Translate

Sunday, May 11, 2014

የአበበ ገላው “ጩኸት” አንደምታ

ዳጉ ኢትዮጵያ (dagu4ethiopia@gmail.com)

አንድ የማህበራዊ ድረ-ገጽ ወዳጄ “በአበበ ገላው የሰሞኑ ድርጊት ምን አስደሰተህ?” ሲል ግራ በመጋባት ጠየቀኝ፡፡ የወዳጄ ጥያቄ የአበበ ገላው በፕሬዚደንት ኦባማ ፊት የኢትዮጵያውያንን የነፃነት ጩኸት ማስተጋባት በኔ በኢትዮጵያ ምድር የምኖር ዜጋ ላይ ስለሚኖረው አንደምታ በጥልቅ እንዳስብ አደረገኝ፡፡Abebe Gellaw interrupted President Obama's speech
ዜጎች ሐሳባቸውን በነጻነት መግለጽ በማይችሉባት ሐገር፤ ይልቁንም “ለዚህ ሥርዓት ጥሩ አመለካከት የለህም፣ የወጣት ሊግ፣ የሴቶች ፎረም፣ የነዋሪዎች ፎረም ወዘተ በተሰኙ የስርዓቱ አደረጃጀቶች አልተሳተፍክም” በሚል – መገለል፤ ባስ ሲልም መዋከብና ከስራ መፈናቀል በሚደርስበት ሐገር የማስበውን የሚተነፍስልኝ፣ አንደበት የሚሆንልኝ ሳገኝ ብደሰት፣ ባሞግሰው – ጀግና ብለው ምን ይገርማል? የህዝቡን ይሁንታ አግኝቼ ተመርጫለሁ፣ ኮንትራት ተሰጥቶኛል ወዘተ የሚል ማመካኛ እየደረደረ በምከፍለው ግብር የሚተዳደሩ የህዝብ ንብረት የሆኑ ሚዲያዎችን ወደራሱ የግል ንብረትነት አዛውሮ ጠዋት ማታ ሳልጠግብ – ጠግበሃል፣ በሥራ አጥነት እየተንከራተትኩ – ሥራ በሽ በሽ አድርጌልሃለሁ፣ የኑሮ ውድነቱ አጉብጦኝ – ኑሮህ ተሻሽሏል እያለ የራሱን ሹማምንት ምቾት የኔ እንደሆነ አድርጎ ለኔው የሚለፍፍ ስርዓት ባለበት ሐገር የነጻነት ጥማቴን የሚናገርልኝን አበበን ባወድሰው የሚያስገርመው ምኑ ነው?

በአምቦ፣ ሐሮማያ፣ አፋር፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ተምቤን፣ ጎንደር ወዘተ በወንድም እሕቶቼ፣ በእናት አባቶቼ ላይ የሚደርሰውን አፈና፣ ግርፋት፣ ከመኖሪያ ማፈናቀል፣ ግድያ፣ አላግባብ ከስራ ማባረር ወዘተ ሳወግዝ “የ… ከተማ ነዋሪዎች መንግስት የወሰደውን እርምጃ አደነቁ… ከግድያው የተረፉትም አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠየቁ” እየተባለ በስርአቱ የፕሮፖጋንዳ አንደበቶች ጩኸቴን ስቀማ – ያልኩት ቀርቶ ለመንግስት ጆሮ የሚጥመው በኔ ስም ሲነገር – አበበ ትክክለኛውን ጩኸቴን ሲጮህልኝ እልል ብል፣ ትክክለኛ ብሶቴን ለአደባባይ ሲያበቃልኝ አበጀህ ብለው ተሳሳትክ የሚለኝ ማነው?
በሐገር ውስጥ በመሆን ስርዓቱ ያሰፈነውን የፍርሐት ቆፈን ወግድ ብለው በብዕራቸው ብሶቴን የተነፈሱልኝን፣ ጩኸቴን የጮሁልኝን ተቃዋሚዎች፣ በጋዜጠኝነት ሙያቸው አገዛዙ ያመጣብኝን የመረጃ ረሐብ ሊያስታግሱልኝ የሞከሩ ጋዜጠኞችንና ጦማሪያንን ሰብስቦ በፈጠራ ክስ በእስር ሲያጉራቸው አሰፈንኩት ብሎ ያሰበውን የህዝብ ድምጽ እርጭታ በነጎድጓዳማ ድምፁ የሰበረልኝን – ስርዓቱ ለሚዘጋው እያንዳንዱ በር በአንጻሩ በትግል የሚከፈት ሌላ በር እንደሚኖር በተግባር ያረጋገጠልኝን አበበን አበጀህ የኔ አንደበት ብለው ወዴት ላይ ነው ጥፋቴ?
“የዋህ ነህ – የአበበ ገላው ድምጹን ማሰማት ስርዓቱን አያፈርሰውም፣ ኦባማ በስርዓቱ ላይ ማዕቀብ እንዲጥል፣ በአደባባይ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰውን በደል እንዲያወግዝ አያደርገውም”ይሉኛል፡፡ እኔስ እሱን መች ጠበቅኩና? ለተበዳይ በደሉ መሰማቱ በራሱ የድሉ መጀመሪያ መሆኑን አታውቁም? ለታፈነ ሰው ጩኸቱ ለአደባባይ መብቃቱ፣ በደሉ ለጆሮ መድረሱ በራሱ ስኬት ነው፡፡ እንጂማ ጀርባዬ ላይ ሆኖ የሚያጎብጠኝን፣ እንደ እንስሳ ስለ ሆዴ እንጂ ስለ ነጻነቴ እንዳልጠይቅ የሚያስፈራራኝን፣ ስራ፣ የመኖሪያ ቤት ወዘተ በጥረቴ ሳይሆን ለስርዓቱ ባጎበደድኩት መጠን የማገኘው ድርጎ ያደረገብኝን ስርዓት ወግድልኝ ብሎ የማሽቀንጠሩ ኃላፊነት የኦባማ ሳይሆን የኔ መሆኑን መቼ አጣሁት? ገዢዎቼ የወንበር ስስት፣ የስልጣን ስጋት ስላለባቸው የአቤን ድርጊት ከወንበራቸው ከመነቅነቅ አንጻር ሊመዝኑት ይፈልጋሉ፡፡ የኔ መስፈሪያ ሌላ ነው፡፡ የማይወክለኝን ከወንበሩ የመነቅነቁ፣ ከምርጫ ኮሮጆ በመጣ የዜጎች ይሁንታ ሳይሆን ከሩስያ በመጣ የኤኬ 47 ጠመንጃ ጉልበት መንግስትነትን የያዘውን ስርአት የማንኮታኮቱ የቤት ሥራማ የኦባማ አስተዳደር ሳይሆን የኛ የኢትዮጵያውያን የመሆኑን ሐቅ መቼ ሳትኩት?
ደግሞስ እውነትን በሐይል ለስልጣን መናገር ያለውን ጉልበት መቼ አጣችሁት? ይኸው አበበ አይደል እንዴ በሐገር ውስጥ በጠመንጃና በእስር ቤት ሐይል፣ በውጪ ሐገር በብልጣ ብልጥነት ሸፋፍነው ይዘውት የነበሩትን የአምባገነንነት ማንነት በአለም አደባባይ እርቃኑን አስቀርቶ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለክውታ (ምናልባትም ለህልፈት)፣ የስርአቱን ቲፎዞዎችም ለከፍተኛ ብስጭት የዳረገው? ትግሉ ፈርጀ ብዙ መሆኑን አትርሱ እንጂ፡፡ የቀድሞው መሪ ድምጻችን ይከበር ብለው ወረቀት ይዘው አደባባይ የወጡ ወንድሞቻችንን ግንባር በአልሞ ተኳሾቻቸው አስነድለው መቼ ዝም አሉ? “ባንክ ሊዘርፉ ሲሉ ተገደሉ” ብለው በወጣቶቹ ወላጆች ላይ የስነ ልቦና ጦርነት አልከፈቱም? ይህን ግፍ ያዩ ብዙዎች በኢትዮጵያ ሰማይ የእውነትና የፍትሕ ፀሐይ መቼም አትወጣም ብለው ተስፋ እንዲቆርጡ አልደረጉም? ስለዚህ የአበበ ድርጊትም አፋኞቻችንን – “እውነት ታፍና መቼም አትቀርም፤ ጠመንጃም የእውነትን ወሊድ ያዘገየው ይሆናል እንጂ እስከወዲያኛው አያስቀረውም” የሚለውን ሃቅ በአእምሯቸው እንዲያቃጭል ማድረጉ በራሱ ድል አይደለም? ይልቁንም ክስተቱ የተፈፀመው የስርአቱ ጥቅመኞች ቀድሞ በአካል፣ ሞተውም በ”ራዕይ” የሚመሯቸውን ግለሰብ ልደት ለማክበር ተፍ ተፍ ሲሉበት በነበረው ወቅት መሆኑ በስርአቱ ደጋፊዎች ላይ የፈጠረውን የስነ ልቦና ጉዳት እስኪ ወደ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ጎራ በሉና ታዘቡ!
“አበበ አንድ ግለሰብ ነው… ጩኸቱም ምንም ለውጥ አያመጣም” ይላሉ፡፡ እንዴ… የነፃነት መንፈስ እኮ ሁሌም ሲጀመር በአንድ ወይም በጥቂት ሰዎች ነው፡፡ ደግነቱ ግን ቶሎ ይዛመታል፡፡ ውቂያኖስ ሳይገታው፣ ፖለቲካዊ ድንበሮች ሳያስቆሙት፣ የመረጃ አፈና ሳያግደው ወደሺዎች ከዚያም ወደ ሚሊዮኖች ይጋባል፡፡ ምርጫ 1997ን ማስታወስ ይቻላል፡፡ ጥቂቶች የነፃነት መንፈስን ከታሰረበት ፈተው ለቀቁት፡፡ በወራት ጊዜ ውስጥ ከገጠር እስከ ከተማ – ከድሐ ጎጆ እስከ ቤተ መንግስት ተቆጣጠረው፡፡ ዛሬም በአበበ ገላው የተለኮሰው የነጻነት ችቦ የነጻነት እጦት ብርድ ሆኖ ያንዘፈዘፈንን በሙቀቱ ሲያፍታታን፤ የአምባገነንነት ትኩሳት ጭንቅላታቸው ላይ የወጣውን ገዢዎቻችንን ነበልባል ሆኖ ሲፈጃቸው መመልከታችን አይቀሬ ነው፡፡
እናም … እናም… እናም… በወንድሜ አበበ ገላው ሥራ ደስ ተሰኝቻለሁ – ተነቃቅቻለሁ – ተስፋንም ሰንቄያለሁ፡፡ ነገ ይህ የነፃነት ስሜት በአእላፋት ላይ ተጋብቶ ገዢዎቻችንን በየሔዱበት ሲያስጨንቅ፣ አንገት ሲያስደፋ፣ ሲያብረከርክና ሲያፍረከርክ አሻግሬ እያየሁ…

No comments:

Post a Comment