በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምዕራብ ጎጃም ዞን በጐንጅ ቆለላ ወረዳ በሸበሌ ቀበሌ ዘመናዊ የግብርና አሠራር ለአካባቢው ነዋሪዎች በማሠልጠንና አብሮ በመሥራት ላይ የነበረ ወጣት የግብርና ኤክስፐርት፣ ፖሊስ በጥይት ደብድቦ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደገደለው ዘመዶቹና የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
በአካባቢው ለፖሊሲ ኮሙዩኒቲንግ ሥራ ከወረዳው በተላከ ፖሊስ በጥይት ተደብድቦ ሕይወቱ አልፏል የተባለው የግብርና ኤክስፐርት ዘለዓለም ፀሐይ የሚባል የ29 ዓመት ወጣት መሆኑን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በ2002 ዓ.ም. ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በግብርና የትምህርት ዘርፍ ከተመረቀ በኋላ፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ‹‹ያሳደገኝን አርሶ አደር መርዳት አለብኝ›› በማለት ከከተማ ሥራ ይልቅ ገጠሩን መርጦ ሲያገለግልና ሲያሠለጥን እንደነበር አስረድተዋል፡፡
ከክልሉ፣ ከዞኑና ከወረዳው ሳይቀር ልዩ ምሥጋናና አድናቆት ሲቸረው የቆየ ኤክስፐርት እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ ለቀበሌው ተመድቦ የነበረው ረዳት ሳጅን ታከለ በላይ የተባለ ፖሊስ፣ ከቤቱ ጠርቶ ለሕጋዊ ሥራ በተሰጠው መሣሪያ በጥይት ደብድቦ እንደገደለው ተናግረዋል፡፡ በጥይት ከመግደሉ በፊት በድንጋይ መትቶ ጥሎት እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡
ፖሊሱ ግድያውን ሊፈጽም የተነሳበት መሠረታዊ ምክንያት ይኑረው ወይም አይኑረው ለጊዜው የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ ግድያውን በፈጸመበት ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ግን፣ ገዳይ ሟችን ከተኛበት ቀስቅሶ ‹‹ኳስ እንጫወት›› በማለት ወደ ሜዳ ወስዶት ሲጫወቱ ቆይተው ለማንም ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ከተጨቃጨቁ በኋላ፣ ተጠርጣሪው ገዳይ በድንጋይ ጭንቅላቱን መትቶ ከጣለው በኋላ፣ ወደ ቤቱ በመግባት መሣሪያ አምጥቶ እንደገደለውና እጁን ለፖሊስ እንደሰጠ አስረድተዋል፡፡
የገደለበትን ምክንያት ምን እንደሆነ ወደፊት በምርመራ የሚታወቅ ቢሆንም፣ መግደሉን አምኖ እጅ ሲሰጥ የክልሉ ፖሊስ ኃላፊነቱን በመውሰድ ቤተሰቦቹንና የአካባቢውን ነዋሪዎች ማፅናናትና እንዲረጋጉ ማድረግ ሲገባው፣ ይህንን ሳያደርግ በመቅረቱ ቤተሰቦቹንና ነዋሪውን እንዳስቆጣ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት በማሰብ የመከላከያና የፖሊስ ሠራዊትን ሲመለምል ከአቋም መለኪያ በተጨማሪ ያለውን ሥነ ምግባር፣ አስተዋይነትና የትምህርት ደረጃውን መሠረት አድርጎ ይሆናል የሚል ግምት እንዳላቸው የገለጹት ነዋሪዎቹ፣ አሁን አሁን ግን በክልሉ ከባህር ዳር ጀምሮ፣ በአንዳንድ ዞንና ወረዳዎች በታጣቂ ፖሊሶች እየደረሰ ያለው የግድያ ወንጀል ሥጋት ውስጥ እንደከተታቸው አስረድተዋል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልሉ መንግሥት በፖሊስ አመላመልና ሠልጥነው በሥራ ላይ ያሉትን ፖሊሶች ሥነ ምግባር፣ ከተሰጣቸው ተልዕኮና ሕዝብን ከማገልገል አንፃር እየተገበሩት ስለመሆኑ መፈተሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የአገሪቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርናን በተሻለና ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል ከተማ ትቶ ከአርሶ አደሩ ጋር ደፋ ቀና ሲል በአሰቃቂ ሁኔታ በፖሊስ ስለተገደለው ወጣት የግብርና ባለሙያ፣ ትኩረት ሰጥቶ ለቤተሰቦቹና ለነዋሪናዎች ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
ወጣቱ የግብርና ኤክስፐርት በፖሊስ ስለመገደሉና ስለተወሰደው ዕርምጃ ማብራሪያ እንዲሰጥ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን ተጠይቆ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የፖሊስ ሹም ድርጊቱ መፈጸሙን አረጋግጠዋል፡፡ ግድያው የተፈጸመው ታስቦበትና ሆን ተብሎ ሳይሆን፣ በጨዋታ ላይ እያሉ ሲበሻሸቁ በድንገት ገዳይ ተበሳጭቶ በደም ፍላት ያደረገው ሳይሆን እንደማይቀር የፖሊስ ሹሙ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ውሎ ፍርድ ቤት መቅረቡንና በጊዜ ቀጠሮ ላይ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. የተገደለው ወጣት ዘለዓለም ፀሐይ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ቀለበት ካደረገላት ዕጮኛው ጋር በሚያዝያ ወር 2006 ዓ.ም. ጋብቻ ለመፈጸም ፕሮግራም እንደነበረው ቤተሰቦቹ ገልጸዋል፡፡ ሟቹ በተወለደበትና ወላጆቹ በሚኖሩበት በምዕራብ ጐጃም ዞን በአዴት ወረዳ በዴንሳ ቀበሌ ውስጥ በበዓታ ቤተ ክርስቲያን ጳጉሜን 1 ቀን 2005 ዓ.ም. የቀብር ሥርዓቱ መፈጸሙን ቤተሰቦቹ አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment