Translate

Monday, May 5, 2014

የኃይለማርያም ደሳለኝ ቁልቁለቶች (ጋዜጠኛ ተመሰገን ደሳለኝ )

Temesgen Desalegn "Fact" Ethiopian Amharic newspaper editorበ2005 ዓ.ም መጀመሪያ አቶ ኃይለማርያም “ጠቅላይ ሚኒስትር” ተደርጎ በኢህአዴግ ሲሾም፤ በፓርቲው ውስጥ አክራሪ ብሔርተኛ የአመራር አባላት ከመኖራቸው አኳያ፤ መቼም ቢሆን “ራሱን ችሎ ይቆማል” ብሎ መጠበቁ ተምኔት እንደሆነ በርካታ የፖለቲካ ተንታኞች መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ይህ ኃይል እንኳን እንደ ኃይለማርያም ላለ የድል አጥቢያ መሪ ቀርቶ፣ ከድርጅቱ ምስረታ ጀምሮ እስከ ምኒሊክ ቤተ-መንግስትም ድረስ ታላቅ የተጋድሎ ታሪክ ለነበረው አቶ መለስም ቢሆን ክፍተት ካገኘ አለመመለሱን የ93ቱ ሣልሳዊ ህንፍሽፍሽ በግልፅ አሳይቶ ማለፉ አይዘነጋም፡፡ በተጨማሪም ራሱ መለስ ዜናዊ በድህረ ምርጫ 97 የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ዘብጥያ ወርደው የነበሩትን የቅንጅት አመራሮች “ከእስር እንዲፈቱ ብፈልግም አክራሪው ኃይል ተቃወመኝ” ማለቱን ዊክሊክስ የተሰኘው የመረጃ መረብ የአሜሪካ አምባሳደርን ጠቅሶ ይፋ ማድረጉ ይህንኑ ያስረግጣል፡፡ የአምባሳደሩ መረጃ የተጋነነ፤ አሊያም “ተጋግሮ የቀረበለት ነው” ሊባል ቢችል እንኳ “ጭስ በሌለበት…” እንዲሉ፤ በግንባሩ ውስጥ አክራሪ ኃይል ለመኖሩ በጠቋሚነት ሊወሰድ ይችላል፡፡

ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ መለስን ከተካበት ዕለት አንስቶ፣ ያደረጋቸው ዲስኩሮችም ሆኑ ለቀረቡለት ጥያቄ የሰጣቸው ምላሾች በአክራሪው ኃይል ተጽእኖ ሥር ማደሩን ያሳያል፡፡ የድርጅቱ የታሪክ ንባብም ቢሆን፣ በአቅመ ደካማ የመጠቀም የፖለቲካ ጨዋታው የሰነበተ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ኃይለማርያም ከሹመቱ በኋላ ከባሕሪው አፈንግጦ፣ ዝነኛዋን የመለስ ዜናዊን ሕዝባዊ ሽብር መፍጠሪያ ‹‹ቀይ መስመር››ን፤ ‹‹እሳት መጨበጥ›› በሚል ተክቶ የተቃውሞ እንቅስቃሴን በሙሉ እስከማስፈራራት መገፋቱም የዚሁ ውጤት ይመስለኛል። በተቀረ እርሱ ወደ ሥልጣን በመጣበት መጀመሪያ አካባቢ፣ ‹‹ኃይማኖተኛ››ነቱን ብቻ በመጥቀስ ‹‹ቤቴን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት›› በሚል ሥርዓታዊ ማፍያነትን ባደራጁ ጓደኞቹ ላይ ጅራፍ እስከማወናጨፍ ይደርሳል ተብሎ መገመቱ፣ በግንባሩ ውስጥ የተንሰራፋውን አክራሪ ኃይል በቅጡ ካለመረዳት የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እዚህ ጋ ሳይጠቅስ የማይታለፈው ጥቅምት 10 ቀን 2005 ዓ.ም የወጣው ‹‹ሪፖርተር ጋዜጣ›› በልዩ እትሙ፣ ኃይለማርያም ‹‹ቄስ›› ተብሎ ሊቀባ አንድ ወር ሲቀረው በትምህርት ምክንያት ከሀገር እንደወጣ ካስነበበበት ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ ወደ ፖለቲካው ከመቀላቀሉ በፊት የሚያመልክበትን ‹‹የኢትዮጵያ ሐዋርያት ቤተክርስቲያን›› ቄስ ህዝቅኤል ጎዴቦን ‹‹ፖለቲካ ውስጥ መግባት ሀጢአት አይሆንብኝምን?›› ሲል መጠየቁን ጋዜጣው አትቷል፡፡ ግና፣ ምን ዋጋ አለው? ባልተጠበቀ ፍጥነት ከተራ ፖለቲከኝነት አልፎ የሀገሪቱ መሪ ለመሆን በመብቃቱ፣ ‹‹ቅስና››ው በመንገድ ሊቀር ተገደደ እንጂ፡፡ እርሱም ቢሆን ዛሬ እንዲህ አይነት ጥያቄ አያነሳም፤ በፈሪሃ እግዚአብሔሩም ቦታ፣ ፈሪሃ ኢህአዴግ ተተክቷል፡፡ እናም ከእስልምና መንፈሳዊ መሪዎች እስከ ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ያሉ ንፁሀን፣ በራሱ አነጋገር ‹‹እሳት በመጨበጣቸው›› ወደ ‹‹ቃሊቲ›› ተላልፈው ምድራዊውን ገሀነም ይቀበሉ ዘንድ ቡራኬ ሰጥቷል፡፡
ሰሞነኛው ጉዳይ
አቶ ኃይለማርያም በስድስት ወር (በጥር) ለተወካዮች ም/ቤት ማቅረብ የነበረበትን ሪፖርት በዘጠኝ ወሩ ባለፈው ሳምንት ባቀረበበት ወቅት፣ ከምርጫው በፊት የፖለቲካ ማሻሻያ መጠበቁ የዋህነት እንደሆነ የጠቆመን፣ የም/ቤቱ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ የጠበበው ምህዳርን አስመልክቶ ላቀረበለት ጥያቄ ‹‹ዲሞክራሲ በአንድ ሳምንት ተበጥብጦ አይጠጣም (ፓርቲው ሥልጣን ከያዘ በቀጣዩ ወር ሃያ ሁለተኛ አመቱን መድፈኑን ልብ ይሏል)፣ ዲሞክራሲ ህልውናችን ነው፣ ቀይ ምንጣፍ አናነጥፍም…›› ጅኒ ቁልቋል በሚሉ የእብሪት ገለፃዎች ማለፉ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ሪፖርቱ በሀሰተኛና በማደናገሪያ ዘገባዎች የታጀለ እንደነበረ መታዘብ ተችሏል፡፡ ለማሳያነትም ያህል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እጠቅሳለሁ፡-
‹‹ዕድገት›› ሲባል…
የኢኮኖሚ ዕድገትን በተመለከተ ጠቅላይ ሚንስትሩ በሪፖርቱ ላይ ‹‹የሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት ሂደት ሲታይ ላለፉት አስር ዓመት (ከ1996-2005) በየዓመቱ በአማካይ 10.9 በመቶ በማደግ ከፍ ባለ የእድገት ጉዞ (Trajectory) ውስጥ መሆኑን አመላክቷል›› ሲል ነግሮናል፡፡ ይሁንና አስሩን ዓመት ትተን የዘንድሮውን በመሬት ላይ ያለውን እውነት እንኳ ብንመለከት የሚያሳየው ተቃራኒውን ስለመሆኑ ለራሱም ቢሆን ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በአገሪቱ ሥራ-አጥነት (በከተሞች 40 በመቶ መድረሱን ጥናቶች ይጠቁማሉ) በአስከፊ መልኩ ተንሰራፍቶ፣ ስደት ዕጣ-ፈንታ ተደርጎ ኩብለላ የዕለት ተግባር በሆነበት፣ ብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ በኑሮ ውድነት እንደ ከባድ ማዕበል ወደላይ ጎኖ፣ ቁልቁል በአናት እየተተከለ በሚንገላታበት፣ ጎዳናዎች ቀን ቀን ልመና በወጡ ምንዱባን፣ ማታ ማታ ደግሞ ነፍሳቸውን ለማቆየት የሚውተረተሩ በዕድሜም በአካልም ትናንሽ የሆኑ ሴተኛ አዳሪዎች ተጥለቅልቆ… ባለበት በዚህ ዘመን ‹በየዓመቱ በአማካኝ 10 በመቶ እያደግን ነው› የሚልን አላጋጭ ሪፖርትን ሰምቶ በቸልታ ማለፉ ሰው የመሆን ጉዳይንም ፈተና ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡
በዚህ ለሶስት ወራት በዘገየው ሪፖርት የዋጋ ንረትን ከአንድ አሃዝ እንዳያልፍ እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል፡፡ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ከየምርጫው አንድ ዓመት በፊት በመለስ ዜናዊ ይቀርቡ የነበሩ ሪፖርቶች እንዲህ አይነት የዋጋ ንረት እንደሚቀንስ የ‹‹ሚያበስሩ›› እንደነበር ይታወሳል፡፡ የኃይለማርያምም ሪፖርት፣ ፓርቲው በምርጫ ዘመቻው ወቅት ሁሌ እንደ ስልት የሚጠቀምበትን ይህንን ጉዳይ አስጩኾ ከተለመደው የግብይት ሥርዓት አፈንግጦ መጠነኛ የዋጋ ማረጋጊያ በማድረግ የእሳት ማጥፊያ ሥራ ለመስራት ከመዘጋጀት ያለፈ ትርጉም ያለው ነገር የሚያመጣ ሆኖ አይደለም፡፡
አብዮታዊ ግንባሩም ቢሆን የምርጫው ማዕበል የሚጠራርገውን ጠርጎ፣ የሚወረውረውን ወርውሮ ማለፉ ላይ እርግጠኛ እንደሆነው ሁሉ፣ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የዋጋ ንረቱ ተመልሶ የቱንም ያህል ወደላይ ቢስፈነጠር የተቆጡ ድምፆች አደባባዩን እንደማይሞሉት ጠንቅቆ ያውቀዋል።
ሌላው የሪፖርቱ አስቂኝ ክፍል የግብርናውን ዘርፍ የተመለከተው ነው፡፡ ይኸውም ካለፈው ዓመት የዘንድሮው በእጅጉ ማደጉን ገልፆ እንደምክንያት ያቀረበው ‹‹ዋናው የዕድገት መሰረት በመሬት ማስፋት ሳይሆን በምርታማነት የመጣ መሆኑን የሚያሳይ ነው›› የሚል ነበር፡፡ ይሁንና እዚህ ጋ የሚነሳው ጥያቄ የዘርፉ ባለሙያ መሆንን የማይጠይቅ ቀላልና ግልፅ ነው፡- የግብርና ቴክኖሎጂ መሻሻል በሌለበት፣ የሰው ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመጣበት (አማካይ የመሬት መጠን ከአንድ ሄክታር ያነሰ ሆኖ)፣ ማዳበሪያ ለፓርቲ አባላት ብቻ በሚታደልበት፣ የዝናብ ወቅትን ብቻ ጠብቆ በሚዘራበት እና መሰል ችግሮች ባጨለሟት ኢትዮጵያችን ምርታማነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገ መባሉ እንዴት ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል? …መቼም በመለኮታዊ ኃይል ከሰማይ በወረደ መና ነው ሊሉን አይችሉም፡፡ ካሉ ግን ምን ማድረግ ይቻላል! ሰውየው ኃይለማርያም፣ ፓርቲውም ኢህአዴግ ነውና፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው የእነርሱ ዕድገት፣ ምርታማነት… ቅብርጥሶ የሚለው ፕሮፓጋንዳ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በምግብ እጦት መጠቃታቸውን ዓለም አቀፍ ተቋማት እየዘገቡ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኢንዱስትሪው ዘርፍ እንደ መስከረም አደይ አበባ በየሜዳው መፍካቱን አብስረውናል፡፡ ይሁንና ሀገሪቱ እንኳን ለግዙፍ ፋብሪካዎች የሚሆን የኃይል አቅርቦት ቀርቶ፣ አነስተኛ ፍጆታ ያለውን የከተማ ነዋሪ የመብራት ፍላጎትም ማሟላት ያለመቻሏ ጉዳይ ፀሀይ የሞቀው፣ ዝናብ ያጨቀየው የአደባባይ እውነታ ነው፡፡ የግልገል ግቤ 3 ፕሮጀክትም ቢሆን፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደደሰኮረው በሚቀጥለው ዓመት ሥራ የሚጀመር አለመሆኑን ግንባታውን የሚያካሄደው ካምፓኒ አስቀድሞ ማሳወቁን ሰምተን አረጋግጠናል፡፡
ሌላው በሪፖርቱ ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ ግርምት የሚያጭረው ከወራት በፊት በሳውዲ አረቢያ አሰቃቂ ጭካኔ የተፈፀመባቸውን ወንድም-እህቶችን በተመለከተ በአምስት መስመር ብቻ ተቀንብቦ የቀረበው ዘገባ ነው፡፡ የዚህን ሥርዓት ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከመራቅም በላይ፣ መበስበሱን የሚያስረግጠው እንዲያ በ21ኛ ክ/ዘመን ሊፈፀም ቀርቶ ይታሰባል ተብሎ በማይታመን ጭካኔ ደማቸው ደመ-ከልብ ሆኖ ስለቀረውና አስክሬናቸው በጎዳና ላይ ስለተጎተተው ወገኖቻችን፡- ‹‹የሳዑዲ መንግስት በተለያየ ምክንያት ሕጋዊ የመኖሪያና የሥራ ፈቃዳቸውን ማስተካከል ያልቻሉ ኢትዮጵያውያን አገር ለቀው እንዲወጡ በወሰነው መሰረት…›› በማለት በሪፖርት ተብየው አቃሎ ማቅረቡ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ሁለት ነገር ያመላክታል፡፡ የመጀመሪያው ሥርዓቱ ለዜጎቹ ደህንነት ደንታቢስ በመሆኑ ቢያንስ በወረቀት ላይ እንኳን ነውረኛውን የሳውዲ መንግስት ለማውገዝ እና ወደፊትም ከእንዲህ አይነቱ ዲያብሎሳዊ ተግባሩ እንዲታቀብ ለማስጠንቀቅ አለመድፈሩን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በዚህን መልኩ ከተባረሩ ስደተኞች መካከል አሁንም ወደዛው የሞት ቀጠና ተመልሰው መሄዳቸው፣ ጠ/ሚንስትሩ እንዲያ የተዘባነነበትን ‹‹ዕድገት›› ልብ-ወለድ ማድረጉን ነው፡፡
መልካም አስተዳደር ሲባል…
የኃይለማርያም ደሳለኝ ሪፖርት በደምሳሳው እውነት ለመናገር የሞከረው መልካም አስተዳደር ያለመኖሩን በተመለከተ ብቻ ነው፡፡ ለማሳያነትም የሚከተለውን ልጥቀስ፡-
‹‹በአገራችን ከፌዴራል ተቋማት ጀምሮ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ደረጃው የተለያየ ቢሆንም፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንደሚታዩ ሕዝቡ በተለያዩ መድረኮችና አገልግሎት በሚያገኝባቸው ሥፍራዎች ቅሬታዎች እያነሳ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡››
ከዚህ በተጨማሪም መንግስታዊ ጉድለቱ ከኪራይ ሰብሳቢነት አንስቶ፤ በመሬት አስተዳደር፣ በታክስ አሰባሰብ እና የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት በማስፈፀም ሂደት፣ በአገልግሎት ተቋማት ውስጥ የሚታይ የአመለካከት ችግር፣ የሥራ ተነሳሽነት አለመኖር፣ ግልፅነት እና ተጠያቂነት መጥፋትንም እንደሚጨምር ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ይሁንና ሰዎቹ እንዲህ በድፍረት ያነበሩት ሥርዓትን ክሽፈት ቢያውጁም፣ ቅንጣት ታህል ‹የሕዝብ ተቃውሞ ሊነሳ ይችላል› የሚል ስጋት የለባቸውም፡፡ ስለምን? ቢሉ፣ በአንድ በኩል ስለዲሞክራሲ ማበብና የሕግ የበላይነት እየዘመሩ፤ በሌላ በኩል በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ተተብትበው ሥልጣንን በገዛ ፍቃድ ካለመልቀቅም አልፎ ቀጣዩን ምርጫ አጭበርብሮ እና ተቀናቃኞችን ጨፍልቆ ለማሸነፍ ዝግጁ መሆን የሚቻለው በእኛይቱ መከረኛ ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነ ገና ድሮ ገብቷቸዋልና፡፡
ሌላው የአገሪቱን ሀብት በጠራራ ፀሀይ የመዝረፍ እውነታውን ለመረዳት ጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርቱን ካቀረበበት ሁለት ቀን ቀደም ብሎ (በ14/8/06 ዓ.ም) የፌዴራል ዋና ኦዲተር የ2005ቱን የበጀት ዓመት በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርት ማየቱ ብቻ በቂ ነው፡፡ መስሪያ ቤቱ በተለያየ ምክንያት ከመንግስት ተቋማት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ እንደባከነ የገለፀው የገንዘብ መጠን በድምሩ 3,207,752,247.05 (ሶስት ቢሊዮን ሁለት መቶ ሰባት ሚሊዮን ሰባት መቶ ሀምሳ ሁለት ሺ ሁለት መቶ አርባ ሰባት ብር ከዜሮ አምስት ሳንቲም) መሆኑን በግላጭ አስቀምጧል፡፡ ይህ እንግዲህ በቀጥታ ከጥሬ ገንዘብ ጋር የተያያዘ ውድመት ነው፡፡ ከዚህ ሌላ በርካታ ችግሮችና ዘረፋዎች መኖራቸውን ሪፖርቱ በስፋት ዘርዝሯል፡፡ ለምሳሌ የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያን የተመለከተውን ማየት ይቻላል፡፡
ይህ መሳሪያ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2005 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ለግብር ከፋዩ ከተሸጠው ውስጥ 89 በመቶው አገልግሎት ላይ ቢውልም፣ የሽያጭ መረጃን ወደ መረጃ ቋት የሚያስተላልፈው 12 በመቶ ብቻ ሲሆን፤ የተቀረው 88 በመቶ ምንም ነገር እንደማያስተላልፍ ተገልጿል፡፡ እናሳ! ይህ ስለምን ሆነ? ለግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ መረጃ የማያስተላልፉት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያዎችስ በእነማን ድርጅቶች እጅ ውስጥ የሚገኙት ይሆኑ? …እውን! ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህ መልስ ይኖረዋልን?
የስኳር ኮርፕሬሽኖችን በተመለከተ
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በሪፖርቱ ላይ ‹‹(አዳዲሶቹ) አብዛኛው የስኳር ፋብሪካዎቻችን በቀጣይ ዓመት ወደ ማምረት ተግባር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል›› በማለት ቢገልፅም፤ የኦዲት ሪፖርቱ ግን ተቃራኒውን ነው የሚያረዳን፡፡ ይገነባሉ የተባሉት ፋብሪካዎች በኮርፕሬሽኑ የአምስት ዓመት ዕቅድ መሰረት ሁለመናቸው ተጠናቅቆ ወደ ማምረት እንደሚገቡ መገለፁ አይካድም፡፡ ነገር ግን የጣና በለስ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ግንባታ እስከ ጥቅምት 2005 ዓ.ም ያልቃል ቢባልም፤ በዛው ዓመት መጨረሻም ቁጥር አንድ 45 በመቶ፣ ቁጥር ሁለት 39 በመቶ ብቻ ሲጠናቀቅ፤ በኦሞ-ኩራዝ ደግሞ የፋብሪካው ግንባታ መጠናቀቅ በነበረበት ዓመት 42 በመቶ ብቻ የተሰራ መሆኑን ሪፖርቱ አጋልጧል፡፡ እንዲሁም እስከ ጥቅምት 2006 ዓ.ም ይጠናቀቃል የተባለው የወልቃይቱ ፋብሪካ የኦዲት ሪፖርቱ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ምንም አይነት የግንባታ ሥራው እንዳልተጀመረ ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የተንዳሆ ስኳር ልማት ፋብሪካ በታቀደለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት 5146.09 ሄክታር መሬት ላይ የነበረው የሸንኮራ አገዳ ምርት ዕድሜው በመራዘሙ ተበላሽቶ እንዲወገድ በመደረጉ፣ ፋብሪካው ማግኘት የሚገባውን 102,440,145.00 (አንድ መቶ ሁለት ሚሊዮን አራት መቶ አርባ ሺህ አንድ መቶ አርባ አምስት) ብር ተገቢ ባልሆነ መንገድ ያሳጣው እንደሆነ የኦዲት ሪፖርቱ አትቷል፡፡ ታዲያ ጠቅላይ ሚንስትራችን ‹በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይጀምራሉ› የሚለን የትኞቹን የስኳር ፋብሪካዎች ይሆን? እግዜር ያሳያችሁ! እንዲህ አይነት ያፈጠጠ ነጭ ውሸት የሚነግረን፣ ፕሮጀክቶቹን እስከዚህ ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ድረስ በበላይነት ይመራ የነበረው አባይ ፀሀዬን አማካሪው አድርጎ ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ይህ ሁኔታ የሚያመላክተው ሌላ ጉዳይ ቢኖር አቶ ኃይለማርያም ዛሬም ‹‹እመራዋለሁ›› ለሚለው አብዮታዊ ድርጅቱ ሩቅ የመሆኑን ምስጢር ነው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በተሾመ ማግስት፣ አቶ መለስ ማሌሊትን ቀብሮ ስለልማታዊ መንግስት ከማንችስተር እስከ ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲዎችና ዓለም አቀፍ የአደባባይ መድረኮች መከራከሩን ያልሰማ የሚመስለው ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በመጀመሪያው ከውጭ ጋዜጠኛ (ከቪኦኤው ፒተር ላይን) ጋር ባደረገው ቃለ-መጠየቅ ላይ ‹‹እኛ ተራማጅ ግራ-ዘመም ነን›› ሲል የተደመጠበትም መግፍኤ ይኸው ይመስለኛል፡፡
ኤርትራ ሆይ! ብረሳሽ…
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት፣ አቶ ግርማ ሰይፉ መንግስት የኤርትራንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማቀራረብ የሚያደርገውን ጥረት አስመልክቶ ያለውን አቋም በተመለከተ ላነሳው ጥያቄ፣ የሰውየው ምላሽ ከእውነታው ፍፁም ያፈነገጠ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የኃይለማርያም ማብራሪያ ሁለቱ ሕዝቦች የቀድሞ ግንኙነታቸውን መልሰው እንዲያጠናክሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኃይማኖት አባቶች እና ምሁራኖች ለሚያደርጉት ጥረት መንግስት ድጋፍ እያደረገ ነው›› የሚል ሲሆን፤ ኤርትራን በተመለከተ ደግሞ ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ በአሸባሪነት ፈርጆ ማዕቀብ ጥሎ እያሰቃያት ከመሆኑም በላይ በአካባቢው ከኢትዮጵያ በስተቀር ተሰሚነት ያለው ሀገር ያለመኖሩን የሚያመላክት አንድምታ አለው፡፡ ይህ ግን ምን ያህል እውነት ነው? ብለን ስንጠይቅ፤ በኤርትራ መገንጠልም ሆነ በለንደኑ ኮንፈረንስ የህወሓትን የበላይነት ያስረገጡትና በአሜሪካን አስተዳደር ተሰሚነት ያላቸው አምባሳደር ኸርማን ኮኽን ኤርትራን ከ‹‹ብርዱ›› ለማውጣት አሜሪካም ሆነች የተባበሩት መንግስታት የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ እና ድንበሩ እንዲሰመር በአደባባይ መጮኽ ከጀመሩ መሰንበታቸውን እንረዳለን፡፡ እንዲሁም ሌላኛው አምባሳደር ዴቪድ ሺንም ኢትዮጵያ ባድመን እስከመስጠት ከሄደች በሁለቱ ሀገራት ሰላም ማምጣት እንደሚቻል ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ እናም እነዚህን ሰዎች ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ አሜሪካውያን ፖለቲከኞች ኤርትራ እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ወዲህ ሽብርተኝነትን ከመደገፍ መቆጠቧን ጠቅሰው በመከራከር ላይ መገኘታቸው እውነታውን ፍንትው አድርጎ ሳያል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኃይማኖት አባቶችና ምሁራኖች…›› ንግግርም በሬ ወለደ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ባለፈ የሀገሬ መንግስት ለተከታታይ አስራ ስድስት አመታት ‹ኤርትራ ሆይ! ብረሳሽ ቀኜ ይርሳኝ›ን የሚዘምረው ሀገር-በቀል ተቀናቃኞቹን በስመ-ሻዕቢያ መጨፍለቅ ሲፈልግ ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡
እኛ ቀጥለናል!
ግንባሩ ‹‹ባለራዕይ›› በማለት ካቆለጳጰሰው የቀድሞ ሊቀ-መንበሩ አቶ መለስ ህልፈት በኋላ፣ በጠባብ ብሔርተኞችና ጥቅመኞች በመሞላቱ መተካካቱን ተከትሎ ይፈረካከሳል የሚል ከውስጥም ከውጪም የሚሰማ ሹክሹክታ ነበር፡፡ በርግጥም የኃይለማርያም ወደ መንበሩ መምጣት ‹‹በአማራና ኦርቶዶክስ የምትመሰለው ሀገር፣ የአናሳውም ሆናለች›› ከሚለው የአቦይ ስብሐት እንቶ ፈንቶ ውጪ፣ ከተጠበቁት ሁነቶች ብዙዎቹን (በተለይ ሥርዓታዊ ልልነት ይፈጠራል የሚለው) በገቢር ከመስተዋል አልታደጋቸውም፡፡ ለዚህም ሁለት ማሳያዎችን እጠቅሳለሁ፡፡ የመጀመሪያው ባሳለፍነው ሳምንት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀረበው ሪፖርትና ማብራሪያ ላይ ተደጋግሞ የተነሳው ‹‹የአፈፃፀም ችግር›› የሚለው ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተብሎ ከበሮ ከተደሰቀለት የተቀመጠ ግብ አኳያ፣ ነባራዊው ሁኔታ ስምም አለመሆኑን ራሱ ኃይለማርያምም ‹‹የአፈፃፀም ጉድለት›› በሚል የዳቦ ስም ሊያሳብብ ከመሞከር በቀር አልካደውም፡፡ አንድ ማዕከላዊ መንግስትን የሚመራ ግንባር፣ ሊያውም እስከ ቤተሰብ የወረደ የኃይል ማዕከል ለመገንባት የሚጥር ስብስብ፤ ከተሞችን እያሰቃየ ላለው የመሰረታዊ ግልጋሎቶች ዕጦትና የተቀመጡ ዕቅዶች አለመሳካት ይህን በመከራከሪያነት ማቅረቡ፤ የስርዓቱ ተቋማት መፈረካከስን ከማስረገጥ ያለፈ የሚነግረን ምስጢር የለውም፡፡
ሌላኛው የአማካሪዎቹ ስብስብ ጉዳይ ነው፡፡ ሰውዬው ከጎኑ የሰበሰባቸውን ጉምቱ ፖለቲከኞች ትተን፤ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ካውንስል የማቋቋም ፍጥነቱን ብናስተውል ስርዓቱ በመለስ ዘመን የነበረውን ጥብቅነት አጥቶ መዋለሉን እንረዳለን፡፡ በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እንዲመራ ካስቀመጠው ዶ/ር ደብረፅዮን ውጪ፣ ‹‹የኢኮኖሚ ካውንስል›› በሚል አይረቤ ስም ለማቋቋም መሞከሩ ሳይበቃ፤ በባጀት ዕጥረት እየተሰቃየ ያለውን አስተዳደሩን ለመታደግ የፋይናንሻል ምንጮችን ከውጪ የሚያፈላልግ ሌላ ካውንስል መሰል ስብስብ ማደራጀቱን ስንታዘብ፤ ስርዓቱ ቢያንስ እንደ መለስ ዘመን መቀጠል በማያስችል ወላዋይነት /Brittle state/ ለመፈተኑ ጥቁምት ይሰጠናል ብዬ አስባለሁ፡፡ በተለይም ጠቅላይ ሚንስትሩ በሪፖርቱ ላይ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት ለማሟላት መንግስት የሐዋላ አግልግሎትን ማጠናከር እንዳለበት ከመግለፅ ባለፈ፣ ከ2000 ዓ.ም መጀመሪያ አንስቶ የህንዱን ካራቱሪ እና ሳውዲ ስታርን ጨምሮ ለበርካታ ባለሀብቶች ስለተሰጠው ሰፋፊ የእርሻ መሬት አንዳችም ነገር ትንፍሽ አለማለቱ የክስረቱ ዋነኛ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ከመሬት ቅርምት ጋር አያይዘው የተቃውሞ ድምፃቸውን ላሰሙ ምሁራንም ሆነ ‹‹አንድ ሄክታር መሬት በሃያ ብር›› መሰጠቱን በመኮነን የድርጊቱን ኢ-ፍትሓዊነት በዘገባው ለገለፀው ታዋቂው ‹‹ኒዎርክ ታይምስ›› ጋዜጣ፣ መለስና ጓዶቹ መከራከሪያ አድርገው ያቀረቡት ‹‹በአጭር ጊዜ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ ችግራችንን ይቀርፋል፣ የቴክኖሎጂና የሙያ ሽግግር እንዲደረግ ያስችላል›› የሚል እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ግና፣ ዛሬ ይህ ጉዳይ ሕልም ሆኖ ለውጭ ምንዛሪ ሐዋላን የሙጥኝ መባሉን እየሰማን ነው፡፡ እንዲሁም በራሱ በመለስ ዜናዊ በ2005 ዓ.ም በርግጠኝነት መውጣት እንደሚጀመር የተነገረለት የነዳጅ ክምችትም ቢሆን፣ ‹‹ውሾን ያነሳ…›› እንዲሉ የተዘጋ ፋይል ሆኗል (በነገራችን ላይ በፓርላማው. የፓርቲው ካድሬዎች ባለስልጣናቱ ላይ የሚያዘንቡት የጥያቄ እሩምታ የሚያመለክተው፣ ፓርላሜንታዊ ዴሞክራሲ ዘግይቶ ወደ ኢህአዴግ ሰፈር መምጣቱን ሳይሆን፣ የፓርቲውን የውስጥ የዕዝ ተዋረድ መሰነጣጠቁን እና ቡድንተኛነት ግንባሩን እያመሰው መሆኑን ነው፡፡ በተቀረ ከዚህ ውጪ ያለው መከራከሪያ ሁሉ ጥሩ የአደባባይ ቧልት ከመሆን የሚያልፍ አይመስለኝም) የሆነው ሆኖ ከላይ ኃይለማርያምን ያብራሩልናል ብዬ ለመጥቀስ ከሞከርኳቸው ጭብጦች በእጅጉ ባለፈ፣ ሪፖርቱን ያቀረበበት ተአብዮ እና የማንአለብኝነት መንፈስ በቅድመ-ምርጫው አንድ ዓመት ውስጥ አንዳችም የፖለቲካ ማሻሻያ እንዳትጠብቁ የሚለው ዋነኛው ሲሆን፤ አቦ ሌንጮ ለታ ‹‹ሰዎች አሳስተውታል›› እንዳለው፤ ዙሪያው ያሉት አለቆች እንዳዘዙት፤ ‹እኛ እየረገጥናችሁ እንቀጥላለን፣ እናንተም በተጨቋኝነታችሁ አዝግሙ› የሚለው ደግሞ ሌላኛው ውስጠ-ወይራ ጥብቅ መልእክቱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡
በመጨረሻም ጠቅላይ ሚንስትር ኃ/ማርያም ጥር 2003 ዓ.ም. ‹‹ምዕራፍ›› ከተሰኘ ኃይማኖታዊ መጽሔት ጋር ቃለ-መጠይቅ ባደረገበት ወቅት ‹‹ከመጽሐፍ ቅዱስ ደስ የሚልዎት ቃል የቱ ነው?›› በሚል ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠውን ምላሽ፣ አንድም ዛሬ የሚከተለውን መንገድ ቆም ብሎ እንዲፈትሽ ለማስታወስ፤ ሁለትም ለዚህ ተጠይቅ መደምደሚያ ይሆን ዘንድ ወደጃለሁና እንደሚከተለው አሰፍረዋለሁ፡-
‹‹መጽሐፍ ቅዱስን እወደዋለሁ፡፡ የዮሴፍ፣ የዳዊት፣ የሙሴ ሕይወት በጣም ይለውጡኛል፡፡ የእነዚህ ቅዱሳን ሕይወት በጣም ያንጹኛል፡፡ ዳንኤልም በጣም ጠቢብ ነው፡፡ ስለዚህም እንደርሱም መሆን መልካም እንደሆነ አስባለሁ፡፡››
ወንድም ኃይለማርያም ደሳለኝ፡- የልብህን መሻት አምላክ ይሙላልህ!!

No comments:

Post a Comment