አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በየመን ባለሥልጣናት እገታ ላይ መሆኑን በማስመልከት የወጣ መግለጫ
ሰኔ 23 ቀን 2006 ዓ.ም
የግንቦት 7፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔ 16 ቀን 2006 ዓም ለሥራ ጉዳይ በየመኒያ አየር መንገድ አይሮፕላን ተጉዞ በትራንዚት ሰንዓ ከተማ እያለ በየመን መንግሥት ፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ መንገድ ታግቷል። አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የመን የጉዞው መዳረሻ አልነበረም፤ ከየመን ጋርም የሚያገናኘው ምንም ጉዳይ አልነበረውም። የየመን መንግሥት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን አግቶ ለአንድ ሰዓት እንኳን ለማቆየት ምንም ምክንያት የለውም። በዚህም ምክንያት ያለአግባብ የታገተብን የንቅናቄያችንን አመራር በአስቸኳይ እንዲፈታ በተለያዩ መንገዶች ላለፈው አንድ ሣምንት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም። እንዲያውም የየመን ባለስልጣናት አምባገኑን ወያኔ ለመርዳት ባለው ፍላጎት ሳቢያ መሪያችንን አሳልፎ ሊሰጠው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት አድሮብናል።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ በሀገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህ፣ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ጊዜውን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ፤ ዝግጁነቱንም በተግባር ያሳየ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። የየመን መንግሥት ከዘረኛውና ፋሽስታዊው ወያኔ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ታጋይ መሪያችን ላይ እየፀመ ያለውን ደባ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ የንቅናቄዓችን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወስኗል።