ነሃሴ ፭ ( አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተቋማት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያና አማራ ክልል ውስጥ የተካሄደውን የጅምላ ግድያ በስፋት አትኩሮት ሰጥተው ዘግበውታል። በዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ መላውን ኦሮሚያ ክልል በጎንደርና አካባቢው በባህርዳር የተካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎች በጸጥታ አስከባሪዎች በግድያ ምላሽ መሰጠቱን ቢቢሲ ዘግቧል። ሁለቱ ታላላቅ የአገሪቱ ብሔረሰቦች አነስተኛ ቁጥር ባለው አንድ ብሄት በመሳሪያ ሃይል በግዳጅ መገዛታቸውንም ቢቢሲ የኢትዮጵያን ሕዝብ ቁጥር በመቶኛ ስሌት ቀመር ይዞ በመውጣት አሰነብቧል። 6.1% የሚሆኑት የትግራይ ብሔር ተወላጆች 34.4% የሚሆኑትን ኦሮሞችና 27% የሚሆኑት አማራዎች ያገለለ አስተዳደር መመስረታቸውን፣ የስልጣን፣ የሃብት፣ ወታደራዊና ደኅንነቱ በህወሃት ቁጥጥር ስር መውደቁን ቢቢሲ በመረጃ አስደግፎ ዘግቧል። የኦሮሚያ ክልልን የመሬት ቅርምትና የወልቃይት ሕዝብን የማንነት ጥያቄዎችም ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል።
አልጀዚራ የዜና አውታር በበኩሉ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ በመንግስት ፀጥታ ሃይሎች የጅምላ ግድያ መቀጠሉን በዜና ትንታኔው ይዞ ወጥቷል። ከሕግ አግባብ ውጪ ዜጎች በጅምላ መታሰር መቀጠላቸውንም ለመላው ዓለም የዜጎችን ሰቆቃ አሰምቷል። በአናሳዎው ህወሃት/ኢህአዴግ የሚመራው ገዥው ፓርቲ 100 % ፓርላማውን ተቆጣጥሪያለው ቢልም ሕዝባዊ ይሁንታ እንደሌለውና የኦሮሞ እና የአማራ ብሔር ተወላጆች ልዩናታቸው በማጥበብ ህብረት መፍጠራቸውን ዘግቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች በሁለት ቀናቶች ብቻ ቁጥራቸው ከመቶ የሚበልጡ ንፁሃን ዜጎችን መግደሉንና ከነዚህ ውስጥም ብዙ የቆሰሉ ቤተ እስራኤሎች እንዳሉበት ከሟቾችና ቁስለኞች ውስጥም ቤተ እስራኤላዊያን እንደሚገኙበት አስታውቋል። በኢትዮጵያ ያለው የደኅንነት ሁኔታ አስጊ እየሆነ መምጣቱንና የእስራኤል መንግስት ቤተ እስራኤሎችን ባስቸኳይ ወደ እስራኤል ካልወሰደ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል ሲል ታዋቂው የእስራኤል ጋዜጣ የዲኦት አህሮኖት አስነብቧል።
የፈረንሳዩ ፍራንስ 24 ደግሞ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በመንግስት አልሞ ተኳሾች ሰላማዊ ንጹሃን ዜጎች በጅምላ መገደላቸውን ዘግቦ ገዥው መንግስት ሕዝባዊውን ተቃውሞ ለመግታት የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡንም አትቷል። በሰሜኑ የአማራ ክልልና በኦሮሚያ ክልል በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ጎዳና ላይ በመውጣት ገዥው መንግስት ባለፉት 25 ዓመታት እንደዚህ ዓይነት ሕዝባዊ ማእበል እንዳልገጠመው ከስፍራው ዘግቧል።
ባለፈው ቅዳሜ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ሰላማዊ ተቃውሞ መካሄዱንና ሰላማዊው ሕዝባዊ ጥያቄዎች በግድያ ምላሽ እንደተሰጠው ፕረስ ቲቪ ዘግቧል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ ፍፁም በሆነ ሰላማዊ መንገድ ተቋውማቸውን ቢያከናውኑም የመንግስት ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በመተኮስ ንፁሀን ዜጎችን ገድለዋል። በተጨማሪም በሀገሪቷ ከባለፈው አርብ ጀምሮ ለሶስት ቀናት የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። የመሬት ወረራው ይቁም፣ ንፁሀኑን የገደሉ ለፍርድ ይቅረቡ የሚሉት መፈክሮች መሰማታቸውንም ፕረስ ቲቪ አክሎ ዘግቧል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎችን በገለልተኛ አለም አቀፍ ታዛቢ ቡድን ማጣራት እንዲደረግበት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውይይት በማካሄድ ላይ መሆኑን ረቡዕ ይፋ አደርጓል። በአለም ዙሪያ የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚከታተለው ይኸው አካል ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል በሯን ክፍት እንድታደርግ በይፋ መጠየቁን ሮይተርስ ከጄኔቭ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ በመባባስ ላይ ያለው ሕዝባዊ አመጽና የፖለቲካ አለመረጋጋት በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ደህንነትን አደጋ ውስጥ እንደከተተው ሪፕሪቭ በሪፓርቱ አመላክቷል። ዋሽንግተን ፖስት በርእሰ አንቀጹ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ከመቶ በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና የአሜሪካ መንግስትና የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚሰጡትን እርዳታ እንዲያጤኑት ጠይቋል። የአሜሪካ መንግስት ግድያውን በማውገዝ መግለጫ ማውጣት አለበት ሲል የአሜሪካንን መንግስት የተለሳለሰ አቋም መያዙን ተችቷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂውማን ራይትስ ወችን የመሳሰሉ በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በሕወሃት መራሹ ገዢው መንግስት የሚፈጸመውን ግድያ፣ እስራት፣ ሰቆቃ፣፣ የዜጎችን አድራሻ ማጥፋትን ኮንነውታል። ገዥው መንግስት አፈናውንና ግድያውን ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች እንዲያቆምና ወንጀለኞች በሕግ እንዲጠየቁ ሲሉ በአጽኖት ጠይቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሰራተኞች በበተነው መረጃ ደግሞ በመላው ኦሮሚያ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ አመጽ ተከትሎ ከዋናው የደብረዘይት አውራ ጎዳና በስተቀር አብዛሃኛው መንገዶች ዝግ ሆነዋል። በአማራ ክልልም ተመሳሳይ ችግሮች የተከሰቱ ቢሆንም ከሰሜን ጎንደር በስተቀር በክልሉ ውስጥ የሚገኙ መንገዶች አገልግሎት መስጠታቸውን አላቋረጡም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች እራሳቸውን እንዲጠብቁና ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል።
በግል መኪናቸውም ቢሆን ከአዲስ አበባ ውጪ በኦሮሚያ ክልል እንዳይጓዙ እያንዳንዳቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ምክርና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ከማንኛውም የተቃውሞ ሰልፎችና መሰል ተግባራትም እንዲታቀቡ ተነግሯቸዋል። መኪኖቻቸው ሙሉ ነዳጅ እንዲኖራቸውና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቢያንስ ለሳምንት የሚያገለግል የመጠጥ ውሃና ምግብ በመያዝ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ድርጅቱ አሳስቧል። የሃይል መቋረጥን ለመከላከል እንዲቻል የመጠባበቂያ ጄነተሮቻቸውን በተጠንቀቅ እንዲያዘጋጁና በጀሪካን መጠባበቂያ ነዳጅ እንዲሞሉ ሲል ተመድ ለድርጅቱ ሰራተኞች ቅድመ ማስጠንቀቂያ መላኩን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለሰራተኞች በላከው መልእክት አስታውቋል።
No comments:
Post a Comment