Translate

Wednesday, May 11, 2016

ኢትዮጵያ በፓናማ ዶሴዎች!

panama papersዋዜማ ራዲዮ- “የፓናማ ዶሴዎች”  (The Panama papers) በመባል የሚታወቁትን ምስጢራዊ ሰነዶች ለህዝብ ይፋ ያደረገው አለማቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች  ቡድን (International Consurtium of Investgative Journalists ) በዚህ ሳምንት ያሰባሰባቸውን ተጨማሪ መረጃዎች ይፋ አድርጓል። መረጃው ሞሳክ ፎንሲካ (Mossack Fonseca) በተባለ ተቋም አማካይነት ድርጅቶቻቸው ከአገራቸው ውጭ በተለይም በፓናማና በሌሎችም ልል የታክስ ሕግ ባለባቸው አገሮችን ያስመዘገቡ ግለሰቦችን ማንነት ይፋ ለማድረግ የሞከረ ነው።
ድርጅትን በተለያዩ አገሮች ማስመዝገብ (ኦፍሾር ምዝገባ) በራሱ ወንጀል ባይሆንም ጥቂት የማይባሉ ኩባንያዎችና ባለቤቶቻቸው ግን ይህን የሚያደርጉት ግብር ለማጭበርበር፥ በሙስናና በሌሎችም ወንጀሎች የተገኘ ሀብትን ለመሰወር ወይ በድብቅ ወደ ሕጋዊነት ለማሸጋገር ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይናገራሉ። “የፓናማ ዶሴዎች”ን ይፋ መሆን ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች ሕጎቻቸውን ወደማጥበቅና በዶሴዎቹ የተጠቀሱትን ግለሰቦች ወደመመርመር ሲሄዱ፥ ስማቸው በዶሴዎቹ በመገኘቱ ስልጣን እስከመልቀቅ በሚያደርስ ውዝግብ ውስጥ የተዘፈቁ ግለሰቦች፥ ለውስጣዊ ውዝግብ የተጋለጡ ድርጅቶች ብዙ ናቸው።

ከመረጃው መብዛት አንፃር አበጥሮ ለመለየት ትዕግስትና ጥበብ ይጠይቃል። የዋዜማ ራዲዮም ከሳምንታት በፊት የወጡንት ጨምሮ ሰነዶቹ በመበርበር ከኢትዮዽያ ጋር ዝምድና ያላቸውን መረጃዎች ተመልክተናል። ተጨማሪ መረጃም አሰባስበናል። የዋዜማ አዘጋጆች አርጋው አሽኔ ና መዝገቡ ሀይሉ መረጃዎችን ሲያገላብጡ- ምንጮችንም ሲጠያይቁ ነበር-
====
“የፓናማ ዶሴዎች” ካካተታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሰው “Engelivest” አንዱ መኾኑን  ባለፈው ወር ዋዜማ ዘግባ ነበር።   ይህ በእስራኤላዊው ባለሀብት በጃኮብ ኤንጅል ባለቤትነት የተመዘገበው “ኤንጅል ኢንቨስት” የተባለው ኩባንያ በአፍሪካ የማእድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማራ ኤለኒልቶ (Elenilto) በሚባል ድርጅት ስም  በሞሳክ ፎንሲካ  የሕግ አማካሪ ተቋም አማካኝነት አስመዝግቦ ነበር።
በኢትዮጵያ የታንታለምና የወርቅ ማዕድን ሥራ ለመሥራት ተመዝግቦ የሚገኘውም ይኸው “ኤለኒልቶ” የተሰኘው ኩባንያ ሲኾን ለዚሁም ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የማዕድን ሥራው አይሪስጊያንማን (Irisgianman) የተባለ አንድ ሌላ የንግድ ድርጅት በትንሿ የካሪቢያን ግዛት በአንጉይላ (Anguilla)አቋቁሟል።
የኩባንያው ባለቤቶች ሁለት እስራኤላውያንና አንድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የጣሊያን ዜግነት ያላቸው ግለሰብ እንደኾኑም ሰነዱ ያሳያል። በስም የተጠቀሱት እስራኤላዊት አይሪስ ሌቨንስታይን ሲኾኑ ሁለተኛው እስራኤላዊ ግን በስማቸው የመጀመሪያ ፊደል ብቻ ነበር በዶክመንቱ ላይ የተጠቀሱት። የእስራኤሉ ሀአሬትዝ (Haaretz ጋዜጣ በስም የተጠቀሱትን እስራኤላዊ አግኝቶ ቢያነጋግራቸውም ”ሚስቴር ዋይ” ተብለው የተጥቀሱትን ግለሰብ ማንነት ሊያገኘው እንዳልቻለ አሳውቆ ነበር። 
Mr Yanai Man
Mr Yanai Man
“ኤለኒልቶ” የተባለው ድርጅት በኢትዮጵያ የታንታለም ማዕድን ሥራ ላይ ለመሰማራት ፍቃድ በጠየቀበት ወቅት የኩባንያውን የቀድሞ ታሪክ በማውሳት የማይታመን ኩባንያ መኾኑን የዘገቡም የአገር ውስጥ ጋዜጦች ነበሩ። ያም ኾኖ ኩባንያው ሥራውን እንዲሰራ ተፈቅዶለት እስካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ድረስ ስራው ላይ እንደቆየና የስራ ውሉ እንደተቋረጠም ተዘግቦ ነበር።
“ኤለኒልቶ” ሥራውን በኢትዮጵያ መጀመሩን ይፋ ባደረገበት ወቅት (እኤአ 2013 ) ዜናውን ብዙ ዓለም አቀፍ የዜና ተቋማት ዘግበውት ነበር። ሚድያዎቹ ከድርጅቱ በቀጥታ የተሰጣቸው በሚመስለው መግለጫ መሰል ዜናቸው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ የማዕድን ሥራ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ እንደሚያገኝ ዘግበው ነበር። ውጤቱ ግን እንደተጠበቀው ሳይኾን ቀርቶ የድርጅቱን አቅም ጥያቄ ውስጥ ባስገባ መግለጫ ውሉን ማቋረጡን የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሐምሌ ወር አሳውቆ ነበር። ይኹንና የድርጅቱ ባለንብረቶች የወርቅ ማዕድን ሥራን በመሰሉ ሌሎች ሥራዎችም ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እነኚህ የዜና ዘገባዎች በወቅቱ የድርጅቱን ውጤታማ ውል ከመግለጻቸው በተጨማሪም የድርጅቱን ባለንብረቶች ስምም በይፋ ይናገሩ ነበር። አንደኛው የኩባንያው ባለቤት አሁን በፓናማው ዶሴ ውስጥ በግልጽ ስማቸው የሰፈረው ጣልያናዊ ዜግነት ያላቸው ጂአንካርሎ ቪሎኔ ሲኾኑ ሁለተኛው ሰው ደግሞ ሚስተር ያናይ ማን እንደኾኑ ተዘግቦ ነበር። 
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ ባደረገችው ማጣራትና ጉዳዩን በቅርበት ከሚያውቁ ምንጮች እንደተገነዘብነው- እኚህ በፓናማ ዶሴ ላይ ስማቸው “Mister Y” በሚል የስማቸው መነሻ ፊደል ብቻ የተመዘገቡት ግለሰብ እኚሁ እስራኤላዊ ሚስተር ያናይ ማን ሳይኾኑ እንደማይቀር ግምት አሳድሯል።   Irisgianman በሚል የተሰየመው ኩባንያ ስምም ከሶስቱ ባለሀብቶ ስም የተውጣጣ ስያሜ ይመስላል። Iris Levenstein, Giancarlo እና Yanai Man።
ሀአሬትዝ በሰራው ምርመራ አይሪስ ለቨንስተይን የተባሉት እስራኤላዊት ግለሰብ ያናገረ ሲኾን እኚሁ እስራኤላዊት ከድርጅቱ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው ለጋዜጣው ተናግረዋል። “የድርጅቱ ፈቃድ ውስጥ ስሜ ቢገኝም የድርጅቱ ባለቤት ሚስተር ዋይ ነው” ብለው መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል። የሚስተር ዋይንም ትክክለኛ ስም ለመናገር ፈቃደኛ አልነበሩም።
ለዋዜማ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ሚስተር ጂያንካርሎ ቪሎኔ የተባሉት የድርጅቱ ሸሪክም ምንም እንኳን ጣሊያናዊ ዜግነት ቢኖራቸውም በእናታቸው በኩል ኢትዮጵያዊ ናቸው። እርሳቸውና ሌሎች ስምንት ወንድሞቻቸው በኢትዮጵያ መኪናና ከባድ ማሽነሪ የማመጣት ስራም እንደሚሰሩም ታውቋል።
የነዚህን የቢዝነስ ሸሪኮች ወስጠ ምስጢር እናውቃለን የሚሉ የኢትዮጵያ የመንግስት ምንጮቻችን አይሪስጊያንማን (Irisgianman) አሁንም ድረስ በአዲስ አበባ ቢሮ ከፍቶ የተለያዩ ስውር እንቅስቃሴዎችን እንደሚያዳርግ ነግረውናል። እኛም ድርጅቱ ባንቢስ ድልድይ አካባቢ ባለ ህንፃ ላይ ሰለመኖሩ አረጋግጠናል።
ይህ ድርጅት በሸሪክነት ከያዛቸው ሰዎች ውስጥ የህወሀት ባለስልጣናት የሆኑ ሁለት ሰዎች በሽርክና አዘውትረው በስብሰባዎች ይካፈሉና ሀሳብም ይሰጡ እንደነበር ቢያንስ ሁለት እማኞች ነግረውናል። ግለሰቦቹ በዚህ ቢዝነስ ይሳተፉ የነበረው የፓርቲያቸውን የንግድ ድርጅት ወክለው ይሁን በግል ማረጋገጥ አልቻልንም።
ሌሎች ድርጅቶችና ግለሰቦች
የፓናማ ስነዶች ከያዙት መረጃና ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠቀሱ በውጪ ሀገር ሰዎች የተመዘገቡ ኩባንያዎች ይገኙበታል። በቂርቆስ ክፍለከተማ ቀበሌ 02/03 የቤት ቁጥር 233 አዲስ አበባ አድራሻቸውን ያደረጉት ራጃን ያ አዲታያ ራባዚያ Rajanya Aditya Ravasia በሪል ስቴት ዘርፍ መሰማራታቸውን የሚጠቁም መረጃ ከተለያዩ ሰነዶች ተመልክተናል፣ በእርግጠኝነት ግለሰቡና ድርጅታቸው በኢትዮዽያም ሆነ እንቀሳቀስባቸዋለሁ በሚላቸው ሀገሮች ሰለሰራው የተብራራ መረጃ የለም።
ከሁሉ ጎልቶ የወጣው ግን ከሁለት አመት ወዲህ በኢትዮጵያ በስፋት መንቀሳቀስ የጀመረው “ፖሊ ኢትዮጵያ ፔትሮሊየም ካምፓኒ ሊሚትድ” (Poly Ethiopia Petroleum Company Limited) ነው። ኩባንያ የተመዘገበው በብሪቲሽ ቨርጂን ደሴቶች ሲሆን፥ መሰረታቸው ቻይና ከሆኑት ፖሊ ፔትሮሊየም ኤክስፕሎሬሽንና ፕሮዳክሽን (Poly Petroleum Exploration & Production Company Limited) ፥ ዮሱን ኢንቨስትመንት አማካሪ (JOESUN INVESTMENT CONSULTING (BJ) LTD) ፥ እና ሻንክሲ ፔትሮሊየም ግሩፕ (Shaanxi Yanchang Petroleum (Group) Co. Ltd) ጋራ ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የፓናማ ዶሴዎች ያሳያሉ። ኩባንያው እጅግ የተወሳሰበ የኩባንያዎችና ባለሃብቶች መረብ አካል እንደሆነ  ዶሴዎቹ በማሻማ መልኩ ያሳያሉ።
“ፖሊ ኢትዮጵያ ፔትሮሊየም ካምፓኒ ሊሚትድ”  በኦጋዴን ክልል ስምንት የነዳጅ ፈለጋ ምድቦች የተሰጡት ሲሆን የካሉብና ሂላላ የጋዝ ፕሮጀክቶችንም ተረክቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በኢትዮያና ቻይና መንግስታት ልዩ ድጋፍ የሚደረግለት ይህ ድርጅት የኢትዮዽያ መከላከያ ሰራዊት ልዩ ጥበቃም እንደሚያደርግለት የአዲስ አበባ ምንጮች ይናገራሉ። ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ እና የህወሀት ቅጥያ ከሆኑ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ጋር አብሮ ይሰራልም  ተብሉዋል ። 
Source-ICIJ
Source-ICIJ
ኢትዮጵያውያን በፓናማ ዶሴዎች
በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የተያዙ ኩባንያዎችም በፓናማ ዶሴዎች ተካተዋል የሚያስቆጭ ነገር ቢኖር እስካሁን በወጡት ሰነዶች ስለኢትዮጵያውያኑ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች የተካተተው መረጃ አነስተኛ መሆኑ ነው። ሆኖም ይኸውም ቢሆን የሚፈነጥቀው ብርሃን አይጠፋም፤ ዱካውን ተከትሎ ለሚመረምርም በርካታ ጥቆማዎች ተካተውበታል። ኩባንያዎቹና ባለሃብቶቹ ከኢትዮጵያ ውጭ የተመዘገቡት ለምን ይሆን? ኩባንያዎቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚሰሩት ስራ ምን ይታወቃል፥ ምንስ ተሸሽጎ ይሆን? ፍለጋው ይቀጥላል።
ዳንኤል ግርማ ባህታ እና ናታን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ
ናታን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ሊሚትድ ሁለት ባለድርሻዎች/ባለአክስዮኖች አሉት፥ ዳንኤል ግርማ ባህታ እና ቼን ጋንግ (CHEN GANG) ። ዮናታን ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ሊሚትድ የስራ አድራሻው  ሆንግ ኮንግ ሲሆን፥ ሕጋዊ ምዝገባውን ያካሄደው  ግን ሲሼልስ ነው፤ በኦፍሾር ኩባንያነት   የተመዘገበው ደግሞ እኤአ አፕሪል 2014 ነው። አንደኛው ባለድርሻ ዳንኤል ግርማ ባህታ አድራሻቸው ሆንግ ኮንግ ሲሆን፥ ሌላኛው ባለድርሻ ቼን ጋንግ  አድራሻቸው ሻንጋይ ቻይና ነው።  ዳንኤል እና ቼን እነማን ናቸው? ድርጅታቸውን ሲሼልስ ያስመዘገቡትስ ለምን ይሆን?
Source-ICIJ
Source-ICIJ
“ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ) ኢንኮርፖሬትድ”
ሌላው ኩባንያ “ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ) ኢንኮርፖሬትድ” (GIRMA AGRICULTURE (ETHIOPIA) INC.) የተባለው ነው። የፓናማ ዶሴዎች እንደሚሉት የ“ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ)” ባለአክስዮ ወይም ከባለአክሶን ባለድርሻዎቹ አንዱ ሶንግ ሄንግ (SONG HENG) የተባለ በቻይና ሻንዶንግ ክፍለ ግዛት የተመዘገበ ሰው/ድርጅት ነው። “ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ)” በበኩሉ በሕጋዊ ሰውነት የተመዘገበው በሚጢጢዋ የካሪቢያን ደሴት አንጉዊላ ሆኖ የስራ አድራሻው ግን ሆንግ ኮንግ ነው፤ የሆንግ ኮንጉ አድራሻ  “ኦርዮን ሀውስ ሰረቪስ” የሚባለው አግናኝ ኩባንያ አድራሻ ነበር። “ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ)” በኦፍሾር ኩባንያነት የተመዘገበው (እኤአ) በጥር 2011 ቢሆንም በለስ የቀናው አይመስልም፤ በመስከረም 2014 ድርጅቱ መሰረዙን ወይም መዘጋቱን  የፓናማ ዶሴዎች ይጠቁማሉ። ይህን መሰል ኦፍሾር ኩባንያዎች የፈቃድ ማሳደሻ  በወቅቱ ባለመክፈል ጭምር ሊሰረዙ ይችላሉ፤ ሆኖም ግዴታቸውን አሙዋልተው በድጋሚ ሊመዘገቡ ይችላሉ።
Source-ICIJ
Source-ICIJ
“ዪዉ ፐርፌክት አስመጪና ላኪ”
“ዪዉ ፐርፌክት አስመጪና ላኪ” (YIWU PERFECT IMP & EXP CO., LTD.) የተባለው ድርጅትም ከኢትዮጵያ ጋራ ግንኙነት ያለው ተብሎ የተጠቀሰ ነው። እ ኤአ በ2008 ተመዝግቦ በ2013 መጨረሻ እንደተዘጋ ወይም ንደተሰረዘ የሰፈረለት ዪዉ፥ ምዝገባውን አካሂዶ የነበረው በሲሼልስ ነበር። የዪዉ ባለቤት ወይም የአክስዮን ባለድርሻ ደግሞ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ከድር ጀሚል ሸሪፍ ነው። የከድር የተመዘገበ አድራሻ አዲስ አበባ፥ ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ፥ የቤት ቁጥር 079 ነው። “ግርማ አግሪካልቸር (ኢትዮጵያ) ኢንኮርፖሬትድ”ን እና “ዪዉ ፐርፌክት አስመጪና ላኪ”ን በኦፍሾር ኩባንያነት ያስመዘገባቸው አገናኝ ኩባንያ ተመሳሳይ ነው፥ ኦርዮን ሀውስ ሰርቪስስ (ORION HOUSE SERVICES HK LIMITED.) የተባለው መቀመጫው ሆንግ ኮንግ የሆነ ድርጅት ነው። “ግርማ” እና “ከድር” ምንና ምን ናቸው?
Source-ICIJ
Source-ICIJ
አዲስ ኮመርስ ግሩፕ (Addis Commers Group Inc.) ከስሙ በቀር በፓናማ ዶሴዎች ውስጥ ተጨማሪ መረጃ ያልተገኘለት ኩባንያ ነው። አዲስ የሚለው ስም እና በእንግሊዝኛ የተፃፈበት መንገድ ግን ከኢትዮጵያ ጋራ የተያያዘ ያስመስለዋል።  አዲስ ኮመርስ ግሩፕ አድራሻውና ምዝገባው ለጊዜው ባይታወቅም በሶስት ሌሎች ኩባንያዎች ውስጥ ባለአክስዮን መሆኑ ታውቁዋል። ሶስቱ ኩባንያዎችም ሃሮልድ ዲቪዥን ካምፓኒ ሊሚትድ፥ ስፕሪንግ ግሩፕ ኮርፕ፥ እና ዌስክለርና ጆን ማርኬቲንግ የተባሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው። ይኸው ኩባንያ ላንደቪል ካፒታል ሊሚትድ የተባለ ኩባንያ ባለድርሻ መሆኑንም ሰነዶቹ ይጠቁማሉ።
በሀገራችን ያለው ዝቅተኛ የመረጃ ምዝገባ እና መረጃን ለህዝብ ተደራሽ የማድረግ ልማድ እንደ ፓናማ ዶሴዎች ያሉ መረጃዎችን በአግባቡ መርምሮ ቁርጥ ወዳለው እውነት መድረስን  ፈታኝ ያደርጉታል። ሆኖም ዋዜማ ሬዲዮ ተጨማሪ ጥረቶችን በማድረግ መረጃውን ለማቅረብ ትሞክራለች።

No comments:

Post a Comment