Translate

Tuesday, August 23, 2016

በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ታስረው የሚገኙ እስረኞች የሶስት ቀን ብሄራዊ ሃዘን እንዲታወጅ ጠየቁ


ኢሳት (ነሃሴ 17 ፥ 2008) 
በተለያዩ ክልሎች ለዴሞክራሲ፣ ፍትህና ነጻነት ሲሉ ህይወታቸውን ያጡ ወገኖችን ለማስታወስ ኢትዮጵያውያን ከነሃሴ 19 እስከ 21 ፣ 2008 የሚቆይ የሶስት ቀን ብሄራዊ ሃዘን እንዲታወጅ በቂሊንጦ ወህኒ ቤት ታስረው የሚገኙ እስረኞች ጠየቁ። 
በአቶ በቀለ ገርባ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ፣ ጉርሜሳ አያኖ፣ ዮናታን ተስፋዬ፣ ፍቅረማሪያም አስማማው፣ መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ እና ብርሃኑ ተክለ ያሬድ በጋራ ተጽፎ ለኢሳት የደረሰው ደብዳቤ፣ “ብሄራዊ የሃዘን ቀን የሚታወጀው የዲሞክራሲና የፍትህ ጥያቄ አንግበው የተሰው ወገኖቻችንን በልባችን ውስጥ ህያው ሆነው እንደሚኖሩ ለማረጋገጥና እነሱም የወደቁለትን አላማ በትግላችን እንደምናሳካው ቃል ለመግባት እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸውም አጋርነታችንን ለማሳየት ነው” ሲል ያስረዳል። 


በኦሮሚያና የአዲስ አባባና ፊንፊኔ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በመቃወም፣ በአማራ ክልል በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ የማንንነትና የድንበር መካለል ጉዳይ፣ በጋምቤላና በደቡብ ክልሎች፣ በኮንሶ ብሄረሰብ እንዲሁም በሌሎች የሃገሪቷ ክፍሎችም የስርዓቱን አፈና በመቃወም ጥያቂያቸውን አንግበው አደባባይ በወጡ ዜጎች ላይ ዘግናኝና ጅምላ ጭፍጨፋ ተካሄዷል እየተካሄደም ይገኛል ያለው ይህ ደብዳቤ፣ በዚህ የነጻነት ጥያቄ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች “ለሶስት ቀናት ከነሃሴ 19-21 ብሄራዊ የሃዘን ቀና በማወጅ እናስባቸው ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን” ይላል።
“እኩልነት በህገ-መንግስቱ ተረጋግጧል ተብሎ በሚነገርበት ዘመን በተደጋጋሚ ህጋዊ ጥያቄዎችን አንግበው አደባባይ የወጡ ዜጎች በትግላችን ዴሞክራሲ አምጥተናል” በሚሉ ገዢዎች ትዕዛዝ በአደባባይ በጥይት ሲደበደቡና ድምጻቸው በአፈሙዝ ሃይል ሲፈተን ከሁለት አስተር አመታት አስቆጥሯል ያለው ከቂሊንጦ የወጣው ደብዳቤ፣ እንዳለመታደል ሆኖ በሃገራችን የገዳዮች ጀግንነት እንጂ የሟቾች ንጹህንነትና በግፍ መገደል የሚነገርበትና የሚጻፍበት ዕድል ባለመኖሩ ለህዝብ ጥያቄዎች ሲባል ህይወታቸውን ካሳለፉ ሰዎች መካከል ህይወታቸው በሰውለት ህዝብ የሃዘን ቀን ተወስኖላቸው እየታሰቡ የሚገኙ ጥቂቶች ሆኗል ብሏል።
በንጹህነታቸው በሞቱ ዜጎች ላይ ማላገጥና እነሱንም መኮነን እጅግ አሳፋሪ ታሪክ የማይረሳው ድርጊት በማለት የህወሃት/ኢህአዴግን ድርጊት የኮነኑት በቂሊንጦ የሚገኙ እስረኞች፣ አምባገነን መሪዎች እነዚህ ንጹሃን ህይወታቸውን የሰውለትን ጥያቄ ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ በሚቆጣጠሯቸው መገናኛ ብዙሃን በዜጎች ላይ የወሰዱት እርምጃ ትክክል እንደሆነ ህዝቡን በማስፈራራት ስራ ተጠምደዋል ሲል ከሷል።
የሃዘን ቀን በታወጀባቸው ሶስት ቀናት፣ ኢትዮጵያውያን ጥቁር የሃዘን ልብስ በመልበስ የፌስቡክ ፕሮፋይላቸውን በጥቁር ወይም በሟች ወገኖቻችን ፎቶ በመቀየር፣ በተሽከርካሪዎች ላይ ጥቁር ጨርቅ በማውለብለብ፣ የሻማ ማብራት ፕሮግራሞች የፓናል ውይይቶቻን በጋራ የህሊና ጸሎቶችን በማከናወን፣ በሃገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሟቾች ቤት በመሄድ አጋርነታቸው በመግለጽ፣ እንዲሁም በተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የተገደሉ ዜጎችን ሙሉ መረጃ እና ፎቶ በማህበራዊ ድረገጾች በተከታታይ በመለጠፍ የመንግስት ጥቃት ሰለባዎችን እንዲያስቧቸው ጠይቋል።
በተጨማሪም፣ “ህዝቡ ሃዘኑን እንዳያደርግ ለማስተጓጎል የሚደረጉ የመንግስት ተጽዕኖዎችን በተለያዩ የምስልና የድምፅ መረጃዎችን ለህዝብ በማቅረብ ለፍትህ ለነጻነትና እኩልነት ሲሉ ህይወታቸውን በሰጡ ወገኖቻችን ስም ጥሪያችንን እናስተላልፈለን” ሲሉ እስረኞቹ ከቂሊንጦ ወህኒ ቤት በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያውያን የወገኖቻችን ህይወት የተሰዋበት አላማ እስኪሳካ ድረስ ትግሉን እንዲቀጥል በጋራ ቃል መግባት እንደሚኖርባቸው እስረኞቹ በዚህ ደብዳቤ ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment