Translate

Thursday, May 29, 2014

ዓባይ እንደዋዛ፤ ግድቡን ከጥላቻ አንጻር ማየት አደገኛ ነው (ዶ/ር አክሎግ ቢራራ፣ ክፍል አራት)

Click here for PDF

የዚህ ተከታታይ ፅሁፍ መሰረታዊ ሃሳብና ትንተና፤ ኢትዮጵያ ዓባይንና ሌሎች ወንዞቿን የራሷን ኢኪኖሚ ዘመናዊነት፤ ለሕዝቧ የምግብ ዋስትና ስኬታማነት፤ እያደገ ለሄደው ወጣት ትውልድ የስራ እድል የመፍጠር ወዘተ መብት ያላት መሆኑን የሚያጠናክር ነው። The Nile is African and Ethiopia is its hub በሚል አርእስት ለአለጀዚራ ያቀረብኩት ፅሁፍ ይኼን ይገባኛልነት በማስረጃ ተደግፎ ያሳያል። በአረብኛ የተተረጎመው ትንተና የብዙ አንባቢዎችን አስተሳሰብ እንደቀሰቀሰ ሰምቻለሁ፤ አሉታዊና ነቀፋ ያለበት ትችት አልደረሰኝም። የኢትዮጵያን ይገባኛልነት ሌሎች የጥቁር አፍሪካ ተፋሰስ አገሮች እንደሚደግፉም አሳይቻለሁ።
Ethiopia's dam on Abbay/Nile riverአከራካሪ ሆኖ ያየሁትና በተከታታይ ለመተንተን የሞከርኩት የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅምና ይገባኛልነት ከጥያቄ ውስጥ ለማስገባት አይደለም፤ ለማጠናከር ነው። ገዢውን ፓርቲ መቃወምና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም መደገፍ የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን አሳይቻለሁ። የኢትዮጵያ ይገባኛልነት፤ ዘላቂ ጥቅምና ደህንነት ከጥያቄ ውስጥ መግባትና ለፖለቲካ መንደርደሪያና መጠቀሚያ ሊሆን አይገባውም እላለሁ። ኢትዮጵያ የባህር በሯን አጥታ ዓባይንም ማጣት ለተከታታይ ትውልድ በደል ነው። ለማስታወስ አፄ ኃይለሥላሴና ደርግ ለማልማት የሞከሩትን ዓባይ ዛሬ እድል ተገኝቶ የተሃድሶ ግድብ ስራ መጀመሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚፈልገው ሂደት የተገኘ ነው። ሕዝቡ በመንፈሱም፤ በጉልበቱም፤ በገንዘቡም እንደሚደግፈው እንሰማለን። ለኢንቬስትመንቱ የሚፈሰው ኃብት የህወሓት/ኢህአዴግ የግል ኃብት አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃብት ነው። ጥቅሙም ለኢትዮጵያ ሕዝብ መሆን አለበት።

የዚህ ትንተና መሰረት እንደ ተሃድሶ ግድብ ያለ የኢኮኖሚና የሃግር ጥንክርና ለማስገኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ከፖለቲካው ፍትሃዊነትና ከሃብት ስርጭት ሚዛናዊነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም የሚል ነው። ይክ ከሆነ የግድቡ ጥቅም ለገዢው ቡድን ብቻ መዋሉ አይቀርም። የህወሓት መስራቾችና መሪዎች ለጥቂቶች ጥቅም “ስልጣን ወይም ሞት” ብለው በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ የጫኑት አደገኛ የከፋፍለህ ግዛው የአገዛዝ ስርዓት ዛሬ ወደ ከፍተኛ አደጋ እያመራ ነው። የተሃድሶ ግድብ ቢሰራም ባይሰራም አሁን ያለውን ቀውስ ሊፈታውና ሊገታው አይችልም። ከጅምሩ ስርዓቱ በማይታረቁ የብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች ልዩነቶች፤ የተፈጥሮ ኃብትን ለተወሰነ ቡድን ባለቤትነት በማሸጋገር፤ ይኼን ስኬታማ ለማድረግ መብቶችን በማፈን ወዘተ ላይ የተመሰረተ ነው። ሕዝብ ከሕዝብ እየለያዩ፤ መሬትን ቆራርሶ ለጥቂቶች ጥቅም እያስተላለፉ፤ ህወሓት በዋና ጠላትነት የፈረጃቸውን ከመሬትና ከሃብታቸው እያስለቀቀና እያደኼየ፤ ሰላምና እርጋታ ለመፍጠር አይቻልም። የስርዓቱ አገልጋይነት ለጭቁኖች መብትና የኑሮ መሻሻል አለመሆኑ በይፋ ሲከሰት ቆይቷል። የኦሞ ሸለቆን፤ የጋምቤላን፤ የቤኒ ሻንጉል ጉሙዝን፤ የአፋርን፤ የኦጋዴንን “ጭቁን” ሕዝብ ከጢቂቶቹ አዲስ ባለኃብቶች ጋር ብናነጻጽር ህወሓትና ደጋፊዎቹ ለማን ጥቅም እንደቆሙ ለማየት አንቸገርም። የጥቂቶች ስልጣን ሊቆይ የቻለውና የሚቆየው የእርስ በርስ ጥላቻንና ግጭትን በማቀጣጠል፤ ሰብአዊ መብቶችን ፍፁም በሆነ መንገድ በማፈን፤ በተለይ የአማራውንና የኦሮሞውን ሕዝብ በማጋጨት፤ እልቂት እንዲስፋፋ በማድረግ፤ አብሮ በመስራትና አብሮ ችግሮቾን በመፍታት ፋንታ ህብረተሰቡን በማራራቅ፤ ባጭሩ በውይይትና በዘዴ ሰላምና እርቅ ስኬታማ እንዳይሆን በማድረግ ነው። ታዛቢዎች አስቸጋሪ ሆኖ ያገኙት አንዳንድ ለፍትህና ለዲሞክራሲ የቆሙ ስብስቦች የህወሓትን የጥላቻ ፈለግ ተከትለው ከሳቱ ላይ ቤንዚን መጨመራቸው ነው። ዙሮ ዙሮ የጥላቻ ፖለቲካ የሚረዳው የሚቃወሙትን ህወሓትን መሆኑን ዋጋ አልሰጡትም። ጥላቻን በጥላቻ፤ እልቂትን በእልቂት፤ አፈናን በአፈና፤ የቂም በቀልን በቂም በቀል ወዘተ የሚተካ ወይንም እነዚህን የመሰሉ የፖለቲካ ባህሎችና ልምዶች የሚያጠናክር ስብሰብ ወይንም ግለሰብ “ለቆመለት ሕዝብ” እውነተኛ አገልጋይ መሆኑ ያጠራጥራል። ህወሓት የሚፈልገውን የሚያደርግ መሆኑ ግን አያከራክርም። ለፍትህና ለእውነተኛ እኩልነት መቆምና የብሄር፤ ብሄረሰብ፤ ኃይማኖት ጥላቻን ማራገብ ሰማይና መሬት ናቸው። አይገናኙም። [ሙሉውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ]

No comments:

Post a Comment