የአውሮፓ፣ የፓስፊክ፣የካሪቢያንና የአፍሪካ ፓርላማ አባላት ስብስባን ከሰሞኑ አዲስ አበባ ማስተናገዷ አይዘነጋም፡፡ በስብሰባው ለመካፈል በዛ ያሉ እንግዶች በከተማይቱ የሶስት ቀናት ቆይታ በማድረግ በአገሪቱ የፓለቲካ፣ የሰብአዊ መብት አያያዝና የሚዲያ ነጻነት ዙሪያ ከመንግስት ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ዳዊት ሰለሞን ከእንግዶቹ ለኢትዮጵያ መንግስት ቀርበው ከነበሩ ጥያቄዎች መካከል አንዱን በመምዘዝ የተሰጣቸውን ምላሽ ያጠይቃል፡፡
የየአህጉራቱ የፓርላማ ተወካዮች በአዲስ አበባ ካደረጉት ስብሰባ በተለይ ትኩረት ስቦ የከረመው ፖርቹጋላዊቷ የአውሮፓ ፓርላማ ተወካይ ሚስ አና ጎሜዝ ከዘጠኝ አመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ነው፡፡ አና በ1997 የተካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ለመታዘብ የመጣው የአውሮፓ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ በነበራቸው ኃላፊነት ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን በማውጣት ምርጫው መጭበርበሩን ማጋለጣቸው በመንግስት ጥርስ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓቸዋል፡፡ በጊዜው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ አና ጎሜዝን የተመለከተ ሰፊ ሃተታ በማቅረብ ወይዘሮዋ የቅንጅቱ አመራር ከነበሩት ብርሃኑ ነጋ ጋር በፍቅር መውደቃቸውን ጭምር መፃፋቸው አይዘነጋም፡፡ መለስ የቲና ተርነርን ተወዳጅ የሙዚቃ ስራ ‹‹What’s love got to do with it›› በመጥቀስ የአና ተቃውሞን ከዶክተሩ ጋር ነበራቸው ካሉት ግላዊ ግኑኝነት ጋር ለማቆራኘት ሞክረዋል፡፡
የፓርላማ አባሏ በኢትዮጵያ የነበራቸውን ቆይታ በማጠናቀቅ ወደ አውሮፓ ከተመለሱ በኋላም ሪፓርታቸውን በማጠናከር በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንከር ያሉ እርምጃዎች እንዲወሰዱ ወትውተዋል፡፡ ውትወታቸው በተወሰነ መልኩ ተቀባይነት በማግኘቱም መንግስት የቀጥታ የበጀት ድገማውን እስከማጣት ደርሷል፡፡ አና ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በአውሮፓ ፓርላማ ቆይታቸው ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዙ የሰብአዊ መብት ሪፓርቶችን ከማቅረብ አልተቆጠቡም፡፡ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ስለተጣሉ ፓለቲከኞችና ጋዜጠኞች ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ በማሰማትም የአውሮፓ ፓርላማ ስለ ኢትዮጵያ ግድ እንዲለው ተማጽነዋል፡፡
ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙና እስክንድር ነጋ የሳካሮቫን ሽልማት ለማግኘት በዕጩነት እንዲያዙ ጥቆማ የሰጡት አና ስለመሆናቸውም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈተ ህይወት በመንግስት ሆን ተብሎ መደበቁንም በመግለጽ መለስ ይህችን አለም የተሰናበቱት በመንግስት በይፋ ከመነገሩ አንድ ወር ቀደም ብሎ እንደነበር መናገራቸውም ከገዥው ፓርቲ ጋር የነበራቸውን የተበላሸ ግኑኙነት የበለጠ እንዳከፋው ለመገመት አያዳግትም፡፡ ወይዘሮዋ የአውሮፓ ፓርላማን በመወከል በስብሰባው ለመካፈል የቪዛ ጥያቄ ማቅረባቸው ከተደመጠ ጀምሮ የሚዲያውን ትኩረት አግኝተዋል፡፡ መንግስት አምርረው ለሚተቹት አና ወደ አገር የሚገቡበትን ቪዛ ይፈቅዳል? የማይፈቅድ ከሆነስ ምን ይፈጠራል? ፡፡
ሁሉን በጥርጣሬ የሚመመለከቱ ወገኖችም ‹‹አና ወደ አገር የሚገቡ ከሆነ ከመንግስት ጋር ተደራድረዋል›› ማለት ነው የሚሉ ቅድመ ግምቶችን ያሰፍሩ ነበር፡፡ በመጨረሻም አና ቪዛውን አገኙ፡፡ ‹‹ቪዛ እንደማገኝ እርግጠኛ ነበርኩ›› የሚሉት የሰብአዊ መብት ተሟጋቿ ‹‹ከዚህ በፊት በብራሰልስ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ ዲፕሎማት የ2ዐዐ2 ምርጫን ለመታዘብ የምፈልግ ከሆነ ቪዛ እንደሚሰጡኝ ነግረውኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በግዜው ሌሎች የምርጫ ታዛቢ ቡድን አባላት በአገሪቱ ያለውን ሁኔታ እንዲመለከቱ ስለፈለግኩ የቪዛ ጥያቄ አላቀረብኩም፡፡ ደግሞም መለስ ባለመኖራቸው ቪዛውን እንደሚሰጡኝ እርግጠኛ ነበርኩ፡፡
ወደ አገሪቱ የመጣሁት የአውሮፓ ፓርላማን በመወከል ነው፡፡ እኔን መከልከል የአውሮፓ ፓርላማን አለመቀበል ስለሚሆን እንደተቀበሉኝ ይሰማኛል›› ማለታቸው ተደምጧል፡፡
አና የተገኙበትን የስብሰባ መድረክ በንግግር የከፈቱት በተፈጥሮ ሞት ስልጣናቸውን የተሰናበቱትን መለስ ዜናዊን የተኩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ነበሩ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው የኢትዮጵያን መንግስት ዴሞክራትነት የሚያሳዩ ዐረፍተ ነገሮችን ተጠቅመዋል፡፡ የፓለቲካ ምህዳሩን ለተቃዋሚዎች የበለጠ ክፍት ለማድረግ በቁርጠኝነት መነሳታቸውን፣ ሙሰኝነትን መዋጋታቸውንና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጭምር ዘብጥያ መውረዳቸውን አስታወቁ፡፡
የቀድሞው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ዲን በንግግራቸው ማሳረጊያ የጠቀሱት ዐረፍተ ነገር ግን ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን በቅርብ ሲከታተሉ የቆዮትን ሚስ አና ጎሜዝን አላስደሰተም፡፡ ‹‹ዛሬ ኢትዮጵያ ለብዙዎች አርአያ መሆን በምትችልበት ደረጃ ላይ ትገኛለች›› ያሉት ኃይለማርያም ‹‹በእስር ቤቶች ውስጥ በፖለቲካ አመለካከታቸው የተነሳ የታሰሩ ፖለቲከኞች የሉም፡፡ ጋዜጠኞች በጻፉት ነገር የተነሳ ለእስር አልተዳረጉም፡፡››
አና ወደ ጉባዔው የመጡት ነገሮችን በዝምታ በመከታተል ሌሎች ባልደረቦቻቸው ስለ ኢትዮጵያ በቅርበት ማወቅ የሚችሉበትን ነገር ለማመቻቸት ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በቸልታ ሊያልፉት አልወደዱም፡፡ የዚህ ዘገባ ፀሐፊ ከአና ጎሜዝ ጋር ከመጡት የፖርላማ አባላት መካከል ኦሌ ስክሚደትን በማግኘት እንደተገነዘበው ወይዘሮዋ መረርና ከረር ባሉ ቃላት በኢትዮጵያ እስር ቤቶች ውስጥ በመማቀቅ ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መኖራቸውን በማስረዳት ያልተጠበቀ ጥያቄ ለፓርላማ አባላቱ አቅርበዋል፡፡ ‹‹በእስር ቤቶች ውስጥ ፖለቲከኞች ጋዜጠኞች መኖር አለመኖራቸውን ለመረዳት ለምን ቃሊቲን እንድንጎበኝ አንጠይቅም?›› በአና ጥያቄ የተስማሙት የስብሰባው ተካፋዮች አንድ ቡድን በማቋቋም በስፍራው ለነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት የጉብኝት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ባይሳካም፡፡ መንግስት ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን በሚከተሉት አስተሳሰብ ይሁን በሚያራምዱት ፍልስፍና የተነሳ ለእስር አልዳረግኩም በማለት ሲናገር የመጀመሪያ ግዜው አይደለም፡፡
አና እንደመሰክሩት በ1997 ምርጫ ገዥውን ፓርቲ በመገዳደር ከፍተኛ ድምፅ አግኝተው የነበሩት ቅንጅቶች ተጠራርገው ቃሊቲ ሲወርዱ አቃቤ ህግ ‹‹አገር በመክዳትና ህገ መንግስታዊውን ስርዓት በኃይል ለመናድ›› በሚል ክሶች ፍርድ ቤት ገተራቸው፡፡ መንግስትም ሰዎቹ የተከሰሱት አገር በመክዳት ወንጀል እንጂ ኢህአዴግን በመቃወማቸው አይደለም አለን፡፡ አቃቤ ህግ በፍርድ ቤት ቅንጅቶች ላይ ያቀረበው ማስረጃ ግን በምርጫ ክርክር ወቅት ያደረጓቸውን ንግግሮች ጭምር ያካተተ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የፍርድ ውሳኔውን ካስተላለፈ በኋላ ታሳሪዎቹ ‹‹በፖለቲካ ውሳኔ›› የተቆለፈባቸውን የብረት ፍርግርግ አልፈው ነጻነታቸውን ተቀዳጁ፡፡ የፖለቲካ እስረኛ የለም›› በማለት ሽንጡን ገትሮ ይከራከር የበረው መንግስት‹‹ በፖለቲካ ውሳኔ›› እስረኞቹን ለቀቀ፡፡
የፖለቲካ እስረኛ ከሌለ እንዴት የፖለቲካ ውሳኔ እስረኛን ነፃ ሊያወጣ ይቻለዋል?፡፡ መኢአድ ከገዥው ፓርቲ ጋር አንድ ስምምነት የተፈራረመባትን ገጠመኝ ማስታወስም ተገቢ ይሆናል፡፡ የምርጫ ስነ ምግባር ኮድን መኢአድ የተፈራረመበት ቀለም ሳይደርቅ መንግስት ከ2ዐዐ የሚልቁ የፓርቲውን አባላት ከእስር ፈትቷል፡፡ እነዚህ ሰዎች የታሰሩበት ምክንያት ከደረቅ ወንጀል ጋር የሚያያዝ መሆኑን መንግስት ሲገልጽ ቢቆይም በመጨረሻ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ተለቅቀዋል፡፡
እንዴት ነው በደረቅ ወንጀል ተከስሶ የታሰረ ሰው በአንድ የስልክ ጥሪ ሊለቀቅ የሚችለው? መኢአድ አባላቶቼ ታሰሩ በማለት ወቀሳ ሲያቀርብ በመክረሙ የሰዎቹ መፈታት የሚያሳየው ወቀሳው እውነተኛ እንደነበር ነው፡፡ ዛሬም በእስር ቤቶች ውስጥ አንዷለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ዘሪሁን ገብረ እግዚአብሄር፣ በቀለ ገርባ፣ አበበ ቀስቶ፣ ኦልባና ሌሊሳን የመሳሰሉ ፖለቲከኞችና አምስት ጋዜጠኞች በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡ ሁሉም በ2ዐዐ1 በወጣው የፀረ ሽብረተኛነት አዋጅ የተወነጀሉ ናቸው፡፡ መንግስት የእነዚህ ሰዎች የእስራት ምክንያት ‹‹ከሽብርተኝነት›› የተጋመደ መሆኑን ቢናገርም የሚያምነው አካል አላገኘም፡፡ የሚበዙት እስረኞች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ሲያደርሱ፣ የማስተማር ስራቸውን ሲከውኑ፣ በቢሯቸው የአዘቦት ስራቸውን ሲፈጽሙ የተያዙ ናቸው፡፡ በፍርድ ቤት የቀረቡባቸው ማስረጃዎችም አለም ሽብርተኝነትን በሚያውቀው ደረጃ የተሰናዱ አልነበሩም፡፡
አና ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በፖለቲካ አሰተሳሰባቸውና በሚጽፉት ጽሁፍ የተነሳ አልታሰሩም የሚለውን ንግግር ካዳመጡ በኋላ ‹‹እንግዲያውስ የታሰሩት ምንድን ናቸው?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡ እነ ውብሸት ታዬ በታሰሩበት ምሽት የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ባስደመጡት ዜና ‹‹የመንግስትን የመሰረተ ልማት ለማፍረስ ሲዘጋጅ ተያዙ›› ያሉ ቢሆንም ተያዙበት የተባለው የማሰሪያ ምክንያት በፍርድ ቤት በማስረጃነት አልቀረበባቸውም፡፡ እስክንድር ነጋ በአንድነት ፓርቲ ቅጥር ግቢ ተገኝቶ ስለ አረብ አብዮትና ኢትዮጵያ ያደረገው ንግግር አስረጂ ተደርጎ ቀርቦበታል፡፡
ርዕዮት አለሙ አውቶብስ ተራ አካባቢ ‹‹በቃ›› ተብሎ የተለጠፈን ፅሁፍ ፎቶ ግራፍ አንስታለች ተብላ መከሰሷ አይዘነጋም፡፡ አንዷለም አራጌ ከወንድሙ ጋር ያደረገው የስልክ ልውውጥ በማስረጃነት ቀርቦበታል፡፡ ጋዜጠኛ ውብሽት ታዬ የቅርብ ዘመዱ ያደረጉትን የአይን ቀዶ ህክምና መሳካት አሜሪካን አገር ለሚገኝ የሰውዬው ልጅ ‹‹ኦፕሬሽኑ ተሳክቷል›› በማለት ኢሜይል ማድረጉ ሌላ ትርጉም ተሰጥቶት ቀርቦበታል፡፡ ታሳሪዎቹ ለፈረደባቸው ፍርድ ቤት የሞራል ጥያቄ በማቅረብ ፍርዱን በደስታ እንደሚቀበሉት ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡እነዚህን ሂደቶች በጥንቃቄና በቅርበት ሲከታተሉ የቆዩት አና ጎሜዝ በአገሪቱ የፖለቲካ እስረኞች የሉም መባሉ አልተዋጠላቸውም፡፡እኔም፡፡እርግጥ ነው በየትም አለም የሚገኝ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ለእስር ሲዳርግ ‹‹በፖለቲካ አመለካከታቸው አሰርኳቸው አይልም››እንዲህ ብሎ እንዲናገር መጠበቅም የዋህነት ሊሆን ይችላል፡፡
ሃይለማርያም ግን ፖለቲከኛ ብቻ አይመስሉኝም ለእግዜር ያደሩ ሃይማኖተኛ ናቸው፡፡ለመንፈሳዊው አለም ያደረ ሰው ደግሞ ከእውነት መወለዱን ይሰብካልና እውነትን በተመለከተ መደራደር አይፈልግም፡፡በዚህ ላይ ሀይማኖተኞች ለህሊና ቅርብ ናቸው፣ህሊና ስላላቸው ስራዎቻቸውን ይመዝናሉ፣አንደበታቸውን ስለሚከፍቱበት ነገር እርግጠኛ መሆንን ያስቀድማሉ፡፡ፖለቲካው የእግዜር ሰዎች እንደሚያስፈልጉት አምነው ወደ መድረኩ የመጡት ኃይለማርያም በጨዋታው ህግ ተገደው ሲዋሹ ማየት ህመም ይፈጥራል፡፡ግን ለምን ይዋሹናል?
No comments:
Post a Comment