው። እነዚህ ምርቶች ደግሞ ምን ጊዜም በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊ ናቸው። ሌላው ወደዚህ ድርጅት በመግባት የሚኖረው የንግድ ልውውጥ ከለማው ዓለም ጋር ብቻ ዓይደለም። ኣባል ከሆኑት ኣገሮች መካከል ሰባ ኣምስት በመቶ የሚሆኑት በማደግ ላይ ያሉ ኣገሮች በመሆናቸው በዚህ ድርጅት መካከለኛነት ከነዚህ ኣገሮችም ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶች ማድረግ የሰለጠነ ሲስተም ውስጥ ገብቶ ንግድ ለመለዋወጥ ሰፊ እድል ይሰጣል። ከበለጸጉ ሃገራት ጋር የሚኖረው የሁለትዮሽ ስምምነትም ኢትዮጵያ ያሉዋትን ተፈላጊ ምርቶች ጥራት በመጨመር ገቢዋን ምርቷን ከፍ ለማድረግ እንድትችል መነሳሳትን ይፈጥርላታል። ከሁሉ በላይ ያሉዋትን ምርቶች ቢያንስ በኣንድ ደረጃ በኢንዱስትሪ ሂደት ውስጥ ኣሳልፋ የምታቀርብበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል ሲስተም ውስጥ እየገባች እንድትሄድ ያደርጋታል።ለምሳሌ ያህል ቡናን ብንወስድ ቢያንስ ቆልቶ ኤክስፖርት ለማድረግ ሽንጧን ገትራ ልትከራከርና ልታሳምን ይገባታል። የዓለም ንግድ ድርጅት በሃገሮች መሃል ፌር ትሬዲንግን የሚያራምድ በመሆኑ በዚያ ጥላ ስር ሆና ከብዙ ሃገራት ጋር እንዲህ ዓይነት የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ለማድረግ ጥቅሙዋን ኣስጠብቃ የሌላውን ጥቅም ኣክብራ የንግድ ስራዋን እንድትሰራ ያግዛታል። ይህቺን ዓለም ከንግድ ልውውጥ ውጭ ማየት ይከብዳል። በመሆኑም ይህን እድል ተጠቅማ በዚያ መድረክ ላይ ወገብዋን ታጥቃና ጠንክራ ሃሳብ እያመጣች ምርቶቹዋን በፌር ትሬድ መርህ መሰረት ማስወጣትና ማስገባት ካልቻለች ተገልለን ኣናድግም:: ኢትዮጵያ ምርቶቹዋን ይዛ በእንደዚህ ዓይነት ዓለም ኣቀፍ ተቋም ፊት መቅረብ ካልቻለች በተደራጁ ሃገራት በሆነ ሲስተም ውስጥ በገቡ ሃገራት ልትበለጥ ትችላለች። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት እድሎችን ቶሎ ወደ ራስ እድል የመቀየር ስራ ካልተሰራ እድገት ኣይመጣም።
በዚህ ድርጅት ውስጥ ሳንታቀፍ ከዓለም የንግድ ሲስተም ወጥተን በግላችን ስንዳክር ቆይተን ገበሬውን ተስፋ በማስቆረጥ ጫት ማስተከል ትልቅ ታሪካዊ ጥፋት ነው። የረጅም ጊዜ ትልም ኖሮን በእንዲህ ዓይነት ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች መድረክ ላይ የኢትዮጵያን የቡና ገበሬ ችግሮች ማንሳት ካልቻልን ስንፍና ይሆንብናል። ቡና ምንም እንኳን ሃገራችን የሚበቅል ቢሆንም ንብረትነቱ የኛ ቢሆንም የዓለም ህዝቦች ገጸ በረከትም በመሆኑ በኣንድ በኩል ለፌር ትሬድ እየተሙዋገትን በሌላ በኩል ግን ምርታችንን ከፍ የማድረግ ሃላፊነት ኣለብን። ገበሬው የበለጠ እንዲያመርት ማበረታታት ይገባናል። የኢትዮጵያ ኤክስፖርት በዋናነት የግብርና ውጤት በመሆኑ ኢንቨስተሮችን ወደዚህ ሴክተር በመሳብና የግብርናውን ኢንዱስትሪ በማሳደግ የሚላኩትን ምርቶች መጨመር ከዚያም ገቢን ለማሳደግ ያስፈልጋል ። ውድድር ይበዛብኛልና ትንሽ ለብቻየ ልቆይ ለማለት የሚያስችል ዓለም ውስጥ ኣይደለንም። የዚህ ድርጅት ኣባል ባንሆንም በዚህች ፕላኔት ላይ ሆነን ከውድድር ኣንወጣም። ውድድርን እንደ የትምህርት ገበታና እንደ እድል እያዩ ኣዳዲስ ኣሳቦችን እያፈለቁ በገበያ መሃል መቆም ነው የሚያዋጣው።
በርግጥ መንግስት ወደዚህ ድርጅት ለመግባት ኣንዱ ያስፈራው ነገር በከፍተኛ ሁኔታ የንግድ ስራ የያዘው መንግስት በመሆኑ፣ግልጽነት የሌላቸው የንግድ ስራዎች ውስጥ በመግባቱ ከነዚህ ግልጽነት ከጎደላቸውና በሚጥር ከሚሰሩ ንግዶች በሚገኘው ትርፍ ተቃዋሚን ዝም ለማሰኘት መጠቀሚያ መሆኑ፣ ከዚያም የሰርቪስ ሴክተሩ እንደ ባንክና ቴሌን ወደ ግል ለማዛወር ባለመፈለጉ ነው። እነዚህን ተቋማት በተለይም ቴሌን ስናይ የመንግስት ዋናው ስጋት ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ሳይሆን የሰኪዩሪቲ ጉዳይ ነው። ኣንዱ የህወሃት የመጨቆኛ መሳሪያ የሆነው ይህ ተቋም ነው። ዜጎች በሃገራቸው የፈለጉትን በስልክ የማውራት መብታቸውን የነፈገ፣ ዓለም በኢንተርኔት ኣገልግሎት ሰማይ በደረሰችበት ዘመን ኢትዮጵያዊያን የፈለጉትን መረጃ እንዳይለዋወጡበት የተደረገበት ሁኔታ ነው ያለው። በመሆኑም የቴሌ ወደ ግል መዛወር ለኢትዮጵያዊያን የነጻነት ጥያቄም ሆኖ ይታያል። ባንኮችም ቢሆኑ ኣብዛኛዎቹ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግስት ተይዘው በኣድልዎ እንደሚሰሩ ይታወቃል። ባለፉት ሁለት ኣስርታት የሰማነው ጉድ ተቆጥሮ ኣያልቅም።
እንዴው የሆድ የሆዳችንን ኣወራን እንጂ ልማትን ኣምጥቶ ህይወት ለማሻሻል የሚቻለው በመጀመሪያ ደረጃ የህዝብ ችግር የሚያሳስበው መንግስት ሲኖር ነው። ኣለበለዚያ ዶክተር ኣክሎግ ቢራራ ኣዘውትረው እንደሚሉት ብልጭልጭ ነገረን እያሳዩን ብዙ ሊሰራ የሚችልን ሪሶርስ በብልጭልጭ ጉዳይ ላይ እያፈሰሱ እንዲሁ ኣብዛኛው ህብረተሰብ ከችግር ሳይወጣ ይቆያል። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ካለብን ሰፊ ችግር መላቀቅ የምንችለው ኣገር ወዳድ፣ የህዝብ ችግር የሚገባው መንግስትን መፍጠር ስንችል ነውና ሁላችን ለለውጥ መነሳት ይኖርብናል።ለውጡ ደግሞ ሁለንተናዊ ቢሆን መልካም ነው። ኣዲስ የኣስተሳሰብ ለውጥ ውስጥ መግባት ኣለብን። ያለፍንባቸውን የህይወት ልምዶቻችንን፣ ታሪካችንን፣ ኣሁን ያለንበትን ሁኔታ የወደፊቱን የሃገራችንን እጣ ፈንታ በሚመለከት የምንተነትንበትንና የምንገመግምበትን መንግድ እንለውጥ። ኣስተሳሰባችንን በመቀየር ነው ኣገራችንን የምንቀይረው።
እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርካት
ገለታው ዘለቀ
geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment