Translate

Tuesday, June 24, 2014

መርህ አልባነት – ከደሞዝ ጭማሪው ጀርባ

መንግስት “የዋጋ ንረትን በማይቀሰቅስ ሁኔታ” “የተጠና” የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ከሀምሌ ወር 2006 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚንስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ መግለፃቸው የሰሞኑን አበይት ዜና ሆኗል። አቶ ኃይለማሪያም “ሌጋሲያቸውን የሚያስቀጥሉላቸው” አቶ መለስ በምርጫ ወቅት ምንም አይነት የደሞዝ ጭማሪ እንደማይደረግ በህይወት በነበሩበት ወቅት ተናግረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ከመንግስት ምንጮች (በተለይም ከስርአቱ የዳታ መጋገሪያ – ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለስልጣን) የሚወጡትን በፖለቲከኞች የሚፈበረኩ አሐዞችን ወደጎን ብለን አሁን ባለው ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ሲቪል ሰርቫንቱ ህልውናውን ማስቀጠል በገመድ ላይ እንደመጓዝ እጅግ አስቸጋሪ ሆኖበታል፡፡ ወሩን በአግባቡ ከማያሳልፍ ገቢ ጋር የገዢው ፓርቲ ፖለቲካዊ ጫና ሲደመር የመንግስት ሠራተኛ መሆን “ካለመኖር አንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብሎ ያለ” የኑሮ ደረጃ ሆኗል፡፡ የአንድ ለአምስት ጥርነፋው፣ ከሥራ ብቃት ይልቅ ፖለቲካዊ ታማኝነትን የሚያስቀድመው የዕድገት መሠላል፣ በየጊዜው የሚመጡ በቅጡ ሳይላመጡ የተዋጡ የአሠራር ስርአቶች (BPR, BSC, ካይዘን ወዘተ)፣ የማይመች የስራ አካባቢ ወዘተ ሲቪል ሰርቫንቱን የሥራ ፍላጎቱ የተቀዛቀዘ፣ ማምለጫ አማራጭ ፈላጊ እና ስልቹ ማድረጉ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡

አሁን መንግስት የሲቪል ሰርቫንቱን የምርጫ ድምጽ መግዣ አድርጎ ያሰበው የደሞዝ ጭማሪ ሐሳብ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው በሰራተኛው እና በቤተሰቡ ኑሮ ላይ የሚታይ ለውጥ ማምጣት ሲችል ብቻ ነው፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ደግሞ በቅድሚያ የኑሮ ውድነቱን የሚያባብሱ ምክንያቶችን በቅድሚያ መለየትና እልባት ማበጀት ግዴታ ነው፡፡ ለ2007 ዓ.ም. የቀረበው ረቂቅ በጀት ላይ ቀላል የማይባለው ክፍል መንግስት ከሐገር ውስጥ ምንጮች በሚወስደው ብድር እንደሚሸፈን እየታወቀ፣ ለታይታ በሚገነቡና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እምብዛም በሆነ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ገንዘብ እየፈሰሰ፣ በወጪና በገቢ ንግድ መካል ያለው ልዩነት (Trade balance) በከፍተኛ ደረጃ እየሠፋ ባለበት ሁኔታ በደሞዝ ጭማሪ ስም የፖለቲካ ድጋፍ ለመግዛት መሞከር መርህ አልባነትን ከማሳየት ባሻገር የሲቪል ሰርቫንቱ ህይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አያመጣም፡፡

No comments:

Post a Comment