መሳይ መኮንን
ከወልዲያው ጭፍጨፋ፡ ከቆቦዎች አይበገሬነት እስከመርሳዎች ጀግንነት፡ ክስተቶችን እዚያው አጠገባቸው እንዳለ ሆኜ ነበር ስከታተል የቆየሁት። ስሜቴ ከወዲህ ውዲያ ሲላጋ፡ ቅጭም ሲል፡ በሀዘን ሲመታ፡ ደግሞም በጀግንነታቸው ልቤ ሲሞቅ፡ ወዲያኑም በሚደርስባቸው የግፍ በትር ውስጤ ሲደማ፡ በሞታቸው ኩምትር ስልበወርቃማ መስዋዕትነታቸው ስጽናና፡ እንዲሁ ላይ ታች ስል ሰነበትኩ። አሁንም ከዚያው ነኝ። ከወልዲያ ምድር፡ ከቆቦዎች መንደር፡ ከሮቢት ሰፈር፡ ከሀራ ገበያ፡ ከጎቢዬዎች ሀገር፡ ከመርሳዎች መንደር፡፡ የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም የሚለው አባባል አይገባኝም። ወሎን ባላውቀውም ይናፍቀኛል።
ፖለቲካው ግሏል። ሙቀቱ ጨምሯል። ህወሀቶች መቀሌ ላይ የቀመሙትን መርዝ በእጅ አዙር ሊረጩት ተሰማርተዋል። የዘርዓይ አስገዶም ያልተጠና ዲስኩር የህወሀቶችን ቀጣይ አካሄድ እርቃኑን ያጋለጠው ሆኗል። አንጻራዊ የህዝብ ድምጽ በማሰማት ቀና ማለት የጀመሩትን የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትወርክና የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅትን ወደ ቀድሞ አገልጋይነታቸውና በቀቀንነታቸው ለመመለስ በህወሀት አማካኝነት የተዘጋጀውና እነዘርዓይ የተላኩበት ዘመቻ ድባቅ ሲመታ ለመታዘብ ችለናል። አፋቸው ተሎጉሞ የከረሙት ወይም ከህወሀት አገልጋይነት መላቀቅ አቅቷቸው ህዝባቸውን ሲያሳዝኑ የምናውቃቸው እነንጉሱ ጥላሁን እንኳን አፍ አውጥተው፡ ወኔ አግኝተው፡ ድፍረት ተላብሰው ”በዘረኝነት ትዕቢት የተወጠረውን” ዘርዓይን እሳት እንዳየ ላስቲክ ኩምሽሽ ሲያደርጉት አይተናል።