Translate

Thursday, May 15, 2014

እምዬ ምኒልክ ሲመጥቅ፣ ወያኔ ሲወድቅ

ከሮበሌ አባቢያ፤ 14/5/2014

ቅጥረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ
ወያኔ በ1983 አዲስ አበባ ሲገባ እግረ መንገዱን የገበሬውን ልጆች፣ ጋዳፊና የአረብ ሀገር ከበርቴዎች ባስታጠቁት ዘመናዊ ታንክና መሣሪያዎች፣ እያጨደ በሬሳቸውና በደማቸው ላይ እየተረማመደ እንደነበር መሪር የቅርብ ትዝታ ነው። በቅጥረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው ጎጠኛው የወያኔ መንግሥት፣ የኢጣልያ ፋሺስት ያወጣውን በተለይ በአማራና በኦሮሞ ላይ ያነጣጠረውን የከፋፈለህ ግዛው ፖሊሲ ኮርጆ በመከተል፣ የአፄ ምኒልክ ሐውልት እንዲፈርስ ለማደረግ ሕዘቡን አነሳስቶ እንደነበር ይታወቃል።ሆኖም ሙከራው ወያኔ አስቦት በነበረበት ወቅት ባይሳካም፣ ሐውልቱን የማንሳት ሃሳብ አሁንም አለ። ስለዚህ ሕወሐት የሚመራው በውስጡ በሚስጥር በተሰገሰጉ ባንዳዎች እንደሆነ እያደር ሊታወቅ ስለቻለ የእምዬ ምኒልክ ወደጆች መዘናጋት የለባቸውም።Ethiopian king Atse Menelik
ሐውልቱና ከኢጣልያን ጋር የተደረጉት ሁለት ከባድ ጦርነቶች
እምዬ ምኒልክ፣ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በገፍ ታጥቆ ኢትዮጵያን ሊወር የመጣውን ጦር፣ አድዋ ላይ ገጥመው ወራሪውን ድባቅ መትተው አንፀባራቂ ድል ሲጎናፀፉ፣ ከሰሜን ሸዋ አብሮአቸው የዘመተው ስምንት ሺህ (8000) ፈረሰኛ የኦሮሞ ሚሊሽያ ሠራዊት በጦርነቱ ለተገኘው ድል ወሳኝ አስተዋፅዖ አድርጎ እንደነበረ በታሪክ የተመዘገበ የጀግንነት ሐቅ ነው። የአድዋው ድል የአውሮፓን ሀያላን መንግሥታትን አስደንግጦ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉአላዊ ነፃ ሀገር እንዲያውቋት አስገድዷቸዋል። ይህ ታላቅ የጥቁር ሕዝብ ድል በዓለማችን ላይ ለሚገኙት ጭቁን ጥቁሮች ሁሉ ሕያው ተስፋ ሰጥቷል።

በሽንፈቷ ሀፍረት የተከናነበችው ኢጣልያ፣ 40 ዓመት ሙሉ በሚስጢር ስትዘጋጅ ቆይታ፦ ሀ) በሚሊሽያዎቻችን ላይ ከሰማይ በአውሮፕላን የቦምብ ናዳ በማዝነብና በዓለም ሕግ የተከለከለውን መርዝ በመርጨት፤ ለ) በምድር በታንክና በመትረየስ የታገዘ መጠነ ሠፊ የሰለጠነ እግረኛ ጦር በማዝመት፤ ሐ) ሕዝቡን በጎሳ ከፋፍላ እርስ በርሱ በማጫረስ፤ መ) አማሮችና ኦሮሞዎች የሥልጣኔ ተፃራሪዎች ስለሆኑ ሌሎች ጎሳዎች በጠላትነት እንዲፈርጇቸው በመስበክ፣ አዲስ አበባን (ሸገርን) እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1936 ዓ.ም ለመቆጣጠር ችላለች። ዋቢ፦ Habešská Odyssea (YeHabesha Jebdu) የሃበሻ ጀብዱ by Adolf Parlesak Translated by Techane Jobre Mekonnen
የፋሺስትን ወረራ ያልተቀበሉት የኢትዮጵያ አርበኞች (በአዲስ አባባና በአካባቢው የሚገኙትን ኦሮሞዎችን ጨምሮ)፣ አራዳ ጊዮርጊስ በዳግማዊ ምኒልክ ሐውልት ዙሪያ ማታ ማታ እየተሰበሰቡ (ሬዲዮ አድማጭ መስለው) ይመካከሩ ነበር። ግራዚያኒ ይህን ሲሰማ ሐውልቱ እንዲነሳና በምሥጢር እንዲቀበር አዘዘ፤ በትእዛዙም መሠረት ሐውልቱ ተነስቶ ሌላ ጋ ተቀበረ። ፋሽስት ኢጣልያ ተሸንፎ ከሀገራችን ሲባረር፣ ሐውልቱ ከተቀበረበት ቦታ ተመልሶ እንደገና በቀድሞ ቦታው ላይ ሊተከል ቻለ።
ጠላት ተገዶ ያከበራቸውን እምዬ ምኒልክን ማክበር የምንኮራበት መብታችን ነው። እምዬ ምኒልክ ሲልቅ፣ የባንዳዎች ውላጅ ወያኔ ሲበሽቅ ሁሌ እደሰታለሁ። ምኒልክ አንድ ያደረጋትን ኢትዮጵያን ወያኔ ሲበታትናት አበክረን መቃወም የውዴታ ግዴታችን ነው። በዚህ ጉዳይ ለሚቃወሙን ተቺዎች መልሳችን ይሄው ነው።
ምኒልክ ከአንኮበር እስከ ሸገር
አፄ ምኒልክ ከአንኮበር ወደ ሸገር ሲመጡ ያጋጠማቸው ተፋላሚ ቱፋ ሙና የተባለ ሐይለኛ የኦሮሞ ገዢ ነበር። አፄው ብልሀተኛ ስለነበሩ አማላጅ ልከው ታረቁና ቱፋ ሙናን ክርስትና አንስተው አበልጅ ሆኑ። የቱፋ ሙና ሰፊ ዘሮች እነ አቶ ብሩ ጎሮንቶ ገፈርሳ ግድብ አካባቢ በስተ ምዕራብ-ደቡብ አንድ ትልቅ ግቢ ውስጥ ይኖሩ ነበር። አቶ ብሩን ባጋጣሚ ሱሉልታ አግኝቻቸው ከተዋወቅን በሗላ፣ ከባለቤቴ ጋር ገፈርሳ ድረስ እየሄድን እንጠይቃቸው ነበር። አቶ ብሩ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት በታላቅ ሥነሥርዓት ገፈርሳ በምትገኘው ቅድስት ማርያም ቤ/ክ በተፈፀመው ቀብራቸውም ላይ ተገኝቻለሁ።
ምኒልክ ከአንኮበር እስከ ሸገር (አዲሰ አበባ) የመጡት በኦሮሞ ባላባቶች የሚታዳደሩትን ግዛቶች አቋርጠው ነው። ቱፋ ሙና ብቻ ነው በነውጥ የተፋለማቸውና ውጊያው በእርቅ የቆመው። በነገራችን ላይ፣ የ1966ቱ አብዮት ሲፈነዳ እኔ አሰከማቀው ድረስ በሸዋ ውስጥ ሰፍኖ የቆየው ባላባታዊ ሥርዓት አራማጆች በአብዛኛው አለጥርጥር የኦሮሞ ተወላጆች ነበሩ።
የተወለድኩት አዲሰ አበባ ቀጨኔ ጋላ ሰፈር በሚባላው መንደር ውስጥ ነው። የከተማውን ዙሪያ ደህና አድርጌ አውቃለሁ። ሸዋ ውስጥ በልጅነቴ በእግሬና በፈረስ ከዚያም ስጎረምስ በመኪና በብዙ አቅጣጫዎች ተዘዋውሪያለሁ። ለምሳሌ፣ ከአዲስ አበባ ተነስተን እስከ 130 ኪሎሜትር ርቀት ዙሪያውን በወፍ በረር ብንቃኝ፣ የክልሉን ባላባትነት የአንበሳውን ድርሻ የኦሮሞ ተወላጆች ይዘውት እንደነበር አያከራክርም ለማለት ይቻላል። አፄ ምኒልክ የመሬት ግብር አስከፈሉ እንጂ የባላባቶችን የመሬት ይዞታ አለምክንያት አልነኩም። ዘውዱንም መሬቱንም እኔ ይዤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ሊቀረው ነው ብለው የመሬት ባለቤትነት በግል የእያንዳንዱ ዜጋ ይዞታ መሆን እንዳለበት በችሎት ላይ ስለመፍረዳቸው በአድናቆት ይነገርላቸዋል።
ስለ ባላባታዊ ሥርዓት የወዝ ሊግና የመኤሶን ፖሊሲ
በዘውዳዊው ሥርዓት ከነበሩት 14 ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ፣ በአካል ተገኝቼ የማላውቃቸው ወለጋንና ኢሉባቦርን ብቻ ነው። ስለ ኢሉባቦር የዚያ ተወላጅ የነበረው ወዳጄ ዶክተር ሠናይ ልኬ ትንሽ አጫውቶኛል። ዶክተር ሠናይ በአፍቃሬ እስታሊንስትነቱ የታወቀ ምሁር ነበር። የባላባታዊ ሥርዓት ጭቆና ያልደረሰብት ብሔር ብሔረሰብ ስለሌለ፣ የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታው በመደብ ትግል ነው የሚል የማያወላወል አቋም ነበረው። በዚያ ጊዜ ስለስታሊን ሥራዎች አንብቤ ባላውቅም፣ እኔም የባላባታዊውን ሥርዓት ጨቋኝነት ከምር እጠላ ስለነበር ከዶክተር ሠናይ ጋር ተቀራርበን ተወደጀን፤ ግን በምኒልክ ቤተ መንግሥት እነ ብ/ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ላይ የተፈፀመውን ግድያ ተከትሎ፣ ሻለቃ ዮሐንስ የተባለ የኢሕአፓ አባል ዶክተር ሠናይን (በ33 ዓመት እድሜው) ወዲያው ስለገደለው ከወዳጄ ጋር የነበረው ግንኙነት ተቋረጠ። ምሁሩ ሠናይ በወጣትነት ሞተ፤ ኢትዮጵያም ጀግና ልጇን አጣች!
ዶክተር ሠናይ የጎሳ ፖለቲካ አጥብቆ ይቃወም ነበር። “በከልቻ ኦሮሞ” በሚል ስያሜ ይንቀሳቀስ የነበረውን የኦሮሞ ጎሳ ቡድን መሪዎችን ተከረክሮ ትግላቸውን ወደ መደብ ትግል እንዲቀይሩ ለማግባባት ያደረገው ብርቱ ጥረት ከሞላ ጎደል ተሳክቶለታል።
ወጣቱ ምሁር ዶክተር ሠናይ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሶሽያሊስት አብዮት ለማካሄድ ገና 30 ዓመት ያስፈልጋል ብሎ ይናገር ነበር። ስለዚህም ነበር ግራ-ዘመም ምሁራን የተሰባሰቡበት የሕዝብ ጉዳይ አደራጅ ጽ/ቤት፣ “አዲሱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት” የተባለውን ፕሮግራም ከሰሜን ኮሪያ ተሞክሮ በመቅዳት በአማርኛ ቋንቋ አዘጋጅቶ በሥራ ላይ ለማዋል የሞከረው።
የልጅ እንዳልካቸው ካቢኔ የመሬት አዋጅ ቢያውጅ ኖሮ ለ30 ዓመት በሥልጣን ላይ እንደሚቆይ ዶክተር ሠናይ የነበረውን ግምት ተናግሮ ነበር። ዳሩ ግን ልጅ እንዳልካችው በሥልጣን ይቀናቀኑኛል ብሎ የፈራቸውን የነ አቶ ከተማ ይፍሩን ቡድን አባላት ሲያሳስር ቆይቶ በመጨረሻ እሱም የደርግ እስረኛ ሆኖ በደርግ ተረሸነ።
የወዝ ሊግ መሪ ሠናይ ልኬና የመላው ኢትዮጵያ ሶሽያሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) መሪ ሐይሌ ፊዳ፣ በመደብ ትግል ነፃነትና ፍትህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰፍናል ብለው የታገሉ፣ በዙሪያቸውም እጅግ በጣም ተከታዮችን ያሰለፉ፣ የአሮሞ ተወላጆች ነበሩ። ሠናይ በኢሕአፓ አባል ሲገደል ሐይሌ በደርግ ተረሸነ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የሁለቱም ምሁራን ተከታዎች፣ “ሰደድ” በተባለው እስከ አፍንጫው በታጠቀ የመንግሥቱ ሐይለማርያም ወታደራዊ ቡድን አዳኝነት ከያሉበት እየተለቀሙ ተገደሉ፤ የሁለቱም ምሁራን ድርጅቶች፣ ማለት የወዝ ሊግና መኢሶን፣ ከሰሙ።
ሀገራዊ አጀንዳ አራመጆቹ የወዝ ሊግና የመኢሶን ድርጅቶች ባይፈርሱ ኖሮ ዛሬ በአምቦ፣ በለቀምት፣ በኢሉባቦር፣ በጂማ፣ በዓለምማያ፣ በድሬዳዋ ወዘተ ዩኒቨረስቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በሚማሩ የኦሮሞ ወጣቶችና በደጋፊዎቻው ላይ፣ በወያኔ መሪዎች ትእዛዝ የአግዓዚ ጦርና ፌዴራል ፖሊስ የፈፀሙት ምንጊዜም የማይረሳ ጭፍጨፋ እንኳን ሊደረግ ባልታሰበም ነበር።
ስለዚህ ታላቁ የኦሮም ሕዝብ ይህን የወያኔ ንቀትና እብሪት ከቶም እንደማይቀበለው በመገንዘብ ፣ አምባገነኑ የኢሐዴግ መንግሥት ጥፋቱን በማመን ይቅርታ ጠይቆ አጥፊዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርብና በሀገራችን ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፈን የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ሁሉን አቀፍ ጊዜያዊ የሸግግር መንግሥት አንዲቋቋም ሁኔታዎችን ማመቻችት አለበት።
አንድነት ሐይል ነው
በአድዋ ጦርነት የተገኘው ድል የአንድነትን ሀይል አስተምሮናል። በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ልዩነቶችን እያሰፋ ሲቪል ጦርነት ውስጥ ሊከተን ነው። ዛሬ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ልዩነቶችን ተቋቁሞ ሰላምን ለማስፈን ብቸኛው ፍቱን መድሐኒት ዳያሎግ ስለሆነ ሁላችንም ተባብረን ወያኔን በቃህ ማለት ተገቢ ነው። ገዢው የወያኔ መንግሥት፣ በአምቦና በሌሎች የኦሮምያ ክፍሎች የተደረገውን ኢሰብአዊ ጭፍጨፋ ለማረሳሳት የሚያሰራጨው የማያዋጣ ከንቱ ፕሮፓጋንዳ፣ የተማሪዎችን የማሰብ ደረጃ ዝቅ ለማድረግ የታሰበ ትዝብት የሚያስከትል ምኞት ከመሆኑ በስተቀር ሌላ ፋይዳ የሌውም። ይልቁንስ ብጥቅጥቅ ያሉት ወያኔን የሚቃወሙ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት ተስማምተው የጋራ ጠላታቸውን በአንድነት ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር ተሰልፈው መፋለም ይጠበቅባቸዋል።
የዛሬዎቹን ኢትዮጵያውያን አንድ የሚያደርጉንን ሁለት ምሳሌዎች ላንሳ፦
ሀ) አፄ ምኒልክ፣ የጦር ጄኔራሎቻቸውን እነ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን፣ መኮንን ወልደሚካኤልን፤ ባልቻ አባነብሶን የመሳሰሉትን በጦር መሪነት መድበው፣ ከዝናኛው ከሰሜን ሸዋ አብሮአቸው የዘመተው ስምንት ሺህ (8000) ፈረሰኛ የኦሮሞ ሚሊሽያ ሠራዊት በጦርነቱ ለተገኘው ድል ወሳኝ አስተዋፅዖ አድርጎ እንደነበረ በታሪክ የተመዘገበ የጀግንነት ሐቅ ነው።
ለ) የወዝ ሊግ መሪ ሠናይ ልኬና የመኤሶን መሪ ሐይሌ ፊዳ፣ በመደብ ትግል ነፃነትና ፍትህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሰፍናል ብለው ታግለዋል። ለዚህም ያበቃቸው በአድዋው ድል በተገኘው ሀገራዊ ሉዓላዊነትና ነፃነት፣ ቀጥሎም በማይጨው ጦርነት ወጣቶቹ እነ አብቹ ከሸዋ፣ ሀብቶም ከሃማሴን፣ ተስፋጽዮን ከትግራይ (መቐለ)፣ ጋሹ ከጎጃም(ዳሞት)፣ ወርቁ ከሰላሌ፣ የየራሳቸውን ጦር በአብቹ የበላይ አዛዥነት ስር አሰልፈው፣ የከምባታው ሚሊሽያ ጦር ለሰባት ወራት በእገሩ ተጉዞ ማይጨው በመድረስ በጀግንነት ተዋግተው የወራሪውን ፋሺስት ኢጣልያ ሠራዊት መግቢያ መውጫ በማሳጣት ባሳዩት የአልበገሬነት ጀግንነትና የከፈሉት መስዋዕተነት ነው። በማይጨው ጦርነት ጊዜም ቢሆን በጦርነቱ ላይ የተሰማራው ሚሊሽያ ለውጊያው ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጠው “በእምዬ ምኒልክ” ስም እየማለ እንደነበር የጦርነቱን ታሪክ የጻፈው ቼኮስሎቫኪው የጦር አማካሪ በጦርነት መስክ ያየውን ሐቅ መስክሯል። ዋቢ፦ Habešská Odyssea (YeHabesha Jebdu) የሃበሻ ጀብዱ by Adolf Parlesak Translated by Techane Jobre Mekonnen
ማጠቃለያ
ሰው በሀገሩ እስረኛ፣ ገበሬው የመንግሥት ጭሰኛ፣ ካድሬው የሕወሐት ፓርቲ ታማኝ ሠራተኛ፣ ተራው ሕዝብ የገዢው መደብ ጥገኛ የሆኑባት ሀገር በዓለማችን ላይ ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ለዚያውም በ21ኛው ክፍለ ዘመን!!! ይህ መቀጠል የለበትም።
ሁላችንም የሐም፣ የሴም የያፌት ልጆች ነን። ካም የሐም የመጀመሪያ ልጅ ነው። ስለዚህ ዛሬ የምንገኝባት ኢትዮጵያ የነዚህ ሶስቱ ጥንታውያን አባቶቻችን ፍጡር ናት። ተጋብተናል፤ ተዋልደናል፤ ለነፃነታችን አብረን ተሰውተናል፤ ወንዞቻችን አስተሳስረውናል። በሌሎችም ሀገር እንደታየው ሁሉ (ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በቻይና) እርስበርስም ተዋግተናል። ስለዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የሚያዋጣን፣ የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥረን በመጣል የግለሰብ ሰብዓዊ መብት የሚከበርባትን የበለፀገች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን መገንባት ነው።
አንድ አዛውንት ከአምቦ ከተማ በ12/5/2014 ለኢሳት ራዲዮ ጣቢያ ባስተላለፉት መልዕክት ወያኔንን ተባብረን በኢትዮጵያዊነት መንፈስ በአንድነት እንድንታገለው ያቀረቡትን ልብ የሚነካ ጥሪ ተቀብለን በሥልጣን ላይ ያለውን አምባገነን መንግሥት ማንበርከክ ግድ ይላል።
ታዋቂው ጋዜጠኛና የሰብዓዊ መብት ታጋይ አበበ ገላው በኦሮምያ የተማሮዎች መጨፍጨፍ፣ የጎንደር ነዋሪዎች በጥይት መረሽን ከልክ በላይ አናዶት “ነፃነት ለኢትዮጵያ!” እያለ ደጋግሞ በመጮሁ ፕሬዚዳንት ኦባማ ያደርጉ የነበረውን ንግግር አቋርጠው ያዳመጡት መሆኑን በአድናቆት በዜና ብዙሃን አይተናል ወይም ሰምተናል። እግዚአብሔር የአርበኛውን የጋዜጠኛ አበበ ገላውን ወኔና የሀገር መውደድ መንፈስ ይስጠን።
እምዬ ምኒልክ እንደገና ሲመጥቅ፣ ወያኔ ሲወድቅ የምናይበት ጊዜ ስለተቃረበ የኢትዮጵያን ትንሣዔ ለማየት የምንጓጓ ልጆቿ ሁሉ ተባብረን እንነሳ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካና የሕሊና እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ የፈቱ!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
rababya@gmail.com

No comments:

Post a Comment