Translate

Friday, May 24, 2013

“…መብቴን ነፃነቱን ጠየቅሁ እንጂ እኔ… ለግንብ ለፎቅ እማ ምን አለኝ ጣሊያኔ”

Abe Tokchaw
Yegna sferየቦሌ መንገድ ተሻሽሎ ተገንብቶ ዛሬ ለትራፊክ ክፍት መሆኑን ሰማሁ፡፡ ጥሩ ነው፡፡ “መንገድ ምናባቱ አይባልም ደርሶ የወሰደውን ሰው ያመጣል መልሶ” ነውና የቦሌም መንገድ የሊማሊሞም መንገድ ቢታደሱ በበኩሌ ደስታዬ እጥፍ ድርብ ነው፡፡ የቦሌውም እኛን እንደወሰደ ይመልሰን ይሆናል የሊማሊሞም “በሊማሊሞ አቋርጡ” የተባሉትን በሙሉ ሊመልስ ይችላልና ሁሉም መንግዶች፤ ሰፋ ሰፋ ብለው መጠበቃቸው ፌሽታችን ነው፡፡
በዛ ሰሞን ከፌስ ቡክ ሰፈር ልጆች የሰማኋት አንዲት ግጥም አለች፡፡ ሙሉ በሙሉ ግጥሟን ማስታወሴን እንጃ መልዕክቷ ግን እንዲህ ይላል///

“…መብቴን ነፃነቱን ጠየቅሁ እንጂ እኔ…
ለግንብ ለፎቅማ ምን አለኝ ጣሊያኔ”
አይነት ነገር ትላለች፡፡
ይሄንን የቦሌ መንገድ መከፈት ዜና እንደሰማሁ ለምን እንደሆን እንጃ… ብቻ…ወደ ጎግል የመልካምድር ካርታ… (Google earth)  ጎራ አልኩና አዲሳባ እንዴት አለች… የሚለውን ከቦሌ ጀምሬ መቃኘት ጀመርኩ… ቀጥታ የቦሌን መንገድ ይዤ መስቀል አደባባይ፤ ከዛም ወደ አራት ኪሎ ሄጄ ቤተመንግስቱ ጣራ ላይ አንጃብቤ የፈረሱትን የሸራተን አካባቢ ቤቶች አይቼ ሽቅብ ወደ ሽሮሜዳ አመራሁ፡፡ …ቀጠልኩ… ወደ እኛ ሰፈር…
እኛ ሰፈር ስደርስ በፎቶግራፉ ላይ ያለችውን ድልድይ አየኋት፡፡ ይቺ ድልድይ የተሰራችው ኢህአዴግ የአዲሳባ አራዳ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ (አዲሳባን ከተቆጣጠረ በኋላ… እንደማለት….) ድልድይዋ ዋዛ አትምሰላችሁ፤ የኛን ሰፈር ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ጋር የምታገናኝ ናት እርሷ ባትኖር ኖሮ የእኛ ሰፈር እና የፈረንሳይ ለጋሲዮን ሰዎች ለመገናኘት፤ ከአዲሳባ እስከ ፓሪስ የሚረዝም ጉዞ ለማድረግ እንገደድ ነበር… አጋነንክ ብለው አይውቀሱኝ ወዳጄ… ኢቲቪ  ቢሆን ኖሮ፤ ስለዝች ድልድይ ለማውራት ሶስት ተከታታይ ዝግጅቶችን ያቀርብልን ነበር፡፡
የሆነው ሆኖ የቦሌ መንገድ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል በዚህ የተነሳ የልማታዊ ጋዜጠኞችም አፍ ክፍት ሆኗል… ልል ነበር፡፡ ነገርየዋ ወደ ስድብ ተጠጋችብኝ፡፡ ነገር ግን ትንሽ ትንሽ መነጋገር አለብን፡፡
በኢህአዴግ ፓርቲ ውስጥ ዋና የስራ እና ዋና የወሬ ሂደት ባለሞያዎች ብዙ ጊዜ ስለ መንግስታችን ቅድስና ሲያወሩ ፎቃ ፎቅ እና ድልድያ ድልድይ እንዲሁም ማሳለጪ ማሳለጪያ…ን መጠቃቀስ ይቀናቸዋል፡፡ ይሄንንም እንደ ትልቅ ተዓምር ይቆጥሩታል….!
እኛ ደግሞ እንዲህ እንበላ…
የቦሌው መንገድ ብርቅ ነው እንዴ… እንኳን እርሱ የኛ ሰፈር ድልድይም ብርቅ አልተባለች! ሃሃ…
መንግስት በመንግስትነት እስካለ ድረስ ከእኛ ሰፈር ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን የምታሻግረውን ድልድይም ሆነ (በነገራችን ላይ እርሷን የሰራናት ራሳችን አዋጥተን ነው) ብቻ ግን፤ እርሷንም ሆነ፣ የቦሌውን ምንገድም ሆነ፣ የጎተራውን ማሳለጫ የመስራት ግዴታ አለበት፡፡ (እንኳንስ ብድርና እርዳታ እየተሰጠው ባይሰጠውም…) ግንባታ ማድረግ የመንግስት ውሎ መግቢያ ስራው ነው፡፡
ከላይ ገጣሚዎቹ አሉ ብዬ እንዳልኩት ጣሊያንም ግንብ ሰርቷል፡፡ ጣልያንም ድልድይ ሰርቷል፡፡ ጣሊያንም ፎቅ ገንብቷል፡፡ ስለዚህ ይሄ ብርቅ አይደለም…! ብርቁ ወዲህ ነው…
ሃያ ምናምን አመት ሰልጣን ላይ መቆየት ይደክምሃል… ሲሉት እሺ… ብሎ የሚታዘዝ መንግስት ማግኘት…  እርሱ ነው ብርቃችን… የጠየቁትን ሁሉ በእስር እና በጥይት ምላሽ ካልሰጠው ሞቼ እገኛለሁ የማይል ስልጡን መሪ ማግኘት እርሱ ነው ብርቃችን… ድምፃችን ይሰማ ሲሉት እሺ ብሎ የሚሰማ ጆሮ ያለው መንግስት ማግኘት ነው ብርቃችን…
ለድልድይማ… ጣሊያንን ማን አህሎት…!

No comments:

Post a Comment