ዳዊት ዳባ
የለውጥ አስፈላጊነት ላይና ወያኔ መራሹ መንግስት ይበቃው ዘንድ ባብዛኛው ዜጋ ከተቻለ የሚለው እንዳለ ብዥታ የለም። ይህ ፍላጎት የብዙ ስረአቱ ውስጥ ያሉ ዜጎችም ጭምር መሆኑን የተለያዩ መረጃዎችን ጨምቆ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል። በርግጥ የለውጡ አስፈላጊነት ላይ የሚስማሙና አይቀሬነቱን የሚያውቁ ነገር ግን ለውጡ የተረጋጋና ችግሮች ያልበዙበት እንዲሆን ይረዳል ብለው አገዛዙ ድርሻ በሚያደርግበት እንዲከወን የሚመኙ አሉ። ፈራ ተባ እያሉ ሀሳቡን አንዳንዴ ያነሱታል። ይህ ሀሳብ ክፋት ባይኖረውም ጥሩ ምኞት ብቻ ነው የሆነው። በትንሹ እንኳ ተቀባይነት እንዲያገኝ አይደለም እንዲሰማ ለማድረግ አገዛዙ ጉልብት አልሰጠው እያለ ብለጭ ድርግም ይላል። አውቆ የሚያደርገው በሚመስል ገና እነዚህ ጥሩ አሳቢ ዜጎች ቁምነገሩን ሲያነሱት አገዛዙ አንጀት ቁርጥ የሚያስደርግ ሰማይ ሰማይ የሚያካክል አጋረዊ ጥፋቶችን አከታትሎ እየፈጸመና እያላገጠበት ያስቸግራል። ለምን ብሎ ለሚጠይቅ?። ቀንደኛ ለሆኑት የስርአቱ ሰዎች ከኛ በላይ ይህ መንገድ እንዳማያዋጣቸውና እድሜያቸውን ማሳጠር ብቻ እንደሆነ አሳምረው ስለሚያውቁ ነው። እውነት ለመናገር ትክክልም ናቸው። የትኛውም ለውጥ የሚመጣበት መንገድ የመጨረሻ ውጤቱ ለነሱ መቶ በመቶ ፍፁም ተመሳሳይ ነው። አስፍተንና እርቀን አስበን፤ ሆደ ሰፊ ሆነን፤ ይቅር ብለናል ብለን መጫኛ ነክሰን ብንለምንም ልንሳምናቸውና ሀሳብ እንዲቀይሩ ለማድረግ አይቻለንም። የሰሩትን ያውቁታል። ስለዚህም ላልቆረጡ ይቁረጥ።