Translate

Thursday, May 16, 2013

ለኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የትግል አንድነት ጥሪ


ሲራጅ ደታንጎ

አዲስ አበባ ዉስጥ በግንቦት 17 ቀን 2005 በሚደረገው ሠላማዊ ሠልፍ የሁሉንም ብሶተኛ ኢትዮጵያዊ ክፍል ጥያቄዎች አንግበን በሙሉ ልብ እንሳተፍ፣ የሕዝቡን አንድነትም ለሚጠራጠሩት ሁሉ በተግባር እናረጋግጥ። በዚህ ወቅት አዲስ አበባ የሚከበረውን የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመት፣ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት ከበርካታ የአፍሪካ ሀገሮችና ከአንዳንድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም እንግዶች ስለሚኖሩ፣ የህዝቡን የፍትኅና የመብት ጥያቄዎች ለዓለም ኅብረተሰብ ጭምር ልናሰማ የምንችበት ጥሩ አጋጣሚም ነው እንላለን። አፋኙንና ግፈኛውን መንግሥትም በዓለም ህዝብ ፊት ይበልጥ ለማጋለጥ ያስችለናል።A call for demonstration in Addis Ababa, Ethiopia
ትልቁ አስፈላጊ ተግባር፣ ምላሽ የሚጠይቁት አንገብጋቢ የፍትኅ፣ የመብት (የዕምነት መከበር ጭምር)፣ የህግ የበላይነት፣ … ጥያቄዎች በግልጽና በአንድነት፣ የችግሮቹ ሰለባ በሆነው ህዝብ በራሱ በአደባባይ በሠላማዊ መንገድና በይፋም መገለጻቸው ላይ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥው አምባገነናዊ ቡድን ሙሉ መብቱንና ሠላሙን ጭምር አጥቷል።
ህዝቡ ሠላም የሚያገኘው፣ ክብሩንና መብቱን ሊያስመልስ የሚችለው፣ ከእንግዴህ በተባበረና ጠንካራ ትግሉ ብቻ ነው።ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ከዓመት በላይ በከፍተኛ ቁርጠኛነትና ብልሃት በግንባር ቀደምትነት ያደሩግት ሠላማዊ ትግል ከእንግዴህ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አካል እንዲሁን ሁኔታዎች ይጠይቃሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃሳቡን በነፃ የመግለጽ መብቱን፣ የመሠለፍና ጥያቄዎቹን በይፋ የማቅረብ መብቱን ጭምር፣ ዛሬ መልሶ ይቀዳጀው፣ ይጠቀምበትም።
ዛሬ ሀገራችን ህግና ፍትኅ የጠፉባት ሆናለች። የህግ የበላይነት፣ በነፃነት የሚሠራ የፍርድቤት፣ ደብዛቸው ጠፍቷል። አንድነትዋ የተጠበቀ፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የምንፈልግ ሁላችን ያለመወላወል ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆመን የትግሉና የመስዋዕትነቱም ተካፋዮች ልንሆን ይገባል።
በዕምነት ተቋሞች ዉስጥ ጣልቃ በመግባት በሙስሊም ኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው እመቃና ወከባ ባስቸኳይ ይቁም፣ የታሰሩት የምእመናኑ ተወካዮችና የሃይማኖት መሪዎችም ባፋጣኝ ይፈቱ!
ፓትሪያርክ ከመሾም ጀምሮ፣ ገ ዳማትን እስከ መድፈርና ማፍረስ፣ ምዕመናን መግደልና ባህታዊያኑን መደብደብ፣ ማሰርና ማሰቃየት፣ ግፍና በደል ናቸውና ያብቁ! መንግሥት በዕምነት ተቋማት ዉስጥ ጣልቃ መግባቱን ያቁም!
በአማራው ብሄረሰብ ተወላጆች፣ በጋምቤላ አኝዋኮችና በሌሎችም ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያሉት ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች የማፈናቀል፣ ዘር የማጽዳት፣ ዘር የማጥፋት አሰቃቂ ተግባሮች በአስቸኳይ ይቁሙ። ካሳ ለተጎጅዎች ይከፈል! ወንጀለኞቹ ለፍርድ ይቅረቡ!
እስር ቤቶችን እያጣበቡ ያሉት የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዚጠኞችና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች በሙሉ አሁኑኑ ይፈቱ!
ጸረሽብርተኝነት በሚል አሳሳች ስያሜ የወጣው ህዝብን እያሸበረ ያለው ዓዋጅ ሳይውል ሳያድር ይነሳ!
“የነጻው ፕሬስ መተዳደሪያ ሕግ” በሚል ስያሜ የወጣው አፋኝ ህግ ይሰረዝ/ይሻር!
ዕምነት የግል ሀገር ግን የጋራ ነችና  መላው ሕዝብ በአንድነት ከታገለ ያለጥርጥር ያቸንፋል!
የሕዝቡን የተባበረ ጉልበት የሚበግረው ምድራዊ ኃይል የለም!

No comments:

Post a Comment