የዘንድሮው ህወሀት በሁለት መልኮች ይገለጻል። አንደኛው በፍርሃት የሚናጥ፡ በማያባራ ህዝባዊ ማዕበል ወንበሩ የተናጋ፡ ወድቀቱን በቅርበት እያየ በስጋት እየተርገፈገፈ የሚገኝ፡ ሳር ቅጠሉ የተጠየፈው፡ ድርጅት ነው። ሌላኛው መልኩ ደግሞ መቃብር አፋፍ ላይ ሆኖ የሚፎክር፡ በመጨረሻው ሰዓት ንሰሀ መግባት ሲገባው ሃጢያቱን የሚከምር፡ ሞት ደጃፍ ቆሞ የሚሸልል፡ ዕብሪትና ጥጋብ በስተርጅናም ያለቀቀው፡ ለአንድም ቀን ቢሆን በስልጣን ለመቆየት ሀገር ከማፍረስ ወደኋላ የማይል፡ ሃላፊነት የጎደለው፡ ሞራል የደረቀበት፡ ''እኔ ከሞትኩ....'' መስመር ላይ ወጥቶ ወደግዙፍና መጠነ ሰፊ ጥፋት የሚጋልብ ድርጅት ነው።
ለጊዜው ወደተቋረጠው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላምራ። የደህነንቱ ሹሙ ቦግ ብሏል። ተቆጥቷል። ፊቱ ቲማቲም መስሏል። ዓይኑን ያጉረጠርጣል። እንደልማዱ ማስፈራራት ላይ ነው። ባሳደግን ተናቅን፡ ባጎረስን ተነከስን ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆኖ በንዴት ይወራጫል። ወዲያውኑ ደግሞ ይቀዘቅዛል። ስሜቱ ይበርዳል። “ከሀይ ስኩል ጀምሮ ያሳደግናችሁ እኛ ነን። በጣም ጠንካሮችና ጎበዞች በመሆናችሁ እኔ በግሌ እኮራባችኋለሁ። ብዙዎች አገር ትተው ሲሰሹ እናንተ ግን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከሕዝብ ጎን በመቆማችሁ ምስጋና ይገባችኋል፤ ሆኖም ግን አገር ሲመራ መቸኮል አያስፈልግም፤ ሰከን ማለት ይገባል” ዓይነት ምክር ለመስጠት ይሞክራል። ጭንቀት። ስጋት። ፍርሃት። ደግሞም ትዕቢት፡ ድንቁርና፡ እየተፈራረቁ ያንገላቱታል።